- ባቱ ኮንስትራክሽንና የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ያላግባብ ጥቅም ማግኘታቸው ተገልጿል
በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በተለያዩ ጊዜያት ሥራ አስኪያጅና በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ ዘጠኝ ተከሳሾች፣ ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠርና ጥቅም ለማግኘት በማሰብ፣ ያላግባብ ክፍያ በመፈጸማቸው በፋብሪካው ላይ በድምሩ ከ96.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት አድርሰዋል ተብለው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መስከረም 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው፣ በፋብሪካው በተለያዩ ጊዜያት ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በአቶ አበበ ተስፋዬና አቶ ፈለቀ ታደሰ፣ የእርሻ ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ በጋሻው፣ የመሬት ልማትና ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ወንድማገኝ ታፈሰና የመሬት ልማት ዝግጅት ሱፐርቫይዘር አቶ ሰለሞን ገነቱ ሲሆኑ፣ በአንድ የክስ መዝገብ የቀረቡ ናቸው፡፡
አቶ አበበ ተስፋዬ በድጋሚ በተካተቱበት ሁለተኛው የክስ መዝገብ ደግሞ፣ የፋብሪካው ኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ዘነበ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ድምፁ፣ የጠቅላላ ሒሳብ ክፍል ኃላፊ አቶ ቢልልኝ ጣሰውና የየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የማነ ግርማይ ላይ ዓቃቤ ሕግ ክሱን አቅርቧል፡፡
ኃላፊዎቹ በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲሠሩ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና ያላግባብ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ባቱ ኮንስትራክሽን አክሲዮን ማኅበር፣ ለሸንኮራ መትከያ የሚሆን የመሬት ድልዳሎ ሥራ ለማከናወን ከተዋዋለው ውጪ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ባቱ ኮንስትራክሽን የመሬት ድልዳሎውን በጥራት ሠርቶ ማስረከብ እንዳለበት በውሉ የተገለጸ ቢሆንም፣ የፋብሪካው ኃላፊዎች ግን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የግዥ አፈጻጸም መመርያን ወደ ጎን በመተው ማኅበሩ በተሻለ ጥራት፣ ፍጥነትና ዋጋ መሥራቱን ሳያረጋግጡ በ24,184,500 ብር ውል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ባቱ ኮንስትራክሽን ሥራውን በተፈለገው ጥራትና ፍጥነት ባለመሥራቱ፣ በፋብሪካው ሠራተኞችና ማሽነሪዎች ሥራው በድጋሚ እንደሚሠራ ኃላፊዎቹ እያወቁ፣ የ19,550,000 ብር እና የ8,807,465 ብር ውል በተደጋጋሚ እንዲፈረም በማድረግ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመርያ መሠረት ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች በቀጥታ ግዥ የግንባታ ሥራ ወይም አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ኃላፊዎቹ እያወቁ፣ ባቱ ኮንስትራክሽን የተረከበውን የመሬት ድልዳሎ ሠርቶ ማስረከብ አለመቻሉን እያወቁ፣ የ29,691,551 ብር ሌላ ተጨማሪ የሥራ ውል መፈጸማቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ ባቱ ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጋር የመሬት ድልዳሎ ለመሥራት በገባው ውል መሠረት የሠራው 3,321.392 ሔክታር ሆኖ ሳለ፣ 225,832 ሔክታር በመጨመር 6,705,302 ብር ክፍያ እንዲፈጽምለት በማድረግ ኃላፊዎቹ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡
የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኃላፊዎች ሌላው በፋብሪካው ላይ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉት፣ ከፋብሪካው ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ለሌለው የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ በመክፈል መሆኑ ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛ የክስ መዝገቡ አስፍሯል፡፡ ፋብሪካውን ለመገንባት ውል የፈጸመው ኦአይኤ (OIA) የሚባል ተቋራጭ ሲሆን፣ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭና ሲምፕሌክስ ኢንፍራስትራክቸርስ ሊሚትድ ንዑስ ተቋራጭ እንደነበሩ የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡ ፋብሪካው ከባንክ በወለድ በተበደረው 31,856,000 ብር ሲሚንቶ የገዛ ቢሆንም፣ ከፋብሪካው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ለሌላቸው የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭና ሲምፕሌክስ ኢንፍራስትራክቸርስ፣ በገቢና ወጪ ላይ ርክክብ ሳይደረግ በፋብሪካው ኃላፊዎች ትዕዛዝ እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ድርጅቶቹ በወሰዱት ሲሚንቶ ዋጋ ላይ ወለዱን 3,657,639 ብር ጨምረው መመለስ ሲገባቸው፣ ዋናውን ዋጋ ብቻ በመክፈላቸው ጉዳት መድረሱን አክሏል፡፡
በተጨማሪም ፋብሪካው በባንክ ብድር በ31,732,195 ብር የገዛውን አርማታ ብረት ለየማነ ጠቅላላ ተቋራጭ እንዲሰጠው ከተደረገ በኋላ፣ ገንዘቡን ሲመልስ ጨምሮ መመለስ የነበረበትን 4,265,721 ብር ሳይጨምር በመመለሱ፣ የተጠቀሰውን ያህል ጉዳት በፋብሪካው ላይ በመድረሱ ኃላፊዎቹ ተጠያቂ መሆናቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ልዩ የጥቅም ተካፋይ በመሆንና የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ በተከሳሾቹ ላይ የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ የዋስትና መብታቸው ላይ ክልከላ ስለሚጥል በማረሚያ ቤት ሆነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡