Saturday, October 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ልዩ ዕውቅና ሰጠ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ልዩ ዕውቅና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

  ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በተከፈተው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዓመታዊ ሲምፖዚየም፣ የድርጅቱ ልዩ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሥልጠና ፕሮግራም (Trainer Plus) የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋምን በሙሉ አባልነት መቀበሉን አስታውቋል፡፡ ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ፉንግ ሊዩ ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው የሙሉ አባልነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬቱን ሰጥተዋል፡፡ ሌሎች 13 ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋማት፣ ኤርፖርቶችና የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

  ኮሎኔል ወሰንየለህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› የተሰኘው የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የሥልጠና ፕሮግራም ሙሉ አባል ለመሆን ለሁለት ዓመት ያህል ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ባለሥልጣኑ ባለሙያዎችን ወደ ውጭ በመላክ ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ላይ እንዲሠለጥኑ አድርጎ፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥርዓተ ትምህርት ቀርፆ በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማፀደቁን ኮሎኔል ወሰንየለህ ተናግረዋል፡፡

  የ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› ሙሉ አባል መሆኑ ባለሥልጣኑ በአቪዬሽን ዘርፍ ያለውን የሰው ኃይል ለማሳደግ እንደሚያስችለውና ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች የአቪዬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሙሉ አባል በመሆናችን በሌሎች አገሮች የተዘጋጁና በዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የፀደቁ 100 ያህል የሥልጠና መርሐ ግብሮች ወስደን መጠቀም እንችላለን፡፡ ከሌሎች ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናትና የአቪዬሽን ማሠልጠኛ ተቋማት ልምድ መቅሰም እንችላለን፡፡ እኛም ለራሳችን ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና መስጠት እንችላለን፡፡ ለጎረቤቶቻችንም ሥልጠና በመስጠት ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያስችለናል፤›› ብለዋል፡፡

  ዶ/ር ሊዩ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የባለሙያዎች እጥረት መኖሩን ገልጸው፣ ለሰው ኃይል ልማትና የሙያ ሥልጠና ትልቅ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ አገሮች ያለባቸውን የአቪዬሽን ባለሙያዎች እጥረት ችግር ለመቅረፍ በሥልጠናው ዘርፍ ድርጅታቸው የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ዶ/ር ሊዩ፣ ብቁ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ለማፍራት የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል፡፡  

  ከ70 ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የማሠልጠኛ ተቋም ለአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችና ቴክኒሺያኖች ሥልጠና የሚሰጥ ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጂቡቲና የሶማሊላንድ ባለሙያዎችን ማሠልጠን ጀምሯል፡፡

  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪዬሽን አካዳሚ ቀደም ሲል የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ‹‹ትሬይነር ፕላስ›› አባል ሆኗል፡፡ የአቪዬሽን አካዳሚው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ደበበ እንደተናገሩት፣ አየር መንገዱ ከአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ ገንብቷል፡፡ አየር መንገዱ ላለፉት 50 ዓመታት ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ባለሙያዎች ሥልጠና ሲሰጥ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የአቪዬሽን አካዳሚውን በማስፋፋት አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ መገንባቱን አስረድተዋል፡፡

  ‹‹በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ4,000 በላይ ባለሙያዎችን የማሠልጠን አቅም አለን፡፡ ከ1,000 በላይ የተለያዩ የአቪዬሽን ባለሙያዎች በማሠልጠን ላይ እንገኛለን፡፡ የገነባነው የማሠልጠን አቅም ከራሳችን አልፈን የሌሎች የአፍሪካ አገሮችን የአቪዬሽን ባለሙያዎች ማሠልጠን የሚያስችለን ነው፤›› ብለዋል፡፡

  የዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ዓመታዊ ሲምፖዚየም በአፍሪካ ሲዘጋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፣ አስተናጋጁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው፡፡ ጉባዔውን የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ከፍተዋል፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን የአቪዬሽን አካዳሚና የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል እንደሚጎበኙና በዚሁ ወቅት አየር መንገዱ ያስገነባቸውን ሦስት አዲስ የአውሮፕላን ጥገና ሃንጋሮች እንደሚያስመርቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

  የተመድ አካል የሆነው ዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1944 ቺጋጎ አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከ52 መሥራች አገሮች አንዷ ናት፡፡ ድርጅቱ ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪን የሚቆጣጠር ነው፡፡ 

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች