– የዶላር ዕጥረት የመገጣጠም አቅሙን እንደገደበው ገልጿል
– አዳዲስ ሞዴሎቹን ለኢትዮጵያ ገበያ ለማስተዋወቅ ሐሳብ አለው
የሊፋን ኢንዱስትሪ ግሩፕ አካል የሆነው ሊፋን ሞተርስ ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሻሻል እንዲረዳው ዋና መሥሪያ ቤት ለመገንባት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
ኩባንያው ለሚገነባው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ፣ 6,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚያስፈልገው አስታውቆ የቦታ ሊዝ ግዥ ለመፈጸም ጫፍ መድረሱንም የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ የሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት፣ ከቢሮ አገልግሎት በተጓዳኝ የሽያጭ ማሳያና የዕድሳት ማዕከልነት ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በሊፋን ኢንዱስትሪ ግሩፕ የድኅረ ሽያጭ አገልግሎት ዳይሬክተር አንድሪው ኩ እንዲሁም የሊፋን ግሩፕ አካል በሆነው የወጪና ገቢ ንግድ ኩባንያ ውስጥ ኃላፊ የሆኑትና ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት የሠሩት ፍራንክ ላው እንዳብራሩት ከሆነ፣ አዲሱ ማዕከል እስካሁን ሲታዩ የቆዩ ችግሮችን እንደሚቀርፍ ተስፋ ተደርጎበታል፡፡
ከኢትዮጵያና ከሌሎችም አገሮች የተውጣጡ የሊፋን ደንበኞች በቻይና፣ ደቡብ ምዕራብ ክፍል፣ ቾንግቺንክ ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የሊፋን ግሩፕ ዋና መሥሪያ ቤትን ጎብኝተዋል፡፡ ከሊፋን ሞተርስ 800 ያህል መኪኖችን በመግዛት ለታክሲ ሥራ ያዋለው የዘ ሉሲ ታክሲ ባለንብረቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አንተነህ ትሪሎ ሊፋን ፋብሪካዎችን በጎበኙበት ወቅት እንደጠቀሱት፣ የድኅረ ሽያጭ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ወቅታዊነት ብሎም የባለሙያ ዕጥረት በመታየቱ ከኩባንያው የሚፈልጉትን አገልግሎት በተገቢው መንገድ የማኅበሩ አባላት ማግኘት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የመለዋወጫ ዕጥረት በማጋጠሙ ከሊፋን ተገቢውን አቅርቦት ሊያገኙ እንዳልቻሉ ለኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡ አንድሪውና ፍራንክ እንደገለጹት ከሆነ፣ ከኢትዮጵያ የሚፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ባለመቻሉ በርካታ ኮንቴይነሮች ውስጥ የታጨቁ መለዋወጫዎችን ማስገባት አልተቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በድኅረ ሽያጭ ወቅት የጥገና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታዩትን ችግሮች ለመቅረፍም ከዋናው መሥሪያ ቤት የሚላክ ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሁኔታውን እንደሚያጠና፣ አስፈላጊው ሥልጠና ለሙያተኞች እንደሚሰጥና ሌሎች ለውጦች እንደሚደረጉ አስታውቀዋል፡፡
በቾንግቺንክ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ዳይሬክተር አቶ ከበደ አበራ በተገኙበት በተደረገው ውይይትም፣ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነበት የሊፋን ሞተርስ ኃላፊዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
ፍራንክ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዱከም ከተማ ኢስት ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ የሚገኘው የሊፋን ሞተርስ መገጣጠሚያ ፋብሪካ በዓመት ከ2,000 በላይ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ቢኖረውም፣ በአሁኑ ወቅት ግን በዓመት 500 መኪኖችን ለመገጣጠም ተገዷል፡፡ ይኼ በመሆኑም ለ500 ሰዎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችልበትን አቅም ወደ 50 ዝቅ በማድረግ እንደገደበው ገልጸዋል፡፡ ይሁንና የውጭ ምንዛሪ ዕጥረቱን የሚፈታበት ሌሎች አማራጭ የመፍትሔ መንገዶችን በማለፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከሊፋን ሞተርስ ጋር አብሮ እየሠራ የሚገኘው ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ ኃላፊዎችም በዓመታዊው የሊፋን ሞተርስ ጉባዔ ወቅት የታደሙ ሲሆን፣ ከኩባንያው ጋር ወደፊት አብረው መሥራት በሚችሉባቸው መስኮች ላይ በመወያየት፣ ባንኩ መስጠት ስለሚችላቸው የፋይናንስ አገልግሎቶች ተነጋግረዋል፡፡ ብርሃን ባንክ ለ800፣ ሊፋን 530 የተባሉትን ሞዴሎች ዘ ሉሲ ማኅበር እንዲገዛ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ አበድሯል፡፡ ወደፊትም ሌሎች እንዲህ ያሉ የታክሲ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለውም የባንኩ ኃፊዎች አስታውቀዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ450 ሺሕ በላይ መኪኖችን በማምረት ከቻይና ውጭ በመሸጥ ትልቅ እንቅስቃሴ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 2025 የቻይና ዓመታዊ የመኪና ምርት 50 ሚሊዮን እንደሚደርስ ሲጠበቅ፣ ከዚህ ውስጥ 10 ሚሊዮኑ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚውል ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ የሊፋን ሞተርስ ድርሻ ሦስት በመቶ እንደሚሸፍን ሲታሰብ፣ ዓመታዊ ምርቱም 300 ሺሕ እንደሚደርስ የሊፋን ኢንዱስትሪ ግሩፕ ፕሬዚዳንት ሙ ታንግ በአራተኛው የሊፋን ዓለም አቀፍ የሽያጭ ወኪሎች ጉባዔ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ ከስድስት ዓመታት በላይ ከሦስት ግዙፍ የቻይና መኪና አምራቾችና ላኪዎች አንዱ በመሆን የሚመደበው ሊፋን ሞተርስ፣ ከፍተኛ ሽያጭ በማከናወን በዓለም የሚጠቅሳቸው አገሮች በተለይ ሩስያና ብራዚል እንደሆኑ ገልጿል፡፡
ከዚህ ባሻገር በቻይና እየተዘወተረ የመጣውን በኤሌክትሪክ የሚሠሩ መኪኖችን የመጠቀም ዝንባሌ በኢትዮጵያም የማስለመድ ፍላጎት እንዳለው የኩባንያው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ ፓንዳ አውቶ የተሰኘ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ መኪና ይፋ ካደረገ የሰነባበተው ሊፋን ሞተርስ፣ ሌሎችም እንደ ሊፋን ማርቬል 7 (ኤም7) ሰባት ሰዎችን መጫን የሚችሉ የቤተሰብ መኪኖችን ጨምሮ ዘንድሮ ከዓለም የተውጣጡ የሽያጭ ወኪሎቹ በተገኙበት ይፋ የተደረገውን X7 ጨምሮ X80፣ X52፣ MyWay እና ሌሎችም አዳዲስ ሞዴሎችን በቅርቡ ለገበያ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡ ሊፋን ሞተርስ አዳዲሶቹን ሞዴሎች ለኢትዮጵያ ገበያ ለማቅረብ እንደሚፈልግም ገልጿል፡፡
ቆንስላ ጄነራል ከበደ አበራም ይኼንኑ በመንተራስ መንግሥት በቅርቡ ያወጣውን ለመንግሥት ኃላፊዎች የውጭ መኪኖች ግዥን የሚከለክለውን መመርያ መሠረት በማድረግ፣ ለመንግሥት ሥራ የሚመጥኑ ተሽከርካሪዎቹን በአገር ውስጥ ገጣጥሞ በማቅረብ ዕድሉን እንዲጠቀምበት አስታውሰዋል፡፡ እንደ ሊፋን ኃላፊዎች ገለጻ በተለይ X80 የተባለው ሞዴል እንደ V8 ያሉትን የቶዮታ ሥሪት መኪኖች ለመተካት የሚችልበት አቅም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ይህ መኪና 2.4 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያለው ሲሆን፣ እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ለገበያ ሊቀርብ እንደሚችል ይገመታል፡፡ አዲሱ X7 መኪና፣ በደቡብ ምዕራብ ሊጂያንግ ከተማ የመስክ ሙከራ የተደረገበት ሲሆን፣ 2.0 ሲሲ የፈረስ ጉልበት ያለው ከመሆኑም ባሻገር፣ በማኑዋልና አውቶማቲክ ትራንስሚሽን ለገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ ከአራት ወራት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ለሙከራ እንደሚመጣም ይጠበቃል፡፡
በቱሪስት መዳረሻዋ ከተማ በሊጂያንግ ከተማ በተካሔደው አራተኛው የምርትና የሽያጭ ወኪሎች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ወቅት፣ በመልካም አፈጻጸማቸውና በግዥ መጠናቸው ከሊፋን ሞተርስ ሽልማት ከተበረከተላቸው መካከል ዘ ሉሲ ሜትር ታክሲ ማኅበር አንዱ ነበር፡፡ ‹‹Outstanding Contribution Award›› በተሰኘው የልማት ዘርፍ ለዘ ሉሲ ሜትር ታክሲ የተበረከተውን ሽልማት አቶ አንተነህ ተረክበዋል፡፡
ለሳምንት በዘለቀው ዓመታዊ የሊፋን ክንውን ወቅት፣ ከየአገሮቹ የተውጣጡ የኩባንያው ወኪሎችና ሸሪኮች፣ በሊጂያንግ ከተማ የተሰናዱ ልዩ ልዩ የመዝናኛ መስተንግዶችን ጨምሮ፣ በቼንግዱንና በዋና መሥሪያ ቤቱ መገኛ በቾንግቺንክ ከተማ የፋብሪካ ጉብኝትን ጨምሮ ሌሎችም ተሳትፎዎችን በማድረግ ወደየመጡበት ተመልሰዋል፡፡
ከ30 ዓመታት በፊት በሞተር ብስክሌቶች መለዋወጫ አምራችነት ሥራውን የጀመረው ሊፋን ሞተርስ፣ በአሁኑ ወቅት በቻይና ቾንግቺንክ ከተማ ስድስት ትልልቅ ማምረቻዎችን ገንብቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሩስያ፣ በአዘርባጃን፣ በብራዚል፣ በአርጀንቲና፣ በኡራጓይ፣ በኢራቅና በሌሎችም አካባቢዎች ከ27 ያላነሱ የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎችን ለመትከል በቅቷል፡፡ ከ117 በላይ አገሮች ምርቶቹን የሚያዳርሰው ሊፋን በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው በ1999 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን፣ በወቅቱ የሆላንድ ካር ኩባንያ የመለዋወጫ አቅራቢ በመሆን አብሮ ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ሆኖም የሁለቱ ኩባንያዎች አብሮነት ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ባለመስማማት ሲደመደም፣ ሊፋን ሞተርስ ራሱን ችሎ በኢትዮጵያ የመገጣጠሚያ ማዕከል በመክፈት ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡