Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትክለብ አልባው አፋር በ727 ሚሊዮን ብር የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት ሊሆን ነው

ክለብ አልባው አፋር በ727 ሚሊዮን ብር የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት ሊሆን ነው

ቀን:

ለስፖርታዊ ዘርፎች መዳከም ምክንያት ሆኖ ይቀርብ የነበረው የማዘውተሪያ ሥፍራዎችና ደረጃቸውን የጠበቁ ብሔራዊ ስታዲየሞች በሚፈለገው መጠን አለመኖራቸው ነበር፡፡ ችግሩ አሁንም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ተብሎ ባይታመንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታዎች የነገውን የተስፋ ጭላንጭል የሚያመላክቱ መሆን ጀምረዋል፡፡

ሁለቱን የከተማ አስተዳድሮች ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የዘመናዊ ስታዲየም ግንባታዎች እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር የዚህ ተመሳሳይ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች የተቋማቱ ወቅታዊ አጀንዳ ሆነው የነበሩበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ የቅድመ ሰው መገኛ ሆኖ በታሪክ መዝገብ የሰፈረው የአፋር ክልልም እንደ አቻዎቹ ሁሉ የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤትነቱን ዕውን ለማድረግ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ ይሁንና ክልሉ እያስገነባው ለሚገኘው ዘመናዊ ስታዲየም የሚመጥን ቀርቶ የተቀሩት ክልሎች በውክልና ጭምር በሚወዳደሩበት ብሔራዊ ሊግ ሊወክል የቻለ ክለብ የሌለው መሆኑ በአሉታዊ ጎኑ እንዲታይ ማድረጉ አይቀርም፡፡ በክልሉ የስፖርቱ ኃላፊዎችም ይህንኑ እንደ ክፍተት ይቀበሉታል፡፡

ክልሉ በመጪው ዓመት የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ያስተናግዳል፡፡ ለዚሁ ክብረ በዓል ተብሎ ግንባታው ከስምንት ወር በፊት የተጀመረው ዘመናዊ ስታዲየምም ለዝግጅቱ ከሚጠበቀው ጊዜ ቀድሞ በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ የግንባታው ሒደት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የሰመራ ስታዲየም ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ፀሐዬ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የሰመራ ስታዲየሞች ፕሮጀክት ይጠናቀቃል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው በሁለት የግንባታ ምዕራፍ በሦስት ዓመት ውስጥ ነው፡፡ አንዱና የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ በመጪው ዓመት 45 በመቶ ማድረስ ሲሆን፣ በቀሪው ጊዜ ደግሞ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቃበት እንደሚሆን የአማካሪ ድርጅቱ ኤምኤች ኢንጂነሪንግ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ የማነ መልካሙ ያስረዳሉ፡፡

የሰመራ ስታዲየም ግንባታ ለብሔር ብሔረሰቦች ዝግጅት ከተቀመጠለት ጊዜ ገደብ አስቀድሞ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ እንደ አማካሪ ድርጅቱ መሐንዲስ ከሆነ፣ ለግንባታው የተያዘለትን በጀት ያለ አንዳች ቢሮክራሲና ውጣ ውረድ በመጠቀም ከመደበኛው የሥራ ሰዓት ተጨማሪ በማድረግ በተቀናጀ አግባብ እንዲቀጥል በመደረጉ እንደሆነ አማካሪ ድርጅቱና ተቋራጩ ያስረዳሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ከ727 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለትም አቶ የማነ ተናግረዋል፡፡   

በዋናነት ለብሔር ብሔረሰቦች ዓመታዊ ክብረ በዓል እንዲደርስ ታሳቢ ተደርጎ ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት እንደቀጠለ የሚገኘው የሰመራ ስታዲየም፣ 17 ሺሕ ሔክታር ይሸፍናል፡፡ ይኽም ከስታዲየሙ በተጨማሪ ለሌሎች ስፖርቶች ማለትም ለዋና፣ ለእጅ ኳስ፣ ለቅርጫት ኳስ፣ ለመረብ ኳስ፣ ለአትሌቲክስና ለመሳሰሉት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን አካቶ እንደሚይዝ የክልሉ የወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር አቶ መዓር አሊሴሮ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ የዘመናዊ ስታዲየም ባለቤት ለመሆን እየተቃረበ ባለበት በዚህ ወቅት ግን ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ሁሉም ክልሎች በውክልና ጭምር እየተሳተፉበት የሚገኘው ብሔራዊ ሊግ አፋርን የሚወክል አንድ ክለብ እንኳ የለውም፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰመራ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን የሚገልጹት በቁጭት ነው፡፡ ምክንያቱም የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች፣ የክትትልና የማስፈጸም አቅም ውስንነት እንጂ የክልሉ ወጣቶች እግር ኳሱን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርቶች የግንዛቤም ሆነ የክህሎት ችግር እንደሌለባቸው ነው የሚናገሩት፡፡ በክልሉ እየተጠናቀቀ የሚገኘው ስታዲየም ለክልሉ ስፖርት ተነሳሽነት የሚኖረው ፋይዳ ቀላል አለመሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከግንባታው ጎን ለጎን ግን እግር ኳሱን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ ያምናሉ፡፡

ኮሚሽነሩ አቶ መዓር አሊሴሮ በበኩላቸው የቅሬታውን ተገቢነት አምነው በቀጣይ ክልሉን የሚወክል አንድ ወይም ሁለት ጠንካራ የእግር ኳስ ቡድን ማቋቋም የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ የክልሉ ወጣቶች በተለይም በአሁኑ ወቅት በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ስፖርቶች አቅሙና ብቃቱ ያላቸው መሆኑ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህንኑ ግምት ውስጥ በማስገባት በፌዴራል ደረጃ ድጋፍና ክትትል የሚደረግላቸው በአጠቃላይ 69 ፕሮጀክቶች በሁለቱም ፆታ ዕድሜያቸው ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ወጣቶችን ዘመናዊና ሳይንሳዊ ሥልጠና በመስጠት ላይ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በሚገኙ 32 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ መስተዳድሮችም የስፖርት ምክር ቤቶች ተቋቁመው ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆኑ ጭምር አቶ መዓር ይናገራሉ፡፡

የውክልናን ጉዳይ አስመልክቶ ኮሚሽነሩ፣ ‹‹እንደ ስፖርት አመራርነቴ ሁሉንም  ክልሎችንና የከተማ መስተዳደሮችን በሚያሳትፈው ብሔራዊ ሊግ አፋርን የሚወክል ቡድን አለመኖሩ ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ በዚያ ላይ በክልሉ ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም እያስገነባን በመሆኑ ይህንን መሠረተ ልማት የሚመጥን አንድ ወይም ሁለት ጠንካራ ቡድኖች ሊኖረን የግድ ይላል፤››  ብለዋል፡፡

በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽንና በአማካሪ ድርጅቱ ኤምኤች ኢንጂነሪንግ አማካይነት በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኘው የሰመራ ዘመናዊ ስታዲየም፣ በወንበር 30 ሺሕ ተመልካቾችን ያስተናግዳል፡፡ የግንባታው ይዘት (ስትራክቸር) ለብሔር ብሔረሰቦች ዓመታዊ በዓል 45 በመቶ ድረስ እንዲጠናቀቅ የተያዘለት ዕቅድ በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ ደርሷል፡፡ ሆኖም የግንባታው ፍጥነት ሥጋት የሚያጭርባቸው ወገኖች አሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ አቶ የማነ መልካሙ፣ ከኮንክሪት ሙሌትና ዝግጅት ጀምሮ ደረጃውን ጠብቆ እየተከናወነ ለመሆኑ ማረጋገጫ ልኬቶች እንዳሉ፣ ግንባታው እየሄደ ያለውም ይህንኑ የምሕንድስና መስፈርትና ልኬት መነሻ አድርጎ መሆኑን ጭምር ተናግረዋል፡፡

ክልሉ በበኩሉ ስታዲየሙ ምንም እንኳ በዋናነት በሚመጣው ዓመት ለሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል እንዲደርስ ያለመ ዕቅድ ቢኖረውም፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ቅርስ ስለሆነ አስፈላጊውን ሀሉ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ ከሚሽነሩ አቶ መዓር ይናገራሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ በበኩላቸው፣  አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን በሌሎችም ክልሎች ተመሳሳይ የስታዲየም ግንባታዎችን ያከናወነ እንደመሆኑ መጠን በጥራት ደረጃ አንዳችም ሥጋት ሊኖር እንደማይገባ ነው ማረጋገጫ የሰጡት፡፡

ቡድን በሌለበት ዘመናዊ ስታዲየም ለምን?

የሰመራ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ በክልሉ የሚደረገውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ታሳቢ አድርጎ መጀመሩ በክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ዘንድ የመሠረተ ልማቱ መገንባት ከበዓል ማድመቂያ ያለፈ ፋይዳ እንዳለው ያምናሉ፡፡ ይህ ግን ለሰመራና ለሎጊያ ወጣቶች ብዙም የሚዋጥላቸው እንዳልሆነ ከአስተያታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣቶቹም ሆኑ ሌሎች የክልሉ ነዋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች መጀመሪያ ለክልሉ ስፖርት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ እስካሁን ባለው የአፋር ስፖርት በየዓመቱ ከሚደረገው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ተሳትፎ ያለፈ እንደ ሌሎች ክልሎች ከእግር ኳሱ ጭምር በሌሎችም ስፖርቶች ጠንካራ መሆን አልቻለም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡

ለዚህ ምክንያት የሚሉት ደግሞ፣ ክልሉ ለስፖርቱ ዘርፍ የሚሰጠው የትኩረት ማነስ ካልሆነ በክልሉ እግር ኳሱን ጨምሮ በአትሌቲክሱ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለአገሪቱ ከፍተኛ ፈተና እየሆነ ላለው ለአጭር ርቀት አፋር ውስጥ ለዚህ መፍትሔ የሚሆኑ ወጣቶች በብዛትም በጥራትም እንዳሉ በጥናት ጭምር የተረጋገጠ እውነታ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የሰመራም ሆነ የሎጊያ እንዲሁም የአሳይታ የሙቀት መጠን እስከ 42 ዲግሪ በሚደርስበት ጊዜ ሳይቀር እግር ኳስ የሚጫወቱ፣ የሚሮጡ፣ በረሃ የሚያቋርጡ፣ እጅ ኳስና ጠረጴዛ ቴኒስ የሚያዘወትሩ በርካታ የክህሎት ባለቤት የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉ፣ ሆኖም ይህ እውነት በሆነበት ስለውክልና ሲነገር መስማት የሚያሳፍር ነው ይላሉ፡፡ የሰው ኃይሉና ሀብቱ ሳይጠፋ ቡድን በሌለበት የዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ለምን ሲሉም የሚጠይቁት ለዚህ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

ኮሚሽነር መዓር በበኩላቸው፣ ‹‹የወጣቶቹ የቁጭት መነሻ ለክልሉ ስፖርት ትኩረት እንዲሰጥ ከመመኘት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አፋር ከቅድመ ሰው ዘር መገኛነቷ በተጨማሪ የተለያዩ በተለይም ለጭስ አልባው ኢንዱስትሪ የተፈጥሮ ስጦታዎች ባለቤት ነው፤›› ብለው፣ በእነዚህ የቱሪዝም ገፀ በረከቶች ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ስታዲየም ግንባታ ሲታከልበት ደግሞ ፋይዳው የበለጠ እንደሚሆን ነው የኮሚሽነሩ እምነት፡፡

ክልሉ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ስፖርቶች አንድ አይደለም፣ ከዚያ በላይ ጠንካራ ውክልና ሊኖረው እንደሚገባ ግን ያምናሉ፡፡ ለዚያ ደግሞ የክልሉ ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚሉት በላይ የክልሉ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ አክለውም የአፋር መዲና ሰመራ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ማለት ለየመን፣ ለጂቡቲ፣ ለሱማሊላንድ እንዲሁም በስፖርቶች ጠላትነት ስለሌለ ለኤርትራና ለሌሎችም አገሮች ማዕከላዊ ከተማ በመሆኗ የስታዲየሙ መገንባት ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ ጭምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...