Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በድርቅ የተፈተነው ሴፍቲኔት 600 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አገኘ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የዓለም ባንክ በሁለት ፕሮግራሞች 1.3 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታና ብድር ሰጥቷል

እየተከሰተ ባለው ተከታታይ ድርቅ እየተፈተነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴፍቲኔት ፕሮግራም፣ ከዓለም ባንክ 600 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ አገኘ፡፡ የዓለም ባንክ ዓርብ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየተተገበረ ለሚገኘው ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከሰጠው ዕርዳታ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ፍትሐዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ለተነደፈው ፕሮግራም 700 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሰጥቷል፡፡

የዓለም ባንክ ለሁለቱ ፕሮግራሞች በድምሩ 1.3 ቢሊዮን ዶላር (30.4 ቢሊዮን ብር) ዕርዳታና ብድር ሰጥቷል፡፡ ዕርዳታና ብድሩን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተና (ዶ/ር) የዓለም ባንክ በምሥራቅ አፍሪካ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ ተፈራርመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከ15 ዓመታት በፊት በድርቅ ምክንያት ለምግብ ዋስትና ችግር የሚዳረጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሴፍቲኔት ፕሮግራም መጀመሩ ይታወሳል፡፡

በሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚታቀፉ ዜጎች የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ፣ ራሳቸውን የሚችሉበትና የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት እንዲሁም አቅመ ደካሞችም በቋሚነት የሚደግፉበት ነው፡፡

ይህንን ፕሮግራም በበላይነት የሚያስተባብረው የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳመነ ዳሮታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተፈጥሮ ክስተት ምክንያት ለምግብ ዋስትና ችግር ለሚዳረጉ ወገኖች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከ15 ዓመታት ወዲህ እነዚህን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጀምሯል ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ፕሮግራም አራተኛ ዙር ላይ ይገኛል፡፡ በመጀመርያዎቹ ሦስት ዙሮች 3.4 ሚሊዮን ዜጎች ራሳቸውን በመቻላቸው ተመርቀዋል፡፡ በአሁኑ አራተኛ ዙር ደግሞ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች የታቀፉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 1.6 ሚሊዮን የሚሆኑት አቅመ ደካሞች በመሆናቸው ቀጥታ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው፤›› ሲሉ አቶ ዳመነ አስረድተዋል፡፡ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ተግባራዊ እየሆነ ያለው ከቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ከጋምቤላና ከአዲስ አበባ በስተቀር በሁሉም ክልሎች ነው፡፡

ነገር ግን ይህ ፕሮግራም በተከታታይ በሚከሰተው ድርቅ መፈተኑ አልቀረም፡፡ አቶ ዳመነ ጨምረው እንደገለጹት፣ በድርቁ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት በምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ራሳቸውን አስችሎ ማስመረቅ አልተቻለም፡፡

‹‹በዚህ ፕሮግራም የሚታቀፉ ዜጎች ለ12 ወራት ራሳቸውን መቻላቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ ራሱን ችሎ የተመረቀ ዜጋ ድርቅ ቢያጋጥም እንኳ ድርቁን የሚቋቋምበት ደረጃ ላይ መድረስ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ባለፉት ሁለት ዓመታት ማስመረቅ አልተቻለም፤›› ሲሉ አቶ ዳመነ ገልጸዋል፡፡

አራተኛው የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2012 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚደረግ ነው፡፡ ለዚህ ፕሮግራም በአጠቃላይ 3.6 ቢሊዮን ዶላር ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን አቶ ዳመነ እንደሚሉት ከውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ጋር ተያይዞ ይህ ገንዘብ ወደ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል፡፡

ይህንን ፕሮግራም የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም ባንክ፣ ዩኤስአይዲና ሌሎች ግብረ ሰናይ ተቋማት ይደግፉታል፡፡ የዓለም ባንክ ባለፈው ዓመት 1.5 ቢሊዮን ዶላር፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች