- አንድ ተጠርጣሪ በ20 ሺሕ ብር ዋስ ሲለቀቁ ሦስት ተጠርጣሪዎች ተቀጥረዋል
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና በመመሳጠር ጥቅም ለማግኘትና ለማስገኘት አስበው፣ ለመንገድ ግንባታዎችና ጥራቱን ላልጠበቀ የአስፋልት ግዥ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ በመፈጸም በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሐሙስ መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በመሠረተባቸው ሁለት ክሶች አስታወቀ፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ የምህንድስና ኦፕሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዶ መሐመድ፣ የዕቅድና አይሲቲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ በቀለ ንጉሤ፣ የሰው ሀብትና የፋይናንስ አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገለሶ ቦሬ፣ ከሐረር-ጅግጅጋ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ያንግ ሬንኋ (በሌሉበት)፣ ሚስተር ኬን ሮበርትስ (በሌሉበት)፣ በግል ሥራ የተሰማሩት አቶ ከበደ ወርቅነህና አቶ እስክንድር ሰይድ (የ80 ዓመት ጡረተኛ ናቸው)፣ የባሥልጣኑ ሠራተኛ የነበሩት አቶ አማረ አሰፋ (በሌሉበት)፣ አቶ ደረጀ ኪዳኔ (በሌሉበት) እና የኢንጂነሪንግና ሬጉላቶሪ ዋና መምርያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዘርፉ ተሰማ በአንድ የክስ መዝገብ የተጠቀሱ ናቸው፡፡
በሌላ የክስ መዝገብ ጥራት የሌለው አስፋልት ከኖክ ኢትዮጵያ ግዥ ፈጽመዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው ተከሳሾች አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል፣ አቶ ገብረ አናንያ ፃድቅ፣ አቶ አሰፋ ባራኪና አቶ ዘለዓለም አድማሱ ናቸው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በመጀመርያ የክስ መዝገቡ ያካተታቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከፍተኛ ኃላፊዎች ከሐረር-ጅግጅጋ ለሚገነባው መንገድ አማካሪነት ውል ከወሰዱት ‹‹Rougten International›› እና ‹‹Pan Africa Construction Plc›› ድርጅቶች ተቀጣሪዎችና በግል ሥራ ከተሰማሩት ሚስተር ያንግ ሬንኋ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ መከፈል ከሌለበት በላይ 58,493,354 ብር ክፍያ በመፈጸም በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ፍርድ ቤቱ ክሱን ለተከሳሾችና ለችሎት ታዳሚዎች በንባብ አሰምቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳብራራው ከሐረር-ጅግጅጋ የመንገድ ግንባታና መሬት ቁፋሮ በውሉ መሠረት 20,192,409 ብር የተመደበ ቢሆንም፣ በተደረገ የለውጥ ክለሳ ወደ 26,013534 ብር ከፍ ተደርጓል፡፡ ለተቋራጩ በተፈጸሙ ተከታታይ ክፍያዎች ላይ 32,111,731 ብር ተጨምሮ በድምሩ 58,125,266 ብር ክፍያ እንደተፈጸመለትም ክሱ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ክፍያው ያላግባብ እንደተከፈለ በፌዴራል ዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት በመረጋገጡ፣ ከቀጣይ ክፍያ እንዲቀነስ ወይም በሌላ መንገድ ግንባታ ላይ እንዲመለስ እንዲያደርጉ ለባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች በደብዳቤ ያሳወቃቸው መሆኑንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል፡፡ ነገር ግን ኃላፊዎቹ ገንዘቡን ለማስመለስ ጥረት ከማድረግ ባለፈ ለመንገድ ሥራው 58,493,354 ብር የተመደበለት በማስመሰል ክፍያው እንዳይመለስ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ኃላፊዎቹ ከሐረር-ጅግጅጋ የመንገድ ግንባታና ፕሮጀክት በአማካሪ መሐንዲስ የቀረበው የዲዛይን የጥራት ደረጃ የአካባቢውን የኃይድሮሎጂና የሚቲዮሮሎጂ ጥናት ደረጃውን የጠበቀ መሆኑንና አለመሆኑን በመመልከት አረጋግጠው የማፅደቅ ኃላፊነት የነበረባቸው ቢሆንም፣ አለማድረጋቸው ጉልህ የሆኑ ከጅግጅጋ ከተማ ማስተር ፕላን ጋር የማጣጣምና የብረት መከላከያ ድልድዮችን የማካተት ሥራዎች ሳይከናወኑ ውል መፈጸማቸውንም አክሏል፡፡ ሁናን ሁንዳ የመንገድና ድልድይ ሥራ ኮርፖሬሽን ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ያንግ ሬንኋ (በሌሉበት) ጋር የ346,262,115 ብር ኮንትራት ውል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ሌሎች ተቋራጮችን በማግለል ወደ ትግበራ ሥራ ካስገቡ በኋላ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ የለውጥ ሥራ ትዕዛዝ (Variation Order) በመስጠት፣ የግዥ መመርያው ከሚያዘው የገንዘብ መጠን ከ30 በመቶ መብለጥ ያልነበረበት ቢሆንም፣ 31.57 በመቶ በማስበለጥ 109,329,357 ብር ጭማሪ ከሕግ ውጪ በቀጥታ ለተቋራጩ እንዲከፈል ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ ተቋራጩም በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን የማጠናቀቂያ ጊዜ ጭማሪ በመፍቀድ ከማጠናቀቂያ ጊዜ በላይ 1,116 የሥራ ቀናትን በመጨመር የዋጋ ማስተካከያ ብቻ 206,115,365 ብር እንዲከፈል ማድረጋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ከሐረር-ጅግጅጋ መንገድ ሥራ ፕሮጀክት በድምሩ 720,292,717 ብር ያላግባብ ክፍያ እንዲፈጸም በማድረግ የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ሌላው ጉዳት አድርሰዋል በማለት ክስ ያቀረበባቸው ከጎሬ- ጋምቤላ ከሚገነባው መንገድ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ኃላፊዎቹ የመንገድ ፕሮጀክቱ ከመጀመሩ በፊት ወይም ከኮንትራክተሩ ጋር ውል ከመፈጸማቸው አስቀድሞ መብታቸው የሚነካ የአካባቢው ነዋሪዎችን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር በመነጋገር በሕጋዊ አግባብ ማስለቀቅና ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ሲገባቸው፣ አለማድረጋቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ለተቋራጩም ካምፕና የኳሪ ማውጫ ቦታዎችን ሳያዘጋጁ ከኮንሶሊዴት ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ውል የተፈጸመ ቢሆንም፣ ነዋሪዎቹ ባለመልቀቃቸው 16.4 ወራት ያለ ሥራ በመቆየቱ ተቋራጩ በውሉ መሠረት ላልሠራበት ጊዜ 64,492,807 ብር ካሳ እንዲከፈለው በማድረጋቸው፣ ኃላፊዎቹ በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስታውቋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛው የክስ መዝገብ ያካተታቸው አቶ ዛይድ፣ አቶ ገብረ አናንያ፣ አቶ አሰፋና አቶ ዘለዓለም ደግሞ ኖክ ኢትዮጵያ ከሚባል ድርጅት ጥራት የሌለው አስፋልት እንዲገዛ በማድረግ የ62 ariation Ordertional Pan Africa Construction Plc,382,177 ብር ጉዳት ማድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡
ኖክ ኢትዮጵያ ባለሥልጣኑ ያወጣውን የአስፋልት ግዥ ጨረታ ያሸነፈ ቢሆንም፣ ለቀረበው ውል የፈጸመበት ‹‹Mc-3000›› የተባለው የአስፋልት ዓይነት ከተቀመጠው ደረጃና ስፔስፊኬሸን ውጪ መሆኑ በላቦራቶሪ ተረጋግጦ እያለ፣ ኃላፊዎቹ አስፋልቱ ጥራት እንደሌለው ገልጸው፣ በ60 ቀናት ውስጥ እንዲመለስ ማድረግ ሲገባቸው ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጋቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ አስፋልቱ ሥራ ላይ እንዲውል በተደረገባቸው መልካ-ሰደሬ፣ በደሌ-መቱ፣ ሻሸመኔ-አላባ፣ ሐዋሳ-ሀገረ ማርያምና ደጀን-ደብረ ማርቆስ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች የመሰንጠቅ፣ ወጣ ገባ የመሆን፣ የማበጥ፣ የመለጠጥ፣ የጎማ ቅርፅ መያዝ፣ ጉድጓድ መፍጠር፣ የመፈረካከስና የጠጠር መበታተን ብልሽት እንደደረሰባቸውም አክሏል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ በፈጸሙት ሥልጣንን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ እንደመሠረተባቸውም ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ከእነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል ጋር በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በታሰሩት አቶ በቀለ ንጉሤ፣ አቶ ሳምሶን ወንድሙ፣ አቶ የኔነህ አሰፋና አቶ ካሳዬ ካቻ ላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ አልመሠረተም፡፡ አቶ ካሳዬ ካቻ በበቂ ዋስ ቢፈቱ ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጹ በ20,000 ብር ዋስትና እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ በቀለ፣ አቶ ሳምሶን የኔነህና በተጠረጠሩበት ከገቢያቸው በላይ ሀብት ማካበት ወንጀል ገና ምርመራውን አለመጨረሱን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ የሰባት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቅድለት ጠይቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ደግሞ ባነሱት ተቃውሞ ዓቃቤ ሕግ ሕጉ የሚፈቅድለትን የ15 ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክስ መመሥረት ካልቻለ እነሱ ያጠፉት ጥፋት እንደሌለ የሚያረጋግጥ መሆኑን ስለሚያሳይ፣ በነፃ እንዲያሰናብታቸው ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡
ዓቃቤ ሕግ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና መብት በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው፣ ሕጉ ክስ ለመመሠረት 15 ቀናትን ከመፍቀድ ወይም ይሰጣል ከማለቱ ውጪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ እንደማይከለክልና ለትርጉም ክፍት መሆኑን በመጠቆም፣ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ እንዲፈቀድለት በድጋሚ ጠይቋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ በአዳር መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ብይን ለመስጠት የቀጠረ ቢሆንም፣ በሥራ መደራረብ ምክንያት እንዳልደረሰለት ገልጾ ለመስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ክስ የተመሠረተባቸው እነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡