Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊትኩረት የተነፈገው ፓርኪንሰን

ትኩረት የተነፈገው ፓርኪንሰን

ቀን:

ፓርኪንሰን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት የሚሄድና እንቅስቃሴን የሚገታ ከባድ የአዕምሮ ሕመም ነው፡፡ በዓለም ውስጥ በ2005 ዓ.ም. ወደ 53 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በፓርኪንሰን ተይዘዋል፡፡ 103,000 ያህሉ ደግሞ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ በሽታው ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን ከሴቶች ይልቅም በወንዶች ላይ እንደሚያመዝን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ብቻ በ2003 ዓ.ም. ወደ 363 የሚጠጉ የፓርኪንሰን ሕሙማን ተገኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 32ቱ ሲሞቱ፣ 11ዱ ደግሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነዋል፡፡ ሕሙማኑም ሊታወቁ የቻሉት በተለያዩ የመንግሥት ሕክምና ተቋማት ለመታከም ሲመጡ ነው፡፡ በየቤታቸው ተደብቀው የቀሩ፣ በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች ያሉት ሕሙማን ደግሞ አይታወቁም፡፡

የበሽታው ምልክቶች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያው ምልክቶች ሚዛን ለመጠበቅ አለመቻል፣ በዕረፍት ወይም በመዝናናት ላይ እያሉ መንቀጥቀጥ፣ ለመራመድ መቸገር፣ ሰውነትን ጨምድዶ መያዝ ሲሆኑ፣ ሁለተኛው ምልክቶች ደግሞ ድብርት፣ የድምፅ ጥራትና መጠን መቀነስ፣ ድርቀት፣ እንቅልፍ ማጣትና የማሽተት ችግር ናቸው፡፡

- Advertisement -

የበሽታው መንስኤ በውል ባይታወቅም፣ ከቤተሰብ በዘርና በአንዳንድ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ሊተላለፍ ይችላል የሚል ግምት አለ፡፡ በሽታውን መፈወስ ባይቻልም፣ በአንቲፓርኪንሰን መድኃኒቶች መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ መድኃኒቶች መካከል አንዱ ሊቭዶፓ ይገኝበታል፡፡

በሽታው እየጠነከረና በዚህም ሳቢያ ለሰውነት መልዕክት የሚያስተላልፉ ሴሎች ሥራቸውን ወደማቆሙ ሲቃረቡ የመድኃኒት ሕክምና አይኖረውም፡፡

በሽታው የተሰየመው በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታውን አስመልክቶ ሰፊና ጥልቅ ጽሑፍ ባሳተመው በዶ/ር ጄምስ ፓርኪንሰን ስም ሲሆን፣ ፀሐፊው በተወለደበት ሚያዝያ 3 ቀን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራን ያካተተ የዓለም የፓርኪንሰን ቀን ይከበራል፡፡

ከኢትዮጵያ በስተቀር በመላው ዓለም ይህ ዓይነቱ አከባበር በዕለቱ ለ20ኛ ጊዜ ይከናወናል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ለስድስተኛ ጊዜ ታስቦ ይውላል፡፡ ቀኑም ታስቦ የሚውለው የፓርኪንሰን ሕሙማን ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ ኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ፓርክ ድረስ የእግር ጉዞ በማድረግ ሲሆን፣ በወቅቱም ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚከናወን ፓርኪንሰን ፔሸንትስ ስፖርት ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ታለሞስ ዳታ ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ክብራ ከበደ የተባሉ የፓርኪንሰን ሕመምተኛ ያቋቋሙት ይህ የበጎ አድራጎት ድርጀት ለሕሙማን ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ከሚያበረክታቸው ድጋፎች መካከል የመድኃኒትና የአልባሳት አቅርቦት ይገኝበታለ፡፡ በዚህም መሠረት ለአንድ የፓርኪንሰን ሕመምተኛ ለመድኃኒት መግዢያ ብቻ በየወሩ 600 ብር ያወጣል፡፡ ድርጅቱ ከተመሠረተበት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዋናነት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው ብሬድ ፎር ዘ ወርልድ ከተባለው የጀርመን በጎ አድራጎት ተቋም ነው፡፡

በሽታው ትኩረት ቢሰጠውና በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስቃይና ለሞት ከሚዳርጉ በሽታዎች መካከል ቢካተት ሕሙማኑ በየዕለቱ የሚወስዱትን መድኃኒት በነፃ አለበለዚያም በግማሽ ዋጋ እየከፈሉ የመጠቀም ዕድል ሊኖራቸው እንደሚችል አቶ ታለሞስ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በበሽታው ዙሪያ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ለማካሄድ፣ በተለያዩ የሕክምና ተቋማት ለሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች በሽታውን አስመልክቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት፣ በበሽታው ሳቢያ የመንቀሳቀስ እክል ላጋጠማቸው አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍና ዊልቸር እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ኦፊሰር ዶ/ር ሙሴ ገብረሚካኤል እንደገለጹት፣ ፓርኪንሰን ለብዙ ዓመታት ትኩረት ተነፍጎት የቆየበት ምክንያት ከምርምር ተቋማት በበሽታው ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መረጃ ባለመቅረቡ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ዕቅድ ውስጥ ተካትቷል፡፡ ዕቅዱም በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የፓርኪንሰን ቀን ሲከበር ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ከማከናወን የዘለለ አይደለም፡፡

የነርቭ ስፔሻሊስቱ ፕሮፌሰር ረዳ ተክለሃይማኖት ከብዙ ዓመታት በፊት በአንድ የገጠር አካባቢ በፓርኪንሰን ላይ ጥናት እንዳካሄዱ፤ በጥናታቸውም መሠረት ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ያለው የሚጥል በሽታ ሆኖ እንደተገኘና የፓርኪንሰንን ችግር ግን ከመጨረሻዎቹ ሁለተኛ ሆኖ እንዳገኙት ከፍተኛ ኦፊሰሩ ተናግረዋል፡፡

ከዛ ወዲህ በሽታው ሊጨምር ወይም ሊቀንስ እንደሚችል፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ሆነ ከሌሎች የምርምር ተቋማት ይህንኑ አስመልክቶ የመነጨ መረጃ እስካሁን እንዳልቀረበ፣ በዚህ ደረጃ ለሚገኝ በሽታ ትኩረት እንዲቸረው መደረጉ በእጅጉ አስቸጋሪና ከባድ እንደሚሆን አስረድተወል፡፡

ዶ/ር አብርሃም አሰፋ የአርመር ሀንሰን ሪሰርች ኢንስቲትዩት የሪሰርችና ኢኖቬሽን ተጠባባቂ ምክትል ዳይሬክተር ስለዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው ‹‹ኢንስቲትዩቱ በፓርኪንሰን ዙሪያ የምርምር ሥራ አላካሄደም፡፡ ምክንያት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ተላላፊ በሆኑ በሽታዎች ዙሪያ የክሊኒካል ሪሰርች ሥራ ሲያከናውን በመቆየቱና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይኸው እንደጠበቀ ሆኖ የሕክምና አገልግሎት የሚሻሻልበትን ሐሳብ የሚያቀርብ የክልኒካል ሪሰርች ማዕከል ወይም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክሊኒካል ምርምር ክንፍ በመሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከመንቀሳቀስ ባሻገር ፓርኪንሰንን አስመልክቶ የሞከረው ሥራ እንደሌለ የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...