Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክአዲሱ የዓለም አቀፍ ስምምነት መዋዋያ አዋጁ በወፍ በረር ሲፈተሸ

አዲሱ የዓለም አቀፍ ስምምነት መዋዋያ አዋጁ በወፍ በረር ሲፈተሸ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በአገሮች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ አካል ስለሚሆኑም በችግር ጊዜ መፍትሔ ለመሻት በሕግነት ያገለግላሉ፡፡ አገሮች ያጋጠሟቸውንም ይሁን ወደፊት እንዳያጋጥማቸው የሚፈልጉትን ወይም እንዲሆን የሚሹትን በሁለትዮሽ ወይም ባለብዙ ወገን ውል ላይ ማስፈር የተለመደ ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አገሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስምምነቶቹን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ሕግ የተለመደው አጠራር ‘ውል’ (treaty) የሚለው ነው፡፡ ውል (treaty) የሚደረግበትን (የሚቋቋምበትን) ሁኔታና ውጤታቸው ምን መሆን እንዳለባቸው የሚገዙ ሌሎች ዓለም አቀፍ ውሎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በአገሮች መካከል ብቻ የሚፈጸሙትን የሚመለከት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. የ1969 ዓ.ም. የቬና የውሎች ስምምነት ነው፡፡ ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ ውሎ ተፈጻሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ ከአንድ መቶ አሥር የሚበልጡ አገሮች ያፀደቁት ቢሆንም ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም. ብትፈርምም እስካሁን ድረስ ተቀብላ  አላፀደቀችውም፡፡  

ሁለተኛው ደግሞ፣ በአገሮችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው የሚዋዋሉበትን ሁኔታ ሥርዓት ለማስያዝ በ1986 ዓ.ም. የወጣው ሌላው  የቬና  የውሎች ስምምነት ነው፡፡ ይኼን ስምምነት ሥራ ላይ ለማዋል ቢያንስ ሠላሳ አምስት አገሮች ተቀብለው ማፅደቅን ስለሚጠይቅና አሁን ላይ አንድ አገር ስለሚጎድል ገና ሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ፈራሚም  አይደለችም፡፡  

ኢትዮጵያ፣ እነዚህን ስምምነቶች ቢኖሩም ባይኖሩም ውል የምትዋዋልበትን ሥርዓት የሚገዙ ሕጎች ሊኖሯት ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ሲባል የስምምነቶቹን ረቂቅ ማዘጋጀት፣ መደራደር፣ መፈራረም፣ ውሉን መቀበል፣ ውሉ የፀደቀበትን ሰነድ መለዋወጥ፣ የየአገሮቹ ሕግ አውጪ ምክር ቤት (ቤቶች) ስምምነቱን ያፀደቁበትን አሳትሞ ማውጣት ከመንግሥታት ወይም እንደሁኔታው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የተደረገውን ውል በየአገሩ ሕግ መሠረት የተፈጸመና በሕግ የተደገፈ መሆኑን፣ ፈራሚው ባለሥልጣንም ውሉን ለመዋዋል ተገቢው ሥልጣን (በሕግ ወይም በውክልና ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው) መሆኑን ማረጋገጥን ያካትታል፡፡

በዋናነት ዓለም አቀፍ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆነው በአገሮች ላይ ነው፡፡ አገሮችም ከዚሁ ሕግ የሚመነጩ መብትና ግዴታ አላቸው፡፡ ለዓለም አቀፍ ሕግ  ምንጭ በመሆን ከሚያገለግሉት ውስጥ ደግሞ በአገሮች መካከል የሚፈጸሙ ስምምነቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተለያየ ስያሜ ይጠራሉ፡፡ ስምምነት (agreement)፣ ውል (treaty)፣ መግለጫ (declaration)፣ ፕሮቶኮል፣ ቻርተር፣ ኮንቬንሽን ወዘተ እየተባሉ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ሁሉም አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ አንዱ ሌላውን ተክቶ ጥቅም ላይ ይውላል ማለትም አይደለም፡፡ ይሁን  እንጂ ሁሉም ዓለም አቀፍ ስምምነት እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደማንኛውም ውል፣ በነፃ ፈቃድና በቅን ልቦና ከተፈጸሙ ተስማሚዎቹ ላይ የአስገዳጅነት ጠባይ ይኖራቸዋል፡፡ አገሮች በነፃ ፈቃድ የሚዋዋሏቸው ከሆኑና የሕግነት ጠባይ ካላቸው የሚዋዋሉበት ሥርዓት መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ረቂቅ ውል ማዘጋጀት ወይም ሲዘጋጁ ተሳታፊ በመሆን መደራደር፣ ከድርድር በኋላ በሚኒስትሮችና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የሚፀድቁበት፣ የሚሻሻሉበትና ቀሪ የሚሆኑበትን ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ነው፡፡

የስምምነቶቹን መነሻ በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አንደኛው፣ የስምምነቱ ዝግጅትና ድርድር ውስጥ ኢትዮጵያ ተሳታፊ ሆና ወይም ሳትሆን ነገር ግን ለፊርማ ክፍት ለማድረግ ውሳኔ ሲሰጥ ተሳታፊ የሆነችባቸውን ይመለከታል፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ድርድሩ ተጠናቅቆ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኗን ትገልጻለች፡፡ ስምምነቱ ሲደረግ መንግሥትን ወክሎ የፈረመው ሰው እንደገና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀጥሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስፀደቅ  ይጠበቅበታል፡፡ ይህ አካሄድ ማፀደቅ (ratification) ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ውል ተዋዋለች የሚባለው ምክር ቤቱ አፅድቆት በአዋጅ ሲወጣ ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፣ ኢትዮጵያ የድርድሩ አካል ብቻ ሳይሆን የስምምነቱ አካል ያልሆነችባቸው ብሎም ሥራ ላይ የዋሉ፣ ለፊርማ ክፍት የሆኑበት ጊዜ ያለፈባቸው ወይም ስምምነቱ የተወሰኑ አገሮችን ብቻ የተመለከተ ከነበረ የእነዚህ ስምምነቶች አባል ለመሆን የምትከተለው መንገድ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ፣ ስምምነቶቹን ኢትዮጵያ እንድትቀበላቸው የሚፈልግ የመንግሥት አካል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ ቀጥሎም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቁበት ሁኔታ ነው፡፡ ይህ አካሄድ መቀበል (Accession) ይባላል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቀበለው መሆኑን የሚገልጽ የማፅደቂያ ሰነድ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመላክ ቀድመው ተዋዋይ አገሮች በተራቸው ሲቀበሏት ስምምነት ተደረገ ይባላል፡፡  

ኢትዮጵያም ይኼንን የዓለም አቀፍ ስምምነት ማድረጊያ የሕግ ሥርዓት በ1923ቱ ሕገ መንግሥት ጀምሮ አሉ፡፡ እስከ 2009 የበጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ሥራ ላይ የነበረው በደርግ ዘመን የወጣው አዋጅ ቁጥር 25/1980 ነበር፡፡ በቅርቡ የወጣው ይህ የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋያና ማፅደቂያ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1024/2009 ከመፅደቁ በፊት መጤን የነበረባቸው ነጥቦችን መጠቆም የዚህ ጽሑፍ ዓለማ ነው፡፡ ጉድለቶቹን ለማሳየት ሲባል የአዋጁን ይዘት በቅድሚያ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፡፡

አዋጁ በአጭሩ ሲቃኝ

የአዲሱ አዋጅ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነት የምትፈርም መሆኗን በመግለጽ እነዚህ ስምምነቶች በሚደረጉበት ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆን ስላለባቸው ይኼን ለማድረግ እንዲቻል ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች ሕጎች ጋር የሚጣጣም ስምምነቶችን መደራደሪያ፣ መዋዋያ፣ መፀደቂያና ቀሪ ማድረጊያ ሥርዓቱን ማሻሻል በማስፈለጉ የወጣ አዋጅ ነው፡፡

አዋጁ፣ በአራት ክፍሎች የተደለደሉ ሃያ ሁለት አንቀጾችን ይዟል፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ውስጥ የተካተቱት ዋና ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከመደርደር ጀምሮ ቀሪ እስማድረግ ድረስ ባሉት ሒደቶች ውስጥ የሚተገበሩ ሥርዓቶችንና ጽንሰ ሐሳቦችን የተተረጎሙበትና የተፈጻሚነት ወሰኑን የተቀመጠበት ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ አዋጁ የሚያገለግለው መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለመደራደር፣ ለመዋዋል፣ ለማፀደቅና ቀሪ ለማድረግ ሥራ ላይ የሚውል ነው፡፡

ሁለተኛው ክፍል መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከመደራደሩ በፊት መደረግና መሟላት ያለባቸውን ሒደቶች ይዘረዝራል፣ ያብራራልም፡፡ አንድ ስምምነት ላይ ድርድር ለማድረግ ሐሳብ ማቅረብ የሚችለው የመንግሥት አካል ብቻ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሙያ ማኅበራት ወዘተ ድርድር እንዲደረግ ለመንግሥት ሐሳብ ስለሚያቀርቡበት ሁኔታ አዋጁ ዝምታን መርጧል፡፡

ማንኛውም የመንግሥት አካል ድርድር እንዲደረግ ሐሳብ ሲያቀርብ የሚመለከታቸው አካላትንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አማክሮ ስለስምምነቱ ማብራሪያ፣ኢትዮጵያን ምን እንደሚጠቅማትና ምን ግዴታ እንደሚጥልባት የሚገልጽ ሰነድ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ድርድር የሚደረግበት ስምምነት የሌሎች ሕጎችን መሻሻል የሚጠይቅ ከሆነ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ማማከር አስፈላጊ ነው፡፡ ፀድቀው ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የክልሎችን አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚጠይቅ ከሆነ ከፊርማ በፊት አስተያየት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በስተቀር ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኘበት ካልሆነ በስተቀር ድርድር ለማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሙሉ ሥልጣን ውክልና ሰነድ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ድርድራቸው ያለቁ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ ስምምነት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ብድር፣ ዕርዳታና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚደረጉ ከሆነ ሒደቱን በሙሉ የሚከታተለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይሆን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡

የአዋጁ ሦስተኛው ክፍል ደግሞ በአምስት አርእስት ሊከፈሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ እነዚህም ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሚጸድቁበትን፣ የሚሻሻሉበትን፣ የሚታገዱበትን፣ ቀሪ የሚሆኑበትን እንዲሁም እየተፈጸሙ መሆናቸውን ክትትል የሚደረግበትን ሥርዓት የሚገልጹ ናቸው፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመፅደቅ የሚቀርብ ማናቸውም ስምምነት ከነአማርኛ ቅጂው፣ በጥቅል የስምምነቱና የድንጋጌዎቹ ማብራሪያና ረቂቅ ማፅደቂያ አዋጅ እንዲሁም ከተለያዩ አካላትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምሮ የተደራደረው አካል ማቅረብ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ላይ የሚጥለው ግዴታና የሚገኘውን ጥቅም ማካተት አለበት፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካፀደቀው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይላካል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማፅደቂያ አዋጁ ላይ ስምምነቱ እንዲካተት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ተከታትሎ የሚስፈጽመውንም አካል ይሰይማል፡፡ ከስምምነቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ተዓቅቦ ያደረገችባቸውንና (ያልተቀበለቻቸው ድንጋጌዎች) መግለጫ (የተረዳችበትና የምትተረጉምበት ሁኔታ) ካለም የማፅደቂያ አዋጁ ላይ መካተት አለባቸው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቁ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈረመ  የማፀደቂያ ሰነዱን አገሪቱ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመላክ ያስመዘግባል ወይም ለሚመለከተው አገር በመላክ ይለዋወጣል፡፡

የፀደቁ ስምምነቶችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለበት አካልና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማስፈጸም አለበት፡፡ የአፈጻጸም ሁኔታውንም በዓመት ሁለት ጊዜ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርም ብድር፣ዕርዳታና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት ስለተፈረሙ ስምምነቶች እንዲሁ ሪፖርት ያቀርባል፡፡ አንድን ስምምነት ለማሻሻል ሲያስፈልግ ሒደቶቹ ከላይ ከተገለጸው አንድን ስምምነት ለማፅደቅ የሚያስፈለገው ሒደት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

አንድ የፀደቀ ስምምነትን ቀሪ ለማድረግ ወይም ለማገድ አስፈላጊ መሆኑን ስምምነቱን አስፈጻሚው አካል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የተስማማሙበትን፣ የልዩነት ሐሳብም ካለ እሱን ጨምሮ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ሲፀድቅና ኋላም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተመሳሳይ መልኩ በአዋጅ ቀሪ ማድረግ ወይም ማገዱን ማጽናት አለበት፡፡

 ዕገዳው ወይም ቀሪ ማድረጉ አስቸኳይ ከሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጊዜያዊነት በማገድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ከሆነ በሰባት ቀናት ካልሆነ ሥራ እንደጀመረ ያፀድቃል፡፡ በጊዜያዊነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደረገ ዕገዳም ይሁን መደበኛ ወይም ቀሪ ማድረጉን ለተዋዋይ ወገኖች ወይም ለአስቀማጩ አካል ማሳወቅ አለበት፡፡

አራተኛው የአዋጁ ክፍል የተሻሩ ሕጎችን የሚገልጽ፣ ደንብና መመርያ የሚወጣን አካል የሰየመ፣ መሸጋገሪያ ሕግን ማመልከቻና ከመቼ ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል የሚገልጹ አንቀጾችን ይዟል፡፡

ሳይፈተሹ የፀደቁ ድንጋጌዎች

በመጀመሪያ መጤን ያስፈልገው የነበረው ጉዳይ ደግሞ ከትርጉም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንዳንድ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ኢትዮጵያ ተቀብላ ከማፅደቋ በፊት ማሻሻያ የተደረገባቸው ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው ስምምነት እንዳለ ሆኖ ሌላ ተጨማሪ ማሻሻያ በሚኖረው ጊዜ የሚፀድቀው፣ ተዓቅቦ ካልተደረገ በስተቀር ከነማሻሻያ ስምምነቶቹ  ነው፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም አቀፍ ስምምነት ምንነትን በሚተረጉምበት ክፍል ማሻሻያዎቹን ጭምር እንዲያካትት ሆኖ ትርጓሜ አልተሰጠውም፡፡ የተሻረው አዋጅ ቁጥር 25/1980 ላይ ግን በአንድ ወይም በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑና በተዛመዱ ሰነዶች ላይ የሰፈረና ማንኛውንም ስያሜ የያዘ ሊሆን እንደሚችል ስለተገለጸ ይህ ዓይነት ችግር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ትርጓሜ ከሁለቱም የቬና ስምምነቶች (ኮንቬንሽንስ) የተለየ ነው፡፡

ኢትዮጵያ አንድ ዓለም አቀፍ ስምምነትን በምትቀበልበት ወይም በምታፀድቅበት ጊዜ የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ሳትቀበል ልትቀር ትችላለች፡፡ እንዲሁም የተወሰኑ ድንጋጌዎችን ወይም ጽንሰ ሐሳቦችን የተረዳችበትን፣ የምትተረጉምበትንና የተቀበለችበትን ሁኔታ መግለጫ በመጨመር ተቀብላ ልታፀድቅ ትችላለች፡፡ ያልተቀበለቻቸውንም መግለጫዎቿንም በማፅደቂያ አዋጁ ላይ መገለጽ እንዳለባቸው አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡

ተዓቅቦ ያደረገችባቸውንም መግለጫዎቹንም በመጨመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የማፀደቂያ ሰነዱ ላይ በመግልጽ ስምምነቶቹን ለሚያስቀምጠው አካል ይልካል፤ የሁለትዮሽ ከሆኑ ደግሞ ይቀያየራል፡፡ በአዋጁ ላይ የገንዝብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የተፈራራማቸውን ዋና ቅጂ ከማስቀመጥ ባለፈ የመለዋወጥ ሥልጣን ስላልተሰጠው፣ ግዴታም ስላልተጣለበት የብድር፣ የዕርዳታና የተደራራቢ ግብር ለማስቀረት የሚደረጉ ስምምነቶችንም የሚቀያየረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለውና በአዋጁ ላይ ያልተቀመጠው ተዓቅቦና መግለጫ በሁለትዮሽ ስምምነቶች በተለይም የብድር፣ ዕርዳታና ተደራራቢ ግብር ለማስቀረት የሚደረጉ ውሎችን ይመለከታል ወይ? የሚለው አንዱ ነው፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነት በሚሆንበት ጊዜ በተለምዶ ድርድሩ እንደገና ይቀጥላል እንጂ ተዓቅቦ ማድረግ አልተለመደም፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለትዮሽ ስምምነት ላይ ተዓቅቦና መግለጫ (አንዳንድ መግለጫዎች ተዓቅቦ ስለሚመስሉ) ማድረግ መቻሉ ወይም እንደገና ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲመለስ የሚደረግ ስለመሆኑ መገለጽ ነበረበት፡፡

ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ወይም ያፀደቀቻቸው ስምምነቶችን ለሚመለከታቸው አካላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ከነተዓቅቦዎቹና መግለጫዎቹ ይላካሉ፡፡ ተዓቅቦዎቹና መግለጫዎቹ ላይ ሌሎች ተዋዋይ አገሮች የሚሰጡትን ምላሽ መከታተል  ግድ ነው፡፡ ለነገሩ ሌሎች አገሮችም ያደረጓቸውን ተዓቅቦዎችና መግለጫዎችንም መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የታቀበችባቸውንም ሆነ መግለጫ የሰጠችባቸውን ሌሎች አገሮች ምንም ምላሽ ካልሰጡ እንደተቀበሏቸው ይቆጠራል፡፡

ኢትዮጵያ ተዓቅቦ ማድረጓን ወይም የሰጠችውን መግለጫ የሚቃወሙ አገሮች በሚኖሩበት ጊዜ እነዚህ ድንጋጌዎች በኢትዮጵያም በተቃወመውም አገር ላይ አይፈጸሙም፡፡ በዝምታ ሲታለፉ ግን ኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ አይሆኑም፤ ምላሸ ያልሰጡ አገሮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነትም ቢሆን ይፈጸምባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች አገሮች የሚያደርጓቸው ተዓቅቦዎችና መግለጫዎች ኢትዮጵያ በዝምታ ስታልፋቸው እሷ ስትገደድባቸው በተቃወመች ጊዜ ግን ተዓቅቦ አድራጊውም ኢትዮጵያም አይገደዱበትም፡፡

እነዚህ ድርጊቶች ጥብቅ ክትትልና ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮች በመሆናቸው፣ የአገሪቱንም ጥቅም ሊጠቅምም ሊጎዳም ስለሚችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተከታሎ እንዲሁም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል (ለምሳሌ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማስወሰን) ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ በእርግጥ የሌሎች አገሮችን አቋም መነሻ በማድረግ ዝምታን መምረጥም ሆነ ተቃውሞ ማቅረብ የአገሪቱ አቋም ሆኖ ስለሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ/ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውክልና መስጠት ይጠበቅበት ነበር፡፡  

ሌላው ሊጤን ይገባው የነበረው ደግሞ ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው ስምምነቶች የሚሻሻሉበትን ሁኔታ የሚመለከተው አንቀጽ 14(2) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ንዑስ አንቀጽ የሚደነግገው ኢትዮጵያ ያፀደቀችው ስምምነት ላይ የይዘት ለውጥ የማያመጣ ስህተት ተፈጽሞ ከሆነ በምን መንገድ መሻሻል እንዳለበት ሥርዓት ማበጀት ነው፡፡ በስምምነቱ ውስጥ ስህተት በምን መንገድ መታረም እንዳለበት የሚገልጽ ድንጋጌ ካለ በዚያው መሠረት ይታረማል፡፡ ካልሆነ ግን ስምምቱን ካደረጉት አገሮች ጋር ከስምምነት በሚደረስበት አካሄድ እንደሚስተካከል ይገልጻል፡፡ ሳይስተካከል ቢቀርስ የሚከተለው ሒደት ምን መሆን እንዳለበት አዋጁ የሚለው ነገር የለም፡፡ በጥቅሉ እነዚህ ሒደቶች ከሚኒስትሩ ጋር በመመካከር እንደሚፈጸሙም ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ከሚኒስትሩ ጋር የሚመካከረው ከማን ጋር እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ምናልባት ሚኒስትሩ ከሌሎች አገሮች ጋር በመመካር እንደሚሠራ ለመግለጽ ቢሆን ይሻል ነበር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ይህ አንቀጽ የይዘት ለውጥ የማያመጣ ስህተትን የሚመለከት ብቻ በመሆኑ፣ የይዘት ለውጥ የሚያመጣ ስህተት ከተፈጸመ ስምምነቱ በምን መንገድ እንደሚታረም ወይም የስምምነቱ ዕጣ ፋንታ ምን ሊሆን እንደሚገባ ወይም ምን መደረግ እንዳለበት መግለጽ ተገቢ ነበር፡፡

በርካታ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የሚከተሉ አገሮችም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን (ውሎችን) የመዋዋል ሥልጣኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይሆን የፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ በአዲሱ አዋጅ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ዓለም አቀፍ ውሎችን መዋዋል አይችልም፡፡ የሙሉ ሥልጣን ውክልና ስለሌለው መዋዋል የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ለነገሩ ምክንያታዊም ተጠያቂያዊም የሚሆነው ዓለም አቀፍ ውሎችን ለመዋዋል አገሪቱን ወክሎ ውክልና መስጠት የነበረበት የአገሪቱ ተወካይ የሆነው ርዕሰ ብሔሩ (ፕሬዚዳንቱ) ነበር፤ ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንቱ የሚዋዋልበት አጋጣሚ ቢፈጠር እንኳን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውክልና በመቀበል ነው፡፡ ውክልና ከመስጠትም ባለፈ፣ የፀደቁ ውሎችንም ለመለዋወጥ ወይም ለማሳወቅ የሚዘጋጁት ሰነዶች ላይ መፈረም የነበረበት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔሩ ነበር፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጊዜያዊነት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማገድ እንደሚችል ይገልጻል፡፡ የመጀመሪው ነገር አንድን ጸንቶ የሚገኝን ዓለም አቀፍ ውል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያሳውጅ እንደሚችል ጉዳይ አገሪቱ ላይ አደጋ የመፍጠር ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሊከሰት መቻሉም አጠራጣሪ ነው፡፡ ይህ በማይሆንበት ሁኔታ በአስቸኳይ ለጊዜው ማገድ ሕጋዊ የሆነበት ዓላማ ተጠያቂያዊ አይደለም፡፡

ሌላ መነሳት ያለበት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉን ሚና የሚመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ አዋጁ ድርድር በሚደረግበት ረቂቅ ስምምነት የሌሎች ሕጎችን መሻሻል የሚጠይቅ ከሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስተያየት መጠየቅ እንዳለበት አንቀጽ 4(2) ላይ ተገልጿል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ምን ማድረግ እንዳለበት አዋጁ ምንም ነገር አይገልጽም፡፡ ቀድሞ የነበረው አዋጅ ግን ጉዳዩን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ (የፍትሕ ሚኒስትሩ) ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ እንዳለበት ይገልጻል፡፡ ሌላው እዚህ ላይ አብሮ መነሳት ያለበት የሚሻሻለው ሕግ የክልል ቢሆንስ ምን ዓይነት ሒደት መከተል እንደሚገባ መገለጽ ነበረበት፡፡  

በተጨማሪም አዋጁ ስምምነቶች በሚፀድቁበት ጊዜ ክልሎች የሚኖራቸው ሚና ግልጽ አለመሆኑ ነው፡፡ የፌደራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች  ዓለም አቀፍ ስምምነትን በሚዋዋሉበት ጊዜ የክልሎች ሚና ግልጽ ነው፡፡ የፌደራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ሁለት የፌደራል ሕግ አውጭ ምክር ቤት ያላቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ውሎች ሲደረጉም ከክልሎቹ በኩል በመሆን የሚሳተፈው የላይኛው ምክር ቤት ነው፡፡

 በኢትዮጵያ ግን የፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲህ ዓይነት ሚና ስለሌለው ስምምነቶች ሲደረጉ ክልሎችን የሚወክል አካል የለም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይመስላል አዋጁ አፈጻጸሙ የክልሎችን ድጋፍ የሚፈልግ ከሆነ ከሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት አስተያየት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ተደንግጓል፡፡ ይኼ አንቀጽ በፌዴራሉ መንግሥት አተያይ የሚፀድቀው አዋጅ ክልል ላይ የሚፈጸም ሲሆን እንጂ ማንኛውንም ውል አይመለከትም፡፡

ለነገሩ አስተያየቱን የሚሰጠው የክልሉ ሕግ አውጭ ምክር ቤት ይሁን አስፈጻሚው ግልጽ አይደለም፡፡ የተሰጠው አስተያየት ውሉን ለማፅደቅ በሚወጣው አዋጅ ውስጥ ስለማይካተት ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡  

ሌላው ከክልሎች ጋር የሚያያዘው ጉዳይ የክልሎች ዓለም አቀፍ ስምምነት የማድረግ ችሎታን (Jus Tractatuum) የሚመለከተው ነው፡፡ የፌደራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ክልሎቻው ዓለም አቀፍ ስምምነትን የማድረግ ችሎታን በተመለከተ አሠራሩ ጉራማይሌ ነው፡፡ በተወሰኑት አገሮች፣ ክልሎች እንዲህ ዓይነት ስምምነቶችን ማድረግ ፍጹም ክልክል ነው፡፡ አሜሪካና ሜክሲኮ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በሌሎች ዘንድ ደግሞ ክልሎች መስማማት እንዲችሉ ሕገ መንግሥታቸው ይፈቅዳል፡፡ ሲውዘርላንድ፣ ጀርመን፣ ኦስትሪያና ቤልጂየምን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አርጀንቲና በክልሎቹ (ፕሮቪንስ) ብቻ ተፈጻሚነት ያላቸው፣ የፖለቲካ ጉዳይን የማይዙ በፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና ስምምነቶችን መዋዋል እንዲችሉ ሕገ መንግሥቱ ይፈቅዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዓለም አቀፍ ስምምነትን የመደራደርና የማፅደቅ ሥልጣን የተሰጠው ለፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ ለፌዴራል ከተሰጠ ክልሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የማድረግ ሥልጣን የለውም ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ኢትዮጵያ እንደ አገር ድንበር ስለሌላት ከሌሎች አጎራባች አገሮች ጋር ስምምነት ማድረግ የሚችሉት ክልሎች ስለሚሆኑ ሙሉ በሙሉ ክልሎች ሥልጣን የላቸውም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በተግባርም ክልሎች ውይይቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ባለፈም የኢንቨስትመንት ውሎችንም ክልሎች ሲፈራረሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ አዋጁ ለእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ‹‹ጆሮ ዳባ ልበስ›› ብሏቸዋል፡፡ እነዚህ ሊነሱ ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ለማሳያ ይሆኑ ዘንድ ናሙና ብቻ ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...