Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ገበያ አዋኪዎች

ገበያ ውስጥ እንደልብ ይገኝ የነበረ ምርት ላይ የአቅርቦት ዕጥረት ሲከሰት የዋጋ ለውጥ ይከሰታል፡፡ በገበያ ውስጥ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ልዩነት ከተፈጠረ ዋጋ ላይ ለውጥ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ ችግሩ የተጋነነ ዋጋ መፈጠሩ ነው፡፡ ገበያው እንዲህ ያለውን አጋጣሚ በእልልታ ለማስተናገድ የተመቸ ነው፡፡ በአጋጣሚው መክበር የሚፈልጉ ‹‹ደፋር ነጋዴዎች›› በብዛት አሉ፡፡

ወትሮውንም የትርፍ መጠን ምን ያህል መሆን እንደሚገባው መጥኖ አገልግሎት የመስጠት ልማዱም ቅንነቱም ደብዛዛ በመሆኑ፣ ገበያው ውስጥ ዕጥረት ተከሰተ በተባለ ቁጥር ዋጋው ይቆለላል፡፡ እርግጥ ነው በዕጥረቱ ምክንያት ዋጋው መጨመሩ በሳይንሱም ቢሆን የሚገለጽ ቢሆንም፣ ችግሩ የሚጨመረው ዋጋ ዕጥረቱን በምን ያህል እንደሚገልጸው ግን አይታወቅም፡፡ ብዙውን ጊዜ ዕጥረቱ የፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ተመጣጣኝነት አይታይበትም፡፡

ይህ ክፉ አመል በብዙዎች ዘንድ ከተለመደ ቆይቷል፡፡ አንዳንዶች በአጋጣሚው ለመክበር ካደረጉት መሯሯጥ ሊጠቀስ የሚገባው፤ ገበያውን በመበረዝ ሸማቹን ካነቃነቁ አጋጣሚዎችን መካከል ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስብ ፈጽሞ ሊረሳኝ የማይችለው ጨው ጠፋ በመባሉ የተከሰተው ትርምስ ነው፡፡ በጥቂት ሳንቲሞች ልንገዛው እንችል የነበረውን ጨው አቅርቦቱ ‹‹ጠፋ›› በተባለበት ወቅት አብዛኛው ሸማች መደብሮችን ወርሮ፣ ያለልክ ሲሸምት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከአንድ ብር ባልበለጠ ገንዘብ ይሸጥ የነበረው ጨው አራት እና አምስት ብር በኪሎ ሲቸበቸብ ታዝበናል፡፡ እግርጥ ነው ገበያ በነጋዴውም በሸማቹም ወገን በሚነዛ ወሬ ወይም ሥጋት የሚነዳባቸው ክስተቶች ይፈጠራሉ፡፡ የፍላጎትና አቅርቦት ትንታኔ የሚሰጥባቸው ሳይንሳዊ ንድፈ ሐሳቦችም ይህንኑ ይደግፋሉ፡፡ ወደፊት ሊፈጠር የሚችል የዋጋ ጭማሪ ሥጋት፣ የምርት አለመኖር፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ጦርነት ሥጋት ወይም ሌሎች መሰል ሥጋቶች ሊኖሩ እንሚችሉ ሲገመት ዋጋ ይንራል፡፡

በአንፃሩ ወደፊት ምርት እንደልብ እንደሚኖር ሲታሰብ፣ ዛሬ ላይ ያለው ዋጋ ነገ እንደሚቀንስ ሲገመት እና ሌሎችም ምክንያቶች ሲኖሩ ፍላጎት ስለሚቀንስ  የምርት ዋጋ መቀነሱ አይቀርም፡፡ እንዲህ ያሉት ክስተቶች ለዋጋ ለውጥ ከሚጠቀሱ፣ በሳይንስም ከሚደገፉት ውስጥ ይመደባሉ፡፡  

ይሁንና የጨው መጥፋት በተወራ ሰሞን በተለይ አዲስ አበቤዎች እየተደዋወሉ ጨው ሊጠፋ በመሆኑ የቻሉትን ያህል እንዲሸምቱ አንዳቸው ለሌላው ሲያስጠነቅቁ፣ ላልሰማው ሲያሰሙ ተመልክተናል፡፡ በወቅቱ ግን ጨው ሊጠፋ ስለመሆኑ ወይም ስለመጥፋቱ የሚያረጋግጥ አንድም ተጨባጭ ምክንያት አልነበረም፡፡ ሸማቹም ሁኔታውን በማገናዘብ ራሱን ከማረጋጋት ይልቅ፣ ወሬውን በማራገቡ እንደ ልብ ገበያ ይወጣ የነበረውን ጨው ነጋዴዎች እንዲሸሽጉት ምክንያት ሆኗቸው ነበር፡፡ አንድ ምርትን ከገበያ ማሸሽና መሸሸግ በሕግ የተከለከለው በቅርቡ ነው፡፡ ሆን ተብሎ የሚፈጸም የምርት መደበቅ ገበያ እንደሚያዛባ ታምኖበታል፡፡

በመሆኑም አጋጣሚውን አግኝተው የከበሩበት ጥቂት አይደሉም፡፡ ክስተቱ ነጋዴውም ሸማቹንም ትዝብት ላይ የጣለ ሲሆን፣ ወሬውን የነዙት ግን አጋጣሚውን  ተጠቅመውበታል፡፡ እንደጨው አይሁን እንጂ ገበያ ውስጥ የለም በተባለ ዕቃ ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ተገቢነት የሚያጠያይቅ ሆኗል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአንድ ኪሎ ቲማቲም ዋጋ 40 ብር ድረስ ለመሸጡ እንደምክንያት የቀረበው በአንድ አምራች አካባቢ የቲማቲም ምርት በመቀነሱ ቢሆንም፣ የምርት ችግር ያልገጠማቸው የቲማቲም አቅራቢዎችና ነጋዴዎች ግን በማይመለከታቸው ሰበብ ዋጋ መጨመራቸው የቲማቲም ገበያውን በማዛባት አስቸግሮ መሰንበቱን ታዝበናል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የሚፈለገው ምርት ገበያ ላይ ባለመገኘቱ ዋጋ ሲጨምር ለምርቱ ምትክ የሚሆኑት ምርቶች ገበያው ላይ ይበራከታሉ፡፡ ቲማቲም በሌሎች ምርቶች ሊተካ  ይችላል፡፡ ወይም ከነጭራሹ ለፍጆታ ባለመጠቀም ዋጋው እንዲስተካከል ማስገደድ ይቻላል፡፡ ይህ ግን ምርቱ እያለ እጥረት መፈጠሩ ሲታወቅ ሊወሰድ የሚችል ዕርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ሊያነጋግር የሚችለው ግን እጅግ አስፈላጊና ምትክ የሌላቸው እንደ የመድኃኒት ምርቶች ያሉት ሲጠፉ ምርጫ ስለማይኖር ሸማቹ ላይ የሚደርሰው ጉዳት በቀላሉ ሊታለፍ የማይችል ይሆናል፡፡

 የመድኃኒት ምርቶች እጥረት መኖሩን የተገነዘቡ በአጋጣሚው እየተጠቀሙበት መታየታቸውን እየሰማን ነው፡፡ ከሰሞኑ የአንድ ቤተሰብ አባል የታመመችበት አባወራ፣ ከታዘዙላት መድኃኒቶች ውስጥ ሊያገኝ ያልቻላቸው በመኖራቸው በእግር በፈረስ ለማፈላለግ ተገዷል፡፡ የጠፋው መድኃኒት በመደበኛ ዋጋው የሚሸጠው 500 ብር ገደማ ሲሆን፣ በአብዛኛው መድኃኒት መደብር ውስጥ ሊገኝ አልቻለም፡፡ መድኃኒቱን ይይዛሉ ወደተባሉ መድኃኒት መደብሮች በማቅናት የተጠየቀው ዋጋ ቀድሞ ይሸጥበት ከነበረው ከአራት እጅ በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሸማች ‹‹ምነው?›› ይላል፡፡ ሻጭም የውጭ ምንዛሪ ችግር ነው ሲል ይመልሳል፡፡ አማራጭ አልነበረውም በተጠየቀው ሒሳብ ሳይወድ በግድ ይገዛል፡፡ ይህ እንግዲህ በገበያ አጋጣሚ የተገኘ የበላይነትን በመጠቀም ዋጋ የማናር ተግባር ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል ነው፡፡  

ቲማቲም ቢወደድ ቲማቲም አልባ ወጥ መብላት ይቻል ይሆናል፡፡ እንደ መድኃኒት ያሉ የሰውን ህልውና የሚወስኑ ምርቶች ግን አቅርቦታቸው ስላነሰ በሚል ሰበብ ዋጋ ቢቆለልባቸውም አቅም እስካለ ለመግዛት የሚያቅማማ አይኖርም፡፡ የተባለውን ዋጋ ከፍሎ ይገዛል፡፡ በመድኃኒት እጥረት ሰው መጉላላቱ አቅም የሌለው እንዲቀጣ የሚያደርግ ሥርዓት ቀስ በቀስ መንሰራፋቱ አሌ እየተባለ መጥቷል፡፡

መንግሥት እንዲህ ያሉ አድራጎቶችን የሚቆጣጠሩ ሥርዓቶችን ቢያበጅም፣ ሕግ ቢያወጣም ገበያውን በተገቢውን መንገድ የገበያውን ሥርዓት መምራት ያቃተው ይመስላል፡፡ አቅርቦቱ የት ቦታ ችግር እንዳለበት፣ የትኛው ምርት በምን ምክንያት ከገበያ እንደጠፋ በአግባቡ ማጥናት፣ መከታተልና ማስተካከል የተቋቋሙት መሥሪያ ቤቶችና የሚመሯቸው ኃላፊዎች ሚና ነው፡፡ ሕዝብ ይጠቁም፣ ይናገር በሚል ገልቱ ሰበብ ቸልታ ማብዛት ሕዝብን ሆድ ከማስባስ በቀር ምንም አይፈይድም፡፡

እነዚህን መሥሪያ ቤቶች የሚቆጣጠሩ፣ ኃላፊዎችን የሚሾሙ አካላትም መዝነው የሰጧቸውን በማይሠሩት ላይ፣ ከዓመት ዓመት ምክንያትና ሰበብ እየደረደሩ ሥራቸውን በሚያንፏቅቁ ላይ ውሳኔ ይስጡ፡፡ እንደውም ‹‹አልቻልኩም ልነሳ፣ ልቀየር፣ ይቅርታ እጠይቃለሁ›› በማለት ወንበር የሚለቁበት አሠራር ይፈጠር፡፡ ይህ ባህል ሲለመድ፣ ሐቀኝነት ሲስፋፋ፣ የማይገባውን ትርፍ የሚያግበሰብሰው፣ ሆን ብሎ ገበያ እያዛባ የሚሸቅጠው ሁሉ አደብ ለመግዛት ይገደዳል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት