Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኳታር ኤሚር ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያ ይመጣሉ

የኳታር ኤሚር ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያ ይመጣሉ

ቀን:

  •  የዲፕሎማቲክና ልዩ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ ስምምነት ይፈረማል

የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ሲመጡ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የዲፕሎማቲክና ልዩ ፓስፖርት የያዙ ሰዎች ያለ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ስምምነት እንደሚፈራረሙ ተገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የኳታር ኤምባሲ ዓርብ መጋቢት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በኳታር ኤሚር የሚመራ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ ከሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይፋ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውም በአፍሪካ አገሮች ከሚያካሂዱት ጉብኝቶች አንዱ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኤሚር ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ የአዲስ አበባ ጉብኝት ሥልጣን ከያዙ ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ የመጀመሪያ እንደሆነ፣ በሁለት ቀናት ቆይታቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩ ተጠቁሟል፡፡

መሪዎቹ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ስለሚያጠናክሩባቸው የንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ከመወያየት በተጨማሪ፣ ቀጣናዊና አኅጉራዊ የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮች ላይም ትኩረት ሰጥተው እንደሚመክሩ ታውቋል፡፡

ኤምባሲው የኢትዮጵያና የኳታር ባለሙያዎች ቡድን እ.ኤ.አ. መጋቢት 31 ቀን 2017 ዓ.ም. ተገናኝተው ለኤሚሩ ጉብኝት ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶችን የማርቀቅ ሥራ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ቀድሞም የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮችን የተቀበለችና ለረዥም ጊዜም ክርስትናንና እስልምናን በሰላም አቻችላ የምትኖር አገር መሆኗን ያስታወቀው ኤምባሲው፣ ከዓረቡ ዓለም ጋር ያላት ግንኙነትም ታሪካዊና ዘላቂነት ያለው ሲል በመግለጫው አብራርቷል፡፡ በተለይም ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት ጠንካራና በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ ነው ያለው ኤምባሲው፣ ኢትዮጵያ የአገሮቹን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት በማክበርና በማስከበር እየተጫወተችው ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ብቸኛዋ የአፍሪካ ነፃና በቅኝ ያልተገዛች አገር ከመሆኗ በላይ፣ የሰው ልጅ መገኛ ነች ሲል የሚያትተው መግለጫው የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤትም እንደሆነች አብራርቷል፡፡ ከዚህ በፊት ፓን አፍሪካኒዝምን የመሠረተች አገር በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሽብርን በመዋጋት በአፍሪካ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ያለው ሚና በተምሳሌትነት የሚጠቀስ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

ከዚህ በፊት ኢትዮጵያና ኳታር አሥራ አንድ ያህል ስምምነቶችን ተፈራርመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ተደጋጋሚ ቀረጥን በማስቀረት፣ የአየር ትራንስፖርትና የኢንቨስትመንት ከለላ ይገኙበታል፡፡ ሚያዝያ 2 እና 3 ቀን 2009 ዓ.ም. የሚካሄደው የኤሚሩ የአዲስ አበባ ጉብኝት የቆዩ ስምምነቶችን እንደገና በመፈተሽና በማዳበር፣ ሌሎች አዳዲስ ስምምነቶችን እንደሚደረጉ ኤምባሲው በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በአካባቢያዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚያካሂዱና የተለያዩ የመግባቢያ ሰነዶች በሁለቱ ወገኖች መካከል እንደሚፈረሙ የገለጸው ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ነው፡፡ የኳታርና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከተጀመረበት እ.ኤ.አ. 1995 ወዲህ በሁለቱ አገሮች መካከል የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን አስታውሷል፡፡

ኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እ.ኤ.አ. በ2008 መቋረጡንና ለመቋረጡ መነሻ ምክንያት የሆነው ደግሞ የኳታር መገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም አልጄዚራ የተባለው ሚዲያ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶችን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንደሚደግፍ ኢትዮጵያ ይፋ ካደረገች በኋላ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ መንግሥት ድርጊቱን በመቃወም ከኳታር ጋር የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጦ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ በታኅሳስ 2009 ዓ.ም. የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሐመድ አብዱልራሒም ጃሲም አል ታኒ በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ‹‹በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ የተደረጉ ተደጋጋሚ ጉብኝቶች ሁለቱ አገሮች በጋራ ለመሥራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፤›› ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡         

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ