መጋቢት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ ከላይ ለተመለከተው ርዕስ አንደ ጽሑፍ በርዕሰ አንቀጽነት አስነብቦናል፡፡ መጣጥፉ ለማስተላለፍ የሞከረው መልዕክቱ ለሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ አንደኛ መንግሥት ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠርና የመደበው በጀት (ፈንድ) ጥሩ ሆኖ ሳለ፣ ጥገኝነትን የሚያበረታታ ከሆነ ግን ዘላቂ መፍትሔ እንደማያስገኝ ይጠቁማል፡፡ ሁለተኛ፣ ወጣቶችን ለመርዳት የተዘጋጀው ፕሮግራም የሌሎች ዜጎችን ጥቅም ጉዳት ላይ መጣል እንደሌለበት ያሳስባል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ከተመሠረተ ጀምሮ ለመንግሥት የሚሰጠው ምክር አዳማጭ ቢያገኝ ኑሮ፣ መንግሥት አሁን የገባበት ችግር ውስጥ ላይገባ ይችል ነበር ከሚሉት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሪፖርተር ጋዜጣን ምክር የማይሰማው ለምንድነው? በእኔ እምነት መንግሥት የሪፖርተርን ብቻም ሳይሆን የሌሎች ወገኖችንም ምክር በሳይንሳዊ እውነት ላይ ተመሥርቶ ስለማይቀርብለት ወይም መንግሥት በዚህ መንገድ የሚቀርብለትን መንገድ ከመቀበል ይልቅ ስለማይቀበለው ይመስለኛል፡፡
ሌላው ችግር በርካታ ሳይንሳዊ እውነቶች ተደጋግሞ ስለሚነገሩ፣ የሚያስተላልፉት ሳይንሳዊ ሀቅ እየተዘነጋ እንደ ተራ ልማዳዊ አነጋገሮች ስለሚወሰዱ መንግሥት ከቁብ አይቆጥራቸውም፡፡ ለምሳሌ፣ ሪፖርተር በዚሁ ርዕሰ አንቀጽ ‹‹ሕመሙን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም››፤ ‹‹ችግሩን ማወቅ የመፍትሔ አካል ነው›› ‹‹በሽታው ሌላ መድኃኒቱ ሌላ›› ወዘተ. እያለ ምክር ይለግሰናል፡፡ ግን ማን ሰምቶት? በሕይወት ለመቆየት መተንፈስ ያስፈልጋል እንደማለት ያለ የተረጋገጠ ዕውነታ ቢሆንም፣ ደጋግሞ ስለሚባል ነው መሰል ሳይንሳዊ እውነትነቱ ይደበዝዛል፡፡
ከላይ የተባለውን አባባል ይበልጥ ለመገንዘብ ይረዳን ዘንድ ከሪፖርተር ጋዜጣ እንደሚከተለው ዘለግ አድርገን እንጥቀስ፡፡ ‹‹በአገሪቱ የሚታዩ ጥናት የጎደላቸው ድርጊቶች ግን በእንጭጩ ካልተቀጩ የሚያስከትሉን ጥፋት ለመገመት ያዳግታል፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ የይድረስ ይድረስ ውሳኔዎች ለጊዜው ፋታ ቢሰጡም ውለው አድረው ግን የማይድን ፅኑ ደዌ ይሆናሉ፡፡ ዕቅዶች ግብታዊና ጊዜያዊ ችግርን ማስተንፈሻ ሲደረጉ ከልማታቸው ይልቅ ጥፋታቸው ይከፋል፡፡ ለወጣቶች የሥራ ዕድሎች ሲፈጠሩ በጥናት ላይ መመርኮዝ ተገቢ ነው፡፡››
ከዚህ ጥቅስ በርካታ ጥያቄዎችን ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን፡፡ በአገሪቱ የሚታዩት ጥናት የጎደላቸው ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው? ምን ዓይነት ጥፋትስ ነው የሚያደርሱት? የማይድን ፅኑ ደዌ ምን ዓይነት በሽታ ነው? በምሳሌ ይበልጥ ቢብራራ የበለጠ ትርጉም በሰጠውና ባስተዋለው ይሆን እላለሁ፡፡ ግን መንግሥት ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር እየተዘጋጀ ያለው ያለጥናት ነው እንዴ?
እንግዲህ ሪፖርተር ባቀረበው ምክር አዘል ርዕሰ አንቀጽ ውስጥ የተለገሰውን ምክር አዳምጦ መንግሥት ተግባራዊ የማድረጉ ዕድል በእጅጉ የተመናመነ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ ይልቅ ለመንሥት አድማጭነት የሚያነሳሳ የበለጠ ዕድል ይኖር ነበር ብዬ የምገምተው ሪፖርተር በዋናው ጉዳይ ላይ አብዝቶ በማተኮር ምክሩን ቢለግስ ይበልጥ መንግሥትን እንዲሰማ ጫና ማሳደር ይቻለው ነበር፡፡ በመሆኑም በእኔ ግምት ከዚህ በታች ያሉት ሐሳቦች ትኩረት ሊደረግባቸው ይገባል እላለሁ፡፡
ልማዳዊ ግንዛቤ ሳይንስ አይደለም
የእኔ መነሻ ሐሳብ ልማዳዊ ግንዛቤ (ኮመን ሴንስ) ሳይንስ አይደለም የሚል ነው፡፡ የሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ ዋና ጉዳይ መንግሥት ፈንድ መሥርቶ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያዘጋጀው ዕቅድ ነው፡፡ ሪፖርተር ሐሳቡ ጥሩ ነው ብሎ የሚጀምረውን እኔ ግን በጥርጣሬ አየዋለሁ፡፡ ፈረንጆች ሲተርቱ፣ ‹‹የሲዖል መንገድ የተነጠፈው በበጎ ፈቃድ ነው፤›› ይላሉ፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ለወጣቶች ሥራ እፈጥራለሁ ሲል፣ ችሎታውና አቅሙ አለውን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ችሎታውና ፍላጎቱ ካለውስ ይኼን ለማድረግ ያለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ውስጥ ለምን ይህንን መፍጠር አልተቻለውም እላለሁ፡፡
ከዚህም በላይ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስፈልጉት ሁኔታዎች በኢኮኖሚክስ ሳይንስ የታወቁ ሆነው ሳሉ፣ እነሱ ባልተሟሉባቸው ዓውድ ውስጥ ዘላቂ የሥራ ዕድል እንዴት ይሆን መፍጠር የሚቻለው? በመጀመሪያ የሰው ልጅ ዛሬ ከደረሰበት ማኅበራዊ ቀውስ አኳያ ከካፒታሊዝም የተሻለ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንዳላመጣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እርግጥ በታዳጊ አገሮች ልማታዊ መንግሥታት አማካይነት የካፒታሊዝም ሥርዓት ተፋጥኖ ሊስፋፋ ይችላል፡፡ በለሙት አገሮች ውስጥም ታሪካዊ ኢፍትሐዊነቱ በዌልፌርዝም ሊስተካከል ይችላል፡፡ ይሁንና ለኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ለመሆን ታሪካዊ ፈተናውን አልፎና ነጥሮ የመጣው ካፒታሊዝም መሆኑ ግን የሚካድ አይደለም፡፡
በካፒታሊዝም ሥርዓት መሬት፣ የሰው ኃይልንና ካፒታልን አቀናጅተው የሥራ ዕድል የሚፈጥሩት በተፈጥሮ ችሎታ፣ በትምህርት ሥልጠናና በግላዊ ተነሳሽነት ሥራ የመፍጠር ችሎታ ያላቸው ግለሰቦች (ኢንተርፕረነርስ) ናቸው፡፡ እንግዲህ፣ ወደተነሳንበት ጉዳይ ስንመለስ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት በሃያ ስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ሥራ የመፍጠርም ሆነ የማስፈጠር ችሎታው ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል፡፡ አለበለዚያማ እንደ ጀማሪ መንግሥት በሥራ መፍጠር ጉዳይ አይጨነቅም ነበር፡፡ ከሕዝብ ቀረጥና ግብር ከሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ አሥር ቢሊዮን ብር መድቦ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እፈጥራለሁ ብሎ መነሳቱ አነጋጋሪ ነው፡፡
መጀመሪያውኑ በሃያ ስድስት ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ወቅት በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር ወይም ማስፈጠር ሳይችል ቆይቶ እንዴት በሥልጣን ሊቆይ ቻለ ብሎ መጠየቅም ይቻላል? ሥራ ያጣ ሕዝብ ‹‹ሥራ አጥነት እንደ ማር ጣፍጦኛልና ሥልጣን ላይ ቆይልኝ፤›› የሚለው አይመስለኝም፡፡ እናም ሪፖርተር ጋዜጣ ችግሩን ላይ ላዩን ነካክቶ ከማለፍ ይልቅ በእነዚህ ዓይነት መሠረታዊ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቶ መሞገት ምክር መስጠት ይበቅበታል፡፡ ልማዳዊ ግንዛቤ ሳይንስ አይደለም የምለውም ለዚህ ነው፡፡ ይኼ ችግር ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› በሚል አገላለጽ የሚፈታ አይደለም፡፡
በለሙት አገሮች ለሥራ ፈላጊዎች ካፒታል የሚያቀርቡ ለትርፍ የተቋቋሙ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ የቬንቸር ካፒታል ድርጅቶች ይባላሉ፡፡ ድርጅቶቹ ሥራ ፈጣሪዎችን (ኢንተርፕረነርስ) አይፈጥሩም፡፡ ሥራ ፈጣሪዎች በተፈጥሮ ክህሎት፣ በትምህርትና በሥልጠና (ያውም ጥራቱን የጠበቀ) እንዲሁም በግል ተነሳሽነት የራሳቸውን ሥራ የፈጠሩ ግለሰቦች ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ግን የአሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ሥራ ፈጣሪዎችንም ለመፍጠር እየሞከረ ይመስላል፡፡ በሕዝብ ይሁንታ ያላገኘ ወይም በተግባር ችሎታ እንዳለው ያልተረጋገጠለት መንግሥት በሚያስተዳድረው ፈንድ አማካይነት ሥራ ፈጣሪዎችን ፈጥሮ፣ የሥራ ዕድልን ለማስፋፋት እየሞከረ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
በልማዳዊ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍም ሆነ ንግግር ለሕዝቡ በቀላሉ ስለሚገባ፣ እውነት ብቻ ሳይሆን ለችግርም መፍትሔ የሚጠቁም ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ‹‹በሽታውን የደበቀ መድኃኒት አያገኝም›› ሲባል ግን ከአጠቃላይ እውነታው በመነሳት ለተለዩና ለተወሰኑ ችግሮች አግባብ ያላቸው ሳይንሳዊ እውነቶች ላይ ተመሥርተን ትንተና ካላደረግን በቀር ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት አይቻልም፡፡ ልማዳዊ ግንዛቤ ሳይንስ አይደለምና፡፡
መቼም የኢሕአዴግ መንግሥት ሥራ የመፍጠር ችሎታ ስለሌለው ሥልጣኑን በገዛ ፈቃዱ ይልቀቅ ወይም በሰላማዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከሥልጣን ይወገድ ለማለት የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ከፖሊቲካው በመለስ ግን አንዳንድ ሐሳቦችን ማቅረብ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተመሠረተውን የአሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ በተመለከተ ሊቀርቡ ከሚችሉ አጠቃላይ የመፍትሔ ሐሳብ የሚከተሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ገንዘቡን እንደ ቬንቸር ካፒታል ሊጠቀሙበት ለሚችሉ የግል ባንኮች በአነስተኛ ወለድ ማበደር፡፡ ገንዘቡ ለተወሰነ ዓላማ የሚውል እንደመሆኑ መጠን ተበዳሪዎች በመለስተኛና በመካከለኛ የግብርና፣ የአግሮ ኢንዱስትሪ፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ወይም የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አዳዲስ ድርጅቶችን ለማቋቋም የሚጠቀሙበት እንዲሆን ማድረግ፡፡
ይህ ሲሆን፣ የግል ባንኮች በተበደሩት ገንዘብ ላይ ወለድ ስለሚከፍሉበት አዋጪ ላልሆኑ አዲስ የቢዝነስ ድርጅቶች አያበድሩም፡፡ ሥራ ፈጣሪዎቹም የቢዝነስ ክህሎቱ ሳይኖራቸውና የተወሰነ ማስያዣ አስይዘው ከባንክ ብድር ለመውሰድ ስለማይደፍሩ፣ የሥራ ፈጠራ ጅማሮውና ሒደቱ ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚሆን ይገመታል፡፡
በርካታ ሰዎች ስለሥራ ሲያወሩ ‹‹ዋናው ፍቅር ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይኼ በልማዳዊ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ አባባል ነው፡፡ ጠለቅ ብለን ስናየው ግን፣ ከፍቅር በፊት ፍትሕ ይቀድማል፡፡ ፍትሕ ከሌለ ፍቅር ሊኖር አይችልም፡፡ በተመሳሳይም መንግሥት ‹‹ለካንሰር ታማሚ የሳንባ መድኃኒት አይታዘዝም›› የሚለው ምክር ገና የገባው አይመስለኝም፡፡ ከገባውም ዝምታን መርጧል ማለት ነው፡፡
ችግሩ በግልጽ ተፍረጥርጦ ሊነገረው ይገባል፡፡ ለሃያ ስድስት ዓመታት ከ300 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የሚጠይቅ ኢኮኖሚ እየመራህ በቂ የሥራ ዕድል ግን ልትፈጥር አልቻልክም፡፡ በአሥር ቢሊዮን ብር መድበህም ተዓምር ስለማትሠራ የአሠራር ሥርዓትን መቀየር አለብህ መባል አለበት፡፡ ብሩን ለግል ባንኮች በማበደር የሚያገኙበትን ትርፍ መልሰው እንዲያበድሩ ማድረግ የሥራ ዕድል እንዲስፋፋ ሊግዝ ይችላል፡፡ ባይሆን የግል ባንኮች ብድሩን የሚያቀርቡት ለሥራ ፈጣሪዎች ብቻ እንዲሆን የሚጠይቅ ግዴታ እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ ቸር ይግጠመን!
(ተክለብርሃን ገብረሚካኤል፣ ከአዲስ አበባ)
* * *
ሥነ ምግባር የስኬት ነጸብራቅ ነውና እንንከባከበው!
ሥነ ምግባር የአንድ ሰው እምነት፣ ስብዕናና እሴቶች ድምር ውጤት ነው፡፡ በባህርያችንና በተግባራችንም ይገለጻል፡፡ እጅግ ውድ ከሚባል ጌጣጌጥ በላይ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ አሸናፊ ለመሆን ሥነ ምግባር ወሳኝነት አለው፡፡ ጆርጅ ዋሽንግተን በአንድ ወቅት ‹‹የአንድ ታማኝ ሰው ጽናትና ሰናይ ምግባራት ይኖሩኝ ዘንድ ሁሌም እተጋለሁ፤›› ብሏል፡፡ የታሪክን እሽክርክሪት የሚቆጣጠረው የሕዝብ አስተያየት (ድምፅ) ሳይሆን የመሪው ሥነ ምግባርና ባህርይ ነው፡፡ ወደ ስኬት የሚደረግ ጉዞ ብዙ እንቅፋቶች ቢኖሩትም በእነዚያ እንቅፋቶች ተሰናክሎ ላለመውደቅ ሰናይ ምግባርና ከፍተኛ ጥረት አስፈላጊ ናቸው፡፡ ተገቢ ባልሆነ ትችት ተሽመድምዶ ላለመውደቅ ጠንካራ ሆኖ መገኘት ግድ ይላል፡፡
አንድ ሰው በስኬት ከፍ ከፍ ባለ ቁጥር እሱን ጎትቶ ለማውረድ የሚሠለፉ በርካቶች ናቸው፡፡ በተራራ አናት ላይ የቆመ ሰው እዚያ ላይ የደረሰው እንደሁ በድንገት (በዕድል) ሳይሆን፣ ብዙ ተጋግጦና ታግሎ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ በየትኛውም የሙያ መስክ ውጤታማ የሆኑ ሰዎች ስኬታማ ባልሆኑ ሰዎች ዘንድ መንቋሸሻቸው የተለመደ ነው፡፡ ማንጓጠጥ ሥራ የማይሠሩ ሰዎች ባህርይ ነው፡፡ እጃቸውን አጣምረው በመቀመጥ የሚሠራውን ሰው ምንና እንዴት መሥራት እንዳለበት ሊነግሩት ይሞክራሉ፡፡ ዘለፋዎች ከግባችሁ እንዲያደናቅፏችሁ፡፡ አትፍቀዱላቸው፡፡ ለዘለፋና ለሒስ እጅ አትስጡ፡፡ ወቀሳን በመፍራት ሥራ ከመሥራት የሚታቀቡ ይኖራሉ፡፡ እየሠራችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ግን ብዙ ተቺና ወቃሽ ሊያጋጥማችሁ ይችላል፡፡ ማንም ሰው መተቸትን አይወድም፡፡ ሆኖም ከቅን ልቦና ከሚመነጭ ሒስ ራሳችንን የምናሻሽልበትን ትልቅ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን፡፡ በትችት ላለመጎዳት ጠንካራ ልብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ጠቃሚ ትችትን ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግም ጠንካራ ስብዕናን ይጠይቃል፡፡ የስኬታማ ሰው መለያም ይኼ ነው፡፡ ስኬታማ ሰው ራሱን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ተገቢ የሆነውንና ያልሆነውን መለየት አያዳግተውም፡፡ ስኬታማ ሰዎች ተዓምራትን አይጠብቁም፡፡ ቀላሉን አቋራጭ መንገድም አይሹም፡፡ ፍላጎታቸው እንቅፋቶቻቸውን የሚወጡበት ብርታትና ጥንካሬ ነው፡፡ የሚለኩት ምን ያህል እንደቀራቸው እንጂ ምን ያህል እንዳጡ አይደለም፡፡ ምኞት ብቻውን ዕውን አይሆንም፡፡ ምኞት ዕውን የሚሆነው ወይም ለውጤት የሚበቃው ከፅናትና ከጥረት ጋር ነው፡፡ ፀሎትም ቢሆን ተሰሚነት የሚኖረው ወኔ በተሞላበት ድርጊት ሲታጀብ ነው፡፡ ወኔና ሥነ ምግባር ለስኬት አስፈላጊ ቅመሞች ናቸው፡፡ ባህርይ በተለይም ፍትሐዊነትና ሀቀኝነት ያለ ወኔ ብቻውን ውጤታማ አይሆንም፡፡ ወኔም እንደሁ ያለ ባህርይ ከግብ አይደርስም፡፡ ስለዚህ መልካም ሥነ ምግባር ወኔና ጥረት ተጣምረው ስኬታማ ስለሚያደርጉን ይህ እንዲኖረን እንትጋ፡፡
(ተክልዬ ጀማነህ፣ ከምሥራቅ አዲስ አበባ)
* * *
‹‹ሪሚሽን›› ከካንሰር መዳን እንጂ የካንሰር ተመልሶ መምጣት አይደለም
“እንደሠማይ የራቁ መድኃኒቶች” በሚል ርዕስ ረቡዕ መጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በማኅበራዊ ዓምድ ሥር የወጣውን ጽሑፍ አንብቤ መሠረታዊ ጉድለት የተንፀባረቀበት፣ ስህተቱም የሚያስተዛዝብ ሆኖ ስላገኘሁት ጋዜጣው ተገቢውን ዕርማት እንዲያደርግ ለማሳሰብ ይኼንን ደብዳቤ ልኬያለሁ፡፡
በጽሑፉ ለዓለም ስለምትባል የካንሰር ታማሚ ልጅና ስለቤተሰቧ የሚያትት ዘገባ ቀርቧል፡፡ እንዲህ የሚል ነገርም ተገልጿል፡፡ ‹‹…ይኼ የካንሰር ትግል ግን በዚሁ አላቆመም፡፡ ለዓለምም ሆነች ቤተሰቦቿ ያስጨነቃቸው ጉዳይ የበሽታው ተመልሶ መምጣት (ሪሚሽን) ነበር››፡፡
የካንሰር ሕመምተኛ የሆነ አሊያም የነበረ ማንኛውም ሰው፣ አሊያም በካንሰር ሕክምና አሰቃቂ ሒደቶችን ያለፈ የቤተሰብ አባል ያለውም የነበረውም ሰው ሊናገር እንደሚችለው ‹‹ሪሚሽን›› የሚለው ቃል ከምድራዊ ቃል በላይ የሚናፈቅና ከሐኪሞች አፍ ሲወጣ ከተሰማም ከሞት የመነሣት ያህል ትርጉም የሚሰጠው ታላቅ የምሥራች ቃል ነው። ምክንያቱም ‹‹ዘ ካንሰር ኢዝ ኢን ሪሚሽን›› ስለሚባል ነው፡፡ ይህም ማለት በአጭሩ ካንሰሩ ጠፍቷል፣ ድነሃል፣ ድነሻል ማለት ስለሆነ ነው።
ካንሰሩ ሪሚሽን ላይ ነው ሲባል፣ ሕመምተኛው ከካንሰር ነፃ ሆኗል ማለት እንጂ ‹‹የበሽታው ተመልሶ መምጣት›› ፈጽሞ ማለት አይደለም። ይህን ለማወቅም የግድ በካንሰር መታመም ወይም በዚያ ስቃይ ውስጥ ያለፈ ሰውን ማወቅ አይጠይቅም። ሪሚሽን ምን ማለት እንደሆነ የሚስረዱ በርካታ የመረጃ ምንጮች አሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሐተታዎች ሲቀርቡ ወይም ሲዘገቡ አግባብ የሆኑ መሠረታዊ የመረጃ ምንጮችን በመጠቀም ነገሩን መመርመር ለጋዜጠኞች መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነውና ይታሰብበት፡፡ ቸልተኝነት እንደ ሙያዊ ወንጀለኝነት ሊያስቆጥር ስለሚችል፣ የሚቀርቡ መረጃዎች ተጣርተው ተፈትሸው ቢሆን መልካም ነው።
(ዳንኤል በላይነህ፣ አዲስ አበባ)