Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየፌዴራል ሥርዓቱ ነው ችግራችን ወይስ እኛ ነን

የፌዴራል ሥርዓቱ ነው ችግራችን ወይስ እኛ ነን

ቀን:

ችግሮቹ?

በገነት ዓለሙ

“ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የተሰኘችው ኢትዮጵያ ነፃ የሆኑ የተለያዩ አገሮች የኅብረት አገር ለመሆን የመፈለግን ጉዳይ በየአገራቸው ሕዝብ ካስወሰኑ በኋላ ለጋራ ጉባዔ የየአገር ተወካዮቻቸውን ልከው ያቋቋሟት አገር ሳትሆን፣ ፊትም የነበረች ግን በሕገ መንግሥት ጉባዔ ነባር የግንኙነትና የአወቃቀር መሠረቷን ቀይራ የቀጠለች አገር ነች፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በመግቢያው ላይ “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአገራችን ኢትዮጵያ . . . ” ብሎ መጀመር የቻለው ለዚህ ነው፡፡ በመግቢያው  ውስጥ የተቀመጡት መሠረተ ሐሳቦች፣

  • ኢትዮጵያ የየራስ ባህልና አሠፋፈር ያላቸው ሕዝቦች ተሳስረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር በመሆኗ፣
  • አብሮ በመኖርም ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው ስላመኑ፣
  • መጪው የጋራ ጥቅምም የተዛባ ግንኙነትን አርሞ የጋራ ጥቅምን በማሳደግ ላይ መመሥረት ስላለበት፣
  • ጥቅማቸውን፣ መብታቸውን፣ ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋገፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት አስፈላጊ መሆኑን በማመን፣
  • በራሳቸው ፈቃድ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን በመጠቀም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መቋቋሙን የሚገልጹ ናቸው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 2፣ 8፣ 9፣ 40፣ 50፣ 51፣ 52 እርስ በርሳቸውና ከቀሪዎቹ አንቀጾች ጋር ተገናዝበው ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሉዓላዊት አገር መሆኗን በግልጽ ያሳያሉ፡፡ አንቀጽ 2 የኢትዮጵያ ግዛት የፌዴራል አባላቱን ወሰን የሚያጠቃልል መሆኑን ሲያሳውቅ፣ አንቀጽ 40 (3) “ . . . መሬት . . . የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው” ብሎ ያውጃል፡፡ ሕጉ ይህንን ቢልም መሬትን የየክልልና የየብሔር ብሔረሰብ ንብረት አድርጎ የቆጠረ ብሔረተኛ አስተሳሰብ ሕዝብ ውስጥና መንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ ሲያሳስትና ጥፋት ሲያሠራ እናገኛለን፡፡

አንቀጽ 8(1) “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው” ሲልም በማያሻማ ሁኔታ የአገሪቱ ሥልጣን አዛዥነት የፕሬዘዳንት ወይም የጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን የእነሱ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ አዛዥነታቸው (የሥልጣን ባለቤትነታቸው) የሚገለጸውም በተወካዮቻቸውና በቀጥተኛ ውሳኔያቸው አማካይነት ነው (አንቀጽ 8፣3)፡፡  እነዚህ ንዑስ አንቀጾች በብሔረተኛ አዕምሮ ውስጥ ውላቸውን ስተው ልክ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ሉዓላዊ ህልውና ያለው ተደርጎ ይታሰባል፡፡

በአንቀጽ 8(1) ንዑስ አንቀጽ የአማርኛ ቅጂ ውስጥ ያለው “የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን” በእንግሊዝኛው “”Ethiopia’s Sovereign Power/Ethiopian State Sovereignity”  በሚል ዓይነት አገላለጽ በመቀመጥ ፈንታ፣ “All Sovereign Power” ተብሎ መቀመጡ ለአሳቻ ትርጉም ሳያመች አልቀረም ሊባል ቢችልም፣ የአማርኛው ቅጂ ውስጥ ቁልጭ ብሎ የተቀመጠውን እሳቤ የተረዳና በአንቀጽ 106 ላይ የሠፈረውን የመጨረሻ ሕጋዊ ዕውቅናን ለአማርኛው ቅጂ የሰጠ ድንጋጌ ያስተዋለ ሰው መምታታት አይደርስበትም፡፡ እውነቱን ለመናገርም የአሳቻ ግንዛቤው ምንጭ ከአንቀጹ ይልቅ ሉዓላዊነትንና የመሬት ድርሻን ከብሔረሰብነት ጋር ያያያዘ ብሔረተኛ ፖለቲካ አዕምሮ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ነው፡፡ በንዑስ አንቀጹ የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቅጂ ውስጥ የታየው የአገላለጽ ልዩነትም ሉዓላዊነትን የየብሔረሰብ ከማድረግ ፍላጎት ጋር በጊዜው የተደረገውን መጓተት የሚጠቁም የቃላት ጨዋታ ይመስላል፡፡ እንዲያ ቢሆን ኖሮ እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ክልል በተመድ የታወቀ ይዞታ ያለው፣ የውጭ ግንኙነቱን ራሱን ችሎ የሚመራ ቁመና በኖረው፣ ኢትዮጵያም ፌዴራል ሪፐብሊክ ከመሆን ይልቅ ኮንፌደሬሽን ወይም የአውሮፓ ኅብረት ዓይነት ማኅበረሰብ በሆነች ነበር፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ክልላዊ መንግሥታት የኢትዮጵያ አካል እንጂ በየራሳቸው ሉዓላዊ አይደሉም፡፡ አገሪቱን በጥቅል የሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙት ወደየክልሎች ወርደው ታይተው ሳይሆን፣ “ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ሕዝብ በሆነው” በተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት ነው (አንቀጽ 50፣3)፡፡

ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ የደነገገ፣ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል አለፍና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን አስማምቶ ለማስተዳደር በፍፁም አያንስም፣ አይጠብም፡፡  አንዳንዶች ለልብ መከፋፈል የዳረገን ባሻ ጊዜ የራስ ክልል ከመፍጠር አንስቶ ከአገሪቱ እስከ መለየት ድረስ የሰፉ መብቶችን የሰጠው ሕገ መንግሥት ነው ብለው ያስባሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ እነ እከሌን ምን አካሰሳቸው ብሎ ምክንያቱን ለማወቅ ከመሞከር ፈንታ የመክሰስ መብትን ጥፋተኛ በሚያደርግ መንገድ ውስጥ የሚነጉድ ነውና ችግራችንን ወደ ማወቅ አያደርሰንም፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንከኖች እንዳሉት አይካድም፡፡ ይህን ጉዳይ በሚመለከት ረገድ እንኳ አንቀጽ 39 ውስጥ አሳሳች የሆነ አገላለጽ እናገኛለን፡፡ አብሮ ለመሆን በመስማማት ላይ፣ በአብሮነት የቅንብር አማራጮች ላይ፣ ወይም አብሮነትን በመቀጠልና በማቋረጥ ላይ የፖለቲካ ውሳኔ በመስጠትና በሕዝቦች ዕጣ/ዕድል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ በራስ ቋንቋ መማርና መተዳደር፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ የፖለቲካ ዕጣን በዴሞክራሲ መወሰንና የመሳሰሉት በተግባር እንዲሟሉ የሚፈለጉ መብቶች ናቸው፡፡ በዚሁ ረገድ “የብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ መወሰን” የሚባል “መብት”ን በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ ለማግኘት ብንሻ መቃዠት ይሆናል፡፡

ብሔረሰቦች ይቅሩና አገሮችም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ሁኔታ ዛሬ እንደሌለ ግልጽ ነው፡፡ የሕዝቦች የልማት፣ የግስጋሴ፣ የሰላምና የደኅንነት ዕጣ ፈንታ በራስና በሌሎች ፍላጎት (በውስጥና በውጭ ሰበዞች ተራክቦ) የሚወሰን ነው፡፡ እስከ መገንጠል በሚደርስ ደረጃ የፖለቲካ ዕጣን የመወሰን ጉዳይ ከእነ አፈጻጸም ሥርዓቱ በሕገ መንግሥት ሠፍሮ ባለበት ሁኔታ እንኳ፣ የውሳኔው ተጨባጭነት በፍላጎትና መሥፈርቱን ለማሟላት በመቻል ብቻ አይለካም፡፡ ፍላጎትን ለሰላምና ለግስጋሴ ከማበጀቱ አኳያ በቅጡ ማመዛዘንን ይጠይቃል፡፡ በስሜት ያልታወረ ትክክለኛ ግምገማ ቀደም ተይዞ የነበር ፍላጎትን ከማጥራትም አልፎ፣ በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ሊያስቀይር ይችላል፡፡ ግልብና የተጣደፈ ግምገማም ወደ መቀመቅ መንደርደሪያ ሊሆን ይችላል፡፡ ግምገማው ከናካቴው፣ የውሳኔ መብቴንና ውሳኔዬን በተግባር የሚያከብር ማኅበራዊና መንግሥታዊ አንጀት በዕውን አለ ወይ? ከሚል ጥያቄ የማያልፍ (አስቀድሞ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታን የማደላደል ሥራን የሚደቅን) ሊሆንም ይችላል፡፡

አብሮ መኖርንና መነጠልን በማይመለከቱ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ውሳኔዎች እንኳ በዛሬው ዓለም የአዋጭነትና የመመዘኛነት ግምገማን የሚጠይቁ ሆነዋል፡፡ ዚምባቡዌ ኖራ ኖራ በነጮች ተይዞ የቆየ ሰፊና ምርጥ መሬትን ለገዢነት ድጋፍ መግዣ ከማዋል ባልራቀ ሩጫ ስታከፋፍል፣ አውሮፓና አሜሪካ አፍነው ያደረሱባት እስከ ዛሬም የሚያማቅቃት የኢኮኖሚና የገንዘብ መንኮታኮት ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ለዚህ ግፍ ምዕራብያኑ የቱንም ያህል ተወቃሽ ቢሆኑም፣ የሚገኙበትን ዓለማዊ ሁኔታ በቅጡ ተረድተውና ከሥልጣን ግብግብ ዘለው ይህንን የመከራ ውርጅብኝ ከመከሰቱ አስቀድሞም ሆነ ከጅምሩ የማምከን አገራዊ ኃላፊነትን ያልተወጡት የዚምባቡዌ ገዥዎችና ፖለቲካኞች ዋነኛ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም፡፡ የዚምባቡዌ የውድቀት ልምድ የሚሰጠው ትልቅ ትምህርት፣ ዕጣችን በየራሳችን ብቻ አለመወሰኑን ያጤነ ጠንቃቃነት በዛሬው ጊዜ ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ለጠንቃቃነት ዋስትና የሚሆነንም የሕገ መንግሥት አንቀጾችን ከማረም ቅድሚያ አመለካከታችንን ከዛሬው ዓለም እውነታ ጋር ለማስማማት፣ ማኅበራዊ አዕምሯችንን በትክክለኛ ዕይታ፣ በዴሞክራሲያዊነትና በእኩልነት ለማበልፀግ መቻል ነው፡፡ ይህም ከአፍንጫ ባልራቁ ክፍልፋይ ፍላጎቶች ውስጥ ከመትረክረክ መውጣትንና ያለውን ሕገ መንግሥት የኅብረተሰብና የመንግሥት መኗኗሪያ ከማድረግ ተግባር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዕድገትና ሰላም ከአገር አልፎ አካባቢያዊ የመደጋገፍና የመግባባት አድማስን ሲበዛ ይፈልጋል፡፡ ይህን የግድ የሚያደርገው እየተጠቃለለ በመሄድ ላይ ያለው ዓላማዊ ሁኔታ የነደፈው ፍኖተ ካርታ ብቻ አይደለም፡፡ አካባቢያችን በተለይም የአፍሪካ ቀንድና ዙሪያ ገባው የእርስ በርስ ግንኙነት ለውስጥ ሰላምና ለአገር ልማት ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከኅብረ ብሔራዊ ይልቅ ብዙ የብሔር ብሔረሰብ ቡድኖች ተፈጥረው የመሬት፣ የሀብት፣ የሥልጣን፣ የሥራ፣ የፌዴራላዊ ልማትና የተቋማት ድርሻንና ቅርጫን በመተሳሰብ ላይ መብከንከናቸውና ዘብ መቆማቸው ቀላል ችግር አይደለም፡፡

በ2009 ዓ.ም. መሰናበቻ ላይ አዲሱን ዓመት ለመቀበል ግርግሩና ሆያ ሆዬው የበዛበት የመንግሥት ዝግጅት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የዚህ ዝግጅት አካል ሆኖ ከሔሊኮፕተር በተበተነ አንድ ጽሑፍ መሠረት ኢትዮጵያ ‹‹እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሀብት [የ] ሌለበት አገር›› ነች፡፡ ጉዳዬንና ጽሑፌን የምቀጥለው ይህንን እንዳላየ ዓይቼ ነው፡፡ አገራችን ቢያንስ ቢያንስ የተፈጥሮ፣ የሰው ኃይልና የዕውቀትም ሀብት አላት፡፡

ይህን የአገሪቱን የተፈጥሮ፣ የሰው ኃይልና የዕውቀት ሀብት በየብሔር ወይም በየክልል አጥር ውስጥ ሸንሽኖ የደሃና የሀብታም ክልል ማነፃፀሪያ አድርጎ ማየትና የእነዚህ ብሔር አባል የሆነ ሰው በያዘው ገንዘብና ጥበብ መጀመርያና በቅድሚያ የዚያን ብሔር መጥቀም ያለበት አድርጎ ማሰብ እኩል የማልማት ዕድልን ክፉኛ ይታገላል፡፡ እየተጋጋለም ነው፡፡ አንዱ ችግራችን ይህ ነው፡፡ የአገሪቱ ሁሉን አቀፍ የዕውቀትና የማቴሪያል ሀብት የሁሉንም አካባቢ የልማት አቅም ለማውጣትና ለማሳደግ የመዋሉ የሁሉም መብትነት ገና በአግባቡ መሬት አልቆነጠጠም፡፡ ክልልተኛና ጎሰኛ ዕይታ የአካባቢው ተወላጅ ያልሆነውን አልሚ ሀብት ሊቦጠቡጥ እንደመጣ አድርጎ ይጠረጥራል፡፡ ያንጓልላል፡፡ ተንጓላዩም ባዕድ ቦታ እንዳለ እያሰበ ልማት ከማስፋፋት ይልቅ ትርፍ ወደ ሌላ የማሸሽ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር አድሮና ከርሞ አስፈሪ በቀልና መፈናቀልን ሊዘረግፍ የሚችል መሆኑ እነሆ በተግባርና በውጤቱ እየመሰከረ ነው፡፡ ይህን የመሰለ አጥፊ አዝማሚያ አስቀድሞ በማሸነፍም ሆነ ላልተዛባ የሀብትና የልማት ሥርጭት ከሽፋን ያለፉ ኅብረ ብሔራዊ የባለቤትነት ስብጥር ያላቸው የኢንቨስትመንት ኩባንያዎችን መፍጠርና ማበረታታት ተገቢና ብልህ መሆኑ፣ በባለሀብቱም ሆነ በመንግሥት በኩል አሁንም ገና አልተጤነም፡፡ ሚድሮክ በኦሮሚያ ተጨማሪ የወርቅ ማዕድን መሬት ሲሰጠው በልማትና በአካባቢ ጥበቃ ስም የተደረገው ተቃውሞ (2002) እውነተኛ ይዘት ሀብታችን ተዘረፈ አልነበረም? ቢጂአይ (BGI) የተባለው የፈረንጅ ኩባንያ የቢራ ውጤቶችን (ለአገር ልጅ ኩባንያ የማድላት ችግር ሳይገጥመው) እንደ ልቡ ሲቸበችብ፣ ዳሽን ቢራ ግን በውስጣዊ ኩርፊያ የመጠመዱ አንዱ ምክንያት ይኼው አይደለም ወይ?

ሌላም ዓይነት ችግር አለ፡፡ መንግሥት ወደፊት ከአየር ንብረት መዛባት ጋር ገበያ የማያጣውን የምግብ ሰብልና የባዮ ነዳጅ ተክል ልማት በተመለከተ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያህል ፈቅዶ፣ በዋናነት በውስጥና በውጭም ያሉ የአገር ልጆችን በአክሲዮን እያስተባበሩ ከማንቀሳቀስ ይልቅ ለውጭ ኩባንያዎችና መንግሥታት እስከ 99 ዓመታት ሰፋፊ መሬት በሊዝ በመስጠት ‹‹ተሸጥን›› ለሚል ቅሬታ ሌላ መነሻ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡   

በሌላ በኩልም ሐረርን የሚያህል ትንሽ (ሚጢጢ) ክልል (340 ካሬ ኪሎ ሜትር) አንስቶ እንደ ኦሮሚያ ያለ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላ ጫፍ የተዘረጋ ሰፊ ክልል (353,690 ካሬ ኪሎ ሜትር) የሚገኙበትና መጀመርያ አምስት ሆነው የተቋቋሙት (ክልል ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ፣ አሥርና አሥራ አንድ) ክልሎች በስተኋላ ወደ አንድ የተጠቃለሉበት መዋቅር፣ ለየክልሎቹ ከሚሰጠው ድጎማ ጋር የተያያዘ ጥቅም የጠባብ ሩጫዎች መፍለቂያነቱ ማቆሚያ አላገኘም፡፡ ከእኛ ያነሰ የሕዝብ ቁጥርና የቦታ ስፋት ያለው ክልል ሆኖ ቀጥታ ድጎማ ሲያገኝ እኛ ብቻ በአንድ ላይ የምንታጨቀው በምን አንሰን ነው? እነ እከሌ ልዩ ወረዳ ሲባሉ፣ እኛ ለምን አንባልም? እኛ የራሳችን መለያ ያለን ራሳችንን የቻልን ብሔረሰብ ሆነን ለምን በአንድ ስያሜ ከሌላው ጋር እንጠራለን? ለምንስ እንዳበላለን? የእኛ አካባቢ ራሱን የቻለ አስተዳደር ባለመሆኑ በልማት ተዘነጋን፣ . . . እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች የሚኮራባቸውና ድል እስኪገኝ ድረስ ትግል የሚደረግባቸው ዓላማዎች እየሆኑ ይገኛሉ፡፡

ለእነዚህ ዓይነት ግንዛቤዎችና ጥያቄዎች መፍለቂያ የማይሆን የመዋቅርና የ‹‹አቅጣጫ›› ማስተካከያ እስካልተደረገና ክፍልፋይነትን ሰፊ አመለካከት እስካልሸፈነው ወይም እስካልተካው ድረስ፣ ክልሎች እርስ በርሳቸው ከአጎራባች ክልሎች ጋር በይገባኛል ጥያቄ ሲታመሱ መኖራቸው፣ እንዲሁም ሁሉም ብሔረሰብና ጎሳ ክልል እስኪሆን ድረስ ችግሩ ማቆሚያ ላይኖረው ነው፡፡

የኦሮሚያ ከክልላዊ መንግሥታት ከሁሉም ግዙፍ ነው፡፡ በዚህና ኢትዮጵያ ውስጥ በያዘው ሥፍራ ምክንያት ከትግራይ በስተቀር የማይዋሰነው ክልል የለም፡፡ የሐረሪ ክልልም ውስጡ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ከኦሮሚያ ጋር ‹‹ጉዳይ›› አለኝ የማይል ክልል የለም፡፡ ወይም ኦሮሚያ ጉዳይ አለኝ የማይለው ክልል የለም፡፡ የአዲስ አበባን የኦሮሚያ የእሰጥ አገባ ችግር ምንጭ ራሱ (የድንበር የልዩ መብት ጭምር) ‹‹ባለቤትነት›› በመሆኑ መፍሔው እዚህ ላይ መረባረብ ነው፡፡

ብሔርተኛ ስንጥርጣሪነት ለዴሞክራሲ ያለውን አስቸጋሪነት በሌላ ገጽም እንመልከተው፡፡ ብሔረሰባዊ ወገንነትን/ማንነትን መሠረት አድርገው የሚፈጥሩ ስብስቦች ሕዝብ የተሻለ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማራጭ ያለው የቱ ነው? በሚል ሚዛን ፓርቲዎችን ከመለካት ፋንታ በየብሔር ወገንተኝነታቸው እንዲመርጣቸው የሚያጥር ነው፡፡

በየብሔር መደራጀት እንደተጠበቀ ሆኖ ብሔረሰቦች ፓርቲዎችን ባላቸው አማራጭ ለማበላለጥ ዕድል ሊያገኙ የሚችሉት ለየብሔሩ ከአንድ የበለጡ ፓርቲዎች (ያውም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዓላማን የልዩነት መሠረት ያደረጉ) ከተፈጠሩ ብቻ ነው፡፡ ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ቢያንስ ወደ አንድ መቶ ስልሳ አካባቢ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ብሔረ ብዙ ስብጥር ባለበት አካባቢ ወይም በአገራዊ ሁኔታ የሚያመጣው ለውጥ የለም፡፡ ለምሳሌ ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ከአንድ የበለጡ የሐረሪ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአማራ፣ ወዘተ ፓርቲዎች የምርጫ ውድድር ቢያደርጉ ዞሮ ዞሮ ብሔረሰባዊ የአደረጃጀት አጥሩ ሁሉም በየብሔሩ ካሉ አማራጮች ውስጥ ከማማረጥ እንዳይወጣ ያደርገዋል፡፡

የትልቁም ሆነ የትንሹ ብሔረሰብ ብሔርተኝነት ከማንም ቅድሚያ በራሱ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በብሔርተኛ አመለካከት መደራጀት ምንም ቢሆን የራስን ብሔር የማስቀደምና ሌላውን የማንጓለል ጣጣ ውስጥ ይጥላል፡፡ በብሔረሰባዊ አደረጃጀት ሥልጣን ሲያዝም የአድሏዊነት ችግሩ አብሮ ይወጣልና ሁለተኛ ዜጋ ሆንኩ የሚል ቅሬታ መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ለመላቀቅና የሁሉንም ጥቅም ለማገናዘብ የሚያስችለው መፍትሔ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ከዴሞክራሲ ጋር ሲገናኝና የብሔረሰብ መብት በዴሞክራሲ እኩልነት ውስጥ ሲስተናገድ፣ የብዙኃኑንም ሆነ የአነሳዎች መብት የመቻቻል ዕድል ያገኛል፡፡ በአጭሩ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በገጠርም ሆነ በከተማ በብሔረሰብነት ሳይገደቡና ሳይከፋፈሉ የሚያዋጣቸውን ፕሮግራም እንዲመርጡ፣ ብሔረሰብነት አልፈው የሄዱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዓላማዎችን ማበጀትና መቦዳደን ግድ ነው፡፡

ሌላውና ዋነኛው ብርቱ ያለመግባባትና የግጭት መነሻ የክልሎች የግዛት የባለቤትነት መብት ነው፡፡ ክልሎችን ሉአላዊ የአስተዳደር ይዞታቸውን፣ የመሬትና የግዛት ድርሻቸው አድርጎ ማየት ገዢ ሐሳብ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የአንዱ ወይም የሌላው ክልል ‹‹የግዛት አንድነት›› የማይነካ፣ የማይነጣጠል፣ የክልሉ ግዛትና የእሱም የገዥነት መብቶችም ለሌላ ‹‹ባዕድ›› ክልል የማይተላለፍ ተደርጎ ይታመናል፡፡ የድንበር ግጭቶች አንዱ መነሻ ይኼው ነው፡፡ ይህ ብሔርተኛነትን የተጠናወተው ግብታዊ ግንዛቤና ንቃት ሉዓላዊነትን ከኢትዮጵያ ወስዶ የየክልሎች የየብቻና የየቅል ሥልጣን ያደርጋል፡፡

ይህንንና የወቅቱን የአገራችንን አደገኛ ቀውስ (የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭት) አምጦ የወለደውን የክልሎችን የአስተዳደር ይዞታ ጉዳይ መለስ ብለን አፍታትተን እንቃኘው፡፡

በየትም አገር የአወቃቀርና የአስተዳደር ይዞታዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በፌዴራላዊና በአሃዳዊ አገር መካከል ልዩነት መኖሩ እውነት ነው፡፡ ቀደም ብለን ገና ሲጀመር እንደገለጽነው ፌዴራላዊት ኢትዮጵያን የመሠረቷት ከዚህ በፊት ለየብቻቸው የኖሩ የየብቻ ሕዝቦችና መሬቶች ባለቤቶች አይደለም፡፡ ከዚህም የተነሳ ወደ ፌዴራሉ ማኅበር ስገባ እኔ ‹‹ያዋጣሁት›› መሬትና ግዛት፣ የጥንት የጠዋቱ የባለቤትነት ‹‹ግዛት›› የሚሉት ነገር የለም፡፡ የዛሬ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የረዥም ዘመን ለውጥ ውጤቶች ናቸው፡፡ በጦርነት፣ በፍልሰት፣ በንግድ፣ በባሪያ ፍንገላ፣ ወዘተ ሕዝብ ከላይ እስከ ታች የተንቀሳቀሰባት አገር ናት፡፡ ስለዚህም የራስን ንፁህ የሆነ ባህልም ሆነ የግዛት ድርሻ መከፋፈል የሚባል ነገር የለም፡፡

ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 46 የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው፡፡ ክልሎች የሚዋቀሩት (እንደ እንግሊዝኛው መንፈስም “Delimit” የሚያደርጉት) በሕዝብ አሠፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ብዙዎቻችን ይህንን የአከላለል መሠረት የሆነውን ጉዳይ ከራሱ ከምንጩ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ ‹‹ለእኔ ነው የምትነግረኝ?›› ብሎ ከሚገነፍለው ስሜታችን ማንበብ እንወዳለን፡፡ ክልሎች የሚዋቀሩት ወይም የኢትዮጵያ ምድር ለክልሎች የሚከፋፈለው ቋንቋን ብቻ ሳይሆን፣ ከቋንቋ በተጨማሪም የሕዝብ አሠፋፈርን፣ ማንነትንና እንዲሁም የሕዝብ ፈቃድን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አንደኛው ጉዳይ ይኼኛው ነው፡፡ ለዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተገዝተናል ወይ? ብሎ መጠየቅ ደግሞ ሌላ ጥያቄም ነው፡፡ አግባብም ነው፡፡

አከላለሉና የክልሎች የአስተዳደር መዋቅር መታየትና መመዘን ያለበትም ተስማምቶ ለመተዳደርና ዕድገትን ለማምጣት በሚኖረው ብቃት ነው፡፡ እንዳለ ለማቆየትም ሆነ ለማሻሻል መሠረት መሆን የሚገባው ዋናው ጉዳይ ለጋራ ትድድር ይበልጥ ማመቸቱ ነው፡፡ እንዳለ ስለማቆየትና ወይም ስለማሻሻል እንኳን ማውራት ራሱ ችግር አለው፡፡ በድሮ ሥርዓት በተለይም በአሃዳዊ የድሮ ሥርዓት ናፋቂነት ያስከስሳል፡፡

መጀመርያ ነገር ቋንቋንና ባህልን ተከትሎ ያለቀለት (የተዋጣለት) የውስጥ ድንበር ማበጀት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹የብሔረሰቦች ሙዚየም›› ብትሆንም ሕዝቦቿ በጦርነት፣ በፍልሰት፣ በንግድ፣ በባርያ ፍንገላ፣ ከላይ እስከ ታች፣ ከታች እስከ ላይ ጭምር ተንቀሳቅሰው ተሠራጫጭተዋል፡፡ ተመሰቃቅለዋል፡፡ ተላልሰዋል፡፡ የኦሞ ሕዝቦች ሰሜን ድረስ ተበትነዋል፡፡ አማራና ትግሬ ታች ጋሞ ጎፋ ድረስ ዘልቀዋል፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ መሀል አገዳና የዳርና የመሀል ሕዝቦች ዋና ማላላሻ ቅመም ሆኖ ኢትዮጵያን አያይዟል፡፡ ስለዚህም የኦሮሞና የአፋሩን፣ የኦሮሞና የሶማሌውን፣ የኦሮሞና የአማራውን፣ የኦሮሞና የጉራጌውን ‹‹ትክከለኛ››ውን መለያያ መስመር ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡

ክልሎች የተዋቀሩትም እንዲህ ዓይነት ‹‹ትክክለኛ›› መስመር ለማበጀት፣ ብሔር ብሔረሰቦችን በመገኛ ሥፍራቸው ለማጠርና ለመገድገድ ሳይሆን የተግባባ ትድድርና አስተዳደራዊ አሃዶችን ለማቋቋም ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ ግን የክልሎች የአስተዳደር መዋቅር የመሬት ድርሻ ክፍፍል ማረጋገጫ ተደርጎ ታየ፡፡ በዚያ መልክዓ ምድራዊ ይዞታና ግዛት ውስጥ ብቸና ባለቤትነትን የማስከበርና የመተሳሰብ ጉዳይ ሆነ፡፡ ገና ሲጀመር ድንገት መገንጠል ቢመጣ እየተባለ ግዛት ቆጠራ ውስጥ መግባት ብሔራዊ ግንዛቤና ንቃት ሆነ፡፡ የአንድ ወረዳ ወይም ቀበሌ በሌላ ክልላዊ አስተዳደር ውስጥ መግባት መሬትን በመንጠቅ ተተረጎመ፡፡ መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን የማንነት አካል፣ የአስተዳደር ይዞታን የድርሻና የቅርጫ ካርታ አድርጎ የሚያይ አመለካከት ነገሠ፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ደም ያቃቡ የመሬት መናጠቅ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ የቅርቡና የዛሬ አገራዊ አጀንዳ የሆነውን የሁለቱን ክልሎች ግጭት የወለደው ይኼው ገዢ አመለካከት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የወለደው ግን አይደለም፡፡ የሕገ መንግሥቱ የተጎሳቆለ አፈጻጸም የፈጠረው ችግር ነው፡፡

ሌሎች ቦታዎችም መቋጫ ያላገኙ ያሸለቡ ፍጥጫዎችና ውዝግቦች አሉ፡፡ የምድርና የግዛት ድርሻ ባለቤትነት ደግሞ ‹‹ነባር››ነትን መሠረት ያደረገ ስለሆነ በአንድ አገር ውስጥ የባለቤትነትና የባይተዋር ግንኙነት ፈጥሯል፡፡ መፈናቀልን፣ መባረርንና መሳደድን ያመጣውም ይኼው ነው፡፡ አንዱ ክልል ወይም ቦታ ባለቤት የሆነ ሰው ሌላው ጋ ባይተዋር እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የትም ብትኖር የትም ብትሠራ (ለዚያውም ‹‹በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት›› የአንቀጽ 32 ሕገ መንግሥታዊ መብት ከተገኘ) የማንነት መገኛህን አትዘንጋ የሚል ርዕዮተ ዓለም ይሰብካል፡፡

ችግሩ ይህን ያህል የሰፋና ከዚህም በላይ አደጋ የሚያስከትል ነው፡፡ የዚህ መፍትሔው በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ አለ፡፡ ሕገ መንግሥቱን ማከም ሳያስፈልግ የድርሻ ምድር የባለቤትነት ‹‹መብት››  የብቻ ምድሬ ባይነት የፈጠረውን አመለካከትና ዕይታ ማውገዝን ይጠይቃል፡፡ የትግራይ፣ የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ . . .  ክልል ብለን ያካለልነውና የሸነሸንነው ለአስተዳደር አመቺነት እንጂ የጋራ የኢትዮጵያን ምድር የድርሻና የቅርጫ ካርታ ለመሥራትና በዚህም መሠረት የእያንዳንዱን ክልል የብቻ ባለቤትነት ለማወጅ አይደለም መባል አለበት፡፡ አሁን የመንግሥትና የገዢው ፓርቲ ርዕዮተ ዓለማዊ ድጋፍ ያለው ይህ ዕይታ በ‹‹አንድ አገር አንድ ምድር›› መተካት አለበት፡፡ ይህ አንድ አገር አንድ ምድር፣ ከሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 40(3) ቋንቋ በመዋስ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው››፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ እንዲህ ያለ የይገባኛል ጥያቄ በተነሳ ጊዜ የምንከተለውና መፈጸም ያለበት አካሄድ ነው፡፡ የክልሎችን ወሰን የሚመለከት ጥያቄ ሲነሳ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት እንደሚፈጸም፣ ክልሎች መስማማት ካልቻሉ ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት እንደሚወሰንና ውሳኔውም የመጨረሻ እንደሆነ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ይደነግጋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት (ቀደም ብለንም እንደገለጽነው) ክልላዊ መንግሥታት የኢትዮጵያ አካል እንጂ በየራሳቸው ሉዓላዊ አይደሉም፡፡ አገሪቱን በጥቅል የሚመለከቱ ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙት በፌዴራሉ መንግሥት ነው፡፡ በፌዴራሉ መንግሥት ውስጥም የክልሎች ውክልና አለ፡፡ ከታች ጀምሮ እስከ ክልል፣ ከክልል እስከ ፌዴራል ደረጃ ያሉ ልዩ ልዩ የሥልጣን አካላት በሕዝብ ወሳኝነት እንዲደራጁና እንዲመሩ የደነገገ፣ ክልል ገብ ጉዳዮችን ለክልሎች፣ ክልል ዘለልና ከክልል አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለፌዴራል ለያይቶ የሰጠ ሕገ መንግሥት የኢትዮጵያ ሕዝቦችንም ሆነ ክልሎችን አስማምቶ ለማስተዳደርና ለመዳኘት በፍፁም ሳያንስና ሳይጠብ ይህን አደራና ግዴታ በተገቢው አፈጻጸም መወጣት ያቃታቸው የመንግሥት የሥልጣን አካላት አሠራር ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ መፈተሽ ያለባት ይህንን ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...