Thursday, September 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

  የሳምንቱ ገጠመኝ

  ቀን:

  የፌስቡክ ገጼን ከፍቼ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማየት ላይ ሳለሁ አንዲት ጓደኛዬ ደወለችልኝ፡፡ የተለመደውን ሰላምታ ተለዋውጠን ወጋችንን ስንቀጥል በመሀል፣ ‹‹እስኪ ፖለቲካው ሠፈር ውስጥ ያሉ ሰዎች የሚባባሉትን ተመልከች፤›› ብላኝ፣ አጣዳፊ ሥራ እንዳላት ከነገረችኝ በኋላ ስልኩን ዘጋችው፡፡ ሁሌም እንደማደርገው የተለመዱትን የዳያስፖራ ወገኖቻችንን ጽሑፎች ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ያው አሰልቺው በነገር መተነኳኮሱ እንዳለ ቀጥሏል፡፡ ዘርን፣ ሃይማኖትንና አመለካከትን በተመለከተ አሳዛኝ ስድቦችም እንዲሁ ተባብሰዋል፡፡

  አንደኛው አሽሙረኛ፣ ‹‹እነ እከሌ የእነ እንቶኔን ሐሳብ መደገፋቸው ይገርማል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለካ አንድ ናቸው?›› ብሎ የጀመረው ነቆራ አንዱን ‹‹ፖለቲከኛ ነኝ›› ባይ የዘመናችን ነገረኛ አሳብዶታል፡፡ አሽሙረኛው ለሐሳብና ለአመለካከት ነፃነት ራሱን ጠበቃ አድርጎ ቢሰይምም፣ ሰዎች አንዳንዴ በጋራ ጉዳይ ላይ በመግባባታቸው ምን ያሳብደዋል? ለምንስ የሰውን ነፃነት ይጋፋል? ያኛውስ ጊዜ ያለፈበትን ተረት አይሉት ታሪክ እያነሳና እየጣለ እከሌን ከእከሌ ሳይለይ መሳደቡና ያ ሁሉ ድንፋታው ምን ይባላል? ‹‹የጋራ ጠላታችን›› በሚሉት ላይ ዓይናቸውን ሳያሹ የሚረባረቡት እነዚህ የኢንተርኔት ‹‹አርበኞች››፣ እርስ በርስ የማያግባባቸው ነገር ሲከሰትም ማሳለፍ የሚባል ነገር አያውቁም፡፡ እንደ ጅብ ይዘነጣጠላሉ፡፡ እነሱ ለሐሳብ ነፃነት ቆመናል ቢሉም በሐሳብ የሚለያቸውን የገባበት ገብተው ከማጥፋት አይመለሱም፡፡ ‹እባብ የልቡን ዓይቶ እግር ነሳው› ማለት እነዚህን ነበር፡፡

  ፊደል ቆጥረዋል የሚባሉት እነዚህ የዳያስፖራ ፖለቲከኞቻችን የሊበራል ዴሞክራሲ በሚቀነቀንባቸውና የሰው ልጆች መብት በሚከበርባቸው አገሮች ውስጥ እየኖሩ፣ ከአንድ የኋላቀር አገር አምባገነን መሪ በማይሻል የዕብድ ጭንቅላት ሲሰዳደቡ ያሳፍሩኛል፡፡ እንዲህ ባለ ጊዜ ያለፍኩበትን ዘመን ሳሰላስል የእኔ ትውልድ አባላት የነበሩት በተለይ ላመኑበት ዓላማ መሳካት ራሳቸውን በከፍተኛ ዲሲፕሊን አስገዝተው ከፍተኛ መስዋዕትነትና መከራ የተቀበሉ ወጣቶችን እያሰብኩ አዝናለሁ፡፡ እነዚህ የዚህ ዘመን ‹‹ፖለቲከኛ ነኝ›› ባዮች ግን የረባ ነገር እንኳ ያነበቡ አይመስሉኝም፡፡ ከመከነ አዕምሮዋቸው የሚወጣው ስድብና ዘለፋ አንዳንዴ ሰው መሆናቸውን ያጠራጥረኛል፡፡

  በአንድ ወቅት አሜሪካ ለስብሰባ በሄድኩበት ጊዜ ብዙ የታዘብኳቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ እኔ እዚያ ሄጄ የነበረው ከተለያዩ የአፍሪካና የእስያ አገሮች የጤና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ሆኜ ነው፡፡ በዋሽንግተን ዲሲ የተካሄደው የ15 ቀናት ስብሰባ ከተጠቃለለ በኋላ፣ ለአንድ ወር ያህል እዚያ ቆይታ አድርጌ ነበር፡፡ ከብዙዎቹ ከአፍሪካ ከመጡ የስብሰባ ታዳሚዎች ጋር ጓደኝነት መሥርቼ ስለነበር፣ አሜሪካ ከሚኖሩ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው ጋር ሲያስተዋውቁኝ ሁሉም ማለት ይቻላል የዩኒቨርሲቲዎችን ደጃፍ የረገጡና ጥሩ ሥራ ያላቸው ናቸው፡፡ በጣም በርካቶችም በትምህርት ላይ እንደሚገኙ ነው የተረዳሁት፡፡ የእኛዎቹ ሰዎች ግን ‹‹ተከድኖ ይብሰል›› ማለት ይቀላል፡፡ እዚያ አገር ከተወለዱት በስተቀር፣ በአብዛኛው ትምህርት አካባቢ የሉም ማለት ይቻላል፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር በረባ እንግሊዝኛ የሚግባቡት በጣም ትንሽ ናቸው፡፡

  በቀደም ዕለት ፌስቡክ ላይ ሆኜ እነዚያን አስፈሪና አሳፋሪ ስድቦች ስመለከት ይኼ ነበር የመጣልኝ፡፡ ምንም እንኳ ስደት ለሰው ልጆች የማይመችና ብዙ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም፣ አሜሪካ ተቀምጦ አለመማር ወይም መማር አለመፈለግ ያናድዳል፡፡ የተማሩትማ የአገሩን የፖለቲካ የውኃ ልክ ያውቃሉ፡፡ ሲስተሙ እንዴት እንደሚመራ ይረዳሉ፡፡ አፍ እላፊ ከሚያመጣው ስድብና ዘለፋ ታቅበው ለሐሳብ ሙግት ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉት ግን ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት አፈንግጠው የሰውን ልጅ ዘር ማንዘር እየጠሩ ይሳደባሉ፡፡ ማንነታችንን ያጎድፋሉ፡፡ የአገራችንን ቱባ ባህላዊ እሴቶች ወደ ጎን እየገፉ በብልግና ያጥረገርጉናል፡፡

  በተነፃፃሪ ደህና ግንዛቤ አላቸው ብለን የምናስባቸው አንዳንድ ጋዜጠኞች  የሚቀርበው የግለሰቦች የወሲብ ጉዳይ ያናደደኝ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ምራቃቸውን የዋጡ የሚባሉ የአንድ ሬዲዮ ጣቢያ ሰዎች አንድ የፕሮቴስታንት ዘማሪና አንዲት ሴት ከትዳር ውጪ መማገጣቸውን በሚመለከት ያቀረቡት ሐተታ፣ ዳያስፖራው አካባቢ ያለውን ችግር ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች ከግለሰቦቹ በስተጀርባ ያሉ የትዳር አጋሮችን፣ ልጆችን፣ ወላጆችን፣ ወንድምና እህቶችን፣ ወዳጆችንና ዘመዶችን ቢያገናዝቡ ኖሮ ይህ ዓይነቱን ስህተት አይፈጽሙም ነበር፡፡ እዚህ ፈሪኃ እግዚአብሔር ያለበት አገር ውስጥ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ይደረግ ነበር? በፍፁም፡፡ እዚያ ዳያስፖራ መንደር ግን ሁሌም ችግር ስላለ ነውር የሆነ ነገር አልታወቅም ብሏል፡፡ ይኼም ያሳፍራል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ግራ ያጋባል፡፡

  የፌስቡካቸውን፣ የሬዲዮናቸውንና የቴሌቪዥናቸውን ሁሉንም ነገር እንከታተል ብንል የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ጉዳይ በጣም ያሳዝናል፡፡ ጥቂቶች እንደፈለጋቸው የሚጋልቡበት ፖለቲካ ደግሞ ያሳፍራል፡፡ ብዙኃኑ አንገታቸውን ደፍተው ከእዚህ ወይም ከእዚያ ጎራ ላለመፈረጅ ሲሉ ድምፃቸው አይሰማም፡፡ እነዚያ ጥቂቶቹ ግን በደመነፍስ የሚፈጽሙት ድርጊት አገርን እንደ ግለሰብ ያሳብዳል፡፡ በሐሳብ መለያየትን እንደ ፀጋ መቁጠር ያቃታቸው እነዚያ ጥቂቶች ስድባቸው፣ ዘለፋቸው፣ ሐኬታቸውና ትዕቢታቸው ለዚህች አገር አይመጥንም፡፡ የፌስቡክ ስድድቡ ሲሰለቸኝ እዚያች ጓደኛዬ ዘንድ ደውዬ፣ ‹‹ኧረ እባክሽ ሰለቸኝ ይኼ ጉድ?›› ስላት፣ ‹‹የዝቅጠት ምልክቱ ከሰውነት ወርዶ አውሬ መሆን ነው፤›› አለችኝ፡፡ ድሮስ ከዝቅጠት ምን ይጠበቃል? ከካንሰር ሕመም የማይተናነሰው የዳያስፖራዎቻችን ዕብደት ሕክምና አያስፈልገውም ትላላችሁ? እኔ በበኩሌ በጣም ሰለቸኝ፡፡ እዚህ ላይ ግን ፌስቡክን ጥሩ የሐሳብ ማቀባበያና የበርካታ ጥቅሞች ማስገኛ ያደረጉ መኖራቸውን አልረሳሁም፡፡ እዚህ እኛ አገር እጅግ ምጡቅ ሐሳበችን በሠለጠነና በሚገርም አተያይ የሚተርኩልን የዘመናችን ጀግኖችም አሉ፡፡ እኔን የመረረኝ ግን ‹‹የጅል ለቅሶ መልሶ መላልሶ› የሆኑት ናቸው፡፡ ማን ነበር ‹ላይበስሉ ዝም ብለው ማገዶ ይፈጃሉ› ያላቸው?

  (አ.መ.(ዶ/ር)) 

   

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img