ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በደረሰው የእሳት ቃጠሎ 23 የቀጠሮ እስረኞች መሞታቸውና በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአደጋውም ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፡፡ የቃጠሎውን መንስዔና የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከአደጋው በኋላ ምርመራ አድርጓል፡፡ የምርመራውን ሪፖርትም ረቡዕ መጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡ ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ያቀረቡትን የምርመራ ውጤትና ከቋሚ ኮሚቴው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት በምክር ቤቱ መለስተኛ መሰብሰቢያ አዳራሽ ለሦስት ሰዓታት ቆይታ አድርገዋል፡፡ ኮሚሸነሩ ያቀረቡትን ሪፖርትና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር እንደሚከተለው አሰናድቶታል፡፡
የሪፖርቱ የተጨመቀ ይዘት
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የደረሰው የእሳት አደጋ መንስዔና ያስከተለው ጉዳትን ለመመርመር በአደጋው ወቅት የነበሩ የቀጠሮ እስረኞች እማኝነትን፣ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎችን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሞት ወንጀል ምርመራ አባላትን፣ ቃጠሎውን ለማጥፋት የተንቀሳቀሱ የአዲስ አበባ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ሠራተኞችን፣ በአደጋው ለተጎዱ ሕክምና የሰጡ ተቋማት ባለሙያዎችንና የአስከሬን ምርመራ ካደረገው ቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ባለሙያዎችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በመሰብሰብ ሪፖርቱን አጠናቅሯል፡፡
የዓይን እማኝነታቸውን ከሰጡ የቀጠሮ እስረኞችና የማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው አደጋው ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ ከመቀስቀሱ አስቀድሞ በነበሩት ሁለት ቀናት፣ በማረሚያ ቤቱ የሚገኙ የቀጠሮ እስረኞች የተቃውሞ ጉርምርምታ ያሰሙ ነበር፡፡ ማረሚያ ቤቱ በተለያዩ ዞኖች የተከፋፈለ ሲሆን፣ ዞን ሦስት በሚባለው ግቢ ከሚገኙ የቀጠሮ እስረኞች መካከል በተወሰኑት ላይ የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) በሽታ በመታየቱ ምክንያት፣ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ለበሽታው መከሰት መንስዔ ነው ያለውን የእስረኞች ቤተሰቦች የሚያቀርቡት ምግብ ወደ ውስጥ እንዳይገባ ወስኗል፡፡ ውሳኔውን አስመልክቶም በማረሚያ ቤቱ በሚገኙ ማረፊያዎች ውስጥ የእስረኞች ተጠሪ የሆኑ ግለሰቦችን (እነዚህም የቀጠሮ እስረኞች ናቸው) በማወያየት የውጭ ምግብ ወደ ማረሚያ ቤቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይገባ መወሰኑንና ይህንንም ለታሳሪዎቹ እንዲያሳውቁ አድርጓል፡፡ የእስረኞቹ ተጠሪዎች ሐሙስ ዕለት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ውሳኔን በየክፍላቸው ለሚገኙ ታሳሪዎች ባሳወቁበት ወቅት ‹‹ለምን እኛን ሰብስበው አላሳወቁንም?›› በሚል የተቃውሞ ጉርምርምታ አሰምተው ነበር፡፡
የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ሐሙስ ማምሻውን ያስተላለፈውን ውሳኔ የሚገልጽ ማስታወሚያ በየማረፊያ ክፍሎቹ ግድግዳ ለጥፏል፡፡ ይህንን ውሳኔ የተቃወሙ የቀጠሮ እስረኞች ማረሚያ ቤቱ የሚያቀርበውን ምግብ ማንኛውም የቀጠሮ እስረኞች ባለመመገብ እንዲያድሙ መቀስቀስ እንደ ጀመሩና ከአንዱ ዞን ወደ ሌላኛው አድማውን አስመልክቶ የሚገልጹ ወረቀቶች በእንጀራና በድንጋይ ተጠቅልለው ይወረወሩ ነበር፡፡ ‹‹በአድማው የማይሳተፍ የወያኔ ተላላኪ ነው፤›› ይሉ እንደነበር፣ እንዲሁም ዓርብ ዕለት ጠዋት የማረሚያ ቤቱ አስተናጋጅ ሠራተኞች ቁርስ ለታራሚዎቹ ማቅረብ ሲጀምሩ አድማውን በሚያንቀሳቅሱት ታሳሪዎች መከልከላቸውን የዓይን እማኞቹ ለመርማሪዎቹ መግለጻቸውን የኮሚሽነሩ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ ቅዳሜ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ታሳሪዎች ማረሚያ ቤቱ የሰጣቸውን ዩኒፎርም እያወጡ መሰብሰባቸውንና በእሳት እንዲያያዝ ማድረጋቸውን፣ እሳቱ ሲቀጣጠልም ከየማረፊያ ክፍሉ ፍራሾች፣ ብርድ ልብሶችና ሌሎች ተቀጣጣይ ቁሶች (እንደ ዲዮደራንትና ላይተር) የመሳሰሉትን ወደ እሳቱ ይወረወሩ ነበር፡፡ የታሳሪዎች ተጠሪ የነበረ አንድ ግለሰብን አቃጣሪ ነው በማለት በፌሮ ብረት አናቱ ተመትቶ ከተገደለ በኋላ በእሳት ወደተያያዘ ክፍል መወርወሩን ከዓይን እማኞች መረዳት መቻሉን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ በአንድ ክፍል የነበሩ እስረኞች ከእሳት አደጋው ራሳቸውን ለማትረፍ እንዳይወጡ ከውጭ እንደተዘጋባቸውም ይገልጻል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ጠባቂዎች አስለቃሽ ጭሶችን ወደ ታሳሪዎቹ መተኮሳቸውን፣ እንዲሁም ሌሎች ጠባቂዎች ደግሞ ታሳሪዎቹ ወደ ሚገኙባቸው ክፍሎች ‹‹ከውጭ ወደ ውስጥ›› ይተኩሱ እንደነበር በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ ሊያመልጡ የነበሩ ሁለት እስረኞች አጥር ላይ እንዳሉ ታፋቸው ላይ ተመተው መሞታቸውን፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ተዘግቶባቸው የነበሩ 12 እስረኞች በእሳቱ ተቃጥለውና ከስለው መገኘታቸውን ኮሚሽነሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ 21 የቀጠሮ እስረኞች በጭስ ታፍነውና በእሳት ተቃጥለው መሞታቸውን፣ ሁለት ደግሞ በጥይት ተመተው በድምሩ 23 ታራሚዎች መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባደረገው ምርምራ የለያቸውን ጭብጦችም ለምክር ቤቱ ሪፖርት አድርጓል፡፡ ጭብጦቹ ለደረሰው የሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት እንዲሁም የንብረት መውደም መንስዔ ምን እንደነበርና ለደረሰው ጉዳይ ተጠያቂው ማን ሊሆን እንደሚገባ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡
የቃጠሎው መሠረታዊ መንስዔ በማረሚያ ቤቱ ሁከት እንዲቀሰቀስ አስቀድመው ይፈልጉ የነበሩ የሕግ እስረኞች አማካይነት ሆን ተብሎ አድማ መጀመሩ፣ አድማውን በማንኛውም ጊዜና ወቅት ለማነሳሳት ፍላጎት እንደነበራቸው በተደረገው ምርምራ ለመረዳት መቻሉን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይገልጻል፡፡
በተከሰተው አደጋ 21 ታሳሪዎች በጭስ ታፍነውና በእሳት ተቃጥለው ሕይወታቸው ማለፉ፣ ሁለት ታሳሪዎች ደግሞ ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት ታፋቸው ላይ ተመተው መሞታቸውን ከማረሚያ ቤቱ ባልደረቦችና ከሌሎች እማኞች ቃል፣ እንዲሁም ከሕክምና ማስረጃዎች ተረጋግጧል፡፡ ከሞቱት እስረኞች ውስጥ የሕግ እስረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉና የፀጥታውን ሁኔታ ለአስተዳደር አባላት ከሚያስታውቁት ውስጥ አንዱን የረብሻው መሪዎች ሆን ብለው ለመግደል አስበው በአልጋ ብረት መተው እሳት ወደሚነድበት ቤት እንደተጣለ፣ ሌሎች 11 እስረኞች በድምሩ 12 እስረኞች በአንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፎባቸው እንዲቃጠሉ ተደርጓል፡፡ ይህም እሳት ከማማያዝ ባለፈ በሰው ሕይወት ላይ ሊወስዱት ያቀዱት ሴራ እንደነበር ለመረዳት መቻሉን ዶ/ር አዲሱ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡
ቃጠሎው ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ጠዋት ከመከሰቱ አስቀድሞ በነበረው ቀን የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር የውጭ ምግብ ክልከላውን የሚገልጽ ማስታወቂያ ሲለጥፍ የተቃውሞ ጉርምርምታና ረብሻ የነበረ ቢሆንም፣ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ይህንን ተመልክቶ በአፋጣኝ የወሰደው የመከላከል ዕርምጃ አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በማረፊያ ቤቱ ግቢ ውስጥ የነበሩ የጥበቃ አባላት ‹‹ከውጭ ወደ ውስጥ›› በእስረኛው ላይ ጥይት ይተኩሱ የነበረ መሆኑንና በተከሰተው ጥይትም ከእስረኞቹ መካከል በስምንቱ ላይ የአካል ጉዳት መድረሱም ተረጋግጧል፡፡ የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች የተቀሰቀሰውን እሳት ለማጥፋትና ለመከላከል ያደረጉት ጥረት በማረፊያ ቤቱ የግንባታ ዲዛይን ምክንያት ወደ ውስጥ የሚገባበት መንገድ አጥተው ለማጥፋት መቸገራቸው ተረጋግጧል፡፡ የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች እስኪመጡ ድረስ ጉዳትን ለመቀነስ በማረፊያ ግቢው በተገነቡ ቤቶች ላይ የተገጠመ የእሳት መከላከያ የሌለ መሆኑም ተረጋግጧል፡፡
ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት ከአደጋው ጋር የተያያዙ ሌሎች ጭብጦችንም ለይተው አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ማረሚያ ቤቱ ከቀጠሮ እስረኞች ጋር የነበረው ግንኙነት ይገኝበታል፡፡ በወቅቱ የአተት በሽታ ምልክት የታየባቸው ታሳሪዎች ሕክምና ተደርጎላቸው የዳኑ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የታየውን የበሽታ ምልክት ተከትሎ የእስር ቤቱ አስተዳደር የውጭ ምግብ እንዳይገባ ማገዱን ታሳሪ ተጠርጣሪዎችን በመጥራት የገለጸ ቢሆንም፣ ታሳሪዎቹ በዕግዱ ላይ አስተዳደሩ እንዲያወያያቸው መጠየቃቸው እየታወቀ አስተዳደሩ እንዳላወያያቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህም በግንኙነታቸው ላይ ክፍተት እንዳለ ያሳያል፡፡ የእስር ቤቱ አስተዳደር ታሳሪዎችን በየፈርጁ የመያዝ ሕጋዊ ግዴታ በማረሚያ ቤቶች ማቋቋሚ አዋጅ 365/95 አንቀጽ 25 (2) እንዲሁም የታራሚዎች አያያዝ ደንብት ቁጥር 138/95 (5) (3) (ሐ) ላይ ታራሚዎች ወይም የሕግ እስረኞች በዕድሜያቸው፣ በፈጸሙት ወንጀል ወይም በሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 36 (3) እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታራሚዎች አያያዝ አንቀጽ ስምንት መሠረት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ወጣት አጥፊዎች ከአዋቂዎች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡ ሆኖም ግን የምርምራ ቡድኑ በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ አዋቂዎች ጋር ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት አንድ ላይ ታስረው መገኘታቸውን አረጋግጧል፡፡ አዋቂዎችም ቢሆኑ በተጠረጠሩበት ጋር ወንጀል ተለይተው መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡
ተደጋጋሚና ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ከጠረጠሩት ሁሉንም በአንድ ላይ መያዙ መጥፎ ባህሪዎችን እንዲማሩና በሚፈጠሩ አመጾች ተባባሪ እንዲሆኑ መንገድ ሊከፍት ይችላል፡፡ ይህ አለመደረጉ ክፍተት ያለበት ያደርገዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 16 መሠረት ማንኛውም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ በአደጋው ወቅት ከውስጥ ያሉ እስረኞችን ቁጣና አመፅ ለማስቆም በሚል የጥበቃ አባላቱ ከውጭ ወደ ውስጥ መሣሪያ ባልያዙ እስረኞች ላይ በመተኮስ በስምንት እስረኞች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የጥበቃ አባላቱ የከፈቱት ተኩስ የሚያደርሰው ጉዳት እየታወቀ፣ እንዲሁም ዓላማ የሌለውና ሕግን ያልተከለተ ተግባር ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከኢሰብዓዊ አያያዝ ነፃ የመሆን መብት በሕገ መንግሥቱ፣ በማረሚያ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና ደንብ መሠረት ታራሚዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጥብቆ መያዝ እንዳለባቸው ቢደነገግም፣ በአደጋው ወቅት በጥይት ተመቶ በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል በሕክምና ክትትል ላይ የሚገኝ አንድ የሕግ እስረኛ በእግሩ ላይ የታሰረለት ጀሶ እንደማያንቀሳቅሰው እየታወቀ ሊያመልጥ ይችላል በሚል እጁ ከአልጋ ጋር በካቴና ታስሮ ተገኝቷል፡፡ የሕግ ታሳሪው ለምግብና ለሽንት ካልሆነ በስተቀር እጁ ከአልጋ ጋር በካቴና ታስሮ እንዲቆይ በመደረጉ ከጀርባው ቀና እንዳይልና መገላበጥ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህ ድርጊት ሰብዓዊ ክብርን ከሚጠብቅ አያያዝ የሚቃረን ከመሆኑም በላይ በሕግ እስረኛው ጀርባ ላይ ጉዳት ማድረሱ ተረጋግጧል፡፡
ኮሚሽነሩ ሪፖርታቸውን ያጠናቀቁት ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት ነው፡፡ ከተለዩት ጭብጦች በመነሳትም ረብሻውንና ቃጠሎውን በማስነሳት እንዲሁም 12 ታሳሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ተቆልፎባቸው እንዲቃጠሉ ያደረጉት በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ ብሏል፡፡ በእስር ቤቱ ተቀጣጣይ ቁሶች እንዳይገቡ የሚከለከል ቢሆንም እንደ ላይተር፣ ዲዮደራንት፣ ሲጋራና ሐሺሽ እንደሚገባ በመረጋገጡና ቃጠሎውን ያባባሱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በመሆኑም የተከለከሉት ቁሶች ወደ ግቢው መግባታቸውን ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ የጥበቃ አባላት መኖራቸውን የሚያመለክት በመሆኑ ተጣርቶ በሕግ እንዲጠየቁ ምክረ ሐሳቡን ሰጥቷል፡፡ ቃጠሎው በተነሳበት ወቅት ከመውጣት ይልቅ ተቃውሟቸውን መግለጽ የሚፈልጉ አድመኞች እንደነበሩ የተገለጸ ቢሆንም፣ ብዛት ያላቸው ግን ከእሳቱ ለማምለጥ እየጣሩ ባሉበትና ጩኸት በሚያሰሙበት ሁኔታ አንዳንድ የጥበቃ አባላት በግዴለሽነት ከውጭ ወደ ውስጥ ተኩስ መክፈታቸውና በታሳሪዎች ላይ የአካል ጉዳት ማድረሳቸው አግባብነት የሌለው ዕርምጃ በመሆኑ፣ የሚመለከታቸው አካላት ዕርምጃ እንዲወስድ ወይም በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ በምክረ ሐሳብነት ቀርቧል፡፡
ኮሚሽነር አዲሱ ያቀረቡትን የምርምራ ውጤትና ምክረ ሐሳቦች ሪፖርት ያዳመጡት የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ ይሻሉ ያሏቸውን ጥያቄች አቅርበዋል፡፡ አባላቱ ካነሷቸው ጥያቄዎች መካከል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተከሰተው አደጋ ጋር ለተያያዙት ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር የሰጡት ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ጥያቄ፡- የእሳት አደጋ ከመነሳቱ አስቀድሞ የታራሚዎች ተቃውሞና አመፅ ሳምንት ሙሉ እንደነበረ ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ ይህንን ሁኔታ የማረሚያ ቤቱ ጥበቃና አስተዳደር የሚያውቅ ከሆነ ተቃውሞው ወደ አመፅ እንዳይሸጋገር ዋነኛ ቀስቃሾቹን በመለየት፣ የሰው ሕይወትና የንብረት ውድመት እንዳያስከትል አስቀድሞ ያልተሠራው ለምን እንደሆነ በምርመራ ወቅት የተገኘ ምክንያት ካለ ቢብራራ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ማረሚያ ቤቱ በየሳምንቱ ሳይሆን ዕለት በዕለት ታራሚዎችን ወይም የቀጠሮ እስረኞችን በመከታተል የአደጋ ምክልቶች ካሉ መፈተሽ አለበት፡፡ ቃጠሎ ብቻ አይደለም አደጋ፡፡ ወደ ቂሊንጦ አደጋ ስንመጣ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ጠቋሚ ሁኔታዎች እንደነበሩ የታሳሪዎች ተጠሪዎች ለአስተዳደር አካላት መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ያደረገው ምርመራ ያመለክታል፡፡ ሳምንት ሙሉ አመፅ ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳዩ ጉርምርምታዎች፣ ውይይቶችና ንግግሮች እንደነበሩ በምርመራ ወቅት ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ለኮሚሽኑ መርማሪዎች የገለጹት ችግሩ እዚህ ደረጃ ይደርሳል ብለው እንዳልገመቱ ነው፡፡ በእኛ ምርመራ ግን ምልክቶቹ በቂ ነበሩ፡፡ ምክንያቱም የእስረኞቹ ተጠሪዎች ይህንኑ ሁኔታ ለኃላፊዎች ገልጸው ነበር፡፡ በዚህ ላይ ተመሥርቶ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ግን አልነበሩም፡፡ በሌላ በኩል እስር ቤት ውስጥ እንዲገቡ የማይፈቀዱ ተቀጣጣይ ቁሶች ለቃጠሎው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ በሰው ሕይወት ላይ አደጋ ሊያደርሱ እንደሚችሉ የሚታሰቡ ቁሶች ወደ እስር ቤት እንዲገቡ አይደረግም፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ያለ አሠራር ነው፡፡
የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አደጋው ከመከሰቱ አስቀድሞ በነበረው ወር ውስጥ በማረሚያ ቤቱ ጉብኝት አድርጎ የታዘባቸውን ያልተገቡ ድርጊቶች ለማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች አሳውቆ ነበር፡፡ ሐሺሽ፣ ጫት፣ ክብሪትና ሲጋራ ወደ ማረሚያ ቤቱ እንደሚገባ ባገኘው መረጃ መሠረት ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡ እየገባ ያለው በሌላ በኩል አይደለም፡፡ ኃላፊነታቸውን መወጣት ባልቻሉ የጥበቃ አባላት አማካይነት በመሆኑ እንዲሁም እነሱን የመከታተል ኃላፊነት በተጣለባቸው ኃላፊዎች ቸልተኝነት የተነሳ በመሆኑ፣ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እንዲገባ የማይፈቀዱ ተቀጣጣይ ቁሶች ገብተው ነው እሳቱ የተቀጣጠለው፡፡ በላይተር ነው እሳቱ የተቀጣጠለው፡፡ ስለዚህ አመራሩ ንቁ መሆን ነበረበት፡፡ ማረሚያ ቤቱ ውስጥ የተለያዩ ባህሪ ያላቸው በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ናቸው ያሉት፡፡ ስለዚህ ማረሚያ ቤቱ በየፈርጁ ለያይቶ ነበር እስረኞችን መያዝ የነበረበት፡፡ በእርግጥ ይህንን ለማድረግ የኢኮኖሚ አቅም ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ባለው አቅምስ ጥረት ተደርጓል ወይ? ይህንን ተተግብሮ አላየንም፡፡ ተቀጣጣይ ቁሶቹን እኛ በሰጠነው አስተያየት መሠረት መሰብሰብ ችለው ቢሆን ኖሮ ጉዳቱን መቀነስ አይቻልም ነበር? ወይም በአጠቃላይ መከላከል ይቻል ነበር፡፡
ጥያቄ፡- በጥይት ተመተው የሞቱት ታሳሪዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ተመጣጣኝ ነበር ማለት ይቻላል ወይ? ሌላ አማራጭ አልነበረም?
ዶ/ር አዲሱ፡- እነዚህ እስረኞች ታፋቸው ላይ እንደተመቱ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲሁም ምርመራውን ያካሄደው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒል ይህንኑ አረጋግጧል፡፡ ታፋቸው ላይ እንደተመቱና በፈሰሳቸው ደም ምክንያት እንደ ሞቱ አረጋግጧል፡፡ ይህ ማስረጃም ከሪፖርቱ ጋር ተያይዟል፡፡ ከመሞታቸው በፊት ወደ ላይ ጥይት በመተኮስ ለማስቆም መሞከሩን፣ ነገር ግን ሊቆሙ አለመቻላቸውንና የመጨረሻውን ሦስተኛ አጥር ሊያልፉ ሲሉ መሞታቸውን በምርመራ ለማየት ተችሏል፡፡ ስለዚህ ተመጣጣኝ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ከመደምደማችን በፊት አማራጮች ነበሩ ወይ? የሚለውን እናያለን፡፡ ከዚህ አኳያ ወደ ላይ ተተኩሶ አለመቆማቸውና የመጨረሻው አጥር ላይ መሞታቸውን ዓይተናል፡፡ ከመጨረሻው አጥር ካለፉ ምን ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡
ጥያቄ፡- በጥይት የተመቱትን ሁለት እስረኞች ወደ ሕክምና በመውሰድ ሕይወታቸውን ማዳን አልተቻለም ነበር ወይ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የሕክምና ውጤቱ እንደሚያስረዳው ወደ ሐኪም ቤት ሳይሄዱ ነው እዚያው የሞቱት፡፡ መውሰድ አልተቻለም ነበር ማለት ነው፡፡
ጥያቄ፡- የጥበቃ ኃይሉ እየተቀያየረ 24 ሰዓት ጥበቃ እንደሚያደርግ እንረዳለን፡፡ ይህ ሁሉ ተቀጣጣይ የልብስ ክምር እስኪሰበሰብና ረብሻ ሲጠነሰስ የት እንደነበሩ የተገኘ መረጃ ካለ ቢገለጽ?
ዶ/ር አዲሱ፡- ይህ የእኛም ጥያቄ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ አስተዳደርና የጥበቃ አባላት የት ነበሩ? የሚለው አሁንም የእኛ ጥያቄ ነው፡፡
ጥያቄ፡- በወቅቱ በሥራ አጋጣሚ ቂሊጦ ማረሚያ ቤት አካባቢ ነበርን፡፡ ተኩሱ ለረዥም ሰዓታት የቆየ ነበር፡፡ የተኩሱ ብዛትና በተኩስነቱ ያስገኘው ውጤት ሚዛን እንዴት ይታያል? የሚተኮሰው ወደ ውስጥ መሆኑ አይቀርም፣ ምክንያቱም ውስጥ ነው አመፁ ያለው፡፡ የተተኮሰውና ደረሰ የተባለው ጉዳት ሲነፃፀርም የራሱ ሚዛን ይኖረዋልና ይህንን በአግባቡ አጢናችሁታል ወይ? በአንድ ጠባብ በተለይ ነገር ግን ለረዥም ሰዓት ብዙ ጥይት ሲተኮስና በተኩሱ ደረሰ የተባለው ውጤት ሚዛኑን አስተውላችኋል ወይ?
አቶ አዲሱ፡- ከውጭ ወደ ውስጥ ሲተኮስ እውነት ነው ምን እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ከውስጥ ያሉት እስረኞች ናቸው፡፡ የሚተኮሰው ጥይት ምን ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ግምት ውስጥ ያስገባ አካሄድ መሆን አለበት እንጂ፣ እንዲሁ በእሩምታ መልክ የሚተኮሰው ተኩስ እንዲያው በስምንቱ ላይ የደረሰው ከባድ የመቁሰል አደጋ ነው እንጂ የሰው ሕይወትም ሊጠፋ ይችል ነበር፡፡ ዕርምጃው እንዲሁ ጠቅላላ ዕርምጃ እንጂ የለየ አልነበረም፡፡ ከውስጥ ወደ ውጭ ሲተኮስ በማን ላይ ነው የሚተኮሰው? ለምን ዓላማ ነው የሚተኮሰው? የሟቾችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው ካልሆነ በስተቀር ሊቀንሰው አይችልም ነበር፡፡