Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአዲሱ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ሥራቸውን ጀመሩ

አዲሱ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ሥራቸውን ጀመሩ

ቀን:

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ሬይነር ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ሥራ መጀመራቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡ ኤምባሲው ዓርብ መስከረም 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ አምባሳደሩ ለኢትዮጵያዊያን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አምባሳደሩ ራሳቸውንና የትኩረት አቅጣጫቸውን ለኢትዮጵያውያን ባስተዋወቁበት መልዕክት፣ አብዛኛውን የሥራ ዕድሜአቸውን በአፍሪካ እንደማሳለፋቸው ኢትዮጵያን ከነታሪኳና በአኅጉሩ ያላትን ሚና በእጅጉ እንደሚያደንቁ አስታውቀዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ቆይታቸው የትኩረት መስኮች ብለው የያዙዋቸው ብልፅግናን ማረጋገጥ፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎቶችን ማሻሻል፣ መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ እንዲሁም በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ማበረታታት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በተጨማሪም በሁለቱ አገሮችና ሕዝቦች መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አምባሳደር ሬይነር ገልጸው፣ በጋራም ይህን በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር፣ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ አቅም እንድትጠቀም ዕገዛ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

“እኔና ባለቤቴ ሁለት ልጆቻችንን ያሳደግነው አፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ እናም ይህ አፍሪካዊ ተፅዕኖ ወንድና ሴት ልጆቻችን ዛሬ ለደረሱበት ስኬታማ የወጣትነት ጊዜ ብዙ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ እኔና ቤተሰቤ ወደ መዝናኛ ቦታዎች መሄድና ሽርሽር ማድረግ እንወዳለን፡፡ እናም ሁሉንም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና የመልክዓ ምድር ገጽታዎች ለማየት ጓጉቻለሁ፡፡ እጅግ አስደናቂ የሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ዛሬም ድረስ ሲወደስ ይኖራል፡፡ የወደፊቱ ደግሞ  በእጅጉ ያጓጓኛል፤” ብለዋል፡፡ 

 “አሁን ለሥራ ዝግጁ ነኝ፡፡ ከጎኔ እንደምትሆኑም ተስፋ አደርጋለሁ፤” በማለት ለኢትዮጵያዊያን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

አምባሳደር ማይክል ሬይነር እ.ኤ.አ. በ1988 የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን የተቀላቀሉ መሆናቸውንና በአማካሪ ሚኒስትር ማዕረግ ከፍተኛ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት አባል እንደሆኑ ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 2016 ጀምሮ በሰው ሀብት ቢሮ፣ የደረጃ ዕድገትና ምደባ ክፍል ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከነሐሴ 2015 እስከ ነሐሴ 2016 ድረስ በካቡል (አፍጋኒስታን) የሚሲዮኑ ምክትል አምባሳደር በመሆን የውጭ አገልግሎትን፣ የፀረ አደንዛዥ ዕፅ እንቅስቃሴን፣ የሕግ ማስከበርን፣ እንዲሁም የሚሲዮኑን ቆንስላና አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፎችን በበላይነት መምራታቸው ታውቋል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ 2015 ደግሞ በቤኒን የአሜሪካ አምባሳደር፣  እንዲሁም እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2012 የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና ዋና ዳይሬክተር በመሆን ማገልገላቸው ተገልጿል፡፡

አብዛኛውን የሥራ ጊዜያቸውን በአፍሪካ ያሳለፉት አምባሳደር ሬይነር በሐራሬ፣ በዊንድሆክ፣ በኮናክሪና በጂቡቲ የአስተዳደር ሹም፣ በብራዛቪል የጠቅላላ አገልግሎት ሹም በመሆን መሥራታቸው ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ፣ የዚምባብዌ ጉዳይ መኮንን፣ በሕግ  ጉዳዮች ቢሮ ልዩ ረዳትና የሕግ አስተዳደር መኮንን፣ እንዲሁም በሉግዘምበርግ የቆንስላ መኮንን እንደነበሩም የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከተበረከቱላቸው ሽልማቶች ውስጥ እ.ኤ.አ. የ2008 ሊሞን ሀንት ሽልማት ለአስተዳደራዊ ልህቀት፣ በርካታ ከፍተኛ የውጭ አገልግሎት አፈጻጸም ሽልማቶችና የላቀ የክብር ሽልማቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡ አምባሳደር ሬይነር ከላፋየት ኮሌጅ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የመጀመርያ ዲግሪ፣ እንዲሁም የማስተርስ ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ማግኘታቸውን፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ