Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሺዎችን ቅሬታ ለመፍታት ውሳኔ አሳለፈ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሺዎችን ቅሬታ ለመፍታት ውሳኔ አሳለፈ

ቀን:

  • ተነፃፃሪ ካርታ ያላቸው ማልማት እንዲችሉ ተፈቅዷል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሺዎች እርካታ እስኪፈጠር ድረስ የመልሶ ማልማት ፕሮግራም እንዲዘገይ በወሰነው መሠረት፣ ካቢኔው ባለፈው ሳምንት ተሰብስቦ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስቻላል ተብሎ የተዘጋጀውን ጥናት አፀደቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ለመገምገም ተሰብስቦ በነበረበት ወቅት፣ ይህ ችግር ከፍተኛ የሕዝብ ቅሬታ እያስከተለ ነው ተብሎ ሥራ አስፈጻሚው እንዲፈታው አሳስቦ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው የልማት ተነሺዎች ቅሬት እያቀረቡ መሆኑን በማመን ቅሬታቸው ተፈትቶ እርካታ ሳይፈጠር በበጀት ዓመቱ ሊጀመሩ የታሰቡት አዳዲስ የመልሶ ማልማት ቦታዎች እንደማይጀመሩ፣ ነባሮቹም እንዲዘገዩ ተደርጎ ችግሩ እንደሚፈታ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በተለይ በመሀል አዲስ አበባ በ186 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ተነሺዎች ሲያቀርቡ የቆዩት ጥያቄ ባለመመለሱ ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ 21 ችግሮችን በመለየት ለካቢኔው አቅርቦ ማፀደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዘብረህ ያይኖም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተነፃፃሪ ካርታ ያላቸው የግል ባለይዞታዎች የቦታው ስፋት የራሳቸውን ግንባታ እንዲያካሂዱ የሚበቃ ከሆነ ተፈቅዶላቸዋል፡፡

በዚህ አቅጣጫ የሚስተናገዱ የመልሶ ማልማት ቦታዎች ላይ ያሉ ብቻ መሆናቸውን አቶ ዘብረህ ገልጸው፣ ከመልሶ ማልማት ቦታዎች ውጪ ያሉትን ለማስተናገድ የፌዴራል መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 47/67 መነሻ አቅጣጫ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ጎልተው ሲነሱ ከነበሩት ችግሮች ውስጥ በመልሶ ማልማት ወቅት ለተነሱ ነዋሪዎች በቤተሰብ ቁጥር ልክ ስፋት ያለው መኖሪያ ቤት እንዲቀርብ፣ በልማት ምክንያት ለሚነሱ የቀበሌ ቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚገባቸው ከአንድ በላይ ወራሾች በፍርድ ቤት መብታቸው እየተረጋገጠ እንዲስተናገዱ፣ በቀበሌ ቤት ግቢ ውስጥ አዲስ መኖሪያ ቤት የገነቡ ነዋሪዎችም በ2003 ዓ.ም. ከተነሳው የመስመር ካርታ ጋር ተገናዝቦ እንዲስተናገዱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህ መሠረት ከ186 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ነባር የልማት ተነሺዎች፣ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ተስተናግደው እንዲነሱ ካቢኔው ውሳኔ ማሳለፉ ታውቋል፡፡

ሌላው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወቅቱ የሚነሳበት ቅሬታ አግባብ ካለው አካል ሳይፈቀድ መሬት በራሳቸው ፈቃድ ወስደው ግንባታ ያካሄዱ አካላት ጉዳይ ነው፡፡ አስተዳደሩ ይህንን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት በተለይ ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ያሉ ‹‹ሕገወጥ ግንባታዎች›› ‹‹ሕጋዊ እንዲሆኑ››፣ ከዚያ በኋላ ግን ሕገወጥነት በፍፁም ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ አስተዳደሩ አስምሮበት ነበር፡፡

ይህ ጉዳይ ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ ሕጋዊ እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ሕገወጦች በ2009 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ካርታ ወስደው የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ እንዲዘጋ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ለዓለም ተሠራ ከሚመለከታቸው ነዋሪዎች ጋር ባካሄዱት ውይይት፣ ይህ ጉዳይ በዚህ ዓመት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ምልክቶች አልታዩም፡፡

ቢሮው ሙሉ ለሙሉ ይህን ችግር ለመፍታታት ለ18,879 ባለይዞታዎች ካርታ አዘጋጅቶ ጉዳዩን ለመዝጋት ቢያቅድም፣ ካርታውን መውሰድ የቻሉት 8,624 ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት 10,255 የሚሆኑ ባለይዞታዎች ካርታውን መውሰድ አልቻሉም፡፡

በውይይቱ ወቅት ነዋሪዎች እንደገለጹት ከሊዝ መነሻ ዋጋ ውጪ ያለው ቀሪ ቦታ የሊዝ ዋጋው መብዛቱና ወለዱም እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ፣ ካርታውን ለመውሰድ አቅማቸው እንዳልፈቀደና አስተዳደሩም ጉዳዩን እንዲያጤን ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን አቶ ለዓለም ይህን ጉዳይ አልተቀበሉትም፡፡ እንደ አቶ ለዓለም ገለጻ፣ አስተዳደሩ አግባብ ካለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ይዞታዎችን ለማስተናገድ ብዙ ርቀት ሄዷል፡፡ ጉዳዩ ሕገወጥ መሆኑ እየታወቀ በአካባቢ የሊዝ መነሻ ሒሳብ የሚስተናገደውን 75 ካሬ ሜትር ወደ 150 ካሬ ሜትር መሬት አሳድጓል ብለዋል፡፡

‹‹የተቀረው ይዞታ የሚስተናገደው በሊዝ ጨረታ ዋጋ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ አስተዳደሩ ምንም ሊያደርግ አይችልም፤›› ሲሉ አቶ ለዓለም ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...