Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበዓል ሲመጣ ይብስ የሚያሳስቡ አንዳንድ ነገሮች

በዓል ሲመጣ ይብስ የሚያሳስቡ አንዳንድ ነገሮች

ቀን:

ኢትዮጵያ ከሞታከብራቸው የሕዝብ በዓላት መካከል አንዱ ትንሳዔ ነው፡፡ ትንሳዔ በክርስትና ካሌንደር ውስጥ፣ በክርስትና እምነት ውስጥ ታላቅ ቀን ነው፡፡ እየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ከሙታን ተለይቶ ከመቃብር የተነሳበት ዕለት ነው፡፡

ከካሌንደር አንፃር ትንሳዔን ከሌሎች የሕዝብ በዓላት ለየት የሚያደርገው ሁል ጊዜም እሑድ መዋሉ ነው፡፡ ትንሳዔ እሑድ ላይ ብቻ መዋሉ ለምዕራቡም፣ ለምሥራቁም (ኦርቶዶክስ) የክርስትና እምነት ተከታዮች ለሁሉም እውነት ነው፡፡ ለምዕራባውያን አብያተ ክርስትያናት ትንሳዔ በማርች 22 እና በአፕሪል 25 መካከል፣ በምሥራቅ ደግሞ በአፕሪል 4 እና በሜይ 8 መካከል ባለ እሑድ ላይ ይከበራል፡፡ አንዳንዴም የምዕራባውያን ትንሳዔና የኦርቶዶክስ ትንሳዔ መግጠማቸው እውነት ነው፡፡

ለማንኛውም ግን ትንሳዔ ከኢትዮጵያ የሕዝብ በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡ የሕዝብ በዓላት ሲወርድ ሲዋረድ በመጣውና አሁንም ባለው የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሕዝብ በዓላት ሕግ መሠረት በሕግ ተለይተው የተወሰኑት፣ ‹‹በየዓመቱ እንዲከበሩ የሕዝብ መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የሥራ ክፍሎችና በመንግሥት ያሉት ባንኮች ሁሉ›› የሚዘጉበት ቀናት ናቸው፡፡ የሕዝብ በዓላት፣ ‹‹በእረፍትና በሰላም ተከብረው እንዲውሉ›› የተወሰኑ ናቸው፡፡ በእነዚህ ‹‹በሕግ በታወቁት የሕዝብ በዓላት ቀናት ማንኛውም ሰው ለሕይወቱ ወይም ለሕዝብ አገልግሎት በጣም አስፈላጊ ከሆነ ሥራ በቀር፣ የትርፍ ጥቅም የሚያመጣለትን ማናቸውንም ተግባረ ዕድ ወይም የሙያ ሥራ መሥራት›› የተከለከለ ነው፡፡ ይኼን የሚከለክለው ሕግ ‹‹ለሕይወት ወይም ለሕዝብ አገልግሎት በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ›› ማለትን በዝርዝር ይወስናል፡፡

አሁን በሥራ ላይ ያለው የሕዝብ በዓላትንና የእረፍት ቀንን የሚገዛው ሕግ በ1967 ዓ.ም. የወጣውና በ1988 ዓ.ም. ብቻ የተሻሻለው ነው፡፡ እሱም በሕዝብ በዓላትና በእረፍት ቀናት ያልተከለከሉ ሥራዎች ተብለው ከተዘረዘሩት የሥራ ዓይነቶች በቀር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የግል ድርጅቶችና የንግድ ሱቆች ለሕዝብ አገልግሎት ዝግ ይሆናሉ ሲል ይደነግጋል፡፡ ስለሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀናት የተወሰነውን የጣሰ ማንኛውም ሰው ጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥበት በወንጀል ሕግ መሠረት ይቀጣልም ይላል፡፡

የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ ‹‹የግዴታ እንዲከበሩ በሕግ የተወሰኑትን የበዓላት አከባበር ስለመጠበቅ የወጣውን ሕግ የጣሰ›› በመቀጮ ወይም ከስምንት ቀናት በማይበልጥ የማረፊያ ቤት እስራት ይቀጣል የሚለው፣ የ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተካው ከኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ወዲህ የወጣው ሕግ ነው፡፡

የዘመናዊት ኢትዮጵያ የሕዝብ በዓላት ከ14 በልጠው አያውቁም፡፡ ከ1967 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮና ዛሬ 13 ናቸው፡፡ እሑድ በየሳምንቱ በሕግ የሕዝብ የእረፍት ቀን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የሕዝብ በዓላት ዛሬ 13 ናቸው ስንል ሁልጊዜም የሕዝብ የእረፍት ቀን ሆኖ በሚከበረው እሑድ ላይ የሚውለውን ትንሳዔን ጨምሮ ነው፡፡

ሁሌም በዓል በመጣ ቁጥር ከሚያሳስቡኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ የበዓልና የእረፍት ቀናት የመጠበቅ ሕግ አፈጻጸምና የደረሰበት የዕድገት ደረጃ ነው፡፡ መልሶ ለማስታወስ ያህል ኢትዮጵያ በሕግ ተዘርዝረው የተነገሩ 13 የሕዝብ በዓላት አሏት፡፡ እሑድ በየሳምንቱ ደግሞ የእረፍት ቀን ነው፡፡ እነዚህ የሕዝብ በዓላት እሑድ ‹‹በእረፍትና በሰላም ተከብረው እንዲውሉ›› የተወሰኑ ናቸው፡፡ በ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ ቋንቋም ‹‹የግዴታ እንዲከበሩ በሕግ የተወሰኑ›› ቀናት ናቸው፡፡ ይኼ የአዲሱ የወንጀል ሕግ ቋንቋ የ1949 ዓ.ም. ሕግ ቋንቋ ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት በሕጉ በግልጽ ያልተከለከሉ ሥራዎች ተብለው ከተዘረዘሩት በቀር ሥራ መሥራት ያስቀጣል፡፡ በ1949 ዓ.ም. የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የተፈጻሚነት ዘመን በተለይም በንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ በበዓል ወይም በዕለተ እሑድ ሱቅ በመክፈቱ፣ ሲሠራ በመገኘቱ፣ ወዘተ እየተባለ ሲያዝና ሲቀጣ ማየት የተለመደ ነበር፡፡ ይህ በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በጭራሽ ተለወጠ፡፡ ለውጡ የአሠራርና የተግባር እንጂ የሕግ አይደለም፡፡ ሕጉ አሁንም ያለውና እንዲያውም ያለምንም ለውጥ ማሻሻል፣ ያለምንም ጥያቄና ማሰላሰል እንዳለ ምንም ነገር እንዳልተለወጠ እንዲቀጥል የተደረገው ነው፡፡

የዛሬ የደንብ ማስከበር እንዲህ ያለ የደንብ መተላለፍ ነገር ያለ ስለመሆኑ በጭራሽ አልደረሰበትም፡፡ ዛሬ የሰፈነው በረዥም ጊዜ ውስጥ የተገነባው የሕዝብ ንቃትና ማኅበራዊ ግንዛቤ ከሞላ ጎደል የ1996 ዓ.ም. የወንጀል ሕግ በተግባር ያሻሻለው፣ ያናጋውና ከዚያም በላይ የለወጠው ይመስላል፡፡ ወደኋላ የቀረው፣ በዚህ ሁሉ ዘመን ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ የተፈጠረውን ለውጥ በሕግ አወጣጥ ሥርዓቱ ውስጥ ማካተትና ማንፀባረቅ ያቃተው ሕግ አውጭው፣ ለሕግ አውጭው ሕግ አንቅቶ የሚያቀርበው ሕግ አስፈጻሚው ነው፡፡

ኢሕአዴግ አብዮት አደባባይን በቀድሞ ስሙ መስቀል አደባባይ ብሎ ለመሰየም፣ መስከረም ሁለትን ለመሰረዝና ግንቦት 20ን በየዓመቱ የሚከበር የሕዝብ በዓል ለማድረግ፣ የደቡብ አዲስ አበባን አንደኛውን መንገድ የግንቦት 20 መንገድ ብሎ ለመሰየም ጭራሽ ጊዜ አልወሰደበትም ነበር፡፡ ይኼ የተደረገው በጊዜያዊው የኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት ማለትም ደርግ በወደቀ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ውስጥ ነው፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ግን ግንቦት 20ን በሕግ የሕዝብ በዓል ያደረገ መስከረም 2 የሰረዘ ሕግ የለንም፡፡ የድል ቀን መጋቢት 28 ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደ ቀድሞው ወደ ሚያዝያ 7 ቀን የተመለሰው የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 16/1967ን በአሻሻለው አዋጅ ቁጥር 29/88 ነበር፡፡ እስከዚያም ድረስ ሆነ ከዚያም በኋላ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት፣ የእሱም የሕግ አማካሪዎች ይኼንን ጉዳይ ሥራዬ ብለው ማስተካከልን ተጠይፈው ወይም ከቁም ነገር መቁጠር አቅቷቸው፣ እነሆ ዛሬም ከ26 ዓመታት በኋላ ግንቦት 20 ይፋ ስያሜ የለውም፡፡

የሕዝብ በዓላት፣ በተለይም በሃይማኖት መሠረት የሚከበሩት የሕዝብ በዓላት፣ በመጡ ቁጥር ይበልጥ የሚያስደነግጠው፣ የሚያስፈራራውና የሚያሳፍረው ድኅነታችን ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ፣ የገበያው መልቲነት፣ በታላላቅ በዓላት እንኳን ሥጋ መብላትን የጥቂቶች አድርጎታል፡፡ ዘይት ከደሃ ጓዳ ወጥቷል፡፡ ሽሮና በርበሬ የተቀዳጁት የዋጋ ከፍታ በሽሮ መብላትንና በበርበሬ ማርመድን የድህነት ምልክት እንኳን እንዳይሆን ከልክሎናል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የንግድ ባንኮች እርስ በርስ እየተፋለጡ፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ የገቡበት የውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ውድድርና የማስታወቂያ ይዘት የድህነታችን የተረጋገጠ የምስክር ወረቀት ነው፡፡ ከንግድ ባንኮች ሥራ መካከል አንዱ ገንዘብ ማስተላለፍ ነው፡፡ ገንዘብ ለሚልክ፣ ገንዘብ ለሚቀበል አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ የሐዋላ አገልግሎት ይባላል፡፡ የአገሪቱ ንግድ ባንኮች የሐዋላ አገልግሎት ግን ባለአንድ አቅጣጫ መንገድ ነው፡፡ ከአገር ወደ ውጭ አይወጣም፡፡ ያለውም፣ የተረፈውም ቢሆን አይችልም፡፡ እሱ ሀብታም ቢሆን አገሪቷ ደሃ ናት፡፡ የኢትዮጵያ የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት ከውጭ ወደ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይኼንንም በዓል በመጣ ቁጥር እንደ ጎርፍ የሚያጥለቀልቁን የንግድ ባንክ ማስታወቂያዎች ሳይደብቁና ሳያድበሰበሱ እቅጩን ይነግሩናል፡፡ በድራማ በጭውውት መልክ ጉዳችንን፣ ገመናችንን አደባባይ አውጥተው ያሳጡብናል፡፡ ተቀባዮች እንጂ ሰጪዎች፣ ከጃዮች እንጂ ለጋሶች አለመሆናችንን መልሰው መላልሰው ይነግሩናል፡፡ የሰው እጅ የማየት ክፉ ጉዳችንን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአገር አቅም ጭምር ያሳጡብናል፡፡ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ምንጭ ይልቅ በርካታውን የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው (አራት ቢሊዮን ዶላር ያህል) በዚህ ዘዴ መሆኑም ተደጋግሞ የሚነገረን ሀቅ ነው፡፡

የዘንድሮው የባንኮች የሞት ሽረትና የውድድር ግብግብ ደግሞ እስከ መኪና፣ የመኖሪያ ቤት ድረስ ከፍ ያለ በዕጣ የሚወሰን ሽልማት የቀረበበት በመሆኑ ከአገሪቱ የምንዛሪ ተመን አሠራር ጋር ይጋጫል፡፡ የገንዘብ ምንዛሪውን ተመን ያዛባል እስከ ማለት የደረሰ ሌላ ክስና ቅሬታ ሁሉ አቅርቧል፡፡

እንዲያም ሆኖ የወዳጅ ዘመድ እጅ እያየን እየለመንንና መከራ ዓይተን የሚሰበሰብ የውጭ ምንዛሪ በመንግሥት ባካናነትና በውጭ ዕቃ አምላኪነታችን መልሰን እንከሰክሰዋለን፡፡ የአገሪቱ የውጭ ንግድ ከጉድለት አልወጣም፡፡ በዚያም ላይ ወደ በለፀጉ አገሮች ምርትን በመላክ ላይ የተንጠለጠለ ኢኮኖሚ በዓለም ገበያ ላይ በሚደርስ ቀውስና ሁሉም በሚሮጥበት የገበያ ሽሚያ እንዲሁም በማዕቀብ ለመመታት የተጋለጠ ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግሉ በኩል ያለው አባካኝና አጥፊ አኗኗር አሁንም አልተገታም፡፡

አካሄዳችን ሁሉ የፈረንጅ ዓይነት ሕይወትና አኗኗር አምሮት የመቅዳትና የማባባስ ለውጭ ገበያ የማዘጋጀት ሚና አላቸው፡፡ ዛሬ ከውጭ የማናስገባው ዓይነት የለም፡፡ አልጋና ሶፋ ሳይቀር ከውጭ ይገባል፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚያደርቅ ሥራውም በየአቅጣጨው የተጧጧፈ ነው፡፡

ዶላርን ከጥቁር ገበያ በመግዛትም ሆነ ከውጭ ወደ ውስጥ ሊገባ የሚችለውን ከርቀት የሚያስቀሩ በርካታ አሠራሮች አሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የመግዣ ዋጋ መወደድ፣ የብር ዋጋ መውደቅ፣ የዕቃዎች ዋጋ መጋሸብ ሁሉም የሚከስርበት የአገር ውድቀት ሆናል፡፡

ከግለሰብ ዲኤስቲቪ ጀምሮ እስከ መንግሥት ሚዲያ የሳተላይት ኪራይ ወጪ ድረስ የሚከፈለው ቡና ሸጠን፣ ከዘመድ ከወዳጅ እርጥባን ተቀብለን ከምናገኘው የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ኤልሲ እየተከፈተ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ደግሞ የብሔራዊ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ብቻ ሳይሆኑ የክልል አቻ ተቋማት ጭምር ናቸው፡፡ በዓላት ሲመጡ እነዚህ ተጋግዘው የሚያስታውሱን አገራችን የግብዝነትና የብክነት አገር መሆኗን ነው፡፡

የሕዝብ በዓላት በመጡ ቁጥር (ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በዓመት 13 ጊዜ ይመጣሉ) በተለይም የትንሳዔ በዓል ሲመጣ የሚነሳው ብዙም ገፍቶ ያልሄደ፣ አግባብ ያለው ምላሽ ያላገኘም ጥያቄ የድርብ በዓላት ውጤት ምንድነው የሚለው ነው፡፡ ጥያቄው ሲፍታታ አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ተደርቦ ወይም በእረፍት ቀን ላይ ቢውል ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለው ነው፡፡ እኛ አገር ያው በካሌንደሩና በዕጣ ፋንታ (በዕድል) አዝኖ ድርብ ድርብርብ በዓሉን ‹‹ማጣጣም›› ብቻ ነው፡፡

በሕግ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሠራተኛ ሕግ ብቻ ይመስለኛል፡፡ አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ተደርቦ ወይም በዚህ የሠራተኛ አዋጅ ወይም በማናቸውም ልዩ ሕግ በተወሰነ የእረፍት ቀን ላይ ቢውል፣ በዚህ ቀን የሠራ ሠራተኛ ክፍያ የሚደረግለት በአንዱ የሕዝብ በዓል ብቻ ይሆናል ይላል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ ይኼን የሚወስነው የሕዝብ በዓላት ደመወዝ የሚከፈልባቸው በመሆኑ፣ በወር ደመወዝ የሚከፈለው ሠራተኛ በሕዝብ በዓላት ባለመሥራቱ ምክንያት ከደመወዙ የማይቀነስበት ስለሆነ፣ በሕዝብ በዓል ቀን ሠራተኛው ከሠራ መደበኛው ክፍያ በሁለት ጊዜ ተባዝቶ የሚከፈለው በመሆኑና አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ተደርቦ ቢውል በዚህ ቀን የሠራ ሠራተኛ ክፍያ የሚደረግለት በአንዱ የሕዝብ በዓል ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

የትንሳዔ በዓል ሁሌም እሑድ ላይ ስለሚውል በሕግ የእረፍት ቀን በሆነ ቀን ላይ የሚውል ድርብ በዓል ነው፡፡ ይኼ የሠራተኛ ሕግ መልስ የሚሰጠው በበዓሉ ቀን ሥራ የሠራ ሰው ስለሚከፈለው ክፍያና ክፍያውም የአንድ የሕዝብ በዓል ብቻ መሆኑን ነው፡፡

አሜሪካኖች ከ1971 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በፀና ሕግ ብዙዎቹን በዓሎች ሰኞ ላይ እንዲውሉ አድርገዋቸዋል፡፡ የዚህ ምክንያት የፌዴራል ሠራተኞች የሦስት ቀናት ተከታታይ እረፍት በሳምንቱ መጨረሻ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው፡፡ ይኼን የሰኞ እረፍት ዛሬ ግዛቶች የየራሳቸው ሕግ አድርገውታል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኤምባሲና የዓለም አቀፍ ድርጅት ሠራተኞች በበዓል ወይም በሳምንት እረፍት ቀን ላይ ተደርቦ በሚውል በዓል ምትክ የሚለጥቀውን ቀን ጨምረው የእረፍት ቀን ሲያደርጉ እናያለን፡፡

የተለያዩ አገሮች የሕዝብ በዓላት ሕጎችም ተመሳሳይ መላ ያበጃሉ፡፡ ለምሳሌ የታወቀው አሠራር የሕዝብ በዓላትን ከነሚውሉበት ዕለት በዝርዝር ይወስናሉ፡፡ የዘመን መለወጫ ቀን መስከረም አንድ፣ የመስቀል በዓል መስከረም 17፣ የዓድዋ ጦርነት ድል መታሰቢያ የካቲት 23፣ ወዘተ እያሉ ይዘረዝራሉ፡፡ ቀጥለውም ከእነዚህ የሕዝብ በዓላት መካከል የትኛውም እሑድ ላይ ቢውል የሚቀጥለው ሰኞ በእሑድ ምትክ የሕዝብ በዓል ሆኖ ይውላል ብለው የሚደነግጉም አገሮች አሉ፡፡

ትንሳዔ ሁል ጊዜም እሑድ እንደሚውል ይታወቃል፡፡ ከ13 የሕዝብ በዓላት መካከል ምናልባት ከተወሰኑት በስተቀር (እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ ማዕዶት ጭምር) እሑድ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ ኢዶች ከሌላ በዓል ጋር ሊገጣጠሙ የሚችሉ ናቸው፡፡ ወይም በግልባጩ ለመናገር ኢድ አልፈጥር፣ አረፋና መውሊድ በሚውሉበት ቀን ሌሎች በዓላትም ተደርበው ሊውሉ ይችላሉ፡፡

አንድ በዓል ከሌላ በዓል ጋር ከተደረበ ወይም በሳምንቱ የእረፍት ቀን ላይ ከዋለ፣ ሌላ ተጨማሪ ቀን የሕዝብ በዓል ይሁን ብሎ መጠየቅ ይቻላል?

አሁን በሥራ ላይ ያለው የ1967 ዓ.ም. የሕዝብ በዓላትና የእረፍት ቀናት ሕግ የወጣው፣ ከሌሎች መካከል ‹‹ሕዝቡ ጊዜውን በተንዛዛ የእረፍት ቀናት ሳያሳልፍ በሥራ ተጠቃሚነት በበለጠ እንዲያምን ማድረግ ተገቢ መሆኑን በመገንዘብ›› ጭምር ነው፡፡ ዛሬስ እንዲህ ማለት ይቻላል?

በዓል በመጣ ቁጥር የሚቆረቁር፣ የሚያቃጥል፣ የሚያንገበግብ ነገር ያለበት ሌላ ጉዳይ አለ፡፡ የጋዜጣ አሳታሚዎችና የማተሚያ ቤቶች ግንኙነት ነው፡፡ አሉ የሚባሉ ጋዜጦችን የሚያሳትሙ አሳታሚዎች የራሳቸው ማተሚያ ቤት የላቸውም፡፡ ጉዳዩ ለ25 ዓመታት በቀጠለበት ሁኔታ በተለይም እንዲህ ያለ በዓል በመጣ ቁጥር የጋዜጣውን ማተሚያ ቤት የመግቢያ ቀን የሚወስነው (አንዳንዴም የጋዜጣውን የገጽ የኅትመት ብዛት ጭምር) ማተሚያ ቤቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ይህ ጋዜጣ የግድ ከዓርብ በፊት መግባት አለበት፡፡ ዓርብ ዕለት ድረስ መቆየት ቢፈልግ ተጨማሪ የማሳተሚያ ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ ምክንያቱም ማተሚያ ቤቱ በሕዝብ በዓል ለሚሠራ ሠራተኛ ተጨማሪ ክፍያ ስለሚከፍል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ዓርብ በስቅለት ዕለት ለሚሠሩ ሠራተኞች በሕጉ መሠረት እጥፍ ይከፍላል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በሕዝብ በዓላት ቀን ለሚደረግ በረራ ተጨማሪ አያስከፍልም፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...