የፌዴራሉ መንግሥት በተለያዩ ተቋማቶች ተይዘው የነበሩ መሬቶችን በመረከብ፣ ሦስት ሺሕ ሔክታር መሬት ለአበባና ለአትክልትና ፍራፍሬ (ሆርቲካልቸር) የልማት ዘርፍ እንዲውል መወሰኑ ተሰማ፡፡
የፌዴራል መንግሥት ወደዚህ የመሬት ይዞታ የማሰባሰብ ግዴታ ውስጥ የገባው፣ የክልል መንግሥታት ለአበባና ለአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ልማት መሬት አዘጋጅተው ለማቅረብ ፈቃደኝነት ባለማሳየታቸው መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በዚህ ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ ከመንግሥት የልማት አደረጃጀቶችና እርሻዎች ጥቅም ላይ ያልዋሉ የመሬት ይዞታዎች ተሰብስበው ለሆርቲካልቸር አልሚዎች እንዲሰጥ በተወሰነው መሠረት፣ ሦስት ሺሕ ሔክታር መሬት መገኘቱን ከሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
መሬቱ የተሰበሰበው ከአላጌ የእርሻ ልማት፣ ከአርባ ምንጭ፣ ከደቡብ ኦሞ እርሻ ልማትና ባህር ዳር ከሚገኙ የመንግሥት ይዞታዎች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህም ምክንያት የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች የመሬት ጥያቄ እያቀረቡ ነው ተብሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዝዋይ የሚገኘው ሼር ኢትዮጵያ በአቅራቢያው ከሚገኘው አላጌ እርሻ ልማት መሬት ለማግኘት ጥያቄ ማቅረቡን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በአጭር ዓመታት ውስጥ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ መገኛ ምንጭ የሆነው የሆርቲካልቸር ዘርፍ፣ በ2009 ዓ.ም. መጨረሻ 271 ሚሊዮን ዶላር ማስገኘቱ ታውቋል፡፡