Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉኢኮኖሚያዊ አብዮቱና ሕዝባዊ ተጠቃሚነት

ኢኮኖሚያዊ አብዮቱና ሕዝባዊ ተጠቃሚነት

ቀን:

በአገራችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ዓውድ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ገኖ እየተነሳ የሚገኘው ሐሳብ የኢኮኖሚ ወይም የኢንዱስትሪ አብዮት የሚል ነው፡፡ በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት በቅርቡ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለውን ዕቅድ በተመለከተ የሚቀርቡ የተለያዩ ሐሳቦች ናቸው፡፡ የሐሳቦቹ ይዘት ሲታይ በሁለቱም ጽንፍ ማለትም የማያስፈልግና እስካሁን የተገኘውን ውጤት የሚያበላሽ ነው ከሚለውና ከዚህ አካሄድ ውጪ ለውጥ ማምጣት አይቻልም እስከሚለው ድረስ የሚደርስ ሲሆን፣ በመሀሉ ምክንያታዊ የሆኑ የክርክር ሐሳቦችን የሚያቀርቡ ግለሰቦች አሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ በተለያዩ የኅትመት ሚዲያዎች የቀረቡትን ሐሳቦች መነሻ በማድረግ በእርግጥም በክልሎቹ የተወሰዱ ወይም ሊወሰዱ የታሰቡ ዕርምጃዎች ፌዴራላዊ መንግሥት ከሚከተላቸው የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች ጋር ይጋጫል ወይ? የግሉ ባለሀብትን ሊያቀጭጭ ወይም ፍትሐዊ የንግድ ውድድር እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል ወይ? ለእነዚህ ዕርምጃዎች መውሰድ መሠረታዊ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ጊዜያዊ ግልባዊ ምክንያቶች ናቸው? ወይስ ከዚህ በላይ ሊታይ የሚገባው ነገር አለ? ውሳኔዎቹ ጽንሰ ሐሳባዊ መሠረትስ አላቸው ወይ? በክልሎቹ አካሄድ ተጠቃሚ ወይም ተጎጂ የሚሆነው ማን ነው? የሚሉት ነጥቦች ላይ ምልከታዬን ለማቅረብ ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ አብዮት ለምንና ለማን?

መንግሥታት ቃላትን ሲጠቀሙ ከሕዝብ ጋር ግንኙነት የሚያደርጉባቸው መሣሪያዎች በመሆናቸው ምክንያት የአፍ ወለምታ በሚያስብል ደረጃ ዝም ተብለው የሚወረወሩ አይደሉም፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኢኮኖሚ አብዮት መሠረታዊ መርህ ብሎ ያስቀመጠው የክልሉ ነዋሪዎች ውኃ ዳር ቆመው ውኃ ሊጠሙ አይገባም የሚል ሲሆን፣ በተለይም በክልሉ ውስጥ ብዙ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ያሉ ቢሆንም፣ እነዚህን ሀብቶች የክልሉ ሕዝብ በመጠቀሙ ኑሮውን መግፋት አቅቶት በድህነት ውስጥ የሚኖር በመሆኑ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት የሚል ነው፡፡ ስለሆነም ሐሳቡ ከመሠረታዊነቱ አግላይ ሳይሆን፣ ይልቁንም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ አብዮት ማካሄድ አለብን ሲባል ማኅበረሰቡ በሀብቱ መጠቀም እንዳይችል ያደረጉ መሠረታዊ መዋቅራዊ ምክንያቶችን በመለየትና እነዚህን ከሥራቸው መንግሎ በመጣል፣ የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ ሥራዎችን ማከናወን ነው፡፡ ስለሆነም የሐሳቡ አልፋና ኦሜጋ ድህነት መገለጫና መርህ የሆነበትን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ ብልፅግናና ተጠቃሚነትን መሠረታዊ መገለጫና መርህ ባደረገ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማንበር ነው፡፡

የክልል መንግሥታት የኢኮኖሚ አብዮት በሚል በማለት ዘርፊ ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እንዲያስችል የወሰዱዋቸው ውሳኔዎች ጥልቅ ኢኮኖሚያዊና ጽንሰ ሐሳባዊ ምክንያቶች ያላቸው ናቸው፡፡ ዌበር (Weber) የሚባለው ፈላስፋ በመንግሥትና በማኅበረሰብ ወይም በግሉ ዘርፍ መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት፣ መንግሥት ራሱን ነፃ አድርጎ ለግሉ ዘርፍ ጥሩና ተገማች ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት መወጣት አለበት የሚለው ሐሳብ ለብዙ ዘመናት ተቀባይነት ያለው ነው ይላል፡፡ መንግሥት ይህን የሚያደርግበት ምክንያት ከግሉ ዘርፍ ተፅዕኖ ነፃ የመሆኑ አቅሙ፣ የግሉ ዘርፍ በበቂ ደረጃ ሥጋቶችን አሸንፎ መሥራት ላይ እጥረቶች በመኖራቸው የዚህ ሐሳብ ቅቡልነት እንዲቀንስ አስገድዶታል፡፡ ከዚህ በኋላ በተለይም የልማታዊ መንግሥታት ንድፈ ሐሳቦችን ትርጉም ባለው መንገድ በመቅረፅ የሚታወቁት የኢንስቲትዩሽና ኢኮኖሚክስ ምሁራን የሆኑት ግሬሽንክሮን (Gerschenkron) እና ሔርሽማን (Hirschman) መንግሥት ከማኅበረሰቡ ወይም ከግሉ ዘርፍ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባቸው ግንኙነቶች በተመለከተ ገዥ የሆኑ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ በተለያዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በተለይም በማኑፋክቸሪነግ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት በተለያየ መንገድ ሥጋት የሚያጋጥማቸው በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ይቸገራሉ፡፡ ስለሆነም መንግሥት የግሉ ባለሀብት ያለውን ገንዘብ እንዲያሰባሰብና የግሉ ዘርፍ ተዋናዮች አቅም ክፍተት በመሙላትና የሚቸግራቸውን በጋራ በመቅረፍ የኢንቨስተመንት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም መንግሥት የኢንቨስትመንትና የኢንተርፕሩነርሺፕ አዋላጅነት (Surrogate Entrepreneurship) ሥራውን ያከናውናል ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ኢንቨስትመንት ማካሄድ አትራፊ መሆኑን የግሉ ዘርፍ አመኔታ ቢኖረውም፣ ይህን አመኔታ ወደ ተግባር በመቀየር በኢንቨስትመንት መሳተፍ ላይ ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንዲቻል መንግሥት የሚያስተላልፈው ውሳኔ ‹‹Maximizing Induced Decision-Making›› እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የክልል መንግሥታት ትልልቅ ፕሮጅከቶችን በመቅረፅ አክሲዮን ማኅበራት እንዲቋቋሙ ሲፈልጉና መነሻ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ በባለሀብቶች መካከል መተማመን ለመፍጠር ኩባንያው በሁለት እግሩ እንዲቆም ለማድረግና ለመሳሰሉት መሆኑ ሲታይ ውሳኔው ምን ያህል ጽንሰ ሐሳባዊ ምክንያትና መሠረት እንዳለው መገንዘብ ይቻላል፡፡

የክልል መንግሥታት የወሰዱትን ዕርምጃ በተመለከተ የሚነሳው ሌላው የተሳሳተ አመለካከት ክልላዊና ሲብስም ብሔራዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና ሌላውን ለማግለል የተወሰነ ነው የሚል ነው፡፡ በእርግጥ የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸው በመጀመርያ በክልሉ የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠቀም የክልላቸውን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ የክልሎቹ ተጠሪነት ለክልላቸው ሕዝብ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ለሚፈጠሩ በጎ ነገሮች ወይም መጥፎ ነገሮች ተጠያቂ የሚሆኑት ራሳቸው ክልሎቹ ናቸው፡፡ ይህ መሠረታዊ ሐሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከክልሉ ውጪ የሚመጡ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማለትም በመደበኛ ነዋሪዎች ወይም የንግድ ተቋማት በተለየ ሁኔታ እንዲጎዱ የሚያደርጉ ዕርምጃዎችን መውሰድ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይህን ማድረግ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚካሄደውን እንቅስቃሴ መጉዳቱ የማይቀር በመሆኑ፡፡ በሌላ በኩል ሲታይ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የፌዴራል መንግሥት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያለው ሁሉን አቀፍ ሥልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ክልሎች እንደ ራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ሕይወትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ዕቅዶችን የማውጣትና እንዲተገበር የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

መንግሥታቱ የንግድ ማኅበራት የሚፈጠሩበትን ሁኔታዎች ሲያመቻቹ ወይም ሲያስተባብሩ እነዚህ ድርጅቶች የአገሪቷን የንግድ ሕግ ባከበረ ሁኔታ መመሥረት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚመሠረቱት ድርጅቶች የአክሲዮን ማኅበራት እስከሆኑ ድረስ ግልጽ በሆነ ማስታወቂያ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች አክሲዮን በመግዛት መሳተፍ እንደሚችሉ በተለያየ መንገድ ተገልጿል፡፡ ኦሮሚያ ወይም አማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ አክሲዮን በሚሸጥባቸው ባንኮች ብቻ ሳይሆን፣ ከኦሮሚያ ወይም ከአማራ ክልል ውጪ በሚገኙ አክሲዮን በሚሸጥባቸው ባንኮች አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ግለሰብ ሊገዛ የሚችል መሆኑ ሲታይ፣ አካሄዱ ምኑን ያህል የንግድ ሥርዓቱ በሚፈልገው መንገድ እየተከናወነ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡

የክልል መንግሥታት ተሳትፎ እንዴት?

በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ላይ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት መርህን መሠረት ያደረገ ሐሳብ ተቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት ብዙኃኑ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ልማት ለማረጋገጥ እንዲቻል የግሉን ዘርፍ ግልጽ በሆኑ መርሆች መደገፍና አስፈላጊ የሆነ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲችል፣ ተነፃፃሪ ነፃነት ይዞ መንቀሳቀስ የሚጠበቅበት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በግሉ ባለሀብትና በአርሶ አደሮች መካከል ያለው ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ፣ የጥቅም ግጭቶችን ለማርገብ ግብርና መር የሆነው ኢንዱስትራላይዜሽን ተግባራዊ ለማድረግ በግሉ ባለሀብትና በአርሶ አደሮች መካከል የጋራ ራዕይ እንዲኖር መሥራት እንዴት እንደሚገባው እንዲህ ሰፍሯል፡፡ ‹‹መንግሥት ከዚህ አኳያ ከፍተኛ የአመራር ሚና መጫውት አለበት፡፡ በመጀመርያ ደረጃ ግብርና መር በሆነው የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ አርሶ አደሩና ባለሀብቱ መሠረታዊ የሆነ የጋራ ጥቅም እንዳላቸው፣ በዚህ ውስጥ የጥቅም ግጭቶች እንዲሚኖሩና የጥቅም ግጭቶቹን በምን ዓይነት መንገድ ማጣጣም እንደሚቻል በማሳየት አርሶ አደሩና ባለሀብቱ ለጋራ የልማት ዓላማ አብረው የሚሠለፉበት የጋራ ራዕይ እንዲፈጠር መሥራት አለበት፡፡ የአርሶ አደሩንና የባለሀብቱን የጥቅም ግጭቶች ማጣጣም የሚቻለው ይህንን ለማድረግ የሚያስችል መሠረት ሲነጠፍ፣ አርሶ አደሩም ባለሀብቱም  ምርታማነታቸው በከፍተኛ ደረጃ ሲጨምሩ መሆኑን በመገንዘብ ለምርታማነት መጨመር ሁለቱም ወገኖች በመደገፍና በማስተባበር መንቀሳቀስ አለባቸው፤›› ይላል፡፡

የክልል መንግሥታት የአክሲዮን ማኅበራት ምሥረታ ላይ ያላቸው ድርሻ በአብዛኛው በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኩል የሚይዙት ነው፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው በቦርድ የሚተዳደሩ፣ በአንድ በኩል ትርፍ የማግኘት ዓላማ በሌላ በኩል ደግሞ ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው፡፡ ድርጅቶቹ ሲመሠረቱ የራሳቸው ዓላማዎች ያላቸው ሲሆን፣ እነዚህን ዓላማዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተግበር እንዲያስችላቸው ሌሎች ተግባራትንም ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ ድርጅቶቹ የቢዝነስ ተቋማት በመሆናቸው ምክንያት ዓላማቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚያስችላቸው ሌሎች የገቢ ማግኛ ሥራዎች ውስጥ ሊሳተፉ፣ ማለትም የንግድ ድርጅቶችን የማቋቋም ወይም የአክሲዮን ድርሻ ባለቤት የመሆኑ ሕጋዊ ችሎታ አላቸው፡፡ ስለሆነም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድርሻ ያለባቸው የንግድ ማኅበራት የራሳቸው ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ሲሆን፣ ይህም የሰውነታቸው ሁኔታ ከባለ አክሲዮኖች ካላቸው ሕጋዊ ሁኔታ የተለየ ነው፡፡

ስለሆነም ከዚህ ሐሳብ በመነሳት ሲታይ የክልል መንግሥታት የአኮኖሚ አብዮት ሲሉ እኔ እንደሚገባኝ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት የግሉ ዘርፍ ሊሠራው የሚችለውን የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የመንግሥትነት ድርሻውን በመዘንጋትና የግሉን ዘርፍ ለማቀጨጭ በሚል ምክንያት ሳይሆን፣ በተለያዩ የኢኮኖሚ ተዋናዮች መካከል በተለይም በግል ባለሀብትና በአርሶ አደሩ መካከል ያለውን ቅንጅታዊና ኅብረታዊ ግንኙነት ውጤታማ ለማድረግ እንዲያስችለው ነው፡፡ እንዲሁም ጊዜያዊ የማስተባበርና የጋራ ራዕይ እንዲይዙ የማድረግ፣ በዚህም በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ላይ የተቀመጠውን የመሪነት ሚናውን ለመወጣት በሚል የሚያከናውነው እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የክልል መንግሥታት በንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የመንግሥትነትንና የነጋዴነትን ሀሁ ሳያውቁ በዚያው የሚቀሩ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደነበረው ድርጅቶቹ ህልውና እንዲያገኙ ከተደረገ በኋላ በልማት ድርጅቶች በኩል መንግሥት ያለውን ድርሻ ለአርሶ አደሮችና ለወጣቶች በማስተላለፍ እንደሚወጠሩ ፍላጎቱም ድርጅቶቹ ተገንብተው ማየት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢኮኖሚያዊ አብዮትና የንግድ ውድድር ማረጋገጥ

የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ከንግድ ውድድር መርህ ውጭ ከቶ ሊታሰብ አይችልም፡፡ በተለይም የንግድ ውድድር ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሥራዎች በአገር አቀፍ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ባለሀብቶች ለማፍራት እጅግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ክልሎች የኢኮኖሚ አብዮት በሚል የተለያዩ የኅብረተሰብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ የአክሲዮን ማኅበራት እንዲመሠረቱ ማድረጋቸው፣ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖሩ ተዋናዮች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ ገበያውን በበላይነት በመያዝ ሊፈጸሙ የሚችሉ ፀረ ንግድ ውድድር ተግባራት እንዲቀንሱ ያደርጋል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይም ሸማቹ ማኅበረሰብ አማራጮችን አንዲያገኝ፣ የምርቶችና የአገልግሎቶች ዋጋ እንዲቀንስ በማድረግ የሸማቾች መብትና ጥቅም እንዲረጋገጥ ያደርጋል፡፡

በፕሮጀክቶቹ መሠረት የሚቋቋሙት የንግድ ማኅበራት በመሆናቸው ምክንያት የንግድ ውድድርን ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የወጣው ሕግ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው ይሆናል ማለት ነው፡፡ የድርጅቶቹን መቋቋም በተመለከተ የሚነሳው ሐሳብ የግሉ ዘርፍ የሚሠራቸውን ሥራዎች ድርጅቶቹ ይሠራሉ፣ ስለዚህም ይህ የነጋዴውን ጥቅም የሚጎዳና በሌላ በኩል የክልሎቹን ውሳኔዎች ስህተትነት ለማንበር የሚቀርበው ሐሳብ መንግሥት የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም እየተገበረ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የክልል መንግሥታት በኢኮኖሚ ውስጥ ፈርጣማ አቅም ለመገንባት የሚሄዱበት ጉዳይ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው የሚል ነው፡፡ በመሠረቱ የፕራይቬታይዜሽን ፕሮግራም ዓላማው በግሉ ዘርፍ ውጤታማ ሆነው ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች የሚያከናውኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወርና በዚህም ምክንያት የግሉ ዘርፍና መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ መቀየር ሲሆን፣ አሁን በክልሎች እየተደረገ ያለው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማቋቋም አይደለም፡፡ ወይም ፕሮጀክቶቹ ይተገበርባቸዋል ተብለው በተያዙ አካባቢዎች ላይ እነሱን የሚመስል ድርጅት በመመሥረት ከሕዝቡ ፍላጎት በላይ በማምረት ገበያውን ማጥለቅለቅ አይደለም፡፡ ከመነሻው በድርጅቶቹ የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ ሆኖ ተፅዕኖ የማድረስ አቅም የሚያረጋግጥ አይደለም፡፡ ስለሆነም አፕልና ብርቱካን አንድ አድርጎ ለማነፃፀርና በሁለቱ መካከል ያለውን ተቃርኖ ለማሳየት መሞከር የሚያስኬድ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በዚህ አግባብ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት የሙስናና ኪራይ ሰብሰቢነት ችግሮች እንዲኖሩ በማድረግ ከግል ባለሀብቶች ጋር የማይፈለግ ግንኙነት እንዲኖር የንግድ ውድድሩ ፍትሐዊነት ይዛባል በሚል የሚቀርብ ሐሳብ አለ፡፡ በእርግጥ በአገራችን ነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች በግሉ ባለሀብትና በመንግሥት መካከል የሚኖረው ግንኙነት መርህን መሠረት እንዲሆን ካልተደረገና ይህን በጥብቅ ዲስፒሊን የሚተገበርበት ሁኔታ ካልኖረ፣ የመንግሥት መዋቅር በግል ባለሀብቶች የሚያዝበት በዚህም መንግሥት ለሕዝቡና መንግሥትን ላልያዙት ባለሀብቶች ጉዳት እንደሚሆንና በአጠቃላይ የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ሊያነሳ እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ስለሆነም አማራጩ በአንዱ በኩል ከግሉ ባለሀብት በመራቅ የግሉ ባለሀብት ኢኮኖሚያዊ ውጤት የሚያመጡ የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎች እስከሚገባ መጠበቅ፣ እሱም ከገባ ማለት ነው ወይም የግሉ ዘርፍ ያሉበትን ነባራዊና ህሊናዊ ሥጋቶችን አሸንፎ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ መንግሥት የማስተባበርና መንገድ የማሳየት ሚናውን ሊያከናወን ይገባል የሚል ነው፡፡

የግሉ ዘርፍ እስከሚገባ ድረስ እንጠብቅ ማለት በተለመደው መንገድ ሒደቱንና ዕድገቱንም እናዘግየው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በዚህ አግባብ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባ ከሆነ ለሙስናና ለኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ምክንያት ይሆናል ማለት፣ አንድም መግባት አለመግባቱ ዋስትና የሌለበት በዚህም ሊገኝ የሚችለው ጥቅም የሚታጣበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በሌላ በኩል ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚደረግ ግንኙነት መርህን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ሁለቱም አማራጮች የራሳቸው እጥረቶች ያለባቸው ቢሆንም፣ የሚመረጠው ግን አነስተኛ ችግሮችን ሊፈጥር የሚችለው አማራጭ ማለትም መንግሥት የግሉ ዘርፍ ወደ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል ሥራዎችን እንዲሠራ ማድረግ የሚለው በመሆኑ፣ በዚህ አግባብ የክልል መንግሥታቱ ወስነው መግባታቸው ተገቢና ትክክል ነው፡፡

ሌላው ሁለቱ የክልል መንግሥታት ፋብሪካዎችን ለማቋቋም እየሠሩባቸው የሚገኙት ዘርፎች የግሉ ዘርፍ የገባባቸው ናቸው፡፡ በእርግጥ ከዚህ በላይም ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት ፋብሪካዎቹን የሚያቋቁሙት የክልል መንግሥታት አይደሉም፡፡ የክልል መንግሥታት እያደረጉ ያሉት በሌሎች በልማታዊ መንግሥታት የሚታወቀውን ፋብሪካዎች እንዲወለዱ የማድረግ የአዋላጅነት ሚና (Midwifery Role) እየተጫወቱ የሚገኙ መሆናቸው ነው፡፡ በአንድ አገር ውስጥ የተወሰኑ የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረት፣ የለስላሳ መጠጦች፣ የእንጨት ሥራዎች፣ ትራንስፖርትና ነዳጅ ማደያዎች፣ ሪል ስቴቶች መኖራቸው ብቻ በአገሪቷ ውስጥ በእነዚህ ፋብሪካዎች በቂ የሆነ አቅርቦት አለ የማያስብል መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ፋብሪካዎች ምን ያህሉን ለአገር ውስጥ ምን ያህሉን ለውጭ በመላክ የአገራችንን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እያረኩ የንግድ ሚዛኑን እያስጠበቁ ነው? በማለት መታየት ይኖርበታል፡፡

በአገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ ሸማቹን የሚያማልሉ ምርቶችና አግልግሎቶችን በማቅረብ አሸናፊ መሆን የሚፈልግ ድርጅት ወይም የድርጅቱ የንድፈ ሐሳብ አቀንቃኝ ውድድርን የሚጠላው፣ ወይም ሌላ ድርጅት እንዳይመጣበት የሚፈልገው ተወዳዳሪነት ካለ እሱን ከተመራጭነት ውጪ ስለሚያደርገውና በንፋስ አመጣሽ መንገድ የሚገኘውን የአብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚነት የሚጎዳ ሁኔታ እንዲቀጥል ስለሚፈልግ ነው፡፡ ሐሳቡ ግለሰቡ ካለው ውግንና የሚነሳ በመሆኑ የሚቀርበውን ሐሳብ ከዚህ አንፃር ማየት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት ዘርፍ ስለተባለ ብቻ ክልሎች በአንድ መስመር ብቻ የተገናኙ በሚያስመስል ሁኔታ በክልሎች ድጋፍ እንዲመሠረቱ የተባሉት ድርጅቶች ከሌሎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከሚሠሩት ሥራ ጋር ይደራረባል ማለት ይቻላል፡፡ ግን የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በአንድ መስመር ላይ የባቡር ሐዲድ ተሠራ ማለት ከዚህ የባቡር ሐዲድ ውጪ ከተጓዡ ፍላጎት ወይም ከሚጓጓዘው ዕቃ አንፃር ሌሎች አማራጮችን ሊያቀርብ የሚችል የትራንስፖርት አገልግሎት ሊኖር አይገባም በሚል የሚቀርበው ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን፣ እርግጥ ህላዊ ተቀባይነት ያለው ሐሳብ አይሆንም፡፡ በእርግጥ ክልሎቹ ይህን መሰል ትራንስፖርት እንዲመሠረት ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ ያለ ጥናት የሚገቡበት እንደማይሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኩል ካለው አነስተኛ ድርሻ አንፃር እንኳን ወደ ትግበራ ልግባ ቢል ሌሎች ባለአክሲዮኖች በተለይም የግሉ ባለሀብቶች በፈቃደኝነት መንግሥት በልማት ድርጅቶች በኩል ድርሻ ስላለው በሚል ብቻ ወደ ምሥረታው ይገባሉ ማለት የዋህነት ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ አብዮትና የትራንስፎርሜሽንን ዕቅድ

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ማለትም በኢኮኖሚ ውስጥ ግብርናና ኢንዱስትሪ መካከል ያለውን ግንኙነት ውጤታማ በማድረግ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መሠረት መጣል ነው፡፡ ዕቅዱ በተለይም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት በተመለከተ የተለያዩ ሐሳቦችን ያስቀምጣል፡፡ በዕቅዱ መሠረት ‹‹በተመረጠ አኳኋን በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በተናጠልና በሽርክና የማሽን መሣሪያዎች፣ ለከባድ የኤሌክትሪክ መሣሪያዎች፣ ለከባድ የትራንስፖርት፣ የግንባታና የማዕድን ቁፋሮ መሣሪያዎችና ለከባድ የፔትሮ ኬሚካልና ኬሚካል ማምረቻዎች እንዲሁም ለታዳሽ ኢነርጂ ማመንጫዎቸ ትኩረት ይሰጣል፤›› በሚል ያስቀምጣል፡፡

ስለሆነም ከዚህ በላይ በተገለጹ ዘርፎች ላይ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በሽርክና አሠራር መሠረት የተለያዩ የንግድ ማኅበራትን በማቋቋም፣ ጉልበትንና የግብርና ምርቶችን በስፋት በግብዓትነት ለሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ የግብርና የኢንዱስትሪና የገጠርና ከተማ ትስስሮች እንዲጠናከሩ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡  በዕቅዱ በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ከታዩ ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የሥራ ፈጠራና የድህነት ሁኔታ መሆኑን፣ የሚታቀደው ማንኛውም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት በዜጎች የሥራ ሥምሪትና የደኅንነት ሁኔታ ላይ ለውጥ ማምጣት ያለበት ስለመሆኑና መንግሥት በተለይ ይህን ተልዕኮ እንዲወጣ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የግል ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የሚገባው ስለመሆኑ ተቀምጧል፡፡

የክልል መንግሥታት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በማለት የወሰዱዋቸው ዕርምጃዎች ሲታዩ፣ በአንድ በኩል በግል ባለሀብቶች ተይዘው እሴት ሳይጨመርባቸው የተያዙ የማዕድን ቁፋሮ ቦታዎችን በገቡት ውል መሠረት ባለማከናወናቸው በመቀበል ለሥራ አጥ ወጣቶች መስጠት ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ የማዕድን ዘርፍ ልማትን በተመለከተ ከተቀመጡ መሠረታዊ አቅጣጫዎች ወስጥ አንዱ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር በሚያስልች ሁኔታ ዘርፉ ሊለማ ይገባል የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህንን የዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ደግሞ እሴት የማይጨምሩ ጥሬ የማዕድን ምርት እያወጡ ለገበያ በማቅረብ ከገቡት ውል ውጪ ንፋስ አመጣሽ ትርፍ የሚያጋብሱ አንዳንድ ‹‹ባለሀብቶች›› እንዳይኖሩ ማድረግ እየመረረም ቢሆን ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ለወጣቶች የሥራ ዕድል መንግሥት ማመቻቸቱን በተመለከተ የሚቀርቡ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች አሉ፡፡ የመጀመርያው ወጣቱን ኃይል በተለይም ሥራ አጦች የራሳቸውን የቢዝነስ ተቋም ለመመሥረትና ለመምራት የሚያስችል ልዩ ክህሎት ብቃትና ልምድ የላቸውም። ምንም ያህል ድጋፍና ማበረታቻ ቢደረግላቸው በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ለማቅረብ የሚስችል ግለሰባዊና ተቋማዊ አቅም መገንባት ይሳናቸዋል፡፡ በማለት ወጣቱን ኃይል ዝቅ አድርጎ የመመልከትና በተለያዩ መንገዶች ቢሠራም ሊለወጥ አይችልም የሚል ነው፡፡

ይሁንና በዓለማችን ከፍተኛ የሆኑ ለውጦች እንዲመጡ ያደረጉ ሰዎች በመጀመርያ ሥራ አጦች የነበሩና መንግሥት ባደረገላቸው ድጋፍ ውጤታማ የነበሩ ወይም የሆኑ ናቸው:: ይህ እንኳን ቢቀር ወጣቱን ቢዝነስ የመመሥረትና የመምራት ክህሎት፣ ብቃትና ተወዳዳሪነት እንዲያጎለብቱ ማድረግ የሚቻልበትን አግባብ ከማስቀመጥ ይልቅ ወጣቱ ሥራ አጥ የመሆኑ ዕጣ ፋንታው ይመስል ሊለወጥ አይችልም ማለት ጤነኝነት አይደለም፡፡ እዚህ ላይ በጣም የሚገርመው (Ironic) ወጣቱ የሥራ ዕድል አላገኝም፣ ለመብቱ መታገል አለበት እያሉ ወጣቱን ለማይገባ እንቅስቃሴ የዳረጉ ሰዎች ወጣቱ የሥራ ዕደል ካገኘ አብዛኛው ጥያቄዎቹ መልስ ያገኛሉ፣ ይህ ከሆነ ደግሞ ወጣቱን ለማይገባ ነገር በመዳረግ በመጨረሻ የሚንቁት ወጣት ላይ ለመንገሥ ያላቸው ጥማት የማይሳካ በመሆኑ በዚህ ሥሌት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛው ለወጣቶች መንግሥት በዚህ አግባብ ድጋፎችን አድርጎ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ሳይደክሙ ሳይለፉ ማትረፍ እንደሚቻል የማይገባ መልዕክት ያስተላልፋል የሚል ነው፡፡ በእርግጥ በዚህ አገር ላይ ልማታዊ በሆነ መንገድ ለፍቶ ያተረፈው ምን ያህል እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የክልል መንግሥታቱ ገንዘብ ብቻ ለወጣቱ ሰጥተው የቁጥጥር ሥርዓት ሳያበጁ የሚተው ከሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን ይሆናል፡፡ ስለሆነም መንግሥት ለወጣቱ እርሾ የሚሆን ገንዘብ ሰጥቶ በዚህ አግባብ እንዲጠናከሩ ማድረግ ግን አስፈላጊ መሆኑ ለሐሳብ አቅራቢዎቹም ቢሆን የራቀ አይመስለኝም፡፡ 

በነገራችን ላይ ወጣቶች ተነሱ በሚል መንግሥት የሚወስደው ውሳኔ ወጣቶቹን ለማስደስትና የማይፈለግ ‹ፖፑሊስት› ለመሆን ሳይሆን ይህን ማድረግ ካልቻል እንደ አገር መቀጠል አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ በእርግጥም የወጣቶችን የሥራ አጥነት ጥያቄ ከመመለስ ውጪ እንደ አማራጭ ሊወሰድ የሚችል ጊዜ የሚሰጥ ሌላ አማራጭ ካለ ቢቀርብ የሚመረጥ ይሆናል፡፡ በተለይም በየዓመቱ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ የሚገኘውን የወጣት ኃይል የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥራዎች መከናወን አለባቸው፡፡ በከተማም ይሁን በገጠር የሚገኙ ወጣቶች በሥራ ላይ የማይሰማሩ ከሆነ፣ ያለው አሉታዊ ውጤት አንድም ወጣቶች በራሳቸው ደስተኛ እንዳይሆኑ ማድረግ፣ ወደፊት በቀጣይነት ተቀጥረው የሚሠሩበት ዕድል ማጣበብ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትና ግንኙነታቸው ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ በዚህም ምክንያት ሥራ አጥ በሆነው የወጣት ኃይልና በባለሀብቱ መካከል ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዳይኖር በማድረግ የግል ባለሀብት የሆኑ ድርጅቶች ለማይገባ ችግር እንዲጋለጡ መንገድ የሚከፍት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ማኅበረሰቡ ወጣቶች በትምህርትም ሆነ በሌላ በኩል አሁን ያሉበት ደረጃ እንዲደርሱ በተለያየ መልኩ ወጪ አውጥተውባቸዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ያላቸውን ዕውቅት፣ ትምህርት በመጠቀም ለማኅበረሰቡና በአጠቃላይ ለአገራቸው የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እንዲያስችላቸው የሥራ ዕድል አያገኙም ማለት በራሱ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ኪሳራዎችን የሚያስከትል ነው፡፡ ስለሆነም ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ፣ መንግሥትም የግሉ ባለሀብትም ትኩረት ሰጥተው የጋራ አጀንዳ አድርገው ሊሠሩት የሚገባ ሥራ እንደሆነ መወሰድ አለበት፡፡

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅተ የግሉ ባለሀብት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ማኅበረሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶችና አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ አማራጮችን በማብዛት የማያቀርብበት፤ እንዲሁም አገራችን እንደ አገር በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውድድር ውስጥ ጎልቶ እንድታይ ማድረግ ላይ እጥረቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን እጥረቶች በበቂ ደረጃ ለመፍታት ኢንዱስትሪዎች ወይም ፋብሪካዎች መኖራቸው በጣም አስፈላጊ በመሆኑ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ፣ በተለይም የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማረጋገጥ ያለው ጠቀሜታ ተተኪ የሚገኝለት አይደለም፡፡

በመጨረሻም የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን በመጠቀምና የተጣለባቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነትና በሕዝቡ የተሰጣቸውን የመጨረሻ ዕድል ለመወጣት የክልላቸውን ነዋሪ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀማመሩ ሥራዎችን የራሳቸው እጥረቶች ሊኖራቸው ቢችልም፣ ማንኛውም ሥራ ከእጥረት የፀዳ ባለመሆኑ የሚያመጡትን አዎንታዊ ጥቅሞች በበቂ ደረጃ ባለመረዳት ወይም መረዳት ባለመፈለግ የሚቀርቡ ሐሳቦች ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ክልሎቹ የጀማመሩዋቸው ሥራዎች የራሳቸው ጽንሰ ሐሳባዊ መሠረት ያላቸው፣ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን በመወጣት ላይ የተመረኮዙ፣ የገበያ መር የመንግሥት ፖሊሲን የማይጋፉ፣ በመንግሥት የተለያዩ ሰነዶች ውስጥ በተለያየ መንገድ የተገለጹ፣ አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በተግባር ያለባቸውና ውጤታቸውም በተግባር እየታየ የሚሄድበት ሁኔታ በመኖሩ፣ የሚነሱ ሐሳቦችንና ከሐሳቦቹ ጀርባ የማን ፍላጎት እንዳለ በማወቅ አቋም መያዝ ተገቢ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...