Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብቃት ለሌለው ተቋም ያለጨረታ 501.7 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመዋል የተባሉ የገንዘብ ሚኒስቴር...

ብቃት ለሌለው ተቋም ያለጨረታ 501.7 ሚሊዮን ብር ክፍያ ፈጽመዋል የተባሉ የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተከሰሱ

ቀን:

  • ሦስት ተጠርጣሪዎች የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለመሆን በመስማማታቸው ተለቀቁ

 የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊዎችና የግል ተቋም  ሠራተኞች በጥቅም በመመሳጠር፣ ሚኒስቴሩ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ለመዘርጋትና የአገሪቱን የፋይናንስ አስተዳደር መዋቅሮችን በዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማስተሳሰር ወጥቶ የነበረውን ጨረታ ማሸነፍ ካልቻለ ድርጅት ጋር፣ በሕገወጥ መንገድ የ501,750,722 ብር ውል ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ መሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የመሠረተባቸው፣ በፋይናንስ አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ የተቀናጀ የፋይናንስ ሥርዓት አስተዳደር ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሳ መሐመድ፣ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋ መንግሥቱ፣ የሕግ ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን አባተ፣ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር ሥርዓት ግንባታ ፕሮጀክት ቴክኒክ ኃላፊ አቶ ታገል ሞላ፣ የትራንስናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን መስፍን፣ የትሬዥረር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነገራ፣ የፋይናንስ ግዥ አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ ስህን ጎበና፣ የሕግ ባለሙያ አቶ አክሎግ ደምሴ፣ የኢንፎርሜሽን ሲስተም አስተዳደር ማዕከል ኃላፊ አቶ መስፍን ወርቅነህ፣ የትራንስናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ድርጅት ዳታ አናሊስት አቶ እዮብ በልሁና የትራንስናሸናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ላይ ነው፡፡

ሚኒስቴሩ ከተለያዩ አጋር የልማት ድርጅቶች ባገኘው የበጀት ድጋፍ የፋይናንስ አስተዳደር ዘርፉን ለማዘመንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማስተሳሰር ሁለት ጊዜ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ዘጠኝ የሚሆኑ ተወዳዳሪ ድርጅቶች የቀረቡ ቢሆንም፣ በዓለም ባንክ በተደረገ ግምገማ ተወዳዳሪ ድርጅቶቹ የቴክኒክ ብቃት እንደሌላቸው በመረጋገጡ ጨረታው ውድቅ መደረጉንም ክሱ ያብራራል፡፡

የሚኒስቴሩ ኃላፊዎች ያለጨረታ ቀጥታ ግዥ እንዲፈቀድላቸው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አዋጅና መመርያ መሠረት ውስን ጨረታ እንዲፈቀድላቸውም ጠይቀው እንደነበር ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ኤጀንሲው ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው ኦራክል ከተባለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያና አጋር ድርጀቶች እንዲገዙ ሲፈቅድላቸው፣ በተሰረዙ ጨረታዎች ላይ የቀረቡ የዋጋና የቴክኒክ መሥፈርቶችን እንደ መነሻ ግብዓት በመጠቀም ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ እንዲዋዋሉ በመግለጽ ፈቃድ እንዲሰጣቸውም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡

ነገር ግን ኃላፊዎቹ በጥቅም በመመሳጠር የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግልጽ የሰጠውን ፈቃድ በመጣስ፣ ቀደም ብሎ በወጡ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታዎች ላይ ተወዳድሮ ብቁ ባለመሆኑ ከወደቀው ትራንስናሽናል ኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የ306,149,864 ብር ውል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ የባንክ አገልግሎት ክፍያን በየዓመቱ የሚከፍል የድጋፍ አገልግሎት ክፍያና መቀጮዎችን ጨምሮ 501,730,712 ብር ለኩባንያው ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውንም አክሏል፡፡

በተለይ አቶ ዓለማየሁ ጉጆ፣ አቶ ሙሳ መሐመድ፣ አቶ ነጋ መንግሥቱ፣ አቶ ዋስይሁን አባተና አቶ ታገል ሞላ የመንግሥት ሥራን በማያመች አኳኋን በመምራት የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን እንዲከፈል በማድረጋቸው ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው ፍርድ ቤቱ በችሎት በንባብ አሰምቷል፡፡

በተከሳሾቹ ላይ 20 ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን፣ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በመውሰድ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሮ አቅርቧል፡፡ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ምንጩ ያልታወቀ ንብረትና ገንዘብ ማፍራታቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በተናጠልና በቡድን የመሠረተባቸው የሙስና ወንጀል ክስ ያብራራል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ካቀረባቸው 20 ክሶች ውስጥ ስድስቱን አንብቦ ቀሪውን ሊጨርስ ባለመቻሉ፣ ለመስረከም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመጨረስ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከተከሳሾቹ ጋር ተጠርጥረው ምርመራ ሲደረግባቸው የከረሙት ሠራተኞች አቶ ቲጃን አባ ጎጃም፣ አቶ ተፈራ ፈንታና አቶ ደጉ ላቀው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለመሆን በመስማማታቸው ከእስር መፈታታቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ዶ/ር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ፣ አቶ ታምራት አማረና አቶ ታጠቅ ደባልቄ በበቂ ዋስ ቢፈቱ እንደማይቃወም ዓቃቤ ሕግ በመግለጹ አቶ ታምራት አማረ በ10,000 ብር ዋስትና፣ ሌሎቹ እያንዳንዳቸው በ20,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ቀሪውን ክስ አንብቦ ተገቢ ቀጠሮ ለመስጠት ለመስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...