በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የቡና እሴትን ለመጨመር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሥልጠና የሚሰጥ ማዕከል እንደሚመሠረት ተገለጸ፡፡ ይህ የተገለጸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትና በጣሊያን መንግሥት ዕገዛ እየተተገበረ ያለው ፕሮጀክት ሁለተኛ ምዕራፍ መጀመሩን ይፋ ያደረገ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት፣ ሰኞ መጋቢት 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በተፈረመበት ወቅት ነው፡፡
የአገሪቱን የቡና ምርት ጥራት በማሳደግ፣ የበቀለበት አካባቢን በመለየትና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግና የገበሬውንም ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመው ይህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ የሦስት ዓመታት ቆይታ እንደሚኖረውም ተጠቁሟል፡፡
በጣሊያን መንግሥት የልማት ተራድኦ ድርጅት የ2.5 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተቸረው ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ፣ በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ ኢሊካፌ በተባለው የጣሊያን የቡና ኩባንያና በኤርኔስቶ ኢሊ ፋውንዴሽን ትብብር ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር ጁሴፔ ሚስትሬታ እንደተናገሩት፣ ግብርናውና የኢንዱስትሪው ዘርፍ መሳ ለመሳ ማደግ ይገባቸዋል፡፡ አገራቸውም ለኢትዮጵያ የአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት ልዩ ትኩረት በመስጠት ትረዳለች፡፡ የኢትዮጵያን የቡና ምርትና ጥራትንም በማሳደግ አገሪቱን እነ ብራዚልና ኮሎምቢያን ከመሳሰሉት አገሮች ጋር ተፎካካሪ ማድረግ እንደሚቻል አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪና የቀጣናው ቢሮ ኃላፊ ጉስታቮ አይሸምበርግ በበኩላቸው፣ ፕሮጀክቱ የቡናው ዘርፍ ዘለቄታዊነት ባለውና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መንገድ መካሄዱ የስኬታማነቱ ቁልፍ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ በመቀጠልም ‹‹በዚህ ፕሮጀክት አማካይነት አንደኛ ደረጃ የያዘ ምርት (የኢትዮጵያ ቡና) በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ካለ ቴክኖሎጂ (የኢሊካፌ የቡና ማቀናበር ሥራ) ጋር ቅንጅት ሲፈጥር ማየት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡
መንግሥትን በመወከል በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ሲሆኑ፣ እሳቸውም የቡናው ዘርፍ 25 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጣሪና የኑሮው መተዳደሪያ ምንጭ፣ እንዲሁም አገሪቱ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሪ 20 በመቶ አካባቢ ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የኢትዮጵያን ስትራቴጂክ ሸቀጦች ለመደገፍ ያወጣው መርሐ ግብር አካል የሆነው የቡና ፕሮጀክት፣ ወደፊትም በሻይና በቅመማ ቅመም መስኮች እንደሚቀጥል ያላቸውንም ተስፋ ገልጸዋል፡፡
በቡና ምርትና ግብይት ሥርዓት ዙሪያ የአሠራር ለውጥ ማምጣት ማለትም ምርምር ማድረግ፣ ምርት፣ ጥራትና ሎጂስቲክስን ማሳደግ ብሎም እሴት መጨመር ዙሪያ በመንግሥትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በኩል አጽንኦት ተሰጥቶበት እየተሠራ እንደሚገኝና በዘርፉም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ እንደሚታይ ተስፋ እንደሚያደርጉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት በኢትዮጵያ የጣሊያን መንግሥት የተራድኦ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጂኔቭራ ሌቲሲያ ጽሕፈት ቤታቸው የኢትዮጵያን የቡና ምርት ገበያ ሰንሰለትን ለመርዳት የሚያደርገውን ድጋፍ ካብራሩ በኋላ፣ ‹‹የባህላችሁ አካል የሆነ ይህን የመሰለ ሀብት በመሬታችሁ ውስጥ ይዛችሁ የእዚህን ሀብት መጠንና ጥራት ማሳደግ ግድ ይላችኋል፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር የሚሰናሰል ሲሆን፣ የቡና ገበሬዎችና የአርሶ አደር ማኅበራት ምርጥ የግብርና አሠራር ዘዴዎች ተጠቅመው ምርታማነትን ማሳደግ እንዲችሉ ያግዛል፡፡ በተጨማሪም እሴትን በመጨመር ሒደት የአገር ውስጥ የቴክኒክ ብቃትን ለማሳደግ በአገሪቱ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና የተሻሻለ የቡና አቆላል ጥበብን የሚያስተምር ማዕከል በቅርቡ እንደሚከፈት፣ ይህም ወደፊት ይከፈታል ተብሎ ለሚታሰበው የቡና ኢንስቲትዩት የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደሚሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የቡና ምርት ገበያ ሰንሰለትን ለማሳደግ ለሚደረገው ጥረት በኢሊካፌ ኩባንያ ድጋፍ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ትሪስቴ በተባለች የጣሊያን ከተማ የድኅረ ምረቃ ትምርህት በ‹Universita del caffe› (University of Coffee) እየተከታተሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡