Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው!

    የሕግ የበላይነት በተግባር የሚረጋገጠው የመንግሥትን ሥልጣን ከጨበጡ ጀምሮ ዜጎች በሙሉ ከሕግ በታች ሲሆኑና በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው ሲታመን ነው፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ግን ጥቂቶች ኃይለኛ፣ ብዙኃኑ ደግሞ የጥቂቶቹ ሰለባ ይሆኑና ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል፡፡ በተለይ አገር የሚመራ መንግሥት ባለሥልጣናቱም ሆኑ የበታቾቻቸው ድርጊቶቻቸው በሕግ ካልተገደቡና ተጠያቂነት ከሌለባቸው ቀውስ ይፈጠራል፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ይጣሳሉ፡፡ የአገር ሀብት የጥቂቶች መፈንጫ ይሆናል፡፡ ኃይለኞች ደካሞችን ያጠቃሉ፡፡ ፍትሕን ይደረምሳሉ፡፡ ሥልጣናቸው ተጠያቂነት ስለሌለበት ብቻ እንዳሻቸው እየሆኑ የዜጎችን ሕይወት ያቃውሳሉ፡፡ በአገር አንድነትና ህልውና ላይ አደጋ ይጋብዛሉ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት መኖር የሚገባቸው በሕግ የበላይነት ሥር በሰላምና በፍትሕ ለመኖር ነው፡፡ በዜጎች መካከል እኩልነት ለማስፈን ነው፡፡ ዘለቄታዊነት ያለው ሰላምና መረጋጋት በመፍጠር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መጓዝ ግን አደጋ ነው፡፡

  እንደሚታወቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12 ላይ የመንግሥት አሠራር ተጠያቂነት እንዳለበት ደንግጓል፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት ይላል፡፡ ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜ ከቦታው ማንሳት እንደሚቻልም ተደንግጓል፡፡ ስለሥልጣን አካላት አወቃቀር በአንቀጽ 50 ላይ የፌዴራሉ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት፣ የሕግ አስፈጻሚነትና የዳኝነት ሥልጣን አላቸው ይላል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን፣ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ ሕዝብ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ የክልሎችም እንደዚሁ፡፡ በአንቀጽ 54 ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመላው ሕዝብ ተወካይ መሆናቸውንና ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው አስፈጻሚው አካል ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የአገሪቱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ያስፈጽማል፡፡ ይህ የሕጎች የበላይ በሆነው ሕገ መንግሥት የተሰጠው ኃላፊነት ነው፡፡ ነገር ግን በሕጉ መሠረት እየተሠራ ነው ወይ? በርካታ ችግሮች አሉ፡፡

  በአገሪቱ ውሎና አዳር ውስጥ በግልጽ ከሚታዩትና ከዚያም ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ከነበረው አውዳሚ ግጭት በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በተሠራ የቅርብ ጊዜ ጥናት መገንዘብ የሚቻለው የችግሮችን መጠነ ሰፊ መሆን ነው፡፡ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ጥናቱን ባካሄደባቸው ክልሎችና ተቋማት በተገኙ መረጃዎች ላይ ተመሥርቶ ባካሄደው ትንተና መሠረት፣ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኘው አስፈጻሚ አካል ችግሮች እንዳሉበት ነው፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች የመንግሥት መዋቅሮችን የሚመሩ አስፈጻሚዎች የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤቶችን ተግባርና ኃላፊነትን አሳንሶ ማየት፣ ምክር ቤቶች አስፈጻሚውን የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳላቸው አለመቀበል ወይም አለመገንዘብ፣ የምክር ቤቶችን ቁጥጥርና ጫና በመፍራት እንዳይጠናከሩ መፈለግ በዋናነት ተጠቃሽ የተባሉ ችግሮች ናቸው፡፡ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ጫና ሲደርስባቸው የሕግ የበላይነት አለ ይባላል ወይ? የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች (በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች) በሕግ የተሰጣቸው ሥልጣን ሲጣስ ምን ይሠራሉ?  ሕግ አውጭው አካል በአስፈጻሚው ሲጠለፍ እንዴት አይባልም ወይ?

  ሌላው የአመለካከት ችግር የሕዝብ ተሳትፎ በሚረጋገጥባቸው አካላት ላይ እንደሚታይ ነው፡፡ በዋናነት ግን ችግሩ የሚጎላው የምክር ቤት አባላት ለራሳቸውም ሆነ ለምክር ቤቱ የሚሰጡት ግምት አናሳ እንደሆነ፣ የምክር ቤት ሥራ የሕዝብ ሥራ ነው ብሎ አስቦ አለመምጣት፣ የሕዝብ ወኪል ነኝ ብሎ አለመሥራት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ምክር ቤት ላይ ጥቅም የለም ብሎ ማሰብና ጠቅላላው ነገር የሚንቀሳቀሰው በአስፈጻሚው እንጂ በምክር ቤቱ አይደለም የሚል አስተሳሰብ መኖር ከተጠቀሱት ዋና ዋና ችግሮች መካከል የሚደመሩ ናቸው፡፡ በፌዴራል ደረጃ መንግሥትን የሚመራው አስፈጻሚ አካልን የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች ናቸው የሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 ነው፡፡ ይህ እየታወቀ ባለበት አገር ውስጥ አስፈጻሚው አካል ለምን የችግሮቹ ምሳሌ ይሆናል? አስፈጻሚው አካልም ሆነ ሕግ አውጭው በሕግ የተቀመጠላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ካልቻሉ የሕዝብ ዋስትና ምንድነው? ሌላው የሚያሳዝነው ተግባር በጥናቱ የተመለከተው ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ምክር ቤቶች ድረስ በአስፈጻሚው አካል ያላቸው ተቀባይነትና ተደማጭነት ዝቅተኛ መሆኑ ነው፡፡ በሕዝብ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ መሻሻል የሚገባቸው አሠራሮችና ሌሎች ጉዳዮች በአስፈጻሚው ችላ ከመባላቸው በተጨማሪ፣ ምክር ቤቶች በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን መሠረት አስፈጻሚውን መምራት ሲገባቸው የመታዘዝ ችግሮች እንዳሉ ተመልክቷል፡፡ ጣልቃ ገብነቱም በሚገርም መንገድ ቀርቧል፡፡ ይህንን ምን ይሉታል?

  የሕግ የበላይነት ሲባል እኮ ከሕግ በታች ሆኖ መሥራት እንጂ እንዳሻ ሕግን እየደፈጠጡ መቀጠል አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ለራስ የሚመች ሕግ እያወጡ መግዛት አይደለም፡፡ ዋናውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጨምሮ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳቃታቸው ነው ጥናቱ ያቀረበው፡፡ ሌላው ቀርቶ አስፈጻሚው አካል ላይ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቋሚ ኮሚቴዎችን ማጉላላት፣ ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን፣ በቀጠሮ አለመገኘት፣ ጠንከር ያለ ሐሳብ ብቻ ሳይሆን ለቁጥጥርና ለክትትል የሚወጡ ቋሚ ኮሚቴዎችን የማሸማቀቅ ችግሮች ይታያሉ ተብሏል፡፡ ይህም ከአስፈጻሚው አካል የሚደርስ ተፅዕኖ መገለጫ መሆኑ ተወስቷል፡፡ የሥልጣን የመጨረሻ አካል ነው የሚባለውን ሕዝብ በመወከል በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው ምክር ቤቶች በአስፈጻሚው ተፅዕኖ ሥር ከወደቁ ሌላው ምን ሊሆን ነው? ይህ የአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ በሙያ ማኅበራት፣ በብዙኃን ማኅበራትና በሚዲያው ላይ ጭምር በስፋት እንደሚታይና እነዚህን አካላት እንደ አጋዥ ኃይል ያለማየት ችግር እንዳለ በስፋት ተተንትኗል፡፡ በአጠቃላይ አስፈጻሚው አካል ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት የሌበት አሠራር በማስፈን የችግሮች ዋና ባለቤት ሆኗል፡፡  የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልም ይህንኑ ነው ያፀናው፡፡ የሚሞግቱ ሐሳቦችን የሚያቀርቡና ብልሹ አሠራሮችን የሚታገሉ ግለሰቦች ላይ አስፈጻሚው አካል የማስፈራራት፣ የማሸማቀቅ፣ የመፈረጅና የመሳሰሉት ኢዴሞክራሲያዊ ድርጊቶች ይፈጸምባቸዋል ሲባል ያሳፍራል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ መንገዶች በዜጎች ላይ የደረሱ እንግልቶችና መከራዎች ብዙ የሚባልባቸው ናቸው፡፡

  ይህን ዓይነቱን አስከፊና ብልሹ ድርጊት አስወግዶ ለሕዝብ ፈቃድ ተገዥ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ መመኘት ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ ትግልና ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ የሕግ የበላይነት መሠረቱ በሚገባ ካልተጠናከረና ሥልጣን የያዙ ወገኖች የሕግ ገደብ ካልተደረገባቸው፣ በቅርቡ በአገሪቱ የተወሰኑ ሥፍራዎች ያጋጠመው ሁከት መጠኑ ሰፍቶ ይቀጥላል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፍላጎት ከልብ የመነጨና መስዕዋትነት ጭምር የሚከፈልበት መሆን የሚችለው፣ በቅድሚያ ሕግ እንዲከበር አርዓያ በመሆን ነው፡፡ ሕዝብ በትክክል የሥልጣን ባለቤት ሆኖ በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደርበት ሥርዓት ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ግን ያለው የአምባገነንነት መገለጫ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩት አሳሳቢ ችግሮች እንዲወገዱና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የመንግሥት ሥልጣን የሕዝብ ፈቃድ መፈጸሚያ መሆን አለበት፡፡ አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ዜጎች በምንም ሳይሆን በሕግ ብቻ ዋስትና ሊያገኙ የግድ ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ አሁን ያለው አካሄድ መሠረታዊ ለውጥ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ሥልጣን የሚያዘው በነፃና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ኢፍትሐዊ የሆኑ አሠራሮችና ድርጊቶች መቆም አለባቸው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን አለበት፡፡ ከምንም ነገር በላይ ሕዝብ መደመጥ አለበት፡፡ ሕገወጥነት መቼም ቢሆን ሊወገድ ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ግልጽነትና ተጠያቂነት ይረጋገጥ፡፡ የሕዝብ ተሳትፎና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጠው ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

  የትጥቅ  መፍታት ሒደትና የሰላም እንቅፋቶች

  የትግራይ ተራሮች ከጦር መሣሪያ ጩኸት የተገላገሉ ይመስላል፡፡ በየምሽጉ አድፍጠው...

  በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው

  ብሔራዊ ፀረ ሙስና ኮሚቴ በክልሎችም ሊቋቋም ነው በቅርቡ ተቋቁሞ ወደ...

  የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራና የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ ተቋም የመመሥረት ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ

  የኢንሹራንስ (መድን) ዘርፍን የመቆጣጠርና የመከታተል ኃላፊነት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...