Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ባንኮች ለመረጃ መንታፊዎች ተጋላጭ መሆናቸው ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ባንኮች ለመረጃ መንታፊዎች ተጋላጭ መሆናቸውን አንድ የሩሲያ ኩባንያ አስጠነቀቀ፡፡ ተቀማጭነቱን በሩሲያ ያደረገው ካስፐርስኪ የተባለው ዓለም አቀፍ የመረጃ መረብ ደኅንነትና የኮምፒዩተር ፀረ ቫይረስ ሶፍትዌሮችን በማቅረብ የሚታወቀው ኩባንያ፣ ከሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው በሚነገርላቸው ላዛሩስ በሚባል ስያሜ ለሚጠሩ ዓለም አቀፍ የመረጃ መንታፊዎች ተጋላጭ ናቸው ብሏል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ባንኮች በመረጃ መንታፊዎች ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነና ተጨማሪ ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችልም አስጠንቅቋል፡፡

በቅርቡ ኩባንያው ባወጣው ሪፖርት ተከታታይ የሆኑ የመረጃ መንታፊዎች ጥቃቶች 18 አገሮች ውስጥ በሚገኙ የገንዘብ ተቋማት ላይ እንዳነጣጠሩ ገልጿል፡፡ ከእነዚህም መሀል ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያ፣ ጋቦን እንዲሁም ናይጄሪያ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡

ኩባንያው ይህን ሪፖርት ይፋ ያደረገው በመጋቢት ወር ውስጥ ብቻ ተመሳሳይ ጥቃቶች በእነዚህ አገሮች ውስጥ በመታየታቸው ነው፡፡ ጥቃቶቹ ሊቀጥሉ እንደሚችሉም በመግለጫው አክሏል፡፡ ኩባንያው ከአሥር ዓመት በፊት ኡጅን ካስፐርስኪ በተባሉ ሩሲያዊ ባለሀብት የተቋቋመ ሲሆን፣ ከሁለት ዓመት በፊት በመረጃ ደኅንነት አገልግሎቱና በፀረ ቫይረስ ሥራዎቹ 619 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡

ከሦስት ሳምንታት በፊት ስድስት የአቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ተቀጣሪዎች፣ ከባንኩ ስዊፍት አካውንት ላይ ወደ 1.2 ሚሊዮን ዶላር ከባንኩ ዕውቅና ውጪ በማውጣት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡

የዝርፊያ ሙከራው አቢሲኒያ ባንክ በውጭ ባንኮች ላይ ባሉት አካውንቶች ተፈጽሟል፡፡ አቢሲኒያ በሲቲ ባንክ ኒውዮርክና በኮሜርዝ ኤጄ ፍራንክፈርት ባሉት አካውንቶቹ የዝርፊያ ሙከራዎች ተደርገውበታል፡፡

በሙከራዎቹ 745 ሺሕ ዶላር ከሲቲ ባንክ፣ እንዲሁም ወደ 465 ሺሕ ዶላር ደግሞ ከኮሜርዝ ባንክ ለመዝረፍ ተፈልጎ ነበረ፡፡ በወቅቱ ከኮሜርዝ ባንክ ሊወጣ የነበረውን ገንዘብ ባንኩ ጥቃቱን ቀድሞ ስለደረሰበት መከላከል ችሏል፡፡

ነገር ግን ከሲቲ ባንክ በወቅቱ 189 ሺሕ ዶላር ብቻ ማትረፍ መቻሉ ታውቋል፡፡ በወቅቱ የአቢሲኒያ ባንክ የገበያና የመረጃ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ አስቻለው ታምሩ፣ ሲቲ ባንክ ወደ 600 ሺሕ ዶላር የሚሆነውን ቀሪ ገንዘብ ለመሰብሰብ እየሞከረ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸው ነበር፡፡

አቶ አስቻለው በጉዳዩ ላይ ተለዋጭ ነገር ካለና ዝርፊያው ከመረጃ መንታፊዎቹ ጋር እንደሚገናኝ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርግም፣ መልስ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡

ተከታታይነት ያላቸውና በዛ ያሉ ጥቃቶች ላዛሩስ በተሰኘው የመረጃ መንታፊ ቡድን እየተስተዋለ እንደሆነ፣ የካስፐርስኪ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ኦልጋ ቤዝፒያትኪና ለሪፖርተር በኢሜይል በተደረገ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች በጣም አደገኛ ለሆነና ከፍተኛ መጠን ላለው የገንዘብ ዝርፊያ የሚደረጉ ዝግጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ቤዝፒያትኪና ገልጸዋል፡፡

ከአሁን ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ጥቃቶች ደርሰው ነበር፡፡ በጥቃቶቹ ባንግላዴሽ የተባለ ባንክ 81 ሚሊዮን ዶላር አጥቷል፡፡ የመረጃ መንታፊዎቹ የባንኩን ስዊፍት አካውንት ሰብረው በመግባት ገንዘቡን መዝረፍ ችለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ ከሦስት ዓመት በፊት ሶኒ ፒክቸርስ የተባለው ኩባንያ ላይ ጥቃት ሰንዝሯል፡፡ እንዲሁም ከሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠረው ይህ ቡድን፣ በደቡብ ኮሪያ መንግሥት ላይ ያነጣጠሩ የተለያዩ ጥቃቶች መፈጸሙ ይነገራል፡፡

በካስፐርስኪ ስለወጣው ሪፖርት እሳቸውም ሆነ የኢትዮጵያን የመረጃ መረብ ከጥቃት ለመከላከል የተቋቋመው እንደሚያውቁ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ውስጥ የሚሠሩ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው አሁን ዝርዝር የሆነ መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

ከአሁን ቀደም በኤጀንሲው፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበርና በኢትዮጵያ የመድን ሰጪዎች ማኅበር አማካይነት እንዲህ ዓይነት ጥቃቶችን ለመከላከል በጋራ ለመሥራት ውይይት እንደነበር፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የባንክ ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን ጉዳዩ አሁንም ገና በውይይት ደረጃ ላይ እንደሆነ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡ የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ከተመሳሳይ ጥቃቶች ራሱን ለመከላከል የሚያስችለው ራሱን የቻለ ማዕከል ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡

ከሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጋር ግንኙነት አለው የተባለው የመረጃ መንታፊው ቡድን፣ ትኩረቱን የመረጃ ሥርዓታቸው የላላ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸው አገሮች ላይ እያደረገ እንደሆነ ቤዝፒያትኪና አስጠንቅቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች