Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትስፖርታዊ ጨዋነትና እግር ኳሱ የሚፈልጉት ለየቅል የሆነበት የክለቦች የውይይት መድረክ

ስፖርታዊ ጨዋነትና እግር ኳሱ የሚፈልጉት ለየቅል የሆነበት የክለቦች የውይይት መድረክ

ቀን:

  • የተጨዋቾች የዝውውር ክፍያና አሠራር ክትትል እየተደረገበት መሆኑም ተነግሯል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያከናውናቸው ዋነኛ ተግባራት አንዱ አዲስ የውድድር ዓመት ሲጀመር የድልድል ዕጣ ማውጣት ይጠቀሳል፡፡ በዚሁ ፕሮግራም ላይ ያለፈውን ዓመት የዘርፉን እንስቃሴዎች መቃኘት፣ የተገኙ ውጤቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መገምገም ላይ ያተኩራል፡፡

በዚህ መሠረት ሰኞ መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል በተከናወነ የ2010 ዓ.ም. መርሐ ግብር ዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓትና የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተከናውኖ ነበር፡፡

ምንም እንኳን የ2009 ዓ.ም. ዕቅድ በሚገመገምበት ወቅት የክለብ ኃላፊዎችና ተወካዮች ለአገሪቱ ስፖርት ስላበረከቱት ወይም ስለሚያበረክቱት ስትራቴጅካዊ ዕቅድና አፈጻጸም ከመወያየትና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የጠራ አቋም ከመያዝ ይልቅ፣ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ‹‹የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ›› ዓይነት በሰበብ የተሞላ፣ ሌላኛውን ወገን ከመውቀስና ለተፈጠሩት ችግሮችም ሆነ ስኬቶች የራስን ኃላፊነት ከመውሰድ ይልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ላይ በማሳበብ ያተኮረ ሆኖ ተጠናቋል፡፡

በዕለቱ የአገልግሎት ጊዜውን ያጠናቀቀው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አመራር ክለቦች ከ2010 እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የሚተዳደሩበትን ረቂቅ የውድድር ደንብ በስምንት ምዕራፎች ከፋፍሎ ተሳታፊዎች እንዲወያዩበት አድርጓል፡፡ ከቀረቡት የውድድር ደንቦች መካከል በዓይነታቸውም ሆነ በይዘታቸው ለየት ብለው ከቀረቡት ውስጥ የተጨዋቾች የአደጋና የሕይወት መድን ዋስትና፣ እንዲሁም በውድድር የጨዋታ አመራሮች የሕይወት መድን ዋስትና፣ የተጨዋቾች ምዝገባ፣ ተገቢነት፣ ዝውውር፣ ውሰትና ሌሎችም የተሳታፊዎችን የስፖርት አመራር ብቃትና ብስለት የሚጠይቁ የነበሩ ቢሆንም፣ በነካ ነካ ታልፈዋል፡፡

ከእነዚህ ጉዳዮች ይልቅ ‹‹መውጣትና መውረድ›› እንዲሁም የዳኝነት ክፍተቶች የሚሉት ነጥቦች ብዙ ጊዜ ወስደው አነጋግረዋል፡፡ ቡድን እንዴትና ለምን እንደሚቋቋም? ፋይዳው ጭምር ያልገባቸው መስለው የቀረቡት እነዚሁ አመራሮች ክለባቸው እንዳይወርድ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ከማቀድና ከመሥራት ይልቅ፣ መውረድ ለክለቦች መፍረስ ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ አበክረው ሲከራከሩ የተደመጡበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ በረቂቅ ደንቡ በ2010 የውድድር ዓመት ከፕሪሚየር ሊጉ አራት ወርደው ከከፍተኛ ሊግ ደግሞ አራት እንዲያድጉ ብሎ ያቀረበው መነሻ ጽሑፍ ከመድረኩ በገጠመው ተቃውሞ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ቀድሞ በነበረው መሠረት ሦስት ወርዶ ሦስት እንዲመጣ የሚለው እንዲፀና ተወስኗል፡፡

በውይይቱ 16ቱም የፕሪሚየር ሊግ ክለብ ተወካይዎች ተሳትፈዋል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው የአገሪቱ እግር ኳስ በአሁኑ ወቅት በምን ዓይነት የውጤት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ በአግባቡ የተረዱ የሚመስሉት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ለእግር ኳሱ ውድቀት ምክንያት ተደርጎ በብዙዎቹ አስተያየት ሲቀርብበት የነበረው የእግር ኳስ ዳኞች ስህተትና ስህተት ብቻ ነበር፡፡ ይሁንና ከተሳታፊዎቹ በጣም ጥቂቶቹ ካልሆኑ ብዙዎቹ የሚያስተዳድሯቸው ክለቦች መዋቅራዊ ይዘታቸው፣ የፋይናንስ ሥርዓታቸው፣ ወቅታዊ ብቃታቸው፣ አሠራራቸው፣ የሚጠቀሙት የሰው ኃይልና ለምን እንደተቋቋሙ እንኳን በውል የሚያውቁ ለመሆናቸው መድረክ ላይ ደግመው ደጋግመው የሚያነሷቸው ነጥቦች ማሳያ ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ ለዚሁ አጀንዳ ብለው ረዥም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የመጡ ናቸው፡፡ ይሁንና ለውይይቱ ግብዓት የሚሆኑ ነጥቦች ሲነሱ እንኳ ሳይቀር፣ ለምን አይበቃም በሚል በመድረክ መሪዎች ላይ ተቃውሞ የሚያሰሙ እንደነበሩም ታይቷል፡፡

የመድረኩ አስፈላጊነት

የውይይት ዋነኛ ዓላማ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና ክለቦች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ ያዘጋጇቸው ዓመታዊ የውድድር መርሐ ግብሮች እንደተጠበቁ፣ የነበሩባቸውን ደካማና ጠንካራ ጎን ምን እንደነበሩ በመገምገም ለቀጣዩ የውድድር ዓመት የተሻለ የውድድር ሥርዓት ለመፍጠር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ መድረክ ይመጥናሉ ተብሎ የሚታመንባቸው የክለብ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሊሰጡ የሚችሉ መሆን እንዳለበት ጭምር ይታመናል፡፡

ይሁን እንጂ የአንድን ክለብ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን በሚያስችል እንዲህ ዓይነቱ መድረክ ላይ መታደምና መገኘት የሚገባቸው ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክተው ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ብዙዎቹ የክለብ ተወካዮች በውይይቱ በተለይም ውሳኔ የሚሹ ነጥቦች ሲያጋጥሙ፣ ጉዳዩን ከፍተኛ አመራሮች ሊመክሩበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ መደመጣቸው ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ ተሳታፊዎች፣ በየዓመቱ እንዲህ በመሳሰሉ መድረኮች መገኘት የሚገባቸው የክለብ አመራሮች አይገኙም፡፡ ለዚህም ነው በየዓመቱ ተመሳሳይ ውይይቶች ተደርገው ትክክለኛ የመፍትሔ አቅጣጫ የማይቀመጥላቸው ሲሉ ችግሩን ይጠቁማሉ፡፡ ፌዴሬሽኑም ይህንን መድረክ ሲያመቻች ሁሉም የክለብ መሪዎች እንዲገኙና ችግሮች ብለው በሚያምኑባቸው ነጥቦች ላይ ውይይት አድርጎ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል፡፡

ይህ ባለመሆኑ በየዓመቱ የሚወጡ ደንብና መመርያዎች፣ እንዲሁም ሌሎች አስገዳጅ ሕጎች በአተገባበራቸው ተፈጻሚነት ላይ አከራካሪ ነገሮችን እያስከተሉ እንደቀጠሉ ዘልቋል፡፡ ባለው ሁኔታ ችግሩ ላለመቀጠሉ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ እንደሌለም አስተያየት ሰጪዎቹ ይናራሉ፡፡  

ለ2010 የውድድር ዓመት በወጣው ዕጣ መሠረት የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከሐዋሳ ከተማ ጅማ ላይ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና አዲስ አበባ ላይ፣ አርባ ምንጭ ከተማ ከመቐለ ከተማ አርባ ምንጭ ላይ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከፋሲል ከተማ አዲግራት ላይ፣ ወልዲያ ከተማ ከአዳማ ከተማ ወልዲያ ላይ፣ ደደቢት ከወላይታ ድቻና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመከላከያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጥቅም 27 እና 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ መርሐ ግብሩን ለመጀመር አስቦ የነበረበት ቀን ጥቅምት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ጥቅምት 11 እንዲዘዋወር ተደርጎ ሳለ ነው እንደገና ወደ 27 እና 28 ቀን 2010 እንዲቀየር የተደረገው፡፡ በተመሳሳይ የሴቶች አንደኛና ሁለተኛ ዲቪዚዮን በሁለት ምድብ በእያንዳንዱ አሥር አሥር ቡድኖች የተደለደሉበት የጨዋታ ፕሮግራምም ይፋ ሆኗል፡፡

በክለቦች ብዙም ትኩረት ያላገኛው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልና አደጋው

ባለፈው ዓመትም ሆነ ከዚያ በፊት በተከናወኑ የውድድር ዓመታት ከስፖርቱ ባህሪ ጋር አብረው የማይሄዱ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ሲከሰቱ ነበር፡፡ በዚህም ያልታሰበና ያልተጠበቀ የንብረትና የሕይወት ጉዳት ደርሷል፡፡ የጨዋታ ፕሮግራሞች እየተስተጓጎሉ ቡድኖች ላላስፈላጊ ወጪ ሲዳረጉ ቆይቷል፡፡

የተለያዩ መድረኮች ተፈጥረው ይመለከተናል የሚሉ አካላት የተወያዩበት ቢሆንም ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየባሰ ስፖርቱ ለኅብረተሰቡ ከሚያበረክተው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ ይልቅ የንትርክና የውዝጋብ መንስዔ ሆኖም ቆይቷል፡፡ ይኼ ጥሬ ሀቅ በተለይ ባለፈው የውድድር ዓመት ምልክት ብቻ ሳይሆን በተግባር ታይቷል፡፡

መስከረም 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በጁፒተር ሆቴል ከተዘጋጀው የ2010 ዓ.ም. የዕጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በተጨማሪ፣ የ2009 የውድድር ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ ካቀረበው አጀንዳ መካከል የፌዴሬሽኑ የፀጥታና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ ለውይይት ያቀረበው ሪፖርት ይጠቀሳል፡፡ ይሁንና ሪፖርቱ ለተሳታፊዎች በንባብ ካልሆነ ለእያንዳንዳቸው እንዲደርስ አልተደረገም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ሪፖርቱ ለእያንዳንዱ ክለብ ሊደርስ እንደሚገባ በመግለጽ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡ የፀጥታና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በበኩሉ የቀረበው  ቅሬታ አግባብነት ያለው መሆኑን ተቀብሎ፣ ሪፖርቱ በፌዴሬሽኑ በኩል እንዲደርስ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡

እንደዚያም ሆኖ ክለቦች በፀጥታና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው የቀረበውን ሪፖርት የተመለከቱበት አግባብ የሚያስተዛዝብም የሚያሳዝንም ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ሪፖርቱ የተጋነነ ስለመሆኑ ጭምር አፋቸውን ሞልተው ሲናገሩ የተደመጡም አሉ፡፡ ባለፈው የውድድር ዓመት ብዙዎቹ የክለብ አመራሮች ከጨዋታ ሜዳ ውጭ  የተከሰቱት ቀርቶ ሜዳ ላይ የነበረውን ብቻ በመውሰድ ብዙ ሊያወሩበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ወስደው ሲከራከሩበት የነበረው ‹‹መውጣትና መውረድ›› በሚለው ዙሪያ መሆኑ የኮሚቴው አባላት ሲገረሙ ታይቷል፡፡ ይህም ገረመታ የፈጠረባቸው ነበሩ፡፡

በዚህ መሠረት በውይይቱ ከታደሙት የፀጥታና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው አባላት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሽመልስ ሽፈራው በጉዳዩ፣ ‹‹ለምን ራሳችንን እናታልላለን?›› በማለት በተለይም የችግሩ ዋነኛ መንስዔ ነበሩ ብለው ያመኑባቸውን ክለቦች ስም ሳይቀር ጠቅሰው ትዝብታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ፣ በእነዚህና በሌሎችም መድረኮች የጋራ መፍትሔ ይበጅለታል በሚል ካልሆነ በስተቀር በ2009 የውድድር ዓመት የተከሰተው የፀጥታ ጉዳይ በሪፖርቱ ከተካተተውም በላይ እጅግ አሳሳቢ እንደነበር ጭምር ነው የተናገሩት፡፡

‹‹አትነሳም ወይ እያሉ ብሔር እየጠቀሱ የክለብ ደጋፊ ነን በሚሉ ደጋፊዎች አማካይነት ሲፈጠሩ የነበሩ ችግሮችና ግጭቶች ያስከተሉትን ጉዳት ምን ያህሎቻችን ነን የማናውቀው? ችግሩን 50 በመቶ እንኳ ያላካተተ ሪፖርት እንዴት አድርገን ነው የተጋነነ ነው ብለን በዚህ መድረክ የምንናገረው? የእግር ኳሱ ዓለም አቀፋዊ ባህሪና መገለጫውስ ምንድነው? እግር ኳሱን ጨምሮ ስፖርት ከፖለቲካ፣ ከዘር፣ ከሃይማኖትና መሰል ነገሮች ውጪ ነው  ብለን አይደለም እንዴ የምንናገረው? ለምንድነው እያወቅን እንዳላወቀ የምናስመስለው? ለምንድነው እዚህ መድረክ ላይ ችግሩን ደፍረን ተነጋግረንበት መፍትሔ የማናስቀምጥለት?›› በማለት ኮሚሽነሩ በጉዳዩ የክለቦችን ቸልተኝነት ተችተዋል፡፡

ለውይይቱ ማጠቃለያ የሰጡት የኢትዮጶያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ በበኩላቸው፣ ስፖርቱ ኮሚሽነሩ እንዳሉት የራሱ ቋንቋ እንዳለውና በዚያ ላይ ተመሥርቶ መነጋገር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሲቀጥሉ፣ ‹‹እግር ኳሱ ውስጥ በአመራርነትም ሆነ በሌላ የሥራ ኃላፊነት የምንሠራ ፖለቲከኞች፣ የፓርላማ አባላትና ሌሎችም ልንኖር እንችላለን፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ልንነጋገር የሚገባን በእግር ኳሱ ቋንቋና ቋንቋ ብቻ ሊሆን ይገባል፤›› ብለው፣ ፖለቲካው ራሱን የቻለ የራሱ መድረክ እንዳለው በመግለጽ ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚታየውን ጣልቃ ገብነት ጭምር ተችተዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ከስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ጀምሮ ሌሎችንም በርካታ ችግሮች በአንድ ቀን ጀምር መፍታት ይቻላል ብለው እንደማያምኑ፣ ነገር ግን እንደነዚህ የመሳሰሉ መድረኮች አስፈላጊነት ለእግር ኳሱ ዕድገት እስከሆነ ድረስ የመፍትሔው አካል የማይሆኑበት ምክንያት እንደሌለ ጭምር ነው ያስረዱት፡፡

ከሜዳና መሰል ችግሮች ጋር ተያይዞ ክለቦች ላነሱት ጥያቄና ቅሬታ አቶ ጁነዲን፣ ‹‹እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የአገራችን ክለቦች በካፍና በፊፋ ስታንዳርድ አሁን በሚገኙበት ደረጃ ከወልዲያ ከተማ በስተቀር አንዳቸውም አይኖሩም፡፡ መሆን ያለበት እንደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ችግሮቻችንን የሁላችንም አድርገን መውሰድና የጋራ የመፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጥን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ይህ ባልሆነበት በመወነጃጀል ብቻ የትም አንደርስም፤›› በማለት ነበር የችግሩን ዘርፈ ብዙነት ያብራሩት፡፡

ሌላው መድረኩ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው በፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረ ሥላሴ የተነገረው፣ ክለቦች ተጨዋቾችን የሚያዘዋውሩበት አሠራርና ከዝውውሩ መንግሥት ሊያገኘው የሚገባው የገንዘብ ጥቅም ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ እንደ ውድድር ዳይሬክተሩ ከሆነ፣ ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የሆነ የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብ ይወጣል፡፡ ይሁንና ይህ ገንዘብ በተለይም ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው የሚከፍሉት የፊርማም ሆነ ወርኃዊ ክፍያ በምን ዓይነት የሕግ አግባብ እንደሚከፍሉ፣ ከክፍያውም ለመንግሥት ገቢ የሚደረገው ጥቅም የት ቦታና ለማን እንደሚከፈል መንግሥት በፌዴሬሽኑ በኩል ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑ ተነግሯል፡፡         

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...