Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉማቀድ ምን ይፈይዳል?

ማቀድ ምን ይፈይዳል?

ቀን:

በዳንኤል አረጋዊ ኃይሉ

አዲስ ዓመት ሲመጣ በዓመቱ ልናከናውናቸው የምንሻቸውን ነገሮችን ማቀድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ከአዲስ ዓመት መባቻ ጀምሮ ይህንን ልምዳችንን ከግምት ያስገቡ፣ በዕቅድ መመራትን ማዕከል ያደረጉ፣ የተለያዩ ዝግጅቶች በሬዲዮ ስናደምጥና በቲቪ ስንመለከት ከርመናል፡፡ በዝግጅቶቹ ከተነሱት ጭብጦች ዋነኞቹ፣ “አዲስ ዓመትን ብቻ ጠብቀን ማቀድ አለብን ወይ?”፣ “ዕቅዳችንን ለመተግበር እንቅፋት የሚሆኑብን ነገሮች ምንድን ናቸው?”፣ “ዕቅድ ስናቅድ ምን ምን ነገሮችን ማሟላት አለብን?” እና “ዕቅዳችንን ለመተግበር መከተል ያሉብን ነገሮች ምንድን ናቸው?” የሚሉት ናቸው፡፡ በተከታተልኳቸው ዝግጅቶች ይነሱ የነበሩት የክርክር ሐሳቦችም ሆነ የባለሙያ አስተያየቶች ትልቅ ቁም ነገርን የሚያስጨብጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡

የግል ሕይወትን፣ የንግድ ሥራን፣ መዝናናትን፣ የሕዝብ አስተዳደርን፣ ልጅ ወልዶ ማሳደግን፣ የሥራ መስክን፣ የበጎ አድራጎት ሥራን፣ ወዘተ በዕቅድ መምራት የሥልጣኔ ማሳያ የሆነ ተገቢ ተግባር መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዕቅድ መመራትን ከበለፀጉት አገሮች የስኬት ምንጭ ቁልፉ ምክንያት አድርጎ መውሰዱ ማጋነን አይሆንም፡፡ ዕቅዳቸው ትውልድ ተሻጋሪ በመሆኑ ሲበለፅጉና ሲያተርፉ እንጂ ሲጎዱ አልተስተዋሉም፡፡ በአገራችንም ሕይወታቸውንም ሆነ ሥራቸውን አቅደው እየመሩ፣ በዕቅዳቸው ባስቀመጡት ግብ መሠረት ስኬታቸውን እየለኩ፣ በደካማ ጎናቸው እየታረሙ፣ በጠንካራ ጎናቸው ይበልጡኑ እየጠነከሩና ራሳቸውን እየገነቡ የሚኖሩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች መኖራቸው ዕሙን ነው፡፡ ይህ ሊበረታታና ሁላችንም እያዳበርነው ልንኖር የሚገባ በጎ ልምድ ነው፡፡

በአንፃሩ ደግሞ የግል ሕይወታቸውንም ሆነ ሥራቸውን በዘፈቀደ የሚመሩና ዕቅድ የሚባል ነገር ፈጽሞ የማያውቁ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ከየዕለት ኑሯችን በቀላሉ ማየት የምንችለው ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ ምልከታ በዕቅድ የማይመሩ ሰዎች በሁለት ጎራ ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በአንደኛው ጎራ ያሉት የዕቅድን ጥቅም ያልተረዱ፣ ቢረዱም ግድ የማይላቸውና በዕቅድ መመራት ሥራ የሚሆንባቸው ሰዎች ይገኙበታል፡፡ በሁለተኛው ጎራ የሚገኙት ደግሞ በዕቅድ የመኖርን ጠቀሜታ ቢያውቁም፣ በዕቅድ በመኖር የሚያገኙት ስኬት ሳያቅዱ ከኖሩት ጋር ሲነፃፀር ተገቢውን ያህል ለውጥ በሕይወታቸው ላይ ስላላመጣላቸው አቅዶ ላለመኖር የወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ያለ ዕቅድ ለመኖር የውሳኔያቸው ዋነኛ መሠረት ከእነሱ አቅም ውጪ ያሉ ውጫዊ ምክንያቶች (External Factors) ለዕቅዳቸው መሳካት ወይም አለመሳካት ያላቸው አስተዋጽኦ የላቀ መሆን ነው፡፡

በየትኛውም አገር ቢሆን ነባራዊ ሁኔታዎች ቀድሞ መገመት ወይም መተንበይ በሚቻል አሊያም በድንገተኛ ምክንያቶች ሊደናቀፉ ወይም ሊለወጡ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ ያቀደ ግለሰብ የጉዞ ዕቅዱን ቀድሞ በተተነበየ እሳተ ጎመራ ወይም ከባድ ዝናብ መነሻነት፣ አሊያም ባልተጠበቀ የሽብር ጥቃት ወይም በተጓዡ ድንገተኛ ሕመም ምክንያት ሊደናቀፍ ይችላል፡፡ ከውጫዊ ምክንያቶች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ዕቅድ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከበለፀጉት አገሮች ተሞክሮ ለመረዳት እንደሚቻለው ውጫዊ ምክንያቶችን ማስቀረት ባይቻል እንኳን ውጫዊ ምክንያቶች በዜጎቻቸው ዕቅድ ስኬት ወይም ውድቀት ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉት ተፅዕኖ በአንፃራዊነት ተገማች ናቸው፡፡ ከመገመት አልፎ ተርፎም በዘመናዊ መንገድ ትንበያና ጥቆማ የሚሰጥባቸው ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም የዕለቱን የአየር ንብረት ቀድሞ አውቆ አለባበስን አስተካክሎ መውጣት፣ የአክሲዮን ገበያ (Stock Exchange Market) ሽያጭን የገበያ ሁኔታ ተከታትሎ የንግድ ትርፍን መገመት፣ በእጅ ስልክ ላይ በሚጫኑ ‹አፕሊኬሽኖች› የትራፊክ ፍሰትን ቀድሞ በመለየት በትራፊክ ያልተጨናነቀ መንገድ መርጦ መሄድ፣ አንድ የንግድ ሥራ ለመሥራት የንግድ ፈቃድ ለማውጣት የሚያስፈልገውን ተለክቶ የተቀመጠ መሥፈርት ቀድሞ አውቆ፣ የንግድ ሥራን በተፈለገው ጊዜና ዓይነት መጀመር ወይም የሚማሩበትን ተቋም ዓመታዊ መርሐ ግብር ቀድሞ አውቆ የትምህርትና የትርፍ ሰዓት ሥራን ማቀድ ይቻላል፡፡     

በአገራችንስ ውጫዊ ምክንያቶች በዕቅዶቻችን ስኬት ወይም ውድቀት ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን ተፅዕኖ ቀድመን መገመት የምንችለው ስንቶቻችን ነን? እኔም ሆንኩኝ የማውቃቸው እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ለመከታተል ይረዳን ዘንድ ለመማር የምንፈልገው የጥናት መስክ መኖሩንም ሆነ፣ ምዝገባ ካለ ምዝገባው መቼ እንደሚጀምር ለመጠየቅ 2009 ዓመተ ምሕረትን ጨምሮ ለረዥም ዓመት ወደ ዋናው ሬጅስትራር እንመላለስ ነበር፡፡ በየዓመቱ የምናገኘው መልስ “ማስታወቂያ ተከታተሉ፤” እና “በዚህ ስልክ እየደወላችሁ ጠይቁ፤” የሚል ነው፡፡ ምዝገባ መጀመሩ የሚታወቀው ለምዝገባው ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ነው፡፡ ሳህሉ እንግዳ (ስሙ ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) በተመሳሳይ ተቋም ያጋጠመውን ያወሳል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በቀኑ መርሐ ግብር የድኅረ ምረቃ ትምህርቱን ለመከታተል የመግቢያ ፈተና ወስዶ በከፍተኛ ውጤት ያልፋል፡፡ የምዝገባ ጊዜውን በተስፋ በመጠበቅ ሙሉ ጊዜውን ለትምህርቱ ለመስጠት አስቦ ሥራውን ቢለቅም፣ ፈጽሞ ባልጠበቀው ሁኔታ ፈተናውን ያወጣው የትምህርት ክፍል እንደ ሳህሉ ያሉትን የግል አመልካቾች ትቶ ከመንግሥት ተቋማት የመጡ ተማሪዎች ብቻ እንደሚመዘግብ ማስታወቂያ ለጠፈ፡፡ “በዚያ ዓመት ዩኒቨርሲቲው ያደናቀፈብኝ የመማር ዕቅዴን ብቻ ሳይሆን፣ መልሼ ላገኘው ያልቻልኩትን ለትምህርቴ ብዬ የሰዋሁትን መሥሪያ ቤቴን ጭምር ነው፤” ይላል ሳህሉ ያለፈውን በቁጭት እያስታወሰ፡፡

የሳህሉና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገጠመኝ በዚህ አይቋጭም፡፡ በሌላ ዓመት የድኅረ ምረቃ ትምህርቱን ከተማረ በኋላ አምና በአንድ የጥናት መስክ የዶክትሬት ትምህርቱን ለመማር በዚሁ ተቋም የመግቢያ ፈተና ወስዶ ያልፋል፡፡ በደስታና በጥርጣሬ የመመዝገቢያ ጊዜ ሲጠብቁ ዩኒቨርሲቲው ሌላ “የምሥራች” አሰማቸው፡፡ በዓመቱ ፈተና ወስደው ባለፉበት የጥናት መስክ የሚሰጠው የዶክትሬት ትምህርት ተሰርዟል ተባሉ፡፡ ሊሰረዝ አይገባም ብለው ላይ ታች ቢሉም ትምህርት ክፍሎቹ መርሐ ግብሩን የመሰረዝ ሥልጣን እንዳላቸው ሲነገራቸው ሁሉን ትተው አረፉ፡፡ ሳህሉ ይህንን ገጠመኙን ሲያወሳ፣ “ደግነቱ ካለፈው ተምሬ መመዝገቤን ሳላረጋግጥ ሥራዬን አለመልቀቄም ሆነ ተጨማሪ ውሳኔም አለመወሰኔ ሊደርስብኝ የሚችለውን ጉዳት ቀንሶልኛል፡፡ በአጭሩ እዚህ አገር በተለይ የከፍተኛ ትምህርት እከታተላለሁ ብለህ ከማቀድ ይልቅ የዓመት በዓል የዶሮ ገበያን መገመት ይቀላል፤” ይላል ምሬቱን በሳቅ እያጀበ፡፡

ሰይፈዲን አክመል (ስሙ ለዚህ ጽሐፍ የተቀየረ) በንግድ ሥራ ለረዥም ዓመታት አሳልፏል፡፡ የንግድ ሥራውን ለማስፋፋት የረዥም ዓመት ዕቅድ ቢኖረውም ዕቅዱን ለማሳካት እንቅፋት የሆነበትን ውጫዊ ምክንያት ያወሳል፡፡ “ዓመታዊ ወጪና ገቢያችንን በሰነድ ደግፈን፣ ሒሳባችንን ሠርተን፣ ግብር ከከፈልን በኋላ የሒሳብ ሰነዶቻችን በገቢዎች ቢሮ ኦዲት ይደረጋሉ፡፡ በገቢዎች መሥሪያ ቤት ድርጅቴ ኦዲት የሚደረግበትን ዓመትም ሆነ ጊዜ ቀድሜ የማውቅበት አንዳች መንገድ የለም፡፡ ቀድሞ ካለማወቄ በላይ የከፋው በውስጥና በውጭ ኦዲተሮች አሠርቼ ባቀረብኩት የሒሳብ ሰነድ ውስጥ፣ በድርጅቴ ወጪነት ከተመዘገቡ በሰነድ የተደገፉ ወጪዎች መካከል በገቢዎች ኦዲተሮች ተቀባይነት የሚያገኙትንና የማያገኙትን ሰነዶች እንኳን እኔ፣ እኔ ነኝ ያሉ የተረጋገጠላቸው የሒሳብ አዋቂዎች እንኳን አያውቁትም፡፡”

ችግሩን በምሳሌ ሲገልጸው፣ “ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም. የግብር ዘመን ከአንድ ድርጅት የገዛሁት ጥሬ ዕቃ በወጪነት ተቀባይነት ያገኝልኛል፡፡ በዓመት ውስጥ የሕግም ሆነ የሒሳብ ደንብ ለውጥ ሳይኖር በ2008 ዓ.ም. ግን በተመሳሳይ ምክንያት ከተመሳሳይ ድርጅት በሕጋዊ ደረሰኝ የገዛሁት ተመሳሳይ መጠን ያለው ጥሬ ዕቃ፣ በዚህኛው ዓመት በተመደበው የገቢዎች ኦዲተር ተቀባይነት ላያገኝ ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ ኦዲት ተደርጌ በተጨማሪ ክፈል የምባለውን ክፍያም ሆነ የቅጣት መጠን ልገምተው አልችልም፡፡ ብዙ ብር ብቀጣ በሚል ሥጋት የተነሳ ድርጅቴን ለማስፋፋት ወጪ ማውጣት እየሠጋሁ በየበጀት ዓመቱ ድርጅቴን ለማስፋፋት የምይዘውን ዕቅድ እንዳራዘምኩ አለሁ፡፡ እና እንዴት ብዬ ነው ተገማች ባልሆነ የግብር ሥርዓት ውስጥ ሆኜ ድርጅቴን ለማሳደግ የማቅደው?” በማለት መልስ ያጣሁለትን ጥያቄ መልሶ ይጠይቃል፡፡ 

መልሶ የማልማት ሥራ እየተከናወነባቸው ካሉ ቦታዎች በአንዱ ላይ በነበረው የግል ይዞታቸው ላይ ሕንፃ ለመገንባት ውጣ ውረድ ውስጥ የተነከሩት ዶ/ር ረጋሳ ሁንዱማ (ስማቸው ለዚህ ጽሑፍ የተቀየረ) በአገራችን ያስተዋሉትን ሥራን አቅዶ የማከናወን ሥጋትንና ዕርባና ቢስነት እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡ “ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የሕንፃ ዲዛይን እንድናቀርብ ተነገረን፡፡ በተሰጠን መረጃ መሠረትም ባለ ዘጠኝ ፎቅ ሕንፃ ዲዛይን አሠርተን የግንባታ ፈቃድ ተሰጠን፡፡ ድንበር የማካለል ሥራው በተለመደው ውጣ ውረድ ብዙ ጊዜያት ስለወሰደብን ቀደም ብሎ የተሰጠን የግንባታ ፈቃድ የስድስት ወር ጊዜ አለቀ፡፡ በድጋሚ የግንባታ ፈቃድ ለማሳደስ ስንሄድ የከተማዋ ማስተር ፕላን በመከለሱ ምክንያት በቦታው ላይ ማከናወን የምትችሉት ሕንፃ ባለሰባት ፎቅ እንዲሆን ተወስኗል አሉን፡፡ አሁን ማን ነው ይኼንን ቢሰማ የሚያምነው?” በማለት መልሰው ይጠይቃሉ፡፡

ሐሳባቸውን ሲቀጥሉም፣ “በድጋሚ የሕንፃውን ዲዛይን ባለሰባት ፎቅ በማድረግ ወደ ተለመደው ውጣ ውረድ ገባን፡፡ ከአዋሳኝ ድንበር ጋር በነበረ ሌላ ችግር ምክንያት ግንባታ ባለማከናወናችን፣ አሁንም የተሰጠን የግንባታ ፈቃድ ጊዜ ተጠናቀቀ፡፡ አሁንም በድጋሚ የግንባታ ፈቃዳችንን ለማሳደስ ሄድን፡፡ በሚያስቅ ሁኔታ የከተማዋ ማስተር ፕላን በድጋሚ ስለተከለሰ በቦታው ላይ መገንባት የምትችሉት ሕንፃ ባለሰባት ፎቅ እንዲሆን ተወስኗል አሉን፡፡ በዚህ ምክንያት ዕቅዳችንን ከለስን፡፡ የሕንፃ ሥራውን በትርፍ ጊዜው የሚቆጣጠር የቤተሰብ አባል መድበን፣ እኛ ለሕንፃው የመደብነውን ገንዘብ ለሌላ ሥራ መጠቀም ጀመርን፡፡ የሕንፃውን ዕቅድ ለቀበሌው ትተነዋል!” ይላሉ በምፀት እየሳቁ፡፡

በማስታወቂያ ሥራ ለጥቂት ዓመታት የቆየችው ወ/ሮ ዓይናዲስ ሲርጋጋ (ስሟ ለዚህ ጽሑፍ የተለወጠ) እንደ ሌሎቹ ሁሉ፣ “ዕቅድ እዚህ አገር ምን ይሠራል?” በማለት ትሞግታለች፡፡ ይህንን ያስባላትን ምክንያት የሚከተለው ነው፡፡ “ከውጭ ማስታወቂያ ሥራዎች ሁሉ በዋና ዋና መንገዶች ዳርና በየአደባባዩ የሚሰቀሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች (ቢልቦርድ) ሥራ በጣም አትራፊ በመሆኑም፣ ይህን ሥራ በሰፊው ለመሥራት ዕቅድ አወጣሁ፡፡ አዲስ አባባን እየዞርኩ ክፍት ቦታዎችን ለይቼ ማስታወቂያ የሚያሠሩኝ ደንበኞቼን አሳምኜ የማስታወቂያ ሰሌዳ ለማቆም ፈቃድ ለማውጣት በየክፍለ ከተማው ሄድኩኝ፡፡ አንድ ክፍለ ከተማ ለማስታወቂያ ሰሌዳዎች የሚሆን ቦታ የለንም አሉኝ፡፡ ሦስት ክፍላተ ከተሞች ደግሞ ለማስታወቂያ ሰሌዳዎች መትከያ ቦታ ፈቃድ እንዳንሰጥ ከከንቲባው ቢሮ መመርያ ስለመጣ ፈቃድ አንሰጥም አሉኝ፡፡ ሌሎች ሁለት ክፍላተ ከተሞች በድምሩ ሦስት ቦታዎች ላይ ማስታወቂያ ሰሌዳ እንድሰቅል ፈቀድ ሰጡኝ፡፡ ልብ በል ሁሉም ክፍላተ ከተሞች ጋ የሄድኩት ሁለት ሳምንት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም፣ ሁሉም ክፍላተ ከተሞች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ መመርያና አሠራር ይተገብራሉ፤” ትላለች እየሆነ ባለው ነገር በመደነቅ፡፡

ከቅርብ ወራት በፊት ክፍለ ከተማዎች ለማስታወቂያ ሰሌዳ ማቆሚያ ቦታ ፈቃድ እየሰጡ ነው የሚባል ወሬ ሰምታ ወደ ተለያዩ ክፍላተ ከተሞች መሄዷን ታስታውሳለች፡፡ ከሁሉ በላይ ያስገረማት ግን በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ፈቃድ የመስጠት ተግባር ለአንድ ቀን ብቻ ተከናውኖ ፈቃድ የመስጠት ሥራ መከልከሉ ነው፡፡ ወ/ሮ ዓይናዲስ ሁኔታውን ስታብራራው፣ “በዚች አንድ ቀን የተለያዩ ማስታወቂያ ድርጅቶች በጣት የሚቆጠር የማስታወቂያ ቦታ ሲያገኙ አንድ የማስታወቂያ ድርጅት ብቻ ወደ ስልሳ የሚሆኑ ቦታዎች ላይ ፈቃድ ተሰጠው፡፡ የሚገርመው አብዛኛው የማስታወቂያ ቦታ ፈቃድ የተሰጠው ለአንድ የማስታወቂያ ድርጅት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ማስታወቂያ ድርጅት ለማመን በሚከብድ ፍጥነት በአጭር ቀናት ውስጥ ቦታዎቹ ላይ የማስታወቂያ ሰሌዳዎቹን አቁሞ መጨረሱ ነው፡፡ የተሰቀሉትን ማስታወቂያዎች ይዘትና ቅርፅ ዓይቶ በቀላሉ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ የማስታወቂያ ሰሌዳዎቹን ለማዘጋጀት እጅግ በጣም ብዙ ወራት ያስፈልጉታል፡፡ ስለዚህ ይህ የማስታወቂያ ድርጅት እንደሚፈቀድለት አውቆ የሚሰቅላቸውን ማስታወቂያዎች ቀድሞ አዘጋጅቶ ይጠባበቅ እንደነበረ አለመገመት የዋኅነት ነው፡፡ ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ የፈቃድ መስጠት ሥራ ለአንድ ቀን ብቻ ተከናውኖ ፈቃድ መስጠት ከተከለከለ፣ ቀድሞውንም ፈቃድ መስጠት የተጀመረው ለማን እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም፡፡ እና ይኼንን እያየሁ ለምን ብዬ ነው እዚህ አገር ሆኜ ሥራዬን የማቅደው? እዚህ አገር ከመጣሁ ጀምሮ ዕቅድ አውጥቼ ከሠራሁት ሥራ ይልቅ ፀሎት አድርጌ የሠራሁት ሥራ የተሻለ ውጤት አምጥቶልኛል፤” በማለት ምሬቷን አጋርታኛለች፡፡ 

እያንዳንዳችን ተመሳሳይ ገጠመኞቻችንን ማስታወስ አይከብደንም፡፡ ለወትሮ ታክሲ የምንሳፈርበት የታክሲ መጠበቂያ ምንም ሳናውቀውና አንዳችም ከልካይ ምልክት ሳይተከልበት ጠዋት ወደ ሥራ ለመሄድ ስንወጣ፣ የታክሲ ማቆሚያነቱ አክትሞ ለተጨማሪ የእግር ጉዞና የጊዜ ብክነት ይዳርገናል፡፡ በከተማዋ መሀል የሚገኝ ሕንፃን አንድ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ስለተከራየው የጽሑፍና የፎቶ ኮፒ አገልግሎት ለመሥራት የሁለት ዓመት ውል ፈጽመን፣ የንግድ ቤት ተከራይተን መሥራት በጀመርን በአራተኛው ወር የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ለቆ ሕንፃው የግል ሆስፒታል ይሆናል፡፡ ማስተር ፕላኑ በሚፈቅድለት መሠረት ለቢሮ አገልግሎት ለመሥራት “መሬት ገዝቶ” የሕንፃ ዲዛይን ያሠራ ሰው የግንባታ ፈቃድ ሊያወጣ ሲሄድ ሰባ በመቶ ክፍሎቹ መኖሪያ ቤት ካልሆኑ ፈቃድ አይሰጥህም ይባላል፡፡

ሌላው ቀርቶ አንድ ሠራተኛ በአንድ መሥሪያ ቤት ያለውን የአገልግሎት ዘመን ለማቀድ ተገማች ነገሮች የተመናመኑ ናቸው፡፡ የሠራተኛውን የአገልግሎት ዘመን የሥራ ሕግጋት፣ የሥራ ደንብ፣ የሠራተኛው የሥራ አፈጻጸምና የድርጅቱ ህልውና አሊያም ያልታሰቡ ድንገተኛ ነገሮች ሊወስኑት ይገባል፡፡ በተግባር ግን ሠራተኛው ምን ያህል ቢተጋ፣ ምን ያህል ሕግና ደንብን መሠረት አድርጎ ቢሠራ የአገልግሎት ዘመኑና በሚሠራበት ተቋም በሠራተኝነት የመዝለቅ ዕቅዱ በቅርብ ወይም በሩቅ አለቆቹ ይሁንታ ብቻ ሲወሰን እናያለን፡፡

በ2003 ዓ.ም. የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ፡፡ ከካዛንችስ ወደ ሜክሲኮ በሚሄድ ታክሲ ተሳፍረናል፡፡ የታክሲው መሀለኛ ወንበር ላይ ስሙን የማልጠቅሰው ኮሜዲያን ተቀምጧል፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ነበር፡፡ ታክሲው ንግድ ሚኒስቴር ጋ ሲደርስ መንገድ ተዘግቶ ተሽከርካሪዎች ወደ መስቀል አደባባይ እንዲዞሩ በትራፊክ ፖሊሶች ታዘዙ፡፡ የነበርንበት ታክሲ ወደ መስቀል አደባባይ መዞር ከመጀመሩ ኮሜዲያኑ ስልኩን አውጥቶ መደወል ጀመረ፡፡ “መንገዱ ስለተዘጋ በቡናና ሻይ በኩል ጠብቂኝ፤” አለና ስልኩን ዘጋው፡፡ ልክ መስቀል አደባባይን እንደ ጨረስን መንገዱ ተዘግቶ ወደ ግዮን ሆቴል አቅጣጫ ተጓዙ ተባለ፡፡ ኮሜዲያኑ ስልኩን አወጣ፣ “በቃ የላይኛው መንገድ ስለተከፈተ ዋቢ ሸበሌ ጋ ጠብቂኝ፤” አላት፡፡ የነበርንበት ታክሲ በግዮን ሆቴል አድርጎ በብሔራዊ ቴአትር መብራት ወደ ሜክሲኮ ሲሄድ መንገዱ ተዘግቶ በኮሜርስ ጀርባ ወደ ለገሐር እንዲጓዙ ታዘዙ፡፡ ይኼኔ ተሳፋሪው ሁሉ በጣም መሳቅ ጀመረ፡፡ ኮሜዲያኑ እየቀለደ ስልኩን አወጣ፡፡ “በቃ መልሰው በቡናና ሻይ ሄዱ ስላሉን . . . ” እያለ ማስረዳትና ማፅናናት ጀመረ፡፡ ታክሲው ኮሜርስ ጀርባ እንደ ደረሰ መንገዱ በድጋሚ ተዘጋና ወደ ሰንጋ ተራ አቅጣጫ ተጓዙ ተባልን፡፡ የባሰ ሳቅ ታክሲ ውስጥ ነገሠ፡፡ ኮሜዲያኑ ስልኩን እያመናታ አወጣና፣ “ይኸውልሽ ሚስቴ ባለሽበት ሁኚ፡፡ ዛሬ የእኔና የአንቺን መገናኘት የሚወስነው መንግሥት ነው፤” አላት፡፡    

እኔ ደግሞ እላለሁ የግል ሕይወታችንንና የሥራችንን ዕቅድ ለመከለስ ወይም ለመሰረዝ ሥልጣን ለራሳቸው የሰጡ፣ የማይታዩና የሚታዩ እጆች እዚህም እዚያም አሉ፡፡ ሕይወታችንን በዕቅድ ከምንመራው ይልቅ ሌሎች ያቀዱልንን የመፈጸም ዕድላችን ከፍተኛ ነው፡፡ ውጫዊ ምክንያቶች በዕቅዳችን ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸው በእጅጉ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ዳግም በዕቅድ ላለመመራት ለመማል የሚያስከጅሉ ናቸው፡፡ በዕቅድ መመራት ስኬታማ ሊያደርገን ከሚገባው በላይ ዋጋ ሲያስከፍለን ይስተዋላል፡፡ አቅዶ መኖር ሊያስከብረንና ሊያስወድሰን ሲገባ፣ በማቀዳችን ምክንያት ዕዳ ከፋይ እንሆናለን፡፡

በመሆኑም ማኅበራዊ መስተጋብራችን፣ የግንኙነት አውታሮቻችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ፖለቲካችን፣ የግብይት መንገዶቻችን፣ የአየር ፀባያችን፣ ሕግጋቶቻችን፣ ደንቦቻችን፣ መመርያዎቻችን በግልና መንግሥታዊ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች . . . ተገማች የሚሆኑበትን መንገድ በመፍጠር ፈንታ በይስሙላ “ዕቅድ” እና በደመ ነፍስ መጓዛችንን ከቀጠልን፣ በማቀዳቸው የሚጎዱ ሰዎችን ጉዳት ለመቀነስ በየጓዳናው “እዚህ አገር አቅዶ መኖር ያስቀጣል” የሚል ማስጠንቀቂያ መለጠፍ ይጠበቅብናል፡፡ 

ትዝብቴን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ የምንደማመጥ፣ ሐሳብን በሌላ ሐሳብ ብቻ የምንዋጋ፣ ከግል ክብርና ጥቅማችን በላይ ለአገራችን ቅድሚያ የምንሰጥ የአንድ አገር ሕዝቦች ያድርገን፡፡ ብሩሃን ቀናት ከፊታችን ይቅደሙ፡፡ ሰላም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን (LL.B, LL.M, MSW) አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...