Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች በሐረር መጠለያ

ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች በሐረር መጠለያ

ቀን:

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የሕዝብ መፈናቀልን ለማስቆም ቃል ቢገባም፣ በተለይ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የመጠለያ ጣቢያዎችን አጨናንቀዋል፡፡ እስካለፈው ሳምንት መጀመርያ ድረስም ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 67 ሺሕ እንደደረሰ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉት የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር በርካታ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ የሶማሌ ተወላጆችም በመከላከያ ሠራዊት ዕገዛ ከኦሮሚያ ክልል ወደ ሶማሌ ክልል ተጓጉዘዋል፡፡    

ከሳምንታት በፊት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ፣ እንዲሁም የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ መፈናቀሉ በአስቸኳይ እንደሚቆም ቃል መገባቱ ይታወሳል፡፡

ሪፖርተር ሐረር ከተማ መግቢያ ላይ በተለምዶ ሃማሬሳ በሚባል ሥፍራ የሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ለሦስት ቀናት ተገኝቶ ማረጋገጥ እንደቻለው፣ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ነበር፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌ ክልል ብቻ ሳይሆን፣ ከሶማሌላንድ (ሐረጌሳ) ሳይቀር እየተፈናቀሉ ሲመጡ ነበር፡፡

ከመስከረም 14 እስከ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በሥፍራው ተገኝቶ ለመታዘብ እንደቻለው፣ የተፈናቃዮች ቁጥር በመጠለያ ጣቢያው በየቀኑ እየጨመረ ነበር፡፡ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ መውጫ ላይ የሚገኘው መጠለያ ጣቢያ መጀመርያ ለፋብሪካዎች ለሼድነት እንደያገለግል ተብሎ የተገነባ ቢሆንም፣ አሁን በተፈጠረው ያልተጠበቀ ችግር ወደ መጠለያነት ተቀይሯል፡፡

ሪፖርተር በነበረባቸው ቀናት ብቻ መጠለያ ጣቢያው በአማካይ 3,500 ያህል በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ይዞ ነበር፡፡ እየጨመረ ካለው የተፈናቃዮች ቁጥር የማይመጣጠን ነው፡፡ ይኼ ጣቢያ ሁለት የጉድጓድ መፀዳጃዎችና አንድ አነስተኛ ክሊኒክ በውስጡ ይዟል፡፡

በየጊዜው በሚቀያየሩ ሁኔታዎች ሳቢያ ጣቢያው በማደግ ላይ ያለውን የተፈናቃዮች ቁጥር ለማስተናግድ የአገልግሎትና የአቅርቦት እጥረት አለበት፡፡ ራይስ አባ ሜጫ ከሶማሌ ክልል እንደተፈናቀሉ ከሚነገርላቸው 67 ሺሕ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ቁጥር ግን እስከ መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ያለው ብቻ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የአራት ልጆች አባት የሆነው የ32 ዓመቱ ራይስ፣ ማፈናቀሉ ከጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እንደተደረገ፣ መስከረም 1፣ 2 እና 3 ቀን ተጠናክሮ እንደቀጠለም ያስታውሳል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ደግሞ መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሶማሌ ክልል የፀጥታ ኃይሎች የጉርሱም ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ ሦስት የኦሮሞ ተወላጆች ታፍነው እንደተወሰዱና እስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባና ስቃይ እንደሞቱ ገልጾ ነበር፡፡

ይኼንንም ተከትሎ ከአዲስ አበባ በ500 ኪሎ ሜትር ርቃ በሚገኘውና በጫት ምርቷ በምትታወቀው የአወዳይ ከተማ (ኦሮሚያ ክልል) የተደረገው ሰላማዊ ሠልፍ ግርግር ያስከተለ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ የከተማው ነዋሪ ለሆኑ የሶማሌ ተወላጆች መገደልም ምክንያት ሊሆን ችሏል፡፡

እነዚህም ተከታታይነት የነበራቸው ክስተቶች ብዙዎችን ከፍ ወዳለ የሕዝብ መፈናቀልና እንግልት እንደዳረጉ የእዚህ ችግር ተጠቂና እንደሆነና  የጅግጅጋ ከተማ ነዋሪ እንደነበር  የገለጸው የ32 ዓመቱ  ራይስ አባ ሜጫ አንዱ ነው፡፡  በሐረር ጊዜያዊ መጠለያ የሚገኘው ራይስ ከልጅነቱ ጀምሮ ዕድሜውን ያሳለፈው በጅግጅጋ እንደሆነ፣ ተፈናቅሎ እስከመጣበት ጊዜ ድረስም በንግድ ሥራ በመሰማራት የራሱንም ሆቴል ከፍቶ ይሠራ እንደነበር ይናገራል፡፡

‹‹ጅግጅጋን ብቻ ነበር የማውቀው፡፡ ቤቴ ብዬ የምቆጥረው ጅግጅጋን ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉንም አጣሁ፤›› በማለት ማፈናቀሉ በቡድን በቡድን በመጡ ሰዎች የተከናወነ ነው ይላል፡፡ ‹‹እነዚህ ሰዎች በየቤቱ እያንኳኩ የኦሮሞ ተወላጆች እንዳሉ ይጠይቁና ያጣሩ ነበር፤›› ያለው ራይስ፣ ሰዎቹ ከሴት የኦሮሞ ተወላጆች ይልቅ ወንዶቹ ላይ ጭካኔ ያሳዩ ነበር ብሏል፡፡

ይህ በሚሆንበት ጊዜ ባለቤቱን የሚኖሩበት ቤት ትቶ ሆቴል ውስጥ ለመደበቅ መገደዱን የሚናገረው ራይስ፣ እሱን ሆቴል ድረስ ለመፈለግ ሰዎች ቢመጡም የሚያውቃቸው የሶማሌ ተወላጆች ደብቀው ሕይወቱን እንዳተረፉለት ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

ራይስ ሆቴል በነበረበት ጊዜ መኖሪያ ቤቱ በአካባቢው በሚታወቅ የቀማኛ ቡድን ንብረቱንና ገንዘቡን ባለቤቱን በማፈራራት እንደወሰደበት፣ ይኼም ቀማኛ ቡድን ግርግሩ ከመፈጠሩ በፊት ተመሳሳይ የዝርፊያ ወንጀል ይፈጽም እንደነበር ገልጿል፡፡ ግርግሩ ከተፈጠረ በኋላ ይህ ቡድን በተለያዩ ቦታዎች ዝርፊያ ላይ ይሳተፍ እንደነበር ሪፖርተር ያናገራቸው ከክልሉ ተፈናቅለው የመጡ ግለሰቦች አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በትንሹ ከ12 እስከ 13 ግለሰቦች በሥሩ ያቀፈ ሌላ ቡድን በተለያዩ ሰዎች ጠቋሚነት የኦሮሞ ተወላጆች ቤት በመሄድ የድብደባና የማሰር ተግባራት ያከናውን እንደነበር ራይስ ተናግሯል፡፡ ከተደበቀበት ወጥቶ በመከላከያ ሠራዊት ዕርዳታ ከጅግጅጋ በሕይወት መውጣት የቻለው ራይስ፣ በመንገዱ የሰዎችን አስከሬን እንደተመለከተም አስረድቷል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ግጭቱ ከተፈጠረ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ የመከላከያ ሠራዊት ጣልቃ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ተፈጠረ የሚባለውን ግጭት ምክንያትና የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ በየትኛውም የመንግሥት አካል የተሰጠ መግለጫ የለም፡፡

ሪፖርተር ራይስን መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም. አግኝቶ ባነጋገረበት ወቅት፣ አብረውት ተፈናቅለው የመጡ ዜጎችንም አግኝቶ ለማነጋገር ችሏል፡፡ ራይስን ባገኘበት ጊዜ ከጓደኞቹ በተጨማሪ በየደቂቃው ሳል የሚተናነቃቸው ሁለት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው ልጆቹን ይዞ የነበረ ሲሆን፣ በመጠለያ ጣቢያው ያልተመቸ የአኗኗር ሁኔታ ምክንያት ተፈናቃዮቹ ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሪፖርተር መጠለያ ጣቢያውን በጎበኘበት ወቅት ሁለት መፀዳጃ ቤቶችና አንድ መለስተኛ ክሊኒክ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም እየጨመረ ካለው የተፈናቃዮች ቁጥር ጋር አይመጣጠንም፡፡

በመስከረም ወር የመጀመርያ ሳምንት በነበረው መፈናቀል 41 ሺሕ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ወደ ሐረር ከተማ የመጡ ሲሆን፣ በጊዜው በአራት የተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ተከፋፍለው እንዲጠለሉ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሳምንታት ቆይታ በኋላ አብዛኞቹ ተፈናቃዮች ቤተሰቦቻቸው ይገኙባቸዋል ወደተባሉ የኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሄዱ ተደርገዋል፡፡

እንደ ራይስ ያሉት፣ ወደ ቤተሰብ መሄድ ያልቻሉ ወይም ቤተሰብ የለንም ያሉ ግን ወደ መጠለያው እንዲመጡ ተደርገው፣ ሐረር ውስጥ የነበሩት ቀሪዎቹ ሦስት ጊዜያዊ መጠለያዎች አገልግሎት እንዲያቋርጡ ተደርጓል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ የራይስ ጓደኛ የሁለት ልጆች አባት የሆነው የ32 ዓመቱ  ስለሺ ሞቲ ይገኛል፡፡ ስለሺ ከደገሐቡር ከተማ ተፈናቅሎ የመጣ ሲሆን፣ በጊዜው በግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር ይናገራል፡፡ በነበረው ግርግር ከሌሎች 20 ሰዎች ጋር ተይዞ መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ እስር ቤት መላኩን ይናገራል፡፡ ከቀናት የእስር ቆይታ በኋላም ስለሺ አንድ በግል በሚያውቀው የ50 አለቃ ማዕረግ ያለው የመከላከያ ሠራዊት አባል ዕርዳታ ተለቆ፣ በብዙ እንግልት ሐረር መምጣቱን ተናግሯል፡፡ ቀሪዎቹ ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች ተከፋፍለው እንደተወሰዱ፣ ከዚያ በኋላ ምን እንደገጠማቸውና ከማንም ጋር መገናኘት እንዳልቻለ ስለሺ ተናግሯል፡፡

እነ ስለሺና ራይስ መጠለያ ጣቢያውን በተቀላቀሉ በሁለተኛው ሳምንት የተፈናቃዮች ጠያቂ ነን በሚሉ ሰዎችና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጥረት ነግሶ እንደነበር፣ በዚህም በተፈጠረ ግርግር የአንድ ተፈናቃይ ግለሰብ ሕይወት ሲያልፍ ዘጠኝ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጊዜው ግርግሩ በአጭሩ ባይቀጭ ኖሮ፣ ችግሩ አድጎ ለሐረር ከተማ ህልውና አሥጊ ሁኔታ ይፈጠር ነበር ሲሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሐረሪ ክልል አንድ የሥራ ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

የመጠለያ ጣቢያው ፀጥታ የተረጋጋ ቢሆንም፣ አሳሳቢ ጉዳዮች ተደቅነውበታል፡፡ ለምሳሌ ያህል በጤና በኩል በዋናነት እየሠራ ያለው የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ቢሮ፣ በየጊዜው የአዳዲስ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የመድኃኒት እጥረትና መሰል ችግሮች አጋጥመውታል፡፡

በመጠለያ ጣቢያው ያለው ሁኔታ በብዙ ተግዳሮቶች የተከበበ እንደሆነ ለሪፖርተር የተናገሩት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ አልዩ፣ የመድኃኒት እጥረት ዋነኛው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹መፈናቀሉ ያልተጠበቀና ተፈናቃዮችም ያፈሩትን ንብረት ሳይዙ መምጣታቸው የራሱ ተፅዕኖ አለው፤›› ብለው፣ ከመድኃኒት በተጨማሪ የፍራሽና የብርድ ልብስ እጥረትም መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ጤና ቢሮው መጠለያ ጣቢያው ውስጥ በሦስት ፈረቃዎች የሚሠሩ 15 ያህል የጤና ባለሙያዎች ማሰማራቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ቢሮው የተለየ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ተፈናቃዮች ለይቶ ለመርዳት እየሞከረ ነው፡፡ ለምሳሌ በመጠለያ ጣቢያው አምስት በምግብ እጥረት የተጠቁ ሕፃናት ጤና ጣቢያ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን፣ በማዕከሉ ውስጥ ያሉ 29 አጥቢዎች ደግሞ ተጨማሪ ምግቦችን እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እያለ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው ሲመጡ በመሣሪያ የተመቱ፣ በሳንጃና በመሳሰሉት ጉዳት የደረሰባቸው 25 ተፈናቃዮች በሕይወት ፋና ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆኑ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

ጤና ቢሮው ሐረር ከሚገኘው መጠለያ በተጨማሪ ከሐረር 90 ኪሎ ሜትር ርቃ ባለችው ጭናክሰን ከተማ ለሚገኘው መጠለያ ጣቢያም ዕገዛ ያደርጋል፡፡ እስካለፈው ሳምንት ድረስ በነበረው መረጃም የጭናክሰን መጠለያ ከ150 እስከ 200 ሰዎች አስተናግዷል፡፡

እየጨመረ ያለው የፍላጎት መጠን አሳሳቢ እንደሆነ አቶ አህመድ ያስረዳሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት 3,000 የኦሮሞ ተወላጆች ከሶማሌላንድ መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጾ ነበር፡፡

ነገር ግን ይኼም ቢሆን ቁጥሩ እየጨመረ ነበር፡፡ ጄላን ሰይድ ከሶማሌላንድ ከተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ ሲሆን፣ ለአንድ ዓመት በሐርጌሳ የራሱን የፀጉር ማስተካከያ ቤት ከፍቶ ሲሠራ እንደነበር ይናገራል፡፡

ሪፖርተር ጄላንን በሐረር ከተማ መናኸሪያ አካባቢ ወደ አዳማ ለመሄድ ሲዘጋጅ አግኝቶ ያናገረው ሲሆን፣ ከሐርጌሳ ሲፈናቀል የሶማሌላንድ ፖሊስ የኢትዮጵያ ተወላጆች በሚገኙባቸው ሠፈሮች እየዞረ ኦሮሞዎችን በማሰር ወደ አገራቸው እየላከ ነበር ብሏል፡፡ እሱም በዚህ መንገድ ታስሮ ወደ አገሩ እንደመጣ ገልጿል፡፡

ከሶማሌላንድ በቀጥታ ወደ ቶጎ ውጫሌ ካምፕ የተሻገረው ጄላን፣ የተለያዩ እንግልቶች ደርሰውበት ወደ ሐረር መድረስ መቻሉን፣ ወደ ጅግጅጋ በሚሻገርበት ጊዜ ያገኛቸው ሰዎች በሰጡት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የተማሪ መታወቂያ ተመሳስሎ የካራማራ ኬላን ማለፍ እንደቻለና ከጅግጅጋ ወደ ሐረር መሸጋገሩን ተናግሯል፡፡

ከሶማሌላንድ ምንም ንብረት ሳይዝ እንደተባረረ የሚናገረው ጄላን፣ ከሐረር ወደ አዳማ ለመምጣት የሚያስችለውን የጉዞ ወጪ የሸፈኑለት፣ አብረው የነበሩት ተጓዦች እንደነበሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

መፈናቀሉ በበርካታ ሺዎች የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ ተፅዕኖ የፈጠረ ሲሆን፣ የተሻለ የገቢ የነበራቸውን ግለሰቦችም በቀናት ልዩነት ወደ ተረጂነት መቀየሩ ይነገራል፡፡

ለ20 ዓመታት ጅግጅጋ እንደኖሩ የተናገሩት ሌላው ተፈናቃይ፣ በጅግጅጋ የራሳቸው መድኃኒት ቤት፣ መኪና፣ መኖሪያ ቤት እንደነበራቸውና ይህንን ሁሉ በአንዴ ጥለው እንደመጡ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከጅግጅጋ ከለበስኩት ልብስ፣ ነጠላ ጫማና ኪሴ ውስጥ ከነበረ 400 ብር ውጪ ባዶዬን ነው የወጣሁት፤›› ብለዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረው ችግር ከእዚህ ባለፈ በአካባቢው የጫት ንግድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በሐረር ከተማ የጫት ዋጋ ቅናሽ ሲያሳይ፣ ወደ ሶማሌላንድ ይላክ የነበረው ጫት ደግሞ በአብዛኛው ቆሟል፡፡

ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ 50 ብር የነበረው ከሐረር ጅግጅጋ የሕዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ፣ ተፈናቃዮቹ እስከ 500 ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸው ተነግሯል፡፡

መፈናቀሉን ተከትሎ የመጡ የሰብዓዊ ዕርዳታ ራስ ምታቶች

ከመፈናቀሉ ጋር በተያያዘ ተፅዕኖውን ለመቀነስ በፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር በአቶ ከበደ ጫኔ የሚመራ ኮሚቴ መቋቋሙ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ኮሚቴ ለተጎጂዎች የሚቀርቡ ዕርዳታዎችን በማሰባሰብና በማስተባበር ይሠራል፡፡ በአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር በአቶ ምትኩ ካሳ የሚመራ የቴክኒክ ኮሚቴ የችግሩን መጠን በማጥናት ከለጋሾች ጋር ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ ሲመክር ቆይቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከቀውሱ ባህርይ አኳያ የጥሬ ገንዘብ ዕርዳታ ሊሰጥ እንደሚችል ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መስከረም 17 እና 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ7,000 በላይ ተፈናቃዮችን የጫኑ 69 ተሽከርካሪዎች ሐረር ከተማ ገብተዋል፡፡ ‹‹ለዚህ የሚሆን ተጨማሪ ድንኳኖችን አሠርተናል፤›› ሲሉ አቶ አህመድ ለሪፖተር ተናግረዋል፡፡

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሶማሌ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ እስማኤልን ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ አግኝቶ ለማነጋገር ቢቻልም፣ አቶ እድሪስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ታቅበዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...