Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መፍታት የሚገባንን የወሰንና የመሳሰሉት ችግሮች ባለመፍታታችን እንጂ የሰሜን ጎንደር ሰው መሣሪያ ስለታጠቀ አይደለም አመፅ ተቀስቅሶ የነበረው››

አቶ አየልኝ ሙሉዓለም፣ የቀድሞው ሰሜን የአሁኑ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ

በ2008 ዓ.ም. ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲነሳባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል አንዱ ሰሜን ጎንደር ዞን ነው፡፡ በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከት ከስድስት መቶ በላይ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱና ንብረት መውደሙ ይታወሳል፡፡ ይህ ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ከተስፋፋና የብዙ ሰዎች ሕይወት ከጠፋ በኋላ መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ በጥልቅ ተሃድሶ አማካይነት በአመራሮች ላይ ሹምሽር ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ከአንዱ ወደ ሌላ ቦታ ከተሸጋገሩት አመራሮች መካከል አቶ አየልኝ ሙሉዓለም አንዱ ናቸው፡፡ የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው ከመጀመሩ በፊት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አየልኝ፣ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ነበር፡፡ ሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞን ከተከፈለ በኋላም የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳደሪ ሆነው እየሠሩ ናቸው፡፡ በቅማንት ሕዝበ ውሳኔ፣ በጎንደር የፀጥታ ሁኔታ፣ በጠገዴና በፀገዴ፣ እንዲሁም ሌሎች ተዛማች ጉዳዮችን በተመለከተ ዘመኑ ተናኘ ከአቶ አየልኝ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደሚታወቀው ካለፈው አንድ ወር ወዲህ ማለት ይቻላል ሰሜን ጎንደር (በቀድሞው እንውሰደውና) ዞን የቅማንትና የአማራ ሕዝብ ተቀላቅሎ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ተደርጓል፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ደግሞ በአራት ቀበሌዋች ሊካሄድ የነበረው ሕዝበ ውሳኔ እንዲዘገይ ሆኗል፡፡ የዚህ መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው?

አቶ አየልኝ፡- እንደተባለው የቅማንት የራስ አስተዳደርን ለመወሰን የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄን በምን መንገድ እንፍታው በማለት ከኅብረተሰቡ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደን ስንወያይ ቆይተናል፡፡ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገን የተደረሰው መደምደሚያ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን መሠረት አድርገን እንፍታቸው የሚል ስምምነት ነበር ከኅብረተሰቡ ጋር የደረስነው፡፡ በርከት ያሉ ቀበሌዎች ነበሩ የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች የተነሳባቸው፡፡ በይበልጥ የቅማንት ማኅበረሰብ በሚኖርባቸው አካባቢዎች አማራዎች ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ ቢደረግ ትርጉም ያለው ተወዳዳሪ ልንሆን ስለማንችልና የተለየ ነገር ስለማናመጣ፣ ጊዜና ገንዘብ ከመጨረስ በስተቀር ትርጉም የለውም፡፡ እኛ አብረን እንኖራለን ብለው ፈቃደኛ በሆኑት አካባቢ እንዲሁ ወደ ቅማንት አስተዳደር እንዲካለል ለማድረግ የተስማማንበት ሁኔታ ነበር፡፡

ሁለተኛ አማራ በይበልጥ በሚኖርባቸው አካባቢዎች ደግሞ ቅማንቶቹ አይ እኛ ድምፅ ቢሰጥ የአማራውን ድምፅ ልናሸንፍ ስለማንችል አብረን እንኖራለን፣ ምናልባትም ከተቻለ ደግሞ አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ጐጦች የሚካለሉበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ወደ ድምፅ መግባት የለብንም ብለው የወሰኑ ነበሩ፡፡ በዚህ መሠረት ጥያቄ ከቀረበባቸው የተወሰኑት በነባሩ አስተዳደር፣ የተወሰኑት ደግሞ በቅማንት አስተዳደር እንዲካለል ለማድረግ ስምምነት አለን፡፡ አሥራ ሁለቱ ቀበሌዎች አካባቢ ግን በወቅቱ ስምምነት ማግኘት አልተቻለም፡፡ አማራው እኛ እንበልጣለን ስለዚህ ወደ አማራው ነው ማካለል ያለብን የሚል ጥያቄ አነሳ፡፡ ቅማንቶቹ ደግሞ አይ እኛ እንበልጣለን የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ ስለዚህ ሁለቱን በስምምነት፣ አንዱ ከፍተኛ ቁጥር ስላለው በሚል ሌሎች በጨረሱት መንገድ ሊጨርሱት አልተቻለም፡፡ ከዚያ በኋላ አጠቃላይ ኮንፈረንስ አካሄድን፡፡ ሕዝቡ ተግባብቶ መፍታት ካልቻለ ያለው አማራጭ በድምፅ መወሰን ነው የሚል አጠቃላይ መግባባት ተደርሶ ነበር፡፡ ላዛ ሹምዬ፣ አንከርደዛ ናራ አውዳርዳና ገለድባ የሚባሉ እነዚህ አራት ቀበሌዎች ግን ስምምነት ላይ አልደረሱም፡፡ በተለይ ሁለቱ ናቸው፣ ሁለቱ እንኳ ብዙም ችግር አልነበረባቸውም፡፡ አንከርደዛና ላዛ በፊትም በውይይቱ ላይ መግባባት አልደረስንም፡፡ በሕዝበ ውሳኔ እንጨርሰዋለን ስንላቸው በድምፅ ውሳኔ መሆን የለበትም አናምናችሁም የሚል ጥያቄ አነሱ፡፡ የቅማንት ኮሚቴ አለው፡፡ የተደራጀ ኮሚቴ አለው፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ እንጭበረበራለን የሚል ከፍተኛ ሥጋት አላቸው፡፡ የነበረው ሥጋት ይህ ስለነበረ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከሌላ በማምጣት በቀላሉ እንግባባለን ብለን ነበር ያሰብነው፡፡ ምንም እንኳ ቁጥራችን እንደሚበልጥ ብናውቅም ተጭበርብረን ልንሸነፍ ስለምንችል ወደ ድምፅ አንገባም የሚል አቋም መጀመርያውንም ነበራቸው፡፡ ይህንን ሥጋታቸውንና አቋማቸውን ፈርተን ነው እንግዲህ ምርጫ አስፈጻሚ ከሌላ ክልል እንዲመጣ የተደረገው፡፡ እነሱም አልፎ፣ አልፎ ይህን ያነሱ ስለነበር፡፡ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከሌላ ነው የመጡት፣ እናንተ ታዛቢ ናችሁ፣ ትመርጣላችሁ ስንላቸው ከአብዛኞቹ ጋር መግባባት ቻልን፡፡ ጥርጣሬያቸውን ማስወገድ ቻልን፡፡ የእነዚህኞቹን ግን ሥጋታቸውንና ጥርጣሬያቸውን በወቅቱ ማስወገድ አልቻልንም፡፡

ሪፖርተር፡- የእነዚህ ቀበሌዎች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንድነው የሚሆነው?

አቶ አየልኝ፡- አልቻልንም፡፡ ስለዚህ ጥርጣሬና ሥጋታቸውን ማስወገድ ስላልቻልን ያው ጊዜ ወስደን እንወያይ ብለን አቆየነው ማለት ነው፡፡ በእኛ ፍላጎት አሁንም ውይይት እናደርጋለን፡፡ ሌሎቹ ጋ ያዩትን ተሞክሮ ይወስዳሉ፡፡ ምንም ማጭበርበር አለመኖሩን ከዚያ ትምህርት ይወስዳሉ ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ወደ ውሳኔ ሥርዓቱ ይገባሉ ብለን ነው የምናስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሕዝበ ውሳኔ መደረጉ የማይቀር ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አየልኝ፡- በእኛ በኩል እስካሁን ድረስ ያለን አቋም ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ ነው፡፡ እንወያይ፣ እንምከር ብለዋል፡፡ ይህን ነው እየጠበቅን ያለነው፡፡ አሁን ተጨማሪ ውይይት እናደርግና መግባባት ላይ እንደርሳለን ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የስምንት ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዷል፡፡ ይህንን እንዴት ነው የገመገማችሁት?

አቶ አየልኝ፡- ሒደቱ ሰላማዊ ነው፡፡ የፈለግነው ምርጫው ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ነው፡፡ አሸናፊ የለ፣ ተሸናፊ የለ፡፡ ሁሉም ሕዝቦች በያሉበት ነው የሚኖሩት፡፡ ስለዚህ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረግ፣ የተለያዩ ፀረ ሰላም ኃይሎች በመሀል እየገቡ ቅማንቱንም አማራውንም ያደናግሩ ስለነበር ምንም ዓይነት ትንኮሳ እንዳይኖር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማጠናቀቅ ነው የነበረው ግባችን፡፡ እሱን አሳክተናል፡፡ ሁለተኛ ሕዝቡ በነቂስ እንዲወጣና ድምፁን እንዲሰጥ ነበር ፍላጎታችን፡፡ ከተጠበቀው በላይ ነው ድምፅ የሰጠው፡፡ የተመዘገበውም ከተጠበቀው በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ዕድሉን ወስኗል ማለት ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ጤናማ በሆነ መንግድ በውይይትና በመግባባት ፈትተነዋል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አኳያ ሲታይ በእኛ በኩል የገመገምነው የድምፅ አሰጣጥ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ሰላማዊ ነው፡፡ ስኬታማ ነው፡፡ ሕዝቦች ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ችግርን መፍታት እንደሚቻል ያስተማረ ጥሩ ተግባር ነው ብለን ነው የወሰድነው፡፡

ሪፖርተር፡- በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ተዟዙረን ባየናቸው አካባቢዎች የቀበሌ ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ድምፅ እንዲሰጡ ተደርጓል የሚል ስሞታ ነበር፡፡ ለምሳሌ ኳቤር ሎምየ ይህ ጥያቄ ተነስቶ እንደበር እኛም በቦታው ተገኝተን አይተናል፡፡ የቅማንት ማኅበረሰብ የኳቤር ሎምየ ቀበሌ ያልሆኑ ዜጎችን ወደዚህ ምርጫ ጣቢያ አምጥተው እንዲመርጡ ተደርጓል የሚል ጥያቄ ከአማራው ማኅበረሰብ ሲነሳ ነበር፡፡ ይህን ጥያቄ እናንተ ዘንድስ ደርሶ ነበር? በመጨረሻስ እንዴት ነው ሊፈታ የቻለው? ጥያቄያቸውስ ምን ያህል ተገቢ ነው?

አቶ አየልኝ፡- ይህ የምርጫ ቦርድ ሥራ ነው፡፡ የአስፈጻሚው፣ የአመራሩ አይደለም፡፡ ቅሬታ ቀርቦላቸዋል፡፡ ቅሬታውን ለማጣራት ሞክረዋል፡፡ የምርጫ ጣቢያ የወሰነውን ውሳኔ እንደገና የወረዳ የምርጫ የቅሬታ ሰሚ ለማየት ሞክሯል፡፡ አይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ሰዎቹን ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አምጡ ብሏቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መረጃ እንዳመጡ ነው የሰማነው፡፡ እዚያ ውስጥ እኛ መግባት ስለማንችል የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ያለን መረጃ ግን ምርጫ አስፈጻሚዎች ጠይቀዋቸው በቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ለመሆናቸው ማስረጃ አቅርበው ድምፅ እንዲሰጡ ነው የተደረገው፡፡

ሁለተኛ አሁንም የቀረ ካለ ሥርዓቱን ተከትለው ቅሬታ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ቅሬታን ሥርዓት ባለው መንገድ ማቅረብ ነው የሚፈለገው፡፡ እነሱ ችግር አለ ካሉ አሁንም ቅሬታቸውን ሥርዓት ባለው መንገድ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ የነበረው ነገር ታዛቢዎች አሉ፣ ተወካዮች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ነው ምዝገባ ሲካሄድ የነበረው፡፡ የሾለከ ነገር ግን አይኖርም ማለት አይቻልም፡፡ የሾለከ ነገር ሊኖር ስለሚችል፣ ይህ የሾለከ ነገር ካለ ደግሞ ሥርዓቱን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ይፈታዋል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ በፊት ሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች መከፈሉ ይታወቃል፡፡ አሁን በምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ለተከፈሉ ዞኖች አመራሮች ተመድበውላቸው ወደ ሥራ ገብተዋል?

አቶ አየልኝ፡- አዎ፡፡ እንደተባለው ዞኑ በጣም ትልቅ ቆዳ ስፋት ያለው ነው፡፡ ሰፊ የሕዝብ ብዛት ያለው ዞን ነው፡፡ የተለያየ የአየር ንብረትና አግሮ ኢኮሎጂ ያለው ዞን ነው፡፡ እነዚህንና የመሳሰሉትን ምክንያት በማድረግ እንደተባለው ዞኑ ተከፍሏል፡፡ ወደ ሦስት ነው የተከፈለው፡፡ ዞኑ ከተከፈለ በኋላ አሁን መልሶ የማደራጀት ሥራ እየተከናወኑ ነው፡፡ አስተዳዳሪ፣ ምክትል አስተዳዳሪና ሌላ ከፍተኛ ኃላፊነት የለው ዘርፍም ተሹሟል፡፡ እነዚህ ሦስት ሰዎች ተሹመው መዋቅራቸውን እያደራጁና ቢሮ እየተከራዩ ነው ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ አመራሮች እነማን እንደሆኑ ማወቅ ይቻላል?

አቶ አየልኝ፡- ይቻላል፡፡ አንዱ ዘለዓለም ነው የሚባለው፡፡

ሪፖርተር፡- የአባታቸው ስም ማን ነው የሚባለው?

አቶ አየልኝ፡- ዘለዓለም ይባላል ለጊዜው የአባቱን ስም ረስቼዋለሁ፡፡ የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አምሳሉ ደረጀ ይባላል፡፡ እሱ ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሜን ጎንደር ዞን ወደ ሦስት ዞኖች በመከፈሉ ጎንደር ጎንደርነቱን ያጣል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር በቅርብ ሆኖ ለመፍታትና የኅብረተሰቡን ችግር ለመመለስ ነው የሚሉ አሉና እርስዎ በዚህ ላይ ምንድነው የሚሉት?

አቶ አየልኝ፡- እኔ ጎንደሬነትንም አያሳጣም ባይ ነኝ፡፡ ዓላማው ከፍ ሲል አማራነት፣ ከዚያም ኢትዮጵያዊነትን በአስተዳደር መከለል ይህን የሚያሳጣ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ይኼኛው ዓላማ ባጭሩ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ በቅርብ የመልካም አስተዳደር አገልግሎትና የልማት ድጋፍ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የእኛ አገር ሀብት ካፒታል አይደለም፣ ኢንዱስትሪም አይደለም፡፡ የአርሶ አደር ጉልበት፣ የሕዝብ ጉልበት፣ መሬት ነው ሀብታችን፡፡ የተበጣጠሰ መሬት ነው፡፡ ይህን የተበጣጠሰ መሬት የተበታተነው አርሶ አደር ለማልማት የቅርብ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ በጣም በቅርብ አግዘኸው ሙያዊና አስተዳደራዊ ድጋፍ ሰጥተኸው፣ የቴክኖሎጂ ትውውቅ አድርገህ፣ ደክመህ ነው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የምታደርገው፡፡ ስለዚህ እኔ ከዚህ ነው የማየው፡፡ የሚባለው ነገር በሙሉ መሠረተ ቢስ ነው፡፡ ጎንደሬነትንም የሚያጣበት ሥነ ልቦና የለውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ምንም ብትሠራ ተቃውሞ ያጋጥምሃል እንጂ፣ ይህ ለሰሜን ጎንደር ትንሳዔ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ መንግሥት ትልቅ አደራ የገባበት ጉዳይ ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ ነው የሚያወጣው፡፡ ብዙ መዋቅር ነው እየፈቀደ ያለው፡፡ ስለዚህ ዞኑ ከቆየበት ችግር አኳያ ልለውጠው፣ ልደግፈው፣ በቅርብ አመራር ልስጠው ከሚል እንጂ ከሌላ መነሻ የሚሆን ነገር የለውም፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ አሁን የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ነዎት፡፡ ከዚያ በፊት ግን የአጠቃላዩ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ ሰሜን ጎንደር ዞን ደግሞ የፀጥታ ችግር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲነሳበት ይታያል፡፡ የዚህ ችግር ምንጩ ምንድነው? እስካሁን ድረስ ዞኑን የፀጥታ ችግር የሚፈታተነው ለምንድነው?

አቶ አየልኝ፡- ጥሩ፡፡ እንግዲህ ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው የቆየ ባህል አንዱ ችግር ነው፡፡ የሰሜን ጎንደር ማኅበረሰብ በተለይ ቆለኛው አካባቢ መንገድ የለውም፡፡ መንገድ የሌለው ስለሆነ እርስ በርሱ ስለሆነ የሚተዳደረው የሆነ ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ወደ ፍርድ ቤት፣ ወደ ሕግ መጥቶ በፍርድና በሕግ ከመዳኘት ይልቅ በራሱ የመጠቀም ልምድ አለ፡፡ መገዳደል አለ፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ደም መመላለስ፣ መበቃቀልና የመሳሰሉ ሥራዎች ከኋላቀርነት ጋር የሚያያዙ አሉ፡፡ አካባቢው ካለመልማቱና ካለማደጉ ጋር ተያይዘው የሚመጡ አሉ፡፡ ሁለተኛው የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ለፀረ ሰላም ኃይሎችና መንግሥትን ለሚቃወሙ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በቀላሉ መንግሥት የሚያገኛቸው አይደሉም፡፡ አካባቢው በጠቅላላ መደበቂያ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከሻዕቢያ የሚመጣ የግንቦት ሰባትም በለው አርበኛ ግንባር በዚህ ውስጥ ያልተፈለፈለ የለም፡፡ እነዚህ ሁሉ መደበቂያ የሚያደርጉት ይህን አካባቢ ነው፡፡ የሕዝቡንም ኋላቀርነት ተጠቅመው፡፡ አካባቢው አለመልማቱንና የመሠረተ ልማት አለመኖሩን ተጠቅመው ፀረ ሰላም ኃይሎች በዚህ አካባቢ ይገባሉ ማለት ነው፡፡ ይህ አንድ መደበቂያና መሰብሰቢያ ሆኗቸዋል፡፡ ሁለተኛው ችግር ደግሞ ይህ አካባቢ ከሱዳን ጋር፣ በቅርብ ርቀት ደግሞ ከኤርትራ ጋር ይዋሰናል፡፡ ስለዚህ በኤርትራ በኩል በጋሽና ሰቲት፣ ሁመራና በታች በሱዳን በኩል ተሽሎክሉከው ወደ ሰሜን ጎንደር ወደ መተማና ቋራ ይገባሉ፡፡ ወደ ምዕራብ አርማጭሆ ይገባሉ፡፡ በዚህ ምክንያት አካባቢው ሲታወክ የኖረ ነው፡፡ የሰላም ዕጦት በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ነው፡፡

ስለዚህም በተደጋጋሚ ጊዜ የመከላከያ ኃይል እያገዘ፣ የክልሉ ፀረ ሽብር ኃይል እየረዳ ብዙዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ አንዳንዶቹም በራሳቸውም የማያዋጣ መሆኑን ሲያወቁ ወደ መንግሥት እየተቀላቀሉ ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ደግሞ በ2008 ዓ.ም. የተፈጠረው ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ሲከሰት አካባቢው ለዚህ የተመቸ ስለሆነ ከዚህ ከከተሞች አካባቢም ያኮረፈው በሙሉ ወደነዚህ አካባቢዎች መሰባሰብ ጀመረ ማለት ነው፡፡ ወደ እነዚህ አካባቢዎች ተሰባሰበ፡፡ እነዚህን ኃይሎች ለመነጠል በተደረገው ጥረት በርከት ያሉ የፀረ ሰላም ኃይሎች፣ ተደናግረውም የወጡ እንደገና ደግሞ ቅድም ስለው በነበረው በእርስ በርስ መገዳደልም ከሕግ ርቀው የነበሩ ሰዎች ዱር ገደሉን ይዘናል ማን ይነካናል ብለው በዱር በገደል የነበሩ ነፍስ የገደሉ ሰዎች፣ ከዚያም ባንዳዎችና በሻዕቢያ ተላላኪነት የመጡ የግንቦት ሰባትና የመሳሰሉት ድርጅቶች አካላት ነበሩ፡፡ እነዚህ አብረው እየተቀላቀሉ ነበር፡፡ እነዚህን ለይተን ለማጥራት ነው ጥረት የተደረገው፡፡

ስለዚህ ከሕዝቡ ጋር በሠራነው ሥራ ሰላማዊ የሆኑትንና የተደናገሩትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየመጡ እጃቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ፣ በጣም የተዋጉትን ጥቂቶቹን ደግሞ የመደምሰስ ሥራ ተከናውኗል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ እገዛ አድርጓል፡፡ ስለዚህ አሁን ከሞላ ጎደል ዞናችን ከወትሮው እንዲያውም ከ2008 ዓ.ም. በፊት ከነበረው በተሻለ ሊባል ይችላል፣ ለረዥም ጊዜ ሲገድሉ የነበሩ ሰዎች ሳይቀሩ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ለመንግሥት እጃቸውን እንዲሰጡ፣ ከባለ ደሞቻቸው ጋር እንዲታረቁ፣ ታርቀውም እንዲኖሩ፣ ሌሎቹ በሕግ የሚጠየቁት ደግሞ በሕግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ነው የተሞከረው፡፡ በርከት ያለ ኃይል ነው ለማሰባሰብ የተሞከረው፡፡ አሁን ዞናችን አስተማማኝ ነው፡፡ እንዳያችሁት ይህ ድምፅ አሰጣጥ አይሳካም ይደናቀፋል ተብሎ ነበር፡፡ የተከሰተ ችግር ግን የለም፡፡ አሁንም ጥቂቶች አሉ፡፡ አልፈው አልፈው ከፀረ ሰላም ኃይል ባንዳው፣ ከግንቦት ሰባት ምናምን ከተባሉት ተላላኪዎች ጥቂቶች አሉ፡፡ በቁጥር የምናውቃቸው፡፡ በሽፍትነትም ደረጃ በጣም ብዙ ሰው ያጠፉ እጃቸውን ለመስጠት ያልፈለጉ ኃይሎች አሁን እየተሹለከለኩ አሉ፡፡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነዚህን ዘመቻችንን አጠናክረን የመያዝ ሥራ እናጠናክራለን፡፡ ከሞላ ጎደል ግን አሁን ከወትሮው በተሻለ የአካባቢውን ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነት የሚያውክ ሁኔታ የለም ብለን ነው የምናረጋግጠው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ዕርምጃ ሲወሰድ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ላይም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ይባላል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ላይ ምን ያህል ጉዳት ደርሷል?

አቶ አየልኝ፡- ጥሩ፡፡ በፀጥታ ኃይሉ ላይ የደረሰው ጉዳት ይህን ያህል ነው አይባልም እንጂ ምንም ጉዳት አልደረሰም ሊባል አይችልም፡፡ ጠላትን ነው እየተከታተልን ያለነው፡፡ አካባቢው በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የት እንደሚደበቅ፣ የት ላይ እንደሚቆይህ አታውቀውም፡፡ በዚህ ሁኔታ ምንም የተጎዳ የወገን ኃይል የለም ቢባል የሚታመን ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ኅብረተሰቡ አግዞ፣ ሚሊሻችንም ሆነ አመራራችን ብዙ ቁጥር ያለው ስለሆነ፣ መግቢያ መውጫው ስለሚታወቅ፣ በአጠቃላይ የመረጃ ሥራችንና ሠራዊቱ ከሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ጥሩ ስለነበር ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ እንደመጀመርያ ቢሆን ኖሮ ብዙ ርቀት አይኬድም ነበር፡፡ ከሕዝቡ ጋር በደንብ በመሠራቱና በመግባባቱ ምክንያት ሕዝቡ አሁን መረጃ እየሆነው ነው፡፡ እንዲያውም ያሉበትን እየጠቆመ ጉዳት እንዳያገኛቸው ለማድረግ ሞክሯል፡፡ በጣም ጥቂት የተጎዱ ሰዎችን በፀፀት ነው የሚገልጸው፡፡ በማያውቁት ቦታ አምጥታችሁ አስመታችኋቸው የሚል ኅብረተሰብ ነው ያለው፡፡ ያኔ ሁሉም በሻከረበት ወቅት ተልከው ትንሽ ጉዳት ሲደርስ በማያውቁት ቦታ አምጥታችሁ አስጎዳችኋቸው፣ ይህን አካባቢ እኛ ነን የምናውቀው እኛ ነን የምንመራቸው እንጂ ዝም ብላችሁ ሰድዳችሁ የሚል ስሜት ነው ወዲያውኑ የተፈጠረው፡፡ እኛ ከዚያ በኋላ ከመጀመርያዎቹ አካባቢዎች በዚህ በንቃሽ አካባቢ ሲወርዱ ካጋጠመው ችግር በቀር፣ ከዚያ በኋላ ያለው መከላከያውም አካባቢውን እያወቀና የአካባቢውን ሰው እያቀፈ፣ የፖለቲካ ሥራውም እየተጠናከረ በመምጣቱ ምክንያት እዚህ ግባ የሚል ጉዳት አልደረሰም፡፡ በፍፁም አልደረሰም ለማለት ባይቻልም፡፡ ሁለተኛ ከሱዳን ጋር ያለው ነገር ነው፡፡ ይህ በድንበር አካባቢ የሚያጋጥም ችግር ነው ሁልጊዜ፡፡ በጣም ብዙ ሕገወጥ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ፀረ ሰላም ኃይል ነው የማትለውና ሌላ የፖለቲካ ዓላማ የሌለው ግን ገንዘብ ለማግኘት የሚፈልግ እዚህ ሴቶችን ያጓጉዛል፣ ወጣቶችን የሚያሸጋግር ብዙ ነው፡፡ ሁለተኛ ድንበር ስለሆነ ከብቶች ይነዳሉ፡፡ ይህ የኮንትሮባንድ የከብት ሽያጭ የውጭ ንግዳችንም እየጎዳው ነው፡፡ ሕጋዊ ሰዎች ናቸው ይህን የሚያደርጉት፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ግን ከኅብረተሰቡ ጋር እየኖሩ፣ ከራሳቸው ከብት ጋር ጨምረው ሌላ ከብት መርተው ያሸጋግራሉ፡፡

በሱዳን በኩል ደግሞ ፈላቴዎች የሚባሉ ናይጄሪያ ወይም አልጄሪያ የሚባል ዘር ያላቸው አሉ፡፡ ከብት ነድተው ነው የሚሰደዱት፡፡ ወደዚህ ወደ አልጣሽ የሚባል ከብቶቻቸውን ይዘው የሚመጡ አሉ፡፡ መሣሪያ አላቸው፡፡ ብዙ ጊዜ ከብት ይዘው ይሄዳሉ፡፡ የኢትዮጵያን ከብት ይወስዳሉ፡፡ የእኛው ደግሞ ሄዶ ከብት ይዞባቸው ይመጣል፡፡ አንዳንዴ ይገድላቸዋል፡፡ እነሱም ይበቀላሉ፡፡ ኃይለኛ የግድያ መመላለስ አለ፡፡ ፈላቴዎች ከሚባሉት ጋር ሰሜን ጎንደር ረዥም ጊዜ የቆየ ችግር ነው ያለው፡፡ በኃይለ ሥላሴ ጊዜ አንድ መጽሐፍ ሳነብ 25 ሳንቲም እያስከፈሉ ነበር ወደዚህ የሚገቡት፡፡ 25 ሳንቲም ለአንድ ቀንድ ከብት ይከፈል ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው እነዚህ ወደዚህ አካባቢ የሚመጡት፡፡ አሁን ሰው እየበዛ ይከላከላቸዋል፡፡ ሲከላከላቸው መጋጠም አለ፡፡ የእኛው ሰው ከብት ይወስድባቸዋል፡፡ እነሱ ደግሞ እንደገና ይወስዳሉ፡፡ ይህ አለ፡፡ ከዚያ ውጭ መዓት ዓይነት ኮንትሮባንድ አለ፡፡ ድንበሩ ሰፊ ስለሆነ በርካታ ዓይነት ኮንትሮባንድ ነው የሚካሄደው፡፡ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል፡፡ እንዲያውም ሱዳንና ኢትዮጵያ መልካም ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ እነሱ ጋ ያለው ችግር ምንድነው? አብረንም ስንገናኝ የምንገመግመው ብዙ ጊዜ የእነሱን ሌቦች አሳደው አይይዙም፡፡ አይቀጧቸውም፡፡ እኛ ካገኘን ከእነሱ ይዘው የሚመጡትን የእኛን ሌቦች ፍርድ ቤት እናቀርባቸዋለን፡፡ በርካታ የሱዳን ሰዎችም እዚህ እስር ቤት አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ማለት ነው፡፡

አብሮ የሚኖረው ሕዝብ ውስጥ ሌባ አለ፡፡ እዚያ ገንዘብ የሚፈልግ ሥራ ፈት አለ፡፡ በስርቆት መክበር የሚፈልግ፡፡ መሣሪያ ያዘዋውራሉ፡፡ ብዙ ጥይትና ሽጉጥ ይገኛል፡፡ አንዳንዱ የፖለቲካ ዓላማ ኖሮት አይደለም ለመነገድ ነው፡፡ ገንዘብ ለማግኘት፡፡ ሽጉጡም፣ ጥይቱም የሚመጣው የእኛ አገር ሰዎች ጥይትና ሽጉጥ እንደሚፈልጉ ስለሚያውቁ ለመሸጥ ነው ይዘው የሚመጡት፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር ሁልጊዜም አለ፡፡ ነገር ግን አሁን ቅድም ባልኩት አግባብ ችግሩን ለመፍታት እየተሞከረ ነው፡፡ በሱዳን በኩል አልፈው የሚገቡ ካልሆነ በስተቀር ዋነኛ የተቃዋሚ መሸሸጊያ አይደለም፡፡ አሳልፎ ይሰጣል፡፡ አብረንም እንሠራለን እንደ ወንድማማች፡፡ በጣም ጥሩ ግንኙነት ነው ያለን፡፡ ግን እዚያ ውስጥ የእነሱ ሀብታም ሌባ እኛ ውስጥም አለ፡፡ እነዚህ ሁለቱ የሚፈጥሩት ሕገወጥ ሥራ ግን አለ፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዞን ውስጥ ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር እንዳለ ይነገራል፡፡ በሕጋዊ መንገድም መሣሪያ የታጠቁ እንዳሉ እንዲሁ ይገለጻል፡፡ መንግሥት ደግሞ በዚህ ዞን በተለየ ሁኔታ ትጥቅ ለማስፈታት እየሠራ ነው ይባላል፡፡ ይህ ጉዳይ እውነት ነው?

አቶ አየልኝ፡- ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ቅድም በገለጽኩልህ መንገድ አለ፡፡ ትጥቅ የማስፈታት ሥራ ግን የለም፡፡ ሕጋዊ ፈቃድ የሰጠናቸው አሉ፡፡ ኅብረተሰቡ ዋስትናው ተረጋግጦ መሣሪያውን ይዞ ነው የሚኖረው፡፡

ሪፖርተር፡- በጎንደር ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ የነበረው ግጭት አርሶ አደሩ መሣሪያ ስለታጠቀ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህንንስ እንዴት ያዩታል?

አቶ አየልኝ፡- እንግዲህ ይህንን የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ የእኔ ሐሳብ ግን እሱ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ መሣሪያ ስለታጠቀ አይደለም፡፡ ቅድም እንዳልኩት መንግሥት የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ አካባቢው አስቸጋሪ ስለሆነ ጠላት እየመጣ ኅብረተሰቡን የሚያሰቃይ አለ፡፡ ፀረ ሰላም ኃይል በጣም ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ መሣሪያ የሚይዘው ወዶ አይደለም፡፡ ራሱን ለመከላከል ነው፡፡ ብዙ ሽፍታ ነው የነበረው፡፡ ሽፍታው መሣሪያ የሌለው ቤተሰብ ካለ ገንዘብ እንዲሰጥ ያስገድዳል፡፡ ቤተሰቡ ራሱን መከላከል የሚችልበት አቅም የለም፡፡ መንግሥት ደግሞ ይህንን ሁሉ ማስከበር እንዳይችል ቅድም እንዳልኩት መሠረተ ልማት የለም፡፡ ብዙ አካባቢ መንገድ የለም፡፡ በሁሉም ቦታ ችግሩን መፍታት የቻልንበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የመሣሪያ ፍላጎት የቆየ ባህል ስላለ አብዛኛው አርሶ አደር መሣሪያ አለው፡፡ መሣሪያው ግን ሕጋዊ ፈቃድ አውጥቶ የተሰጠው ነው፡፡ ስለዚህ ሕጋዊ ሆኖ እንዲተዳደር፣ በአግባቡ እንዲያዝና ሥርዓት እንዲኖር፣ መሣሪያው ራሱን ለመጠበቅና ለመከላከል እንዲጠቀምበት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ይህን ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ ላለፈው ዓመት ቀውስ አርሶ አደሩ መሣሪያ ስለያዘ ነው የሚለውን ግን እኛ አልገመገምንም፡፡ ክልሉም ሆነ አገሪቱ አልገመገመችም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግምገማ እንደ ድርጅትም እንደ መንግሥትም የለም፡፡ አንድ ተጨማሪ ነገር ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ መፍታት የሚገባንን የወሰንና የመሳሰሉት ችግሮች ባለመፍታታችን እንጂ የሰሜን ጎንደር ሰው መሣሪያ ስለታጠቀ አይደለም አመፅ ተቀስቅሶ የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- በጠገዴና በፀገዴ መካከል የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ የሁለቱን ክልሎች አመራሮች የሚመለከት ጉዳይ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ጠገዴ ወረዳ በእናንተ ዞን ውስጥ ያለና በእናንተ የሚተዳደር በመሆኑ፣ በቅርቡ በተደረሰው ስምምነት የጠገዴ ወረዳ ሕዝብ ረክቷል ብላችሁ ታስባላችሁ? በእነዚህ አካባቢዎች በነበረው የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የተለያዩ ስሜቶች ሲንፀባረቁ ነበር፡፡ አሁን እዚህ አካባቢ ያለው ሁኔታ ምንድነው የሚመስለው?

አቶ አየልኝ፡- እንግዲህ ኅብረተሰቡ ምን ያህል ረክቷል የሚለው ትንሽ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ መገምገምና ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ ግን ካገኘነው የኅብረተሰብ ክፍልና ከነበረው ውይይት አያይዤ መናገር እችላለሁ፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ሁለት ነው የነበረው፡፡ የመጀመርያው ጥያቄ መንግሥት ይህ ነው ድንበራችሁ ብሎ ወስኖ ይስጠን፡፡ አታጋጩን የሚል ነበር፡፡ ይህ ድንበራችሁ ነው ብላችሁ ስጡን የሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ነገር እውነታው ይታወቅ የሚል ነበር፡፡ እውነታው ምንድነው በ2004 ዓ.ም. ሲከለከል ጠገዴና ፀገዴ ሲከፈሉ የት ላይ ነው መነሻው የነበረው? የተከፈለበት ቦታው የት ላይ ነው የነበረው? የሚለው ይወሰን የሚል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እነሱ ወሰዱት፣ እኛም ወሰድነው የአንድ አገር ዜጎች ነን፡፡ ከማንኛውም ነገር በላይ ደግሞ ወንድማማች ነን የሚል ነበር፡፡ የጠገዴና የፀገዴን ሕዝብ ልትለያየው አትችልም፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ሲፈጠርና ሌላው ጉዳዩን ጫፍ ሲያደርሰው እነሱ ተኮራርፈው አያውቁም፡፡ ከመነጋገር ያለፈ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ነው የነበረው፡፡ አሁን ተወሰነ፡፡ ሁለተኛ አሁን የተለወጠ ከባቢ አለ፡፡ ሕዝብ ሰፍሮበታል፡፡ ያኔ የነበረውን ሁኔታ እናስከብር ብንል አሁን የሠፈረ አለ ያላችሁት እውነት ነው፡፡ አሁን የተቀየረ ነገር አለ ምን እናድርግ ብለን ነው የቀረብነው፡፡ የሚፈልጉት ይህንን ነው የነበረው፡፡ እውነቱ ይታወቅና እንዴት አድርገን እንጠቀምበት፡፡ ችግር የለውም፡፡ ለቀጣዩ እንዳያጣላን ድንበራችን ይወሰን የሚል ነበር፡፡ አሁን ቅር ያላቸው ሰጥቶ መቀበል አትበሉ፣ ነገር ግን አሁን የተለወጠ ነገር አለ፡፡ ስለዚህ የትግራይ ትግርኛ ተናጋሪዎቹ የያዟቸው መንደሮች፣ ወይም የሠፈሩባቸው መንደሮችና እነሱ የሚያርሷቸው የእርሻ መሬቶችን እንደያዙ ወደ ትግራይ ይካለሉ፡፡ ቀሪው ክፍት የሆነውና ለኢንቨስትመንት የተሰጠው መሬት ግን ወደ አማራ ክልል ይከለል መባሉ ምንም አያስከፋም፡፡ ቢመጡም ይዘውት ነው የሚመጡት፣ ቢሄዱም ይዘውት ነው የሄዱት፡፡ ሁለተኛው ወንድሞቻችን ናቸው፣ አስለቅቀን ልንሰዳቸው አንችልም ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ ወይ እንዳሉ ነው የምናመጣቸው፣ እንዳሉ ለማምጣት ደግሞ ቋንቋቸው ከማንነት ጥያቄ ጋር ሌላ ነገር ስለሚኖረው ችግር የለውም በሚል ነው የተሰየሙት፡፡

      ለወደፊት ከሥጋት ነፃ ሆነዋል፡፡ በነገራችን ላይ እዚያ አካባቢ የምታገኘው ሐሳብና ከዚያ ውጪ የምታገኘው ይለያያል፡፡ እነሱ እዚያ ያሉትን ሰዎች እንደ ወንድሞቻቸው፣ እንደ ቤተሰብ ነው የሚታዩት፡፡ ግን ደግሞ በቤተሰብም ውስጥ የሚፈጠር ግጭት ሊኖር እንደሚችልና ያንን ግጭት የሚፈታ ውሳኔ ያስፈልጋል ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ በሌላው አካባቢ ግን የተሸናፊና የአሸናፊ፣ የመስፋፋትና የምናምን አድርጎ የሚያየው አለ፡፡ እና እዚያ አካባቢ ያለው ዕይታና ውጪ ያለው ዕይታ ይለያያል ለማለት ነው፡፡ ይህ ውሳኔ በነገራችን ለክልላችንም ብቻ ሳይሆን ለአገራችን፣ ከዚያም ደግሞ በሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት ትልቅ ችግር የፈታ ነው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ታግለው የመጡና ይህን ሥርዓት በመመሥረት ደረጃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው፡፡ ወደፊትም አስተዋጽኦዋቸው በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሆኖ እንዲቀጥል ሊያደርግ የሚችል ጥሩ ውሳኔ ነው ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመግባባት መፈታቱ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ቢያንስ በፌዴሬሽን ምክር ቤት መፍታት ይቻል ነበር፡፡ ይህ ሌላ ቁርሾ አለው፡፡ ሁለቱ ድርጅቶች ታግለው እንደመጡና ብዙ ችግሮችን በጋራ እንደፈቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጨረሳቸው በጣም ጥሩ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ውጤትና ዕፎይታ ነው ብዬ እወስዳለሁ፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...