Wednesday, February 28, 2024

ሁለንተናዊ ችግሮችን በዘላቂነት የመፍታት ፈተና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ተከስቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2010 ዓ.ም. መግቢያ ድረስ በአገሪቱ እየተከሰተ ያለው ተቃውሞና ግጭት ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ወደ ሥልጣን ከመጣ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ ተቃውሞና ግጭት ሲከሰት ይኼ የመጀመሪያው እንደሆነ፣ የፖለቲካ ተንታኞች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት በ1997 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ ማግሥት ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ የበርካቶች ሕይወት መጥፋቱ አይዘነጋም፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደተከሰተው በመጠኑና በቅርፁ ሰፊ እንዳልነበር ግን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባን የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላን በቀረበ ማግሥት በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ የነበረው ተቃውሞ ወደ ጎንደርና ባህር ዳር፣ እንዲሁም ደቡብ ክልሎች ተሸጋግሮ ከፍተኛ ዋጋ ማስከፈሉ ይታወሳል፡፡ በጎንደር ከተማና ዙሪያው ተቀጣጥሎ የነበረው ሕዝባዊ ጥያቄ ወደ ባህር ዳርና ኦሮሚያ ክልሎች በመስፋፋት፣ ከሰው ሕይወት በተጨማሪ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ ትልልቅ እርሻዎችና ኢንቨስትመንቶች በዚህ ግጭት ሰለባዎች ሆነዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ንብርት ወድሟል፡፡ ከስድስት መቶ የሚበልጡ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ በርካቶች የአካል ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡

በአገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣው የመልካም አስተዳደር ችግርና ሙስና፣ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራና ከወሰን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለዚህ ሕዝባዊ ተቃውሞ ዋነኛ መንስዔዎች እንደነበሩ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነገር ነበር፡፡ እነዚህ ችግሮች መጠናቸውና ቅርፃቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና እየተለወጠ መምጣቱ ደግሞ፣ ወጣቱ ወደ አደባባይ እንዲወጣና መብቱን እንዲጠይቅ አድርገውት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አገሪቱም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በውጣ ውረድ ውስጥ እንዳሳለፈችና ከወትሮው የተለየ መንገድ እንደተከተለች ይታወቃል፡፡ በተለይ በ2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የኢሬቻ በዓል ሲከበር ከ50 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ጉዳዩን ውስብስብ አድርጎት እንደነበር ባለሙያዎች እስከዛሬ ድረስ ይታወቃል፡፡ በእንዲህ ዓይነት በዓል ላይ ፖለቲካዊ አጀንዳን ለማራመድ በመንግሥት በኩልም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ ፍላጎት መኖሩ ደግሞ ለዚህ ችግር ዋነኛ መንስዔ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት በዓላት ከፖለቲካ ውጪ ሆነው መከበር ሲገባቸው፣ ብዙ ወገኖች እጃቸውን ለማስገባት መፈለጋቸው ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ዋነኛ መንስዔ ተደርጎ ሲወሰድም ይሰማል፡፡

የኢሬቻ በዓል ሲከበር እንደዚህ ዓይነት ክስተት የመጀመሪያ ሆኖ ቢወሰድም፣ ክስተቱ ብዙ ጉዳዮች እንዲለወጡ አድርጎ አልፏል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገሪቱ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም ደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ሁከት መነሳትና በኢሬቻ በዓል ላይ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍ፣ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ ከ26 ዓመታት ወዲህ ረጅሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደርጎም ተወስዷል፡፡

በቅድሚያ ለስድስት ወራት በመቀጠል እንደገና ደግሞ ለአራት ወራት ያህል ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ አገሪቱን ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ እንደመለሰና መረጋጋት እንደፈጠረ የወቅቱ ኮማንድ ፖስት የሴክሬታሪያት ኃላፊና የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ተናግረው ነበር፡፡ ለአሥር ወራት ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍንና ወደ ቀድሞ ገጽታዋ እንድትመለስ እንዳደረገ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ አንድምታ እንደነበረው ተነግሯል፡፡ የኮማንድ ፖስቱ አባላት በእነዚህ አካባቢዎች ባከነወኑት ሥራ ለአመፅና ለተቃውሞ ተነሳስቶ የነበራት ወደ መስመር ማስገባት እንደቻሉ ሲነገር ተሰምቷል፡፡ በተለይ ሰሜን ጎንደር ከሱዳን ጋር የሚዋሰን በመሆኑ በዚህ አካባቢ ወጣ ገባ እያሉ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎችን፣ በኮማንድ ፖስቱ አማካይነት መከላከል እንደተቻለ የቀድሞው የሰሜን ጎንደር የአሁኑ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ለአማራ ክልል በተለይም ለጎንደር አካባቢ ከፍተኛ ዋጋ እንደነበረው አቶ አየልኝ ጠቁመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልልም ዘላቂ የሆነ መረጋጋት እንዲኖር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዋጋ እንደነበረው ተነግሯል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው በመላው አገሪቱ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከመኖሩ ድረስ የሚያጠራጥር እንቅስቃሴ እንደነበር አስተያየት ሰጪዎች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መኖሩን እስከሚጠራጠሩ ድረስ ያን ያህል ተፅዕኖ እንዳልነበረው በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም አገሪቱ ወደ ቀድሞ መልኳና ገጽታዋ የተመለሰች እንደሆነ መንግሥት በመመስከር ከዛሬ ሦስት ወራት በፊት አንስቶታል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ያስገደደው የመጨረሻው ምክንያት በኢሬቻ በዓል ላይ የደረሰው አደጋ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ ማግሥት ሌላ ግጭት በአገሪቱ ተከሰተ፡፡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዋሳኝ አካባቢዎች  በተቀሰቀሰ ግጭት፣ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡ በሺሕ የሚቆጠሩት ደግሞ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ተከስተው ለነበሩ ቀውሶች ሌላው ጉዳይ ከወሰንና ከማንነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሲነገር ነበር፡፡ በአማራ ክልል የጠገዴና በትግራይ ክልል የፀገዴ አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ፣ የቅማንትና የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄዎች፣ ከኦሮሚያ የታሰሩ አንጋፋ ፖለቲከኞች፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል መካከል ባለው አስተዳደራዊ ወሰን፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በነጋዴዎች ላይ የተጣለው የቀን ገቢ ግምት ለእነዚህ ሁሉ ቀውሶችና አመፆች መቀስቀስ ምክንያት እንደሆነ ሲነገር ከርሟል፡፡

እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ከጥልቅ ተሃድሶ እስከ የከፍታ ዘመን ንቅናቄዎችን ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በጥልቅ ተሃድሶ ወቅት መንግሥት ለመልካም አስተዳደር እንቅፋት ናቸው ያላቸውን አመራሮች ቦታ ከመለዋወጥ ጀምሮ ከሥልጣን እስከ ማባረር የደረሰ ዕርምጃ እንደወሰደ ገልጿል፡፡ ‹‹እየታደስኩ ነው፣ ሕዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ለመመለስ ቆርጬ ተነስቻለሁ፤›› እያለ በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ ተመሳሳይ ችግሮች እዚህም እዚያም ከመከሰት ግን አልተቆጠቡም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሁለቱ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ነው፡፡

እሑድ መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሰላም ይጠናቀቃል ወይስ እክል ይደርስበታል? የሚለው ጥያቄ አሁንም በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል፡:፡ መንግሥት ‹ችግሬን እየፈታሁ ነው፣ እየታደስኩ ነው› ቢልም አሁንም ችግሮች አሉ፡፡ ለእንዲህ ዓይነት ችግሮች ደግሞ ዘላቂ መፈትሔ ማበጀት ተገቢነት ላይ የብዙዎች ሐሳብ ሆኗል፡፡ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ግልጽ ውይይት ተደርጎ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አስፈላጊ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

መንግሥት እኔ ብቻ ነኝ አዋቂና የችግሩ ቁልፍ ባለቤት ከሚል አባዜ ወጥቶ ከሕዝቡ ጋር በግልጽ በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅበታል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች እየተናገሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በዚህ ይስማማሉ፡፡ አሁን ያለው የፌዴራል ሥርዓት በሕዝቡ መሀል ያሉትን ልዩነቶች የሚያሰፋና የበለጠ ግጭቶችን የሚያጭር እንጂ፣ ለሕዝብ አንድነትና አብሮ መኖር የሚጠቅም እዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ከግምት አስገብቶ ከአንድነት ጋር በተያያዘ የተቀመጡት ነገሮች ማሻሻያ እንደሚያስፈልጋቸው ያምናሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩነቱ መጠበቁና መከበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አንድ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹እነዚህን የሚያጠናክርና ቦታ የሚሰጥ ሥርዓት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የኢሕአዴግ ሥርዓት በሚሄድበት ሁሉ ትክክል ነኝ ቢልም ትክክል እንዳልሆነ ግን በተግባር አሁን ያለው ነገር እያሳየ ነው፤›› ሲሉ አቶ ልደቱ ያብራራሉ፡፡ በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ በስፋትም በይዘትም ከፍተኛ የሆነ የአገር ህልውናን ሥጋት ውስጥ የሚከት ሁኔታ እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ልዩነት ውበት ነው ሊከበር ይገባዋል፡፡ በዚያው መጠን ከዚያ በላይ ደግሞ አንድነት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የምንዘረጋው አስተዳደርና መዋቅር ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፤›› ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡

ትልቁ ችግር ያለው በገዥው ፓርቲ እንደሆነ አቶ ልደቱ ያስረዳሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ እኔ ከምለው አስተሳሰብ ውጪ ለሌላው አስተሳሰብ ሁሉ አይሠራም እያለ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ የባሰ ችግር በአገሪቱ እንዳይከሰት አገራዊ ተሳትፎ ያለው ምክክር እንዲደረግ ተደርጎ፣ በሕገ መንግሥቱና በፌዴራል አደረጃጀቱ ላይ ያሉ ችግሮች እንደገና የሚሻሻሉበት ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ሶማሌና ኦሮሚያ በዚህ መጠን ግጭት ውስጥ የገቡበት ታሪክ እንደሌለ አቶ ልደቱ ጠቅሰዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቀሶ የነበረው የተቃውሞ እንቅስቃሴም በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡ በቆዳ ስፋትም ሆነ በተሳተፈው የሕዝብ ቁጥር በታሪክ ታይቶ እንደማይታወቅ ጠቁመዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የአገሪቱ ችግሮች የበለጠ እየተባባሱ እንደሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የቀደሞ ችግሮች አልተፈቱም፡፡ አዳዲስ ቅሬታዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ መንግሥት ችግሩን አልፈታውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አልፈታውም ብቻ ሳይሆን የችግሩን ትክክለኛ መንገድ አልያዘውም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ቁጭ ብሎ መንግሥት ከራሱና ከሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በዋናነት ደግሞ ከጉዳዩ ባለቤት ሕዝብ ጋር መመካከር እንደሚያስፈለግ አቶ ልደቱ አውስተዋል፡፡  በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ ከተማ በአርሰዴ ሐይቅ እየተከበረ ያለው የኢሬቻ በዓልም ተሳክቶ እንዲከበር፣ ባለፈው ዓመት ተከስቶ እንደነበረው ዓይነት ቀውስ እንዳይፈጠር በዓሉን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም እንደማያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚ ኃይሎች የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡

ይህንና መሰል ሃይማኖታዊ በዓሎች ከፖለቲካ መጠቀሚያነት በፀዳ መንገድ መካሄድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን ችግሩ ምንድነው መንግሥትም መጠቀሚያ ሊያደርጋቸው ይፈልጋል፣ ተቃዋሚ ኃይሉም መጠቀሚያ ሊያደርጋቸው ይፈልጋል፡፡ ይኼ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁለቱ ኃይሎች ከእንደዚህ ዓይነት ድርጊት ራሳቸውን መቆጠብ አለባቸው፤› ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኙና የቀድሞ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ በአብዛኛው ግጭቶች የሚከሰቱት በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጉዳዮች በደንብ ባላደጉና የተረጋጋ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መሠረት ባልጣሉ አገሮች እንደሆነ አስረደተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለው ግጭት ግን ከዚህ የተለየ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቸውን ሲያስረዱ የግጭቶች ተደጋጋሚነትና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና ገጽታቸው እየሰፋ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡

በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በኮንሶ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች በባህሪያቸው በአብዛኛው የተለያዩ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግጭቶች እርስ በእርስ የሚካሄዱ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ በተለይ ድንበርን ተከትሎ ከግጦሽ መሬትና ከመሬት አጠቃቀም ጋር  የሚያያዙ ናቸው ብለዋል፡፡ በክልሎች መካከል ከድንበር ጋር ተያይዘው የሚነሱ ግጭቶች ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጤቶች ናቸው ብለዋል፡፡

የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በተገቢው ሁኔታ ባለመፈታታቸው የመጣ ችግር እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ አድጓል የሚባለው ኢኮኖሚ ሁሉን ባለማዳረሱ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለቤት ባለመሆናቸው የተነሳ የመገለልና የመገፋት ስሜት እየፈጠረባቸው እንደመጣ ይናገራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ባይተዋርነትን የሚያስከትል እንደሆነ አቶ ሙሼ አስታውቀዋል፡፡

‹‹አንዳንድ አካበቢዎች ላይ መሬቱ የእኛ ነው፡፡ ሌሎች መጤዎች መሬቱ ላይ ሠፍረው ይዞታቸው እየተሻሻለ የእኛ ዝቅ ያለበት ምክንያት አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ በመሬታችን መጠቀም አለብን የሚለው አመለካከት ሌላው ከመንግሥት ጋር እየተፈጠረ ያለ ግጭት ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተረፈ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረው የፖለቲካ ምኅዳር በተለያየ ምክንያት እየጠበበ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ሕዝቡ የሚያነሳቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚደመጡበት ዕድል አብሮ መጥፋቱን ገልጸዋል፡፡ ነፃ የግል ሚዲያ መጥፋትና መመናመን፣ በተቃራኒው ኦዲዮ ቪዥዋል ሚዲያ እየተስፋፋ መምጣቱና መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ማተኮሩ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት እንቅፋት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ሕዝቡ እሮሮውን፣ ብሶቱንና ስሜቱን የሚገልጽበት ዕድል የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ሰው የሚኖረው በውጤት ብቻ ሳይሆን በተስፋ ጭምር እንደሆን የጠቀሱት አቶ ሙሼ፣ ችግሬ ተደምጧል፣ ታይቷል፣ የእኔ ጉዳይ ነው የሚል ስሜት እንዲኖረው ማድረግ በራሱ የሚያበረታታ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹በመጀመሪያ ትምህርትህን ጨርሰህ ሥራ ካላገኘህና ሕይወትን መቀጠል የሚያስችል ሀብት እጅህ ላይ ከሌለህ በአገርህ ላይ ባይተዋርነት ይሰማሃል፡፡ በዚህም የተነሳ ውሳኔህን በራስህ ለመወሰን መሄድህ አይቀርም፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ አነሰም በዛ ከዚህ በፊት የፖለቲካ ፓርቲዎች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ እንደነበርና ክፍተትን በመሙላት፣ የሕዝብን ጥያቄ የራሳቸው አድርገው ወደ መንግሥት በማቅረብ፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ሚዲያዎች እንዲያውቁት በማድረግ እየሠሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን መንግሥት ለጥያቄዎች ራሱ ብቻ መልስ ለመስጠት እየሞከረና ባልተደራጀ የፖለቲካ ፍልስፍና እየተመራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በአገሪቱ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ የተከሰተው ችግርም በድንገት የመጣ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ እየተከሰተ ያለው ተቃውሞና ግጭት በሰከነና በተጠና መንገድ መፍትሔ ማግኘት እንዳለበት ባለሙያዎች አሁንም ድረስ እያሳሰቡ ነው፡፡ አቶ ሙሼ እንደሚሉት መፍትሔ ለማግኘት ዘለቄታ ያለው ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ዛሬ ብድግ ብለህ ይህንን ተው፣ ያንን ተው፣ ታገሰኝ በማለት የማይፈቱ ፈጣንና ቀልጣፋ መልስ የሚፈልጉ ነገሮች አሉ፡፡ መንግሥት ራሱ ጠያቂ፣ ራሱ መልስ ሰጪ ሆኖ ሊዘልቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ጥያቄዎችን ከሕዝቡ በቅጡ መሰብሰብ፣ በአጭር ጊዜ ጥያቄዎች እንዴት እንደሚፈቱ ለሕዝቡ ማሳየትና በመካከለኛ ጊዜ የሚፈቱትን መፍታት ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነና እየተዳከመ በመምጣት የባለቤትነት ስሜት ማሳጣቱንና ባይተዋርነት ማምጣቱን አቶ ሙሼ ገልጸዋል፡፡ ያለማቋረጥ በምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፍ በመለመዱ፣ ለምርጫ የነበረው ቦታ እየጠፋ ለመምጣቱ እንደ ምክንያት አንስተዋል፡፡ ምክንያታቸውን ሲያብራሩም ተደራጅቼና ራሴን አጠናክሬ የተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለሞች በመቅረፅ በሒደት መንግሥት የመሆን ዕድል አለኝ የሚለውን ነገር እያጠፋ መምጣቱን ያነሳሉ፡፡ ‹‹ስለዚህ እዚህ ላይ እርምት መወሰድ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በሦሰተኛ ደረጃ እንደ መፍትሔ የሚያስቀምጡት ጉዳይ በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ችግር ነው፡፡ ‹‹እንዴት ነው የአብዛኛውን ብሔረሰብ ጥያቄ መመለስ የሚችል የኢኮኖሚ አቅጣጫ መቀየስ የሚገባን ብለህ መሥራት ይጠበቅብሃል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ችግሮች በቅጡ ፈትቶ ማኅበረሰቡን ኢኮኖሚው ከሚፈጥረው ትሩፋት ተቋዳሽ የሚሆንበት መንገድ ማሰብ አለብህ፤›› ሲሉ  አክለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ ብዝኃነት ባለበት እንደ ኢትየጵያ ዓይነት አገር ብዝኃነት የሰላም ሥጋት የሚሆነው በማንነቶች መካከል እኩልነት ከሌለ፣ ሁሉም ሕዝቦች እኩል የመልማትና የማደግ ዕድል፣ እንዲሁም ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚነት ካጡ ነው፡፡ በአገሪቱ እየተገነባ ያለው ፌዴራላዊ ሥርዓትም የሕዝቦችን ጭቆናና አድልኦ የሚያስወግድ ሕጋዊና ተቋማዊ ሥርዓት መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የማንነቶች እኩልነትና እኩል የመልማት ዕድል ተረጋግጧል፤›› ብለዋል፡፡

እነ አቶ ልደቱ የአገሪቱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ጉዳዮች እየተነሱ እንደሆነ ቢጠቅሱም፣ ዶ/ር ነገሪ ግን ውስጣዊ ሰላምን የማናጋት አቅም ያላቸው ጥያቄዎች ሁሉ መሠረታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለወደፊትም ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የብዝኃነት አያያዝ ጋር ያልተቃኙ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፕሮግራሞችና አቅጣጫዎች ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ሕገ መንግሥታችን ዋስትና ሰጥቷል፤›› ብለዋል፡፡

በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት፣ አንዱ የአገር አንድነት ዘብ፣ ሌላው ግን ተመልካች ተደርጎ የሚታይበት ጊዜ ማክተሙንና አገሪቱ ከመበታተን አደጋ ወጥታ ዴሞክራሲያዊ አንድነቷን በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባች ያለች መሆኗን አስረድተዋል፡፡

‹‹የሕዝቦቿን ብዝኃነት በአግባቡ ማስተናገድ በመቻሏም አስተማማኝ ሰላም እንዲኖራት አስችሏታል፤›› ብለው፣ ሰላሟ በአስተማማኝ መሠረት ላይ በመገንባቱ ደግሞ ፍትሐዊ፣ ፈጣንና ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ እንድትችል እንደረዳት ጠቁመዋል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡባትና በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባት እያሳሰቡ ቢሆንም፣ መንግሥት በበኩሉ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ሰላም በአገሪቱ መረጋገጡን በተደጋጋሚ ጊዜ ተናግሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም በሌለበት ቀጣና ውስጥ ሆና የውስጧን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅና  መከላከል  እንደቻለች መንግሥት ቢገልጽም፣ የፖለተካ ተንታኞች በተለያዩ አካባቢዎች እየተነሱ ያሉ ግጭቶችን እንደ ክፍተት ያነሳሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን አሁን እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡

አገሪቱ ሰላም በሌለው ቀጣና ውስጥ ብትሆንም ከዚህ በፊት በነበረው ታሪክና  አንድነት ምክንያት፣ በአሁኑ ጊዜ የሚታዩ ችግሮች ቀን ሳይሰጣቸው መፈታት እንደሚገባቸው ይናገራሉ፡፡ መንግሥትም እየተፈጠረ ያለውን ችግር እንደ መማሪያ እየወሰደና ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ እየሠራ ስህተቶችን ማረም እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የሁሉንም ዜጎች ሐሳብ በማሰባሰብ በጋራ መፍታትና ወደ አንድነት በሚያመጡ ጉዳዮች ላይ መሥራት ተገቢ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሲሆን እዚህም እዚያም እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች መፍትሔ እያገኙና አገራዊ መግባባት እየተፈጠረ ይሄዳል በማለት ተስፋቸውን ያስረዳሉ፡፡ 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -