Sunday, June 16, 2024

የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች መናድ ይቁም!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዳር እስከ ዳር በጥብቅ የሚያቆራኙት የጋራ እሴቶች አሉት፡፡ እነዚህ እሴቶች በኢትዮጵያዊነት ጠንካራ ገመድ የተያያዙ የኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ ጌጦች ናቸው፡፡ በአራቱም ማዕዘናት በተለያዩ መልከዓ ምድራዊ አሠፋፈሮች ውስጥ ሆነው በሥነ ልቦና ከፍተኛ የሆነ መቀራረብና መወራረስ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ልዩነቶቻቸውን ጌጥ አድርገው በአንድነት ለዘመናት አብረው ኖረዋል፣ አሁንም እየኖሩ ነው፡፡ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና የመሳሰሉትን ልዩነቶች አቻችለው በመተሳሰብና በመፈቃቀር ብቻ ሳይሆን፣ ተጋብተውና ተዋልደው ደግና ክፉ ጊዜያትን አብረው ያሳለፉት ኢትዮጵያውያን በማስተዋል የተሞሉ ናቸው፡፡ አንዱ የሌላውን እያከበረና እያስተናገደ ልዩነቶች መኖራቸው እስከማያስታውቅ ድረስ አብረው የኖሩት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ ኖረዋል፡፡ አንድም ጊዜ ለወራሪዎች ሳይንበረከኩ በተባበረ ክንዳቸው አሳፍረው መልሰዋል፡፡ በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ገዥዎች ከበጎ ተግባራቸው በተጨማሪ ያደረሱዋቸውን በደሎችም፣ የኢትዮጵያዊነት ታላቁን ምሥልና የጋራ እሴቶችን በማስቀደም በመከባበርና በመተባበር አብረው አሳልፈዋል፡፡ ይህንን የመሰለ ማስተዋል፣ አርቆ አሳቢነትና የአገር ፍቅር የተሞሉበት የጋራ እሴቶችን የሚንዱ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ ከምልክትነት በላይም አስፈሪ እየሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ በፍጥነት!

ኢትዮጵያ የብዙኃን አገር ናት፡፡ ሰባት ስድስት ያህል ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ማኅበረሰቦች አሉዋት፡፡ የተለያዩ እምነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ልማዶችም እንዲሁ፡፡ ይህንን ዓይነቱን ብዝኃነት በማስተዋል ማስተናገድ አለመቻል፣ ከኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ጋር ያጣላል፡፡ እነዚህ እሴቶች ልዩነቶችን ውበት አድርገው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የፈጠሩ ናቸው፡፡ በሕዝብ ውስጥ አልፎ አልፎ ችግር ሲፈጠር እንኳ ከመደበኛው የሕግ ማስከበር በተሻለ አገር በቀል የሽምግልናና የእርቅ ሥርዓቶች ፋይዳቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ አሁንም በብዙ ቦታዎች ይሠራባቸዋል፡፡ በቂም በቀል የሚፈጸሙ ድርጊቶች በማኅበረሰቦች ያስወግዛሉ፡፡ ያስገልላሉ፡፡ ይህንን የመሰሉ የበሰሉ ባህሎችና ወጎች ባሉበትና አስተዋይ አረጋውያን በሞሉበት አገር ውስጥ፣ ለዘመናት አብረው የኖሩ ዜጎች መሀል ግጭት መቀስቀስና ለግድያ መዳረግ ተቀባይነት የለውም፡፡ ዜጎች በገዛ አገራቸው ከቀዬአቸው ተፈናቀሉ ሲባል እጅግ በጣም ያሳፍራል፡፡ ሕግ ባለበት አገር ውስጥ ሕገወጥነት ሰፍኖ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች ሲናዱ ዝም መባል የለበትም፡፡ እንዲህ ዓይነት ኃፍረት ማስጠየቅ አለበት፡፡ በሕግ መባል አለበት፡፡

አገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ተግባራዊ ካደረገች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ የአገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ የመገንባት ዓላማ አለው፡፡ እርግጥ ነው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ሌላ አማራጭ ማሰብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ሥርዓቱ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ይገነባል ሲባል፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ የተጠናከረ አገርን በማሰብ ካልሆነ ችግር አለ፡፡ ልዩነትን በማቀንቀን ብቻ ታላቋን ኢትዮጵያ መርሳት ወንዝ አያሻግርም፡፡ ከራሱ ብሔር፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነትና መሰል ተግባራት ውጪ ስለሌላው አያገባኝም የሚለው አስተሳሰብ ሥር እየሰደደ ከሄደ ለአገር ህልውና አደገኛ ነው፡፡ ይልቁንም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶችን ከዳር እስከ ዳር ልቅም አድርጎ በማስቀመጥ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ታላቋን አገር ለመገንባት መነሳት መረባረብ ይጠቅማል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የጋራ ዕድል መመሥረት ያለበት ከታሪክ የተወረሱ የተዛቡ ግንኙነቶችን በማስተካከልና የጋራ ጥቅሙን በእኩልነት በማሳደግ ላይ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብረውለት በነፃነት የሚኖርበት መሠረት ሲጣል፣ የሚያጋጩና ደም የሚያፋስሱ ችግሮች ያበቃላቸዋል፡፡ ይህ ፅኑ የአንድነት መንፈስ የተላበሰ ፍላጎት ከወረቀት ጌጥነት ተላቆ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ድጋፍ መስጠት አለባቸው፡፡

ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያስፈልገው ከዘረኝነትና ከራስ ወዳድነት መፅዳት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የጋራ ጥቅሙና መብቱ በሕግ የበላይነት ሥር ቢከበርለት፣ ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ ያላንዳች ልዩነት ቋንቋዎቹ፣ እምነቶቹ፣ ባህሎቹና አመለካከቶቹ፣ እንዲሁም መብቶቹና ነፃነቶቹ ሊከበሩለት ይገባል፡፡ በተዛቡ አመለካከቶች ሳቢያ የተፈጠሩ ቅሬታዎች ዳግም እንዳይፈጠሩ እየተሠራ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ቅሬታዎች ከመጠን በላይ እየተጋነኑ እየተቀነቀኑ ልዩነቶችን መለጠጥ በመተው፣ ለኅብረ ብሔራዊት አገር ግንባታ መሠረት መጣል ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ግን ኪሳራ ብቻ ነው፡፡ ሕዝባችን በዘወትር ግንኙነቱ እርስ በርሱ እየተከባበረና ዕውቅና እየተሰጣጠ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ አልፎ ተርፎ በጋብቻ በመተሳሰርና በመዋለድ ታላቅ ተምሳሌት ሆኗል፡፡ ፖለቲከኞች በሚፈጥሩት ግጭት ምክንያት መፈናቀልና መሰደድ ሲኖር እንኳ እርስ በርሱ ከለላ እየተሰጣጠ አርዓያነቱን አሳይቷል፡፡ ይህንን የመሰለ ጨዋ ሕዝብ እያመሱ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ መክተት ወንጀል ነው፡፡ በታሪክ የሚያስጠይቅ ወንጀል፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ዘመን አይሽሬ የሆኑ አርዓያነታቸውን ጥለውልን ያለፉ የኩሩ ዜጎች አገር ናት፡፡ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የከፈሉ አኩሪ ዜጎችን ያፈራች አገር፣ በዘርና በእምነት የተቧደኑ ሕገወጦች መፈንጫ መሆን የለባትም፡፡ በአገር ፍቅር የነደደ ስሜት ማንኛውንም ዓይነት ግዴታ ለመወጣት የማያንገራግሩ አኩሪ ዜጎችን ያፈራች ኢትዮጵያ፣ የገዛ ወገኖቻቸውን የሚገድሉና ለመፈናቀል የሚዳርጉ እኩዮች መጫወቻ ልትሆን አይገባም፡፡ ሕዝብ ይከበር ሲባል እኮ አገር በሕግ የበላይነት ሥር ትተዳደር ማለት ነው፡፡ ነጋ ጠባ ግጭት፣ ግድያ፣ መፈናቀል፣ ወዘተ. የሚሰማው ለምድነው? የፌዴራል ሥርዓቱ አንድ የጋራ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ይገነባል እየተባለ አገርን ማዕከል ያላደረጉ ድርጊቶች ለምን ይበዛሉ? አሁን እኮ የእናት አገር ፍቅር ስሜትን ከሙዚቃና ከዲስኩር በላይ ለማየት የተሳናቸው እየበዙ ነው፡፡ የገዛ ወገኑን እንደ ወንድሙና እንደ እህቱ በተቆርቋሪነት ስሜት የሚመለከት ማግኘት ብርቅ እየሆነ ነው፡፡ ትልቁ የኢትዮጵያዊነት ምሥል እየደበዘዘና እየጠፋ ነው፡፡ ይኼ በአጭሩ ካልተገታ አደጋ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ በእኩልነት የሚያስተናግደውን ፌዴራላዊ ሥርዓት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመገንባት መሠረቱ ከተጣለ፣ ኢትዮጵያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊት አገር ማድረግ ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳ፣ እያንዳንዱ ዕርምጃ የተጠናና ሕግን የተከተለ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አጠቃላይ ሕዝቡን የሚያግባቡ የጋራ አጀንዳዎች ሊኖሩ የግድ ይላል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ልዩነትን ብቻ የሚያቀነቅኑ ጠባብ አስተሳሰቦችን ማረም፣ በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሠረተ የጋራ አገር ለመገንባት ትውልዱን ማነፅ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ሁሉንም አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር ማመቻቸት፣ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚጋፉ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚመጥኑና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረቱ ግንኙነቶችን ማዳበር፣ የሕዝብ  ተሳትፎን በላቀ ሁኔታ ማሳደግ፣ ወዘተ. የወቅቱ ጥያቄ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴቶች የተመሠረቱት በመግባባትና በመተሳሰብ ላይ ስለሆነ፣ በዚህ ጉዳይ በጥቅብ መጨነቅ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ህልውና ቀጣይነትና ዘለቄታዊነት የሚኖረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ አሁን እየታየ ያለው ግን አይመችም፡፡ በፍጥነት መታረም አለበት፡፡ የኢትዮጵያዊነትን የጋራ እሴቶች መናድ ይቁም ማለት አለብን!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...