- መንግሥትና ባለሥልጣናትን እንደሚከስ አስታወቀ
የህንዱ ካሩቱሪ ግሩፕ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ ችግር ውስጥ በመግባቱ ምክንያት ባለፈው ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ነቅሎ መውጣቱን ባስታወቀ ማግሥት፣ በአገሪቱ ያሉትን ንብረቶች ለማስወጣት እንዲችል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤቱታውን አቀረበ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጻፈው ደብዳቤም በኦሮሚያና በጋምቤላ ክልሎች ተፈጽመውብኛል ያላቸውን ጥሰቶች አስታውቋል፡፡
የካሩቱሪ ግሩፕ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሳይ ራማ ክሪሽና ካሩቱሪ ለሪፖርተር ባደረሱትና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጻፉት ባለ አራት ገጽ ደብዳቤ፣ በአሮሚያ ክልል ሆለታ ከተማና በባኮ ቲቤ የነበሯቸው የአበባ እርሻዎች፣ እንዲሁም በጋምቤላ ክልል የነበራቸው 100 ሺሕ ሔክታር መሬት የተወረሰባቸው ‹‹በሕገወጥ መንገድ›› ከመሆኑም በላይ፣ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ዋስትና የተገባባቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ስምምነቶች በሚጥስ አካሄድ እንደሆነ ጽፈዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ በኢትዮጵያ በነበራቸው እንቅስቃሴ 75 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ ለ4,000 የሥራ ዕድሎችን እንደፈጠሩ የሚጠቅሱት ካሩቱሪ፣ በሆለታ ለ15 ዓመታት በሚቆይ ስምምነት የወሰዱት 108 ሔክታር የአበባ እርሻ መሬትን ለተጨማሪ 30 ዓመታት ለማራዘም ሲጠይቁ፣ 11.5 ሚሊዮን ብር ካሳ ለገበሬዎች መክፈል እንዳለባቸው እንደተነገራቸው ጽፈዋል፡፡ ምንም እንኳ የሁለት በመቶ ተጨማሪ ክፍያ መሬታቸውን በሊዝ ላከራዩዋቸው ገበሬዎች መክፈላቸውን ቢጠቅሱም፣ ካሳ እንዲከፍሉ የተጠየቁት ገንዘብ ምክንያታዊ አይደለም በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽፈዋል፡፡ የኦሮሚያ የመሬትና የአካባቢ ጥበቃ ቢሮ ከስድስት ዓመታት በፊት የጠየቃቸውን የካሳ ክፍያ በነበረባቸው የገንዘብ እጥረት ሳቢያ በወቅቱ መፈጸም ባይችሉም፣ ከሦስት ዓመት በፊት የተጠየቁትን ገንዘብ እንደሚከፍሉ ባስታወቁ ጊዜ ግን የኦሮሚያ ክልል ሐሳቡን በመቀየር የካሳ ክፍያውን ወደ 26 ሚሊዮን ብር ከፍ እንዳደረገባቸው አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ገንዘብ መክፈል ካልቻሉ፣ ክልሉ በራሱ ገንዘብ ለገበሬዎች ካሳውን በመፈጸም መሬቱን ግን ብቃት ላለው ባለሀብት እንደሚያስተላልፈው እንደነገራቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ የአበባ እርሻውን ለመዝጋት እንደተገደዱ አስታውቀዋል፡፡
በባኮ ቲቤ ወረዳም በኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ቦርድ አማካይነት የ11,700 ሔክታር ተከልሎላቸው እንደነበር፣ ይሁንና ወደ 4,500 ሔክታር ዝቅ እንደተደረገና በእሳቸው ይዞታ ሥር ይገኝ የነበረው መሬት ግን 1,980 ሔክታር ብቻ እንደነበር ያትታሉ፡፡ በዚህ መሬት ላይ 50 የውኃ ጉድጓድ በመቆፈር ጭምር መሬቱን ለሜካናይዝድ እርሻ ሲያዘጋጁ እንደቆዩ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የክልሉ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት በወሰደው ዕርምጃ መሬቱን እንደቀማቸው ሲጽፉ፣ የጠቀሱት ነጥብ ለ4,500 ሔክታር መሬት በ45 ዓመታት ታሳቢ በሚደረግ ሒሳብ የ10 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ወዲያውኑ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸው አግባብ እንዳልነበር ነው፡፡ እሳቸው ‹‹ልጠየቅ የሚገባኝ በ1,890 ሔክታር መሬት ላይ ላለው ኢንቨስትመንት ብቻ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ጉዳዩን በማስመልከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የሚመለከታቸው ሰዎች በቦታው ተገኝተው ሁኔታውን ቢያጣሩም፣ ምንም ሊፈይዱ እንዳልቻሉ ካሩቱሪ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል፡፡
በጋምቤላ ክልል የነበራቸው 100 ሺሕ ሔክታር ከሁለት ዓመት በፊት የተወረሰባቸውም ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ዋስትና ስምምነትን በሚጥስ አኳኋን እንደሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጽፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ግብርና የኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በወሰደው ዕርምጃ ከ98 ሺሕ በላይ ሔክታር መሬት ምንም ዓይነት ልማት ያልተካሄደበት እንደሆነ በመግለጽ መሬቱን እንደነጠቀ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ በአንፃሩ ካሩቱሪ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ 30 ሺሕ ሔክታር መሬት እንዳለሙ (ምን ምን ምርቶች እንዳለሙበት አልጠቀሱም)፣ 35 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደመነጠሩና 110 ኪሎ ሜትር ዕርከን እንዳበጁ ጠቁመዋል፡፡ ይህንንም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያውቀዋል ይላሉ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከህንድ ባንኮች 180 ሚሊዮን ዶላር እንዲበደሩ ፈቃድ ቢሰጥም፣ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ የሚችሉበትን ፈቃድ ሊሰጥ ባለመቻሉ መሥራት እንዳልቻሉ ይናገራሉ፡፡ በአገሪቱ በተከታታይ ዓመታት በተከሰተው ድርቅና በብሔራዊ ባንክ ይሁንታ ማጣት ምክንያት ምርት ሳያመርቱ ከአራት ዓመታት በላይ መቆየታቸው የእሳቸው ጥፋት እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡
እንዲህ ያሉ መሠረታዊ ጥሰቶች ተፈጽመውብኛል ያሉት ካሩቱሪ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደማይኖራቸው አስታውቀው፣ ይልቁንም በአገሪቱ ያላቸውን ንብረት ለማውጣት እንዲፈቅዱላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡ ይህ ጥያቄያቸውም በተስፋ መቁረጥና በተፈጸመባቸው ‹‹ሕገወጥ የመሬት ውርስ›› እንደሆነ አስፍረዋል፡፡ ንብረቶቻቸውን ከማስወጣት ጎን ለጎን መንግሥት ተገቢውን ካሳ እንዲከፍላቸውም ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ ደብዳቤያቸው በተጓዳኝ ሰሞኑን ለሪፖርተር በጻፉት መልዕክት ንብረትን ያላግባብ የመውረስና የኢንቨስትመንት ስምምነቶችና የከለላዎች የመብት ጥሰት ተፈጽሞብኛል በማለት አንቀጽ አጣቅሰው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጨምሮ ሁለት የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚመሠረተውን ክስ በህንድ መንግሥት በኩል እንዲከፈት ለማድረግ፣ ለአገራቸው መንግሥት የሕግ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ከህንድ በላኩት መልዕክት አሥፍረዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ቢቢሲ ያሰፈረውን ዘገባም ዋቢ አድርገዋል፡፡ ይኼውም በዚምባብዌ መንግሥት ንብረታቸው ለተወረሰባቸው ነጭ ገበሬዎች ካሳ ይውል ዘንድ በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ የዚምባብዌ መንግሥት ንብረት ተሸጦ፣ ለተፈናቃይ ነጭ ገበሬዎች እንዲከፋፈል የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ያስተላለፈውን ወሳኔ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የግብርና የኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ለካሩቱሪ የተሰጠው የጋምቤላ እርሻ መሬት እንዲወረስ ሲወስን፣ ምንም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ እንዳልተካሄደበት ከማስታወቁም ባሻገር የኩባንያው ባለቤት ንብረት ሲሸጡ መገኘታቸውንም አስታውቋል፡፡ የካሩቱሪ የጋምቤላ እርሻ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 70 ሚሊዮን ብር ለሚጠጋ የሥራ ማስኬጃ ብድር ማስያዣነት ውሎ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡