Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ውጤቱ እንዴት ይገምገም?

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁና ውጤቱ እንዴት ይገምገም?

ቀን:

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካጋጠመን ሽንፈት ወደ ሌላ ጥልቅ ሽንፈት እንዳንጓዝ ተብሎ የታወጀ ነው፡፡ ሆኖም እንደ አገር ሲታይ የሽንፈት መንገድ መሆኑ አልቀረም፡፡

መንግሥት የሕዝቦችን መሠረታዊና ተገቢ ጥያቄዎችን መመለስ አቅቶት ሲንገዳገድና በኢዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንቅስቃሴውን ለማፈን ሲሞክር፣ ሕዝቦች መብቶቻቸውን ለማረጋገጥ በሰላማዊ መንገድ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ በፅንፈኞች ተጠልፎ አገር ወደማያባራ ሁከት እንዳታመራ ለመግታት የታወጀ ነው፡፡ እንደ አገር በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ የሕዝቦችን ጥያቄዎች መፍታት አቅቶን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንገኛለን፡፡ ለዚህ ነው ሽንፈት የሚሆነው፡፡

በተዘበራረቀ መንገድ ቢሆንም መንግሥት የሕዝቦችን ጥያቄዎች ተገቢነት አምኖ ውስጡ መሠረታዊ ችግሮች ተከስተዋል ብሎ ራሱን ለማደስ ያውም በጥልቅ ለመታደስ ወስኖ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የአዋጁ ጊዜ ገዥው ፓርቲ/መንግሥት ‹‹በጥልቅ እታደሳለሁ›› ብሎ፣ በከፍተኛ ደረጃ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በሚነካ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አዋጁን ከ‹ጥልቅ ተሃድሶ› እንቅስቃሴ ለይቶ ለመገምገም አይቻልም፡፡ በ2008 ዓ.ም. የነበረውን ሁከት ለመግታት ሲታወጅ መሠረታዊ መነሻው ፖለቲካ መሆኑ ታምኖበት ነው ወደ ፖለቲካ ተሃድሶ የተገባው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ አገራችን በሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ከአምባገነናዊ አገዛዝና ጥልቅ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ኋላቀር አስተሳሰብና ባህል ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር፣ ወደ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ግንኙነት፣ ከተበታተነ ኢኮኖሚ (Subsistent Economy) ወደ ዘመናዊ ሉላዊ ካፒታሊስት ኢኮኖሚ፣ ከኋላቀር የደኅንነት አስተዳደር፣ ወደ ሕዝቦችን ማዕከል ያደረገ ዘመናዊ የቁጥጥር፣ የደኅንነት፣ ወዘተ ሽግግር ላይ ትገኛለች፡፡

አገራችን ከብዙ ምዕተ ዓመታት እንቅልፍ በኋላ በመጨረሻው በ19ኛው ክፍለ ዘመን አሁን ያላትን ቅርፅ ይዛ ዘመናዊውን የአገር ግንባታ ሒደት (State Building Process) ነው የተያያዘችው፡፡ የአውሮፓ አገሮችን ሒደት ዋቢ አድርጎ ቻርለስ ቺሊ ‹‹ጦርነት አገሮችን ይገነባል›› (War Makes States) እንዳለው በተለያዩ የውስጥና የውጭ ጦርነቶች አልፋ፣ ነፃነትዋን ጠብቃ፣ በአንፀባራቂ ድሎች ታጅባ፣ ነገር ግን ሕዝቦችዋ የጦርነት በተለይም የእርስ በርስ ጦርነት ሰለባ ሆነው በሒደት ላይ ትገኛለች፡፡ ከገቡበት የድህነት አረንቋ ለመውጣት በሒደት ላይ ይገኛሉ፡፡

የግለሰብና የቡድን በተለይም ‹የራስን ዕድል በራስ መወሰን› (Self Determination) የሚገለጽ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሕዝቦቻችን ጥያቄዎች ሆነውና ዓለም አቀፋዊ ቅቡልነት (Norm) ባገኙበት ሁኔታ፣ ወታደራዊው መንግሥት እነዚህን መብቶች ባለመቀበልና በመርገጥ አገራችንን ለከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ዳርጓታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዋናነት በኢሕአዴግ እንዲሁም በሌሎች ድርጅቶች መሪነት አምባገነናዊ ሥርዓቱን አሸንፈውና አዲስና የተሟላ ሕገ መንግሥት አፀድቀው፣ የአገር ግንባታ ሒደቱን እንደ አዲስ ‹‹አንድነት በብዝኃነት›› (Unity in Diversity) በአዲስና በጎለበተ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ተያይዘነዋል፡፡

እንደ ማንኛውም የአገር ግንባታ ሒደት (ሁልጊዜ ከነበረው ወደ አዲስ መገስገስ ስለሆነ) የአዲስ ሥርዓት ግንባታ ጉዞ አልጋ በአልጋ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡ ውጣ ውረድ/መንገራገጭ (Uphevals) የሚታይበት መሆኑ የግድ ነው፡፡ ጠንካራና ሕዝባዊ መንግሥት በሚኖርበት አኳኋን ሁለት ዕርምጃ ወደፊት አንድ ዕርምጃ ወደኋላ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህ በሁሉም አገር የተከሰተ ሒደት ነው፡፡ ቀጥተኛ (Smooth) የሚባል የአገር ግንባታ ሒደት ሊኖር አይችልም፡፡ በሌላ አገላለጽ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለ ኋላቀርነት በመሪዎችም ዘንድ በተለያየ ደረጃ ስለሚንፀባረቅና በሽግግር ባሉ አገሮች ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት፣ ወደፊት በሚደረገው ጉዞ መንሸራተት (ሽንፈት ሊያጋጥም ይችላል) ሕዝቦችና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ማድረግ በሚችሉት የተሟላ ግስጋሴ፣ ጥልቀትና የተራዘመ እንዲሆንና መንሸራተቱ እንዲያጥርና ጥልቀት እንዳይኖረው መከላከል ነው፡፡

የግስጋሴው ጥልቀት ስንል ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያብብ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ በጎ አስተሳሰብ እንዲጎለብትና ኋላቀርነትን በቀጣይነት ለመታገል፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀጣይና ፈጣን ዕድገት ለማስመዝገብ፣ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ጉዞውን የማቀላጠፍና በሕዝቦች መካከል መተማመንን ብሎም ሰላምን የማረጋገጥ ሒደት ተቋማዊ እየሆነ ሲመጣ ነው፡፡

መንሸራተት (ሽንፈት) ስንል በተቀራኒው ፀረ ዴሞክራሲ አስተሳሰብና ተግባር መጎልበት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች (Crisis) በከፍተኛ ደረጃ ሲከሰት፣ በሕዝቦች መካከል መጠራጠር ሲሰፋ፣ የተገኘው ሰላም ሲናድና ተቋማት ልፍስፍስ ሲሆኑ ነው፡፡

ቅድመና ድኅረ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገራችንን ሁኔታ መንሸራተት (ሽንፈት) ያሳያል፡፡ የሕዝቦች ጥንካሬ ብሎም የአገሪቱና የመሪዎች ማንነት የሚታየው ግን በመንሸራተት ሆነ፡፡ ለቀጣይ ግስጋሴ የሚረዳው ያሉትን ዘሮች (Seeds) በማድነቅ፣ በማጎልበትና በፍጥነት ወደ ቀጣዩ ግስጋሴ መጓዝ መቻላችን ነው፡፡

በትግላችን ያገኘነውን ሕገ መንግሥት፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያሉት በጎ እሴቶችና ልፍስፍስ እያሉ ያሉትን ተቋማት እያስተካከልን በቀጣይነት መገስገስ ይኖርብናል፡፡

ይህ እንዲሆን በቀበሌ፣ በወረዳ ብሎም በክልልና በፌዴራል ደረጃ፣ እንዲሁም በሲቪልና በፖለቲካዊ ተቋማት አዋጁ ሽንፈት መሆኑን ተቀብለን ከዚያ በኋላ ያሉት እንቅስቃሴዎች ቀስ በቀስ ወደ እውነተኛ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በአጠቃላይ ወደ ድል የሚያመሩ መሆኑን መገምገም ይኖርብናል፡፡

  1. ከነበረው አንፃራዊ ሰላም መደፍረስ ማገምገም ችለናል ወይ?
  2. የተወሰዱት ዕርምጃዎች በሕግና በሕግ ብቻ የተወሰዱ ናቸው ወይ? የታሰሩት ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸውን በሚያረጋግጥ መንገድና ለመብታቸው በሰላማዊ መንገድ የበለጠ እንዲታገሉ በሚያበረታታ አካሄድ ነው ወይ?
  3. በሕዝቦች መካከል እየተከሰተ የመጣውን የመጠራጠር ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ለመግታት ተችሏል ወይ?
  4. በኅብረተሰቡና በተቋማት የተደረጉት ግምገማዎች በኅብረተሰቡ ጠያቂነት የተቋማት ግዴታዎችን መወጣት በሚያበረታታ መንገድ ነው የተካሄደው? ወይስ ከእንግዲህ እንዳይደገም መቀጣጫ ነው የሆነው? የሲቪልና የሙያ ማኅበራት ሕገ መንግሥታዊ ነፃነታቸውን እያረጋገጡ ግዴታቸውን በሚወጡበት መንገድ ነው ወይ የተካሄደው?
  5. ሁከቱ የተፈጠረው በአንድ በኩል ጠያቂ ኅብረተሰብ እየጎለበተ በመምጣቱ፣ በሌላ በኩል የልሂቃን ፖለቲካ በመዝቀጡ (Stagnation) እና የፖለቲካ ፓርቲዎች (ገዥው ፓርቲ ጭምር) ሕዝቦችን በብቃት መምራት አቅቷቸው የተፈጠረ መንሸራተት ነው፡፡

     ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተፈጠረውን የሕዝብ መነሳሳት ለምን በሰላማዊ መንገድ ሊጠቀሙበት አልቻሉም? የጠራ ፕሮግራም፣ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ሥልት እንደሚጎድላቸው አውቀው ለማረም እየተንቀሳቀሱ ነው ወይ? ድርጅታዊ ነፃነታቸውን ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከዳያስፖራ ፅንፈኞች ተፅዕኖ ለማላቀቅ እየሠሩ ነው ወይ? ገዥው ፓርቲ ሕገ መንግሥቱን ለማስከበርና ዴሞክራሲያዊ ከባቢ ለማጎልበት እስከምን ድረስ ቁርጠኛ ነው? ገዢው ፓርቲ ከመንግሥት ጋር ያጣበቀውን ለማቋረጥና አገር (State) መንግሥት፣ (Government) እና ገዢው ፓርቲ (Ruling Party) ያላቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት ለማስጠበቅ በቁርጠኛነት እየተንቀሳቀሰ ነው ወይ? ውስጣዊ እድፎችን ለመቅረፍ ተዘጋጅቷል ወይ? ወይስ እንደነበረው ሊሸመግል ነው፡፡

በአጠቃላይ የአገራችን ሕዝቦችና ተቋሞቻችን ስንገመግም በስድስት ወር ጊዜ ወይም በአንድ ዓመት መሠረታዊ ለውጥ ይመጣል ለማለት አስቸጋሪ በመሆኑ የምንገመግመው መሠረታዊ ዕድገት የሚሆኑትን ምልክቶች እያመላከተ ነው ወይ በሚል መስፈርት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው የቀድሞ የኢሕአዴግ ታጋይና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...