‹‹ለቤተሰቦቼ የመጀመርያ ልጅ ነኝ፡፡ ቤተሰቦቼ እኔና ታናናሾቼ ጠዋት ተነስተን ታጥበን ምግብ እንድንበላ፣ ልብሳችንን በአግባቡ እንድንለብስ፣ ትምህርት ቤት እንዳናረፍድና እንድናጠና ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎች ይጠቀሙ ነበር፡፡ እኛን በሚፈልጉት መንገድ ማስኬድ ግን ቀላል አልነበረም፡፡ ከዘዴዎቻቸው መካከል ‹‹ቼሪ ጋር ትወሰዳላችሁ›› የሚለው የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆን ሲያምኑ፣ አዘውትረው ይጠቀሙበት ጀመሩ፡፡ አንድ ቀን ቼሪ ጋር እንወሰዳለን ብለን ተስፋ በማድረግ ከቤተሰቦቻችንን ትዕዛዝ ላለመውጣት እንጣጣር ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው የልጆች ጊዜ አያመልጠንም፡፡ ቼሪና አባባ ተስፋዬ አትዋሹ፣ ታላላቆቻችሁን አክብሩ፣ ለትምህርት ትኩረት ስጡ፣ ለቤተሰቦቻችሁ ታዘዙ የሚሉና ሌሎችም ገንቢ ምክሮች ሲያስተላልፉ እንቀበላለን፡፡ በተለይ ቼሪን በጣም ስለምንወዳት የምትለውን እንሰማለን፡፡ ቤተሰቦቻችን አንድ ቀን ያለችበት ቦታ ይወስዱናል ብለን በጉጉት እንጠባበቃለን፡፡ መቼ እንደሆነ ባናውቅም ያ ቀን ሲደርስ ቼሪ ጋር ለብሰን የምንሄደውን ልብስ መርጠን አስቀምጠንም ነበር፤›› በማለት ትውስታዋን ያካፈለችን ሳራ ሚካኤል ናት፡፡
ሳራ ልጅነቷን ስታስታውስ ቼሪን አትዘነጋም፡፡ እስክታድግ ድረስ ቼሪ በዕውን ያለች እንጂ ፓፔት መሆኗን አታውቅም ነበር፡፡ ቤተሰቦቿ አድርጊ ከሚሏት ነገሮች በበለጠ የቼሪን ምክሮች ትሰማ እንደነበርም ታስታውሳለች፡፡ ይህንን እውነታ የሚጋሯት በርካቶች ናቸው፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚተላለፈው የልጆች ጊዜ ሲነሳ በጉልህ የሚታወሱት ቼሪና አባባ ተስፋዬ ናቸው፡፡ እንደ ዛሬው ቴሌቪዥን በየቤቱ ሳይገባ ቴሌቪዥን ያላቸው ሰዎች ቤት በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በጎረቤት ልጆች ይጨናነቅ ነበር፡፡ የልጆች ጊዜን ለመመልከት ሳምንቱን ሙሉ ይጠባበቁ የነበሩ ሕፃናት ቴሌቪዥን ፊት ለፊት ሰብሰብ ብለው ይቀመጣሉ፡፡ አባባ ተስፋዬ (ተስፋዬ ሳህሉ) በቴሌቪዥኑ ስክሪን ሲታዩ ቆመው ይቀበላሉ፡፡ አባባ ተስፋዬ እርስ በርስ አትገፋፉ ሲሉ ወይም ሌላ ነገር ሲናገሩም ልጆቹ ከመተግበር ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ልጆች ቼሪንም ስለሚወዷት ትዕዛዟን ይቀበላሉ፡፡ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲያደርጉ የሚፈልጉትን ነገር ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው በመደወል በቼሪ በኩል ያስተላልፉ እንደነበርም ይናገራል፡፡
ቼሪ በኮሜዲያን አስረስ በቀለ የተፈጠረች የላም ገፀ ባህሪ ያላት ፓፔት ስትሆን፣ ለዓመታት በሕፃናት ዘንድ እንደተወደደች ዘልቃለች፡፡ አስረስ እንደ ብዙ ሕፃናት ቴሌቪዥን ሲመለከት ከኢትዮጵያ ውጪ በተሠሩ የፓፔት ትርዒቶች ይማረክ ነበር፡፡ ፓፔቶች እንዴት እንደሚሠሩ ለማወቅም ትርዒቶቹን በአጽንኦት ይከታተል ጀመር፡፡ ‹‹ፓፔቶቹን እንዴት ማንቀሳቀስ እንደሚቻል ተመስጬ አይ ነበር፡፡ ፓፔቶች ስለሚወደዱ ልጆችን በሚፈለገው መንገድ መቅረፅ ይቻላል፤›› የሚለው አስረስ፣ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመቀጠር ዕድል ሲያገኝ የፓፔት ትርዒት የማሳየት ምኞቱን የሚያሳካበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ቼሪን ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሲወጡ ጠብቆ በማዘጋጃ ቤት ግቢ ውስጥ አሳየ፡፡ ልጆቹ ባዩት ነገር ሲደሰቱ ትርዒቱ ስኬታማ እንደሚሆን በማመን በቴሌቪዥን መተላለፍ ጀመረ፡፡ ቼሪና አባባ ተስፋዬ የሚጣመሩበት ይህ መርሐ ግብር ወደ 12 ዓመት ገደማ ታይቷል፡፡ ልጆችን ያንፃሉ ተብለው የታመነባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም የግል ንፅህናን መጠበቅ፣ አካባቢን መንከባከብ፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ መሆንና የመሳሰሉት ይዳሰሳሉ፡፡
ልጆች በየዕድሜ እርከናቸው ሊገነዘቧቸው የሚችሉ ሐሳቦችን ለማስጨበጥ ከሚመረጡ መንገዶች የፓፔት ትርዒትና አኒሜሽንን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ፓፔቶች በቀላሉ የልጆችን ቀልብ ስለሚገዙ ለአስተዳደጋቸው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ይቻላል፡፡ በሥነ ልቦና ባለሙያዎች የተሠሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ፓፔቶች ለልጆች ሥነ ልቦናዊ ዕድገት የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ እንደ ንባብ ያሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ ከማስቻል በተጨማሪ የተሻለ ማኅበራዊ ትስስር እንዲፈጥሩም ያግዛሉ፡፡
አስረስ እንደሚለው፣ ለኢትዮጵያውያን ሕፃናት ዕድገት አስተዋጽኦ እንድታደርግ የተፈጠረችው ቼሪ የተጫወተችውን ሚና ከቤተሰቦች በሚሰጠው አስተያየት ተረድቷል፡፡ ወደ ቴሌቪዥን ጣቢያው የሚሄዱና የሚደውሉ፣ ደብዳቤ የሚጽፉ ቤተሰቦች በልጆቻቸው ያስተዋሉትን ለውጥ ይገልጹ ነበር፡፡ ሆኖም ትርዒቱ ልጆችን የሚያታልልና እንደሆነ በማመን የሚነቅፉ እንደነበሩም ይናገራል፡፡ ትርዒቱን የሚያበረታቱ የቴሌቪዥን ጣቢያው አመራሮች እንዳሉ ሁሉ አስፈላጊነቱን የማያምኑበትም ነበሩ፡፡
ትርዒቱ ይዘጋጅበት የነበረው ሁኔታ ምቹ እንዳልነበረ ያስታውሳል፡፡ ከፓፔቷ ጀርባ ሆኖ ሰውነቷን እየተንቀሳቀሰና እየተነጋገረችም እንዲመስል ለማድረግ የሚሞክረው በጠባብ ቦታ ነበር፡፡ ቼሪን ተዓማኒ ለማድረግ በእጁ እያንቀሳቀሳት ከመድረክ ጀርባ ቁምሳጥን ውስጥ ይደበቃል፡፡ ከጊዜ በኋላ ቼሪን ለመጎብኘት ወደ ጣቢያው የሚሄዱ ልጆች ቼሪ ለምን አትቆምም? እያሉ ይጠይቁ ጀመር፡፡ ፓፔቷን ለማቆም የሚያስፈልገውን ግብዓት ማሟላት ስላልቻለ ቼሪን በእጅ የምትንቀሳቀስ (ሀንድ ፓፔት) ቼሪ የምትለብሰውን የመሰለ ልብስ በራሱ መጠን አዘጋጅቶ በመልበስ ወደ መተወን ገባ፡፡ በዚህ መንገድ ለዓመታት ከሠራ በኋላ ዝግጅቱ በ2008 ዓ.ም. ተቋረጠ፡፡
አሁን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን በሚተላለፈው የልጆች መርሐ ግብር ኢትዮጲስ የተባለች ገፀ ባህሪ ይጫወታል፡፡ ኢትዮጲስ ለልጆች በሚዘጋጁ ፌስቲቫሎች፣ የመጻሐፍት ዐውደ ርዕዮችና በልደትም ትገኛለች፡፡ ከኢቢሲና ኢቢኤስ ባሻገር በቅርቡ ሥርጭት የጀመሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የልጆች መርሐ ግብሮች ቁጥርን ቢያሳድጉትም፣ ካለው ፍላጎት አንፃር ዘርፉ ብዙም አልተሠራበትም፡፡
በሌሎች አገሮች ለልጆች መርሐ ግብሮች በየሳምንቱ ጥቂት ሰዓት ከመስጠት ባለፈ የልጆች ዝግጅቶች ብቻ የሚተላለፉባቸው ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ በአገራችን እንደ ዓረብሳትና ዲኤስቲቪ ያሉ አማራጮችን የመጠቀም ዕድል ያላቸው ልጆች ኤምቢሲ ስሪና ካርቱን ኔትወርክ ይከታተላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በነዚህ ጣቢያዎች መጠን የልጆች መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት ሊከብድ ቢችልም ባለው ሁኔታም በቂ ነገር ተሠርቷል ለማለት ይከብዳል፡፡
‹‹ባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለልጆች ዝግጅት የተሰጠው ሰዓት በቂ አይደለም፡፡ በሚፈለገው መጠን ለመሥራት በቂ ግብዓትም የለም፤›› ይላል አስረስ፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለልጆች መርሐ ግብሮች የሚሰጡት ጊዜና እንደ ፓፔት ትርዒት ላሉ ዝግጅቶች የሚመደበው በጀት ጥቂት መሆኑን ይናገራል፡፡ ለአገሪቱ ዕድገት ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል ልጆችን ያማከሉ መበከራት እንዳለባቸውም ያክላል፡፡ ‹‹ትልቁ በጀት መውጣት ያለበት በልጆች ዝግጅቶች ነው፡፡ ዜጋ መቅረፅ ከሚያስችሉ መንገዶች ፓፔት መጠቀም አንዱ ነው፤›› ይላል፡፡
ሐሳቡን የምትጋራው ሳራ፣ ለልጆች የሚሆኑ አገርኛ ዝግጅቶች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸው ሕፃናት ወደ ውጭ እንዲያማትሩ እንዳደረገ ታምናለች፡፡ በተለይም የፓፔት ትርዒት ቤተሰቦችና መምህራን ለታዳጊዎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ስለሚያግዙ ሊተኮርባቸው ይገባል ትላለች፡፡ የትርዒቶቹ ቁጥር መጨመር ብቻውን ለውጥ አያመጣምና የይዘት ጉዳይም ይታሰብበት ስትልም ትናገራለች፡፡ ከቀደሙት ጊዜያት በተቃራኒው በዛሬው የመረጃ ዘመን፣ ልጆች በርካታ የመዝናኛ አማራጮች አሏቸው፡፡ የፓፔት ትርዒቶች ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደርጋሉ? የሚለውን ጥያቄም ታነሳለች፡፡
የአራት ልጆች አባት የሆነው ግርማዬ እጅጉ (ስም ተቀይሯል)፣ የኢትዮጵያ የፓፔት ትርዒቶች ይዘትና የአቀራረባቸው ጥራትም በአሁን ወቅት ልጆች ካሏቸው አማራጮች ጋር የሚወዳደር መሆን አለበት ይላል፡፡ ‹‹ልጆቼ በዓረብሳት የሚተላለፉትን እንደ ዶራና ባርኒ ያሉ ፊልሞችን አዘውትረው ይመለከታሉ፡፡ አንዳንዶቹ ፊልሞች ድብድብ ያለባቸው ስለሆኑ ልጆቼ ተዋንያኑን አስመስለው ለመደባደብ ይሞክራሉ፤›› የሚለው ግርማዬ፣ አገር ውስጥ የሚሠሩና ይዘታቸው ለልጆች የሚመጥን ዝግጅቶች ቢቀርቡ እንደሚመረጥ ያስረዳል፡፡
የፓፔት ትርዒቶች አለመበራከትን እንደ ማሳያ በመውሰድ አጠቃላይ የልጆች መዝናኛ ዘርፍ በስፋት እንዳልተሠራበት ይናገራል፡፡ አገርኛ ይዘት ያላቸው ፕሮዳክሽኖች ሰፊ ገበያ እንደሚኖራቸውም ይገምታል፡፡ በኢቢሲ የሚተላለፈውን ‹‹ፀሐይ መማር ትወዳለች››ን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳል፡፡ ፀሐይ የምትባለው ቀጭኔና ሌሎችም ገፀ ባህሪዎች ቁጥርና ፊደላትን ያስተምራሉ፡፡ ሌሎችም ሕፃናትን የሚያንፁ ጉዳዮችንም ያነሳሉ፡፡
‹‹ፀሐይ መማር ትወዳለች›› ከሦስት እስከ ስምንት ዓመት ያሉ ታዳጊዎችን ያማከለ ሲሆን፣ በዊዝ ኪድስ ወርክሾፕ ከሚዘጋጁ ልጆች ተኮር ዝግጅቶች አንዱ ነው፡፡ የወርክሾፑ አጋር መሥራች ብሩክታዊት ጥጋቡ ‹‹የጥበብ ልጆች›› የተሰኘውን ተከታታይ የልጆች አኒሜሽን ፊልም በዓመቱ መባቻ ላይ ስታስመርቅ ከሪፖርተር ጋር ባደረገችው ቆይታ፣ መሰል ፕሮዳክሽኖች ለልጆች ሥነ ልቦናዊ ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ ገልጻ ነበር፡፡ ግርማዬም የፓፔት ትርዒቶች ትምህርት፣ ጤናና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያተኮሩና የአገሪቱ ልጆችን የሚወክሉ ወይም የሚመስሉ ገፀ ባህሪዎች መፈጠር አለባቸው ይላል፡፡
ከጥንታዊ ግሪክና ግብፅ ጀምሮ የፓፔት ትርዒት ዘመናትን ያስቆጠረ ጥበብ ሲሆን፣ ልጆችን ታሳቢ ካደረጉ ትርዒቶች በተጨማሪ ለአዋቂዎች የሚቀርቡ የፓፔት ተውኔቶችም ታዋቂ ናቸው፡፡ አንገብጋቢ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች በፓፔት ቴአትር የቀረቡባቸው ጊዜዎችም አሉ፡፡ ፓፔተሮች ጣታቸውን ወይም እጃቸውን በመጠቀም የሚያንቀሳቅሷቸው ፓፔቶች እንዲሁም በገመድ በመታገዝና በብርሃንና ጥላ የሚሠሩም ይጠቀሳሉ፡፡
በእንስሳት ወይም በምናባዊ ገፀ ባህሪዎች አምሳያ የሚሠሩ ፓፔቶችን እንቅስቃሴ በመከተል ፓፔተሮች ንግግር ያክሉባቸዋል፡፡ ፓፔቶች በልጆች ያላቸውን ተወዳጅነት ከግምት በማስገባት፣ ከቴሌቪዥን ዝግጅቶች ጎን ለጎን በሕፃናት ቴአትርና በትምህርት ቤቶችም ጥቅም ላይ ቢውሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡ ልጆች የሚወዷቸው የፓፔት ገፀ ባህሪዎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት የመቀበል አዝማሚያቸው ከፍተኛ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
ስለ ተወዳጅ የፓፔት ገፀ ባህሪያት ሲነሳ እ.ኤ.አ. ከ1960ዎቹ ጀምሮ ለዓመታት የዘለቀው ተከታታይ የልጆች ዝግጅት ሴስሚ ስትሪት ይነሳል፡፡ ኤልሞና ቢግ በርድ በልጆች የሚወደዱ የፊልሙ ገፀ ባህሪያት ሲሆኑ፣ ባለፉት ዓመታት ሴስሚ ስትሪት ከአሜሪካ ባሻግር በ150 አገሮች በተለያዩ ቋንቋዎች መቅረብ ጀምሯል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሴስሚ ስትሪት ልዑካን ኢትዮጵያ ተገኝተው ከገፀ ባህሪያቱ መካከል ኤልሞ ላይ በማተኮር፣ ‹‹ኤልሞን እወደዋለሁ›› በሚል ፊልሙን በቃና ቴሌቪዥን በአማርኛ ማስተላለፍ እንደሚጀምሩ አሳውቀዋል፡፡
ልጆችን የሚመጥኑ መረጃዎችን ለማስተላለፍና ለማስተማር ተመራጭ ሆኖ የተገኘው ሴስሚ ስትሪት፣ በኢትዮጵያ ዐውድ ተተርጉሞ እንደሚቀርብ የቃና ቲቪ አጋር መሥራቾች አቶ ዘረሰናይ ብርሃነ መሐሪና ኤልያስ ሹልዝ ይገልጻሉ፡፡ ዘረሰናይ እንደሚለው፣ ልጆች በሚገነዘቡት አቀራረብ ለምሳሌ ጓደኛ ስለማፍራትና ሌሎችም ግላዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ማስተማር ይቻላል፡፡ ልጆችን እያዝናኑ ትምህርት መስጠት ከሚቻልባቸው መንገዶች የፓፔት ትርዒት ቀዳሚ እንደመሆኑ በጣቢያው ለልጆች ዝግጅት በተመደበው ጊዜ ፊልሙ እንደሚታይም ያስረዳል፡፡ የልጆች የመዝናኛ ኢንዱስትሪ አለ ለማለት እንደማያስደፍር የሚናገረው አቶ ዘረሰናይ፣ በዚህ ረገድ ‹‹ኤልሞን እወደዋለሁ›› ለልጆች ዕድገት እንደሚያግዝ ያስረዳል፡፡
‹‹ልጆቻችንን ማስተማር የምንፈልገውን የምናስተምርበት መንገድ ነው፤›› ሲል ገፀ ባህሪውን ይገልጻል፡፡ ሴስሚ ስትሪት የአሜሪካ ሕፃናትን ታሳቢ በማድረግ የተሠራ ቢሆንም በአማርኛ ሲተረጎም፣ በኢትዮጵያ ያሉ ጉዳዮች እንዲሁም በዓለም ላይ ያሉ ሕፃናት ባጠቃላይ ሊጋሯቸው የሚችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ይላል፡፡
ሳራ በልጅነቷ ያስገርሟት ከነበሩ የፓፔት ገፀ ባህሪዎች መካከል የሴስሚ ስትሪትን ቢግ በርድ ትጠቅሳለች፡፡ ደማቅ ቀለም ያላቸው እንደ ቢግ በርድና ኤልሞ ያሉ ገፀ ባህሪዎች የሚቀርቡት ዕውን በሚመስል መንገድ ስለሆነ እንደነሱ ያሉ እንስሳት እንዳሉ ታምን ነበር፡፡ ስለ ቁጥር፣ ፊደል፣ ቤተሰባዊ ትስስር ሲያስተምሩም በአንክሮ ተከታትላለች፡፡ አሁን በሃያዎቹ መጨረሻ የምትገኘው ሳራ፣ ልጆች ሊስቡ የሚችሉ አገሮች የፓፔት ትርዒቶች ቢበራከቱ በቀላሉ የበርካቶችን ትኩረት እንደሚያገኙ ትገልጻለች፡፡ ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው አቶ ዘረሰናይ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ልጆችን የሚወክሉና የልጆቹን ጉዳዮች የሚያንሱ ገፀ ባህሪዎች ጉልህ ሚና አላቸው ይላል፡፡