Monday, June 24, 2024

ደካማ አፈጻጸም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አያኮላሽ!

የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ለአገራዊ ህልውና ፋይዳ የሚኖረው ድህነትን አስወግዶ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ብልፅግና፣ ዴሞክራሲና አስተማማኝ ሰላም ሲያረጋግጥ ብቻ እንደሆነ በመርህ ደረጃ ይታመናል፡፡ ይህ መሆን ካልቻለ ግን ለአገር ህልውና አሥጊ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው አገራዊ ህልውናን የማረጋገጥ ተልዕኮ እንዲኖረው ደግሞ፣ ዘለቄታዊና አስተማማኝ ሥራ መከናወን አለበት፡፡ የአገሪቱ የዲፕሎማሲ መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣ ከመሆኑም በላይ፣ የአገሪቱም ተደማጭነት የዚያኑ ያህል አድጓል፡፡ ይህ ዕድገት የበለጠ እየፋፋና እየተጠናከረ መሄድ አለበት፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ መሠረታዊ ጉዳዮችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አገር የበለጠ እንድታድግ፣ እንድትታፈርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በስፋትና በጥልቀት እንዲገነባ የችግሮችን ምንጭ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ መሠረታዊ ችግር ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ በአሰልቺነቱ የሚታወቀው የአፈጻጸም ድክመት ነው፡፡ ይህ ድክመት በዲፕሎማሲው መስክ ውስጥ እየታየ ነው፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ ከተለያዩ አገሮችና ተቋማት ጋር የሚደረጉ የሁለትዮሽም ሆኑ የባለ ብዙ (Bilateral and Multilateral) ግንኙነቶች በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መከናወን አለባቸው፡፡ በዚህም መሠረት አገሪቱ ድንበር ከምትጋራቸውም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ጉዳይ ከሚኖራቸው አገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ከሐሜትና ከመጠራጠር ውጪ በመርህ ላይ መመሥረት ይኖርበታል፡፡ በሐሜት ላይ ከተመሠረተ ዲፕሎማሲ ይልቅ በመቀራረብና በመነጋገር ላይ የሚደረግ ግንኙነት እንደሚበልጥ ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ከግብፅ ጋር በመሪዎች ደረጃ ባደረገችው ግንኙነት ሳቢያ በርካታ ወሬዎች ተነዝተው ነበር፡፡ ደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ስምምነት ከግብፅ ጋር ማድረጓ መሰማቱ በወቅቱ ግራ መጋባት ፈጥሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መሪዎች አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ወሬው መሠረተ ቢስ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡ የግንኙነቱን ጤናማነትና ወዳጅነት የውኃ ልክ ለማሳየትም በርካታ ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዳላት ለማሳየት ከጂቡቲ፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ወዘተ ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየተገናኘች የተለያዩ ስምምነቶች ስትፈራረም ይታወቃል፡፡ አፈጻጸሙስ?

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከተለያዩ አገሮች ጋር የምታደርገው የዲፕሎማሲ ግንኙነት አደባባይ ወጥቶ ብዙ የሚባልበት የሥጋት ወሬዎች ሲሰሙ ነው፡፡ ዲፕሎማሲ ሁሌም በሥራ ላይ መሆን ያለበትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስከበር የሚውል እንጂ፣ ችግር ሲፈጠር እሳት ለማጥፋት የሚሯሯጡበት መሆን የበለትም፡፡ በየትኛውም ሥፍራ ያለ የአገሪቱን ህልውና የማይፈልግ አካል ድረስ በመሄድ በመጠራጠር ላይ ያለን ወገን ፍላጎት ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከአገሮች ጋር በሚደረግ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በመሳሰሉት የተለያዩ ስምምነቶች ሲፈረሙ ተከታትሎ የማስፈጸም ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ግንኙነቶቹ ለይምሰል የተደረጉ እስኪመስሉ ድረስ በርካታ ስምምነቶች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ ሌት ተቀን ርብርብ ተደርጎባቸው የተፈጠሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች፣ በአፈጻጸም ድክመት ምክንያት ሲኮላሹ ዝም ብሎ ማየት  ተገቢ አይደለም፡፡ ስምምነቶቹ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል አድርገው የተፈረሙ እስከሆነ ድረስ ችላ ባይነት አገር ይጎዳል፡፡ ደካማነትንም ያጋልጣል፡፡

ቀደም ሲል ለዘመናት ፊታቸውን አዙረው ከነበሩት የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች ጋር ሰፋ ያሉ ግንኙነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ በተለይ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌትና የመሳሰሉት አገሮች በዲፕሎማሲው መስክ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ እያንዣበቡ ነው፡፡ እንቅስቃሴያቸው በከፍተኛ በጀት የሚደገፍ እንደመሆኑ መጠን፣ ከአካባቢው አገሮች ጋርም ግንኙነት እየመሠረቱ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋርም በተለያዩ መስኮች ለመተሳሰር ከመግባቢያ ሰነዶች እስከ ዋና ስምምነቶች ድረስ እየተፈራረሙ ነው፡፡ ፍላጎታቸው ምንም ይሁን ምን የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም እስካልነካ ድረስ ጠበቅ ያለ ግንኙነት መመሥረት ይገባል፡፡ ከሐሜትና ከመጠራጠር መውጣት የሚቻለው በሚገባ በመቀራረብ መነጋገር ሲቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረትም አፈጻጸሞችን ማጠናከር ሲገባ የግብር ይውጣ ሥራ ውስጥ መዘፈቅ ተገቢ አይደለም፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እዚህ ድረስ እየመጡ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ሲፈልጉ፣ ፍላጎታቸውን በሚገባ ተገንዝቦ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ማነፃፀር ተገቢ ነው፡፡ ግንኙነቱ ጤናማ ሆኖ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ደግሞ የብልህ ዲፕሎማሲ ተግባር ነው፡፡ አሰልቺውንና ኋላቀሩን የተለመደ የአፈጻጸም ድክመት ከሥር ከመሠረቱ መናድ ያስፈልጋል፡፡ በፍጥነት፡፡

ምንም እንኳ አሁን ዓለም የሚሄድበት አቅጣጫ ውሉ በቅጡ ባይታወቅም፣ ዓለም በተለያዩ የግሎባላይዜሽን ትሩፋቶች ምክንያት የተሳሰረ ነው፡፡ ይህ ጥብቅ ትስስር በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፀጥታና በደኅንነት የሚገለጽ ሲሆን፣ ማሰሪያ ልጡ ደግሞ ዲፕሎማሲ ነው፡፡ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር አገሪቱ ያላት ግንኙነት ዘለቄታዊ ጥቅምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ጥቅም ደግሞ የጋራ ነው፡፡ የሶማሊያን የሰላም ማስከበር ሒደት የሚመራው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኃይል ድንገት ከሶማሊያ እወጣለሁ ቢል አሜሪካንም ሆነ የአውሮፓ ኅብረትን ያሳስባቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ጎን የተሠለፉትን የሰላም አስከባሪ አገሮችንም እንዲሁ፡፡ በአካባቢው ያልተለመደ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲኖርም ሥጋቱ ሁሉንም እንቅልፍ ይነሳል፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ የሥራ ክፍፍል የተደረገበት የግሎባላይዜሽን ትስስር በጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ብልኃት መደገፍ ሲያቅተውና አፈጻጸሙ ሲንገጫገጭ በሁሉም አገሮች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ጠንካራው ትብብር በደካማ አፈጻጸም ሳቢያ ሲጨናገፍ በመንጠራራት ብቻ ምንም ማምጣት አይቻልም፡፡ ዘርፈ ብዙው ዲፕሎማሲ በብልኃትና በጥበብ መመራት አለበት፡፡ በብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንደሚታየው ደካሞች ሰበብ እየፈለጉ የሚደበቁበት ዋሻ ሊሆን አይገባም፡፡ በዓለም አደባባይ በኩራት አንገትን ቀና አድርጎ መንቀሳቀስ የሚቻለው ለኢኮኖሚና ለፖለቲካ ዲፕሎማሲ ልዩ ትኩረት ሲደረግ ነው፡፡ የዲፕሎማሲ ጡንቻን አፈርጥሞ ጠንክሮ በመገኘት ነው፡፡ ተመፅዋችነትና አጉል ተስፋ ቦታ የላቸውም፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ግንኙነቶች እልህ አስጨራሽ ከመሆናቸው የተነሳ ተስፋ የሚያስቆርጡበት ጊዜ አለ፡፡ በዲፕሎማሲ ግን ተስፋ መቁረጥ የለም፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚፈለገው ውጤት እስኪመጣ ድረስ የሆድን በሆድ ይዞ መደራደር የተለመደ ነው፡፡ ተደራዳሪው አካል ጠላት ከሚባሉ አካላት ጋር ዋንጫ የሚያነሳ ቢሆን እንኳ ትዕግሥትና ብልኃት ጥሩ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በኢኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ ኃይል የተሻለ አቅም ካለው የሚያንገራግር ወገን ጋር የሚደረግ ግንኙነትና ድርድር ጭምር ጥቅምን በማቻቻል ላይ እንዲመሠረት ለማድረግ ይቻላል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ከወሬ ቀነስ ከተግባር ጨመር ማድረግ ነው፡፡ የውጭ  ጉዳይ ፖሊሲ መነሻ ብሔራዊ ጥቅምንና ደኅንነትን ማስከበር በመሆኑ፣ የደካሞችና የአቅመ ቢሶች ሰለባ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አገሪቱ ከማንኛውም አገር ሆነ ተቋም ጋር የሚኖራት ግንኙነት ከብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የበለጠ ዓላማ ስለሌለው፣ አፈጻጸምን በየጊዜው መገምገምና በችግሮች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ የመንግሥት የዘወትር ኃላፊነት ነው፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አማካይነት የሚደረጉ ስምምነቶች የወረቀት ጌጥ ሆነው እንዳይቀሩ ነቅቶ መከታተል ያስፈልጋል፡፡ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ከያሉበት ተፈልገው ይህንን ዓላማ ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ደንታ ቢሶች ለዚህ ዓላማ እንቅፋት ስለሚሆኑ ዘወር መደረግ አለባቸው፡፡ በመሆኑም ደካማ አፈጻጸም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አያኮላሽ!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...