ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በተቃውሞ መፈክሮች ታጅቦ በሰላም ተጠናቀቀ፡፡
በዓሉን ለማክበር ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምረው በሆራ ሐይቅ ዙሪያ የተሰበሰቡት የበዓሉ ታዳሚዎች የተለያዩ ባንዲራዎችን ሲሰቅሉና መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮች ሲያሰሙ ነበር፡፡ ታዳሚዎቹ ከተቃውሞ መፈክሮቹ በተጨማሪ አንድነትን የሚሰብኩና የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን የሚያሞግሱ መፈክሮችን በሰፊው ሲያሰሙ ነበር፡፡
በዓሉን አከባበር የሚመሩት አባ ገዳዎች ወደሐይቁ በፖሊስ ታጅበው ገብተው ሥነ-ስርዓቱን ያስፈጸሙ ሲሆን፣ በዓሉም ያለምንም አመጽና ችግር ተጠናቅቋል፡፡
የበዓሉን በሰላም መጠናቀቅ በማስመልከትም የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በእውነተኛ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በዚሁ በዓል ላይ በተከሰተ ሁከትና ረብሻ ከ50 በላይ ሰዎች ተረጋግጠውና ገደል ውስጥ ገብተው መሞታቸው ይታወሳል፡፡