በኳታር በሚገኘው የካታራ ባህል መንደር ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ባህልና ቅርስ የሚያስተዋውቅ ትርዒትና ዐውደ ርዕይ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀርቧል፡፡ ለሁለት ቀናት የቀረበው ባህላዊ የሙዚቃ ትርዒት በኢትዮጵያ እስላማዊ ቅርሶች ዐውደ ርዕይ የታጀበ መሆኑን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ በዶሃ ከተማ በተከበረው የኢትዮጵያ ቀን የተዘጋጀው ዐውደ ርዕዩ በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሠዓሊዎች የሣሏቸውን ያሁን ዘመን ሥራዎችን ጨምሮ፣ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቦታዎች፣ የአገሪቱ እስላማዊ ቅርሶች የሚያሳዩ ፎቶዎችንም አካቷል፡፡ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ማኅበራዊ ሕይወት የያዙ ምስሎችም የዐውደ ርዕዩ አካል ናቸው፡፡
በኳታር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከካልቸራል ቪሌጅ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ዐውደ ርዕይና ትርዒቱ መክፈቻ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደማርያም (ዶ/ር)፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም›› ዳይሬክተር ማሚቱ ይልማና በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ እንዲሁም የካልቸራል ቪሌጅ ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ካሊድ ቢን ኢብራሂም ሱላጢ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡ ዐውደ ርዕዩ እስከ ሚያዝያ 7 ቀን ድረስ ክፍት እንደሚሆን ታውቋል፡፡