Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለወላጆች ራስ ምታት የሆነው የትምህርት ቤት ክፍያ

ለወላጆች ራስ ምታት የሆነው የትምህርት ቤት ክፍያ

ቀን:

ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩ የግል ትምህርት ቤቶች በአገሪቱ ያላቸው የትምህርት አገልግሎት ድርሻ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለአንድ ተማሪ የሚጠይቁት ወርኃዊ ወይም ተርም (2 ወር ከ15) ክፍያ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዓመት ወይም በሁለት ዓመት አንዴ ከ10 በመቶ እስከ 50 በመቶ እንዲሁም ከዚህ በላይ ሲጨምሩም ይስተዋላሉ፡፡

ይህ ወላጆችን በተደጋጋሚ ለመንግሥት አቤት እንዲሉ ያደረገ ቢሆንም፣ ትምህርት ቤቶች ወርኃዊ ክፍያ ላይ የሚያደርጉትን ጭማሪ ሊያለዝብ አልቻለም፡፡

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያና አማራጭ መፈለጊያ ጊዜ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሲከፈት ወይም አጋማሽ ላይ የሚያደርጉትን ጭማሪ አስቀርቷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን በየዓመቱ አሊያም በየሁለት ወላጆች ለልጆቻቸው የሚጠየቁት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ራስ ምታት እንደሆነባቸው በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አቤቱታዎችም በተለያዩ ጊዜያት ይሰማሉ፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች ባለቤቶች በበኩላቸው ባገኟቸው መድረኮች ሁሉ የተማሪ ክፍያ በየጊዜው የሚጨምሩት አብዛኞቹ ተከራይተው የሚሠሩ በመሆናቸው፣ በደመወዝ ተወዳዳሪ ሆነው መምህራን ለማግኘትና የትምህርት ሥራ ወጪው ከባድ ስለሆነ ነው ይላሉ፡፡

በመንግሥት ትምህርት ቤት በሚሰጠው ትምህርት ጥራት እንደማይተማመኑና ለዚህም ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ማስገባታቸውን የገለጹልን ወላጅ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ በየዓመቱ እየጨመረ ኪሳቸውን ቢፈታተነውም የቱንም ያህል ዋጋ ከፍለው ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ማስተማርን እንደሚመርጡ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ምክንያታቸው በግል ትምህርት ቤት ከመንግሥት በተሻለ የልጆቹን የትምህርት አቀባበልና የሥነ ምግባር ሁኔታ በየቀኑ የሚለዋወጡበት የመምህሩና የወላጅ መዝገብ ማግኘት መቻላቸውን ነው፡፡ ወላጅ ለትምህርት ቤቱ ቀድሞ ሳያሳውቅ ተማሪው ቢቀር፣ የቤት ሥራ ባይሠራ፣ በባህሪው ላይ ትላንት ከነበረው ዛሬ ለውጥ ቢያሳይ፣ (በጎም መጥፎም) የግል ትምህርት ቤቶች ለወላጅ ማሳወቃቸው፣ ተማሪዎችንም ያለወላጅ ፈቃድ ከትምህርት ቤት ግቢ የማያስወጡ መሆኑ ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ፡፡

ክፍያው ሲታይ ግን ለወላጆች ከባድና የተጋነነ ነው፡፡ ወላጆች በደመወዛቸው ላይ ጭማሪ ሳያገኙ የተማሪዎች የወር ሒሳብ በየዓመቱ እየጨመረ መሄዱም፣ የቤት ውስጥ አኗኗርን እየጎዳው፣ ወላጆችንም ለጭንቅ እየዳረገ ይገኛል ይላሉ፡፡

የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ወርሂዊ ገቢ ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ የግል ትምህርት ቤቶች የሚጠይቁት ወርኃዊ ክፍያ የወላጆችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆን አለበትም ይላሉ፡፡ ለዚህም ለግል ትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ችግር የሆነውን ቤት ኪራይ ለመፍታት፣ መንግሥት ለሆቴል ብሎ መሬት እንደሚዘጋጀው ሁሉ ለትምህርት ቤት ተብሎ መዘጋጀት አለበት ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለኢንዱስትሪ መንደርና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ካልተሰጠም፣ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ገብቶ የሚሠራ ጥራት ያለው የሰው ኃይል ማግኘት ፈታኝ ይሆናልም ይላሉ፡፡

በሳፋሪ አካዴሚ ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ አባት እንደሚሉት፣ በየሁለት ዓመቱ የሚጠየቁት ወርሃዊ ክፍያ ጭማሪ ልጆቻቸውን በትምህርት ቤቱ ለማስቀጠል ከማይችሉበት ደረጃ ማድረሱን ይናገራሉ፡፡ በትምህርት ቤቱ ትምህርት አሰጣጥም ሆነ በተማሪዎች ሥነ ምግባር ላይ ቅሬታ እንደሌላቸው የሚናገሩት እኚህ አባት፣ ትምህርት ቤቱ በ2010 ዓ.ም. ለሚያደርገው የወርኃዊ ክፍያ ጭማሪ ከወላጆች ጋር ለመወያየት ለዛሬ ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደጠራቸው ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ የሚደረግ የትምህር ቤት ክፍያ ጭማሪ ላይ መንግሥት ገደብ አያበጅም ወይ? ሲሉ የሚጠይቁት ቅሬታ አቅራቢ፣ በተለያዩ ጊዜያት ክፍለ ከተማና ትምህርት ቢሮ ድረስ በመሄድ ቢጠይቁም በነፃ ገበያ ትምህርት ቤቶችን ይህንን ያህል ብቻ አስከፍሉ ብሎ ማስገደድ እንደማይቻል ተገልጾላቸዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች በየዓመቱ መጀመሪያ ለሚያደርጉት ጭማሪ ትምህርት ዓመቱ ከመጠናቀቁ ሦስት ወራት ቀድመው ከወላጅ ጋር መወያየት እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መመሪያ ያሳያል፡፡ በመሆኑም ከግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከወላጆች ጋር ውይይት የጀመሩ፣ ለመወያየት ጥሪ ያደረጉም አሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱ ሳፋሪ አካዴሚ ሲሆን፣ የአካዴሚው ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ አየለ፣ በ2010 ዓ.ም. ወርኃዊ ክፍያ ላይ ጭማሪ ለማድረግ ከወላጅ ጋር ለመወያየት ያቀዱት  ትምህርት ቤቱ የትምህርቱን ጥራት ከማስጠበቅ አንፃር የተለያዩ ወጪዎች ስላሉበት ነው ብለዋል፡፡

ሳፋሪ አካዴሚ በአዲስ አበባ ሦስት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶቹ ያረፉት በሊዝ በተገዙ መሬቶች ላይ ነው፡፡ አቶ ኢዮብ እንደሚሉት፣ ትምህርት ቤቱ በሊዝ ለገዛው ቦታና ለግንባታ 51 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ ባንኮች የተበደረ ሲሆን፣ ብድሩንም መክፈል ጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባስቀመጠው መመሪያ መሠረት የትምህርት ቤቶችና የትምህርት ጥራት መጠበቅ ስላለበትም የትምህርት ቤቱ ግንባታዎች መስፈርቱን ዓላማ ያደረጉ ናቸው፡፡

ትምህርት ቤቱ ከ350 በላይ መምህራንና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችም አሉት፡፡ ተማሪዎችንም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተቀብሎ ያስተናግዳል፡፡ ከቅድመ መደበኛ ተማሪ (ነርሰሪ) እስከ 12ኛ ክፍል ድረስም በወር ከ1014 እስከ 1072 ብር ከ50 ሣንቲም ያስከፍላል፡፡ እንደ አቶ ኢዮብም፣ ትምህርት ቤቱ 80 በመቶ ለሚሆኑት መምህራን 50 በመቶ፣ ለቀሪዎቹ እስከ 50 በመቶ ጭማሪ አድርጓል፡፡ በቀጣይ ዓመት ደግሞ የትራንስፖርት አበል ለመክፈል ዕቅድ ይዘዋል፡፡

መንግሥት ለመንግሥት መምህራን የደመወዝ ጭማሪ፣ ቤት፣ እንደሁም የትራንስፖርት እየከፈለ መሆኑን በማስታወስም፣ ለመምህራን መንግሥት ከሚሰጠው ክፍያና ጥቅማ ጥቅም የተሻለ መስጠት ካልተቻለ፣ ለግል ትምህርት ቤቶች መምህራን ማግኘት ፈታኝ እንደሚሆንም ይናገራሉ፡፡

ትምህርት ቢሮው የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቁ ጠንካራ መሥፈርቶች አስቀምጦ የኢንስፔክሽን ሥራ እንደሚሠራ፣ መሥፈርቶቹን ከዓመት ዓመት ያላሟሉት ላይም ዕርምጃ እንደሚወስድ በማስታወስም፣ ጥሩ ዜጋ ለማፍራት፣ ወላጆች በልጆቻቸው እንዲደሰቱና እንዲኮሩ ለማድረግ ትምህርት ቤቱ በሥነ ምግባርም ሆነ ጥራት ባለው ትምህርት የታነፁ ተማሪዎችን ለማውጣት ሲል ተመጣጣኝ ጭማሪ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ለ2010 ዓ.ም. የ30 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ያሰበ ሲሆን፣ ይህንን ከማድረጉ አስቀድሞ ከወላጆች ጋር ለመወያየትና ከስምምነት ለመድረስ ማቀዱን፣ ይህም የሚከናወነው በትምህርት ቢሮ መመሪያው መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ወላጅ ሲያዝንና ሲከፋ ማየት አንፈልግም፣ አማራጭ ስላጣን ነው፣ ወላጆች ላይ ኢፍትሐዊ ጭማሪ ማድረግ ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤቱ እንዲያስወጡ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ከባንክ ተበድሮ ለሚሠራው ትምህርት ቤታችን ራስ ምታት ነው›› የሚሉት አቶ ኢዮብ፣ ወላጆችም ሆነ የወላጆች ኮሚቴው አካዴሚው ያለውን ገቢና ወጪ በፈለጉበት ጊዜ ማየት እንደሚችሉ አክለዋል፡፡

በየጊዜው እየናረ የሄደውን የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ወርኃዊ ክፍያ አስመልክተን ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት፣ የግል ትምህርት ቤቶች ከወላጆች ጋር ጭማሪው ከመደረጉ ሦስት ወራት አስቀድሞ ተወያይተው በአሳማኝ ምክንያት ከስምምነት ደርሰው ጭማሪ ማድረግ የሚችሉበት አሠራር በመመሪያ መቀመጡንና ቀድሞ መወያየቱ ያስፈለገውም ወላጆች ከአቅማቸው በላይ ክፍያ ከተጫነባቸው ሌላ አማራጭ ትምህርት ቤት እንዲያገኙ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቶች ሸማቹን (ወላጆችን) አሳታፊ አድርገው የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ማድረግ እንደሚችሉና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መመሪያ በሚያዘው መሠረትም ወላጆቸን ቀድመው ማወያየትና ከውሳኔ መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ወላጆችን ሳያወያዩ ለሚያደርጉት ጭማሪ ግን በባለሥልጣኑ የዳኝነት ችሎት ትምህርት ቤቶች ይከሰሳሉ፡፡ ወላጆችም ከመመሪያ ውጪ ተጨምሮብናል የሚሉት ክፍያ ካለ በ8478 ወይም በ8077 በመደወል አቤት ማለት ይችላሉ ብለዋል፡፡

በአስተደደሩ ደረጃ ከሚገኑት 2132 የትምህርት ተቋማት 460ው ብቻ የመንግሥት ሲሆኑ፣ የተቀሩት 79 በመቶ ያህሉ የግል ናቸው፡፡ የግል ትምህርት ተቋማት በተማሪ ደረጃም 53 በመቶ ያህሉን ይዘዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምሕርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላራቶሪ ኤጀንሲ፣ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ላይ ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. ያደረገውን ኢንስፔክሽን አስመልክቶ በኅዳር 2009 ዓ.ም. ላይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ የተገኙ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች፣ ለትምህርት ቤት ግንባታ የሚውል ቦታ ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ለትምህርት ቤት ግንባታ ተብሎ ለብቻ ቦታ እንደማይዘጋጅ፣ ጨረታ ሲወጣም ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር እንዲወዳደሩ እንደሚደረግና ትምህርት ቤቶች ካለባቸው ጫና አንፃር በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን በጨረታ አሸንፈው መሬት ማግኘት እንደማይችሉም ቅሬታ አቅርበው ነበር፡፡

ሆኖም ትምህርት ቤት እንደ አንድ ትልቅ ኢንቨስትመንት ተቆጥሮ ለግንባታ የሚሆን ሥፍራ ለብቻ ሲሰናዳለት አይስተዋልም፡፡ የግል ትምህርት ቤት ባለቤቶችም ይህን ክፍተት በመጥቀስ ለቤት ኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንዳለባቸውና ለትምህርት ቤት ወርኃዊ ክፍያ መወደድ ዋናው ምክንያትም ይኸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡  

በወቅቱ በተደረገ ኢንስፔክሽንም የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት በውጤትም ሆነ በሥነ ምግባር የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ሆኖም ከተማሪዎች ወርኃዊ ክፍያ መወደድ ጋር በተያያዘ በየጊዜው ይወቀሳሉ፡፡

የክፍያ መጠን እየጨመረ ሲሄድ እንጂ ሲረጋጋም አይስተዋልም፡፡ በዚህም ወላጆች መቸገራቸውን በተደጋጋሚ ይናገራሉ፡፡ ትምህርት ቢሮው እንደ አማራጭ ያስቀመጠውም ክፍያ ከመጨመሩ በፊት ወላጆችና ትምህርት ቤቱ እንዲወያዩና ከስምምነት እንዲደርሱ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ያስቀመጠውን ክፍያ መክፈል የማይችሉ ወላጆች ሌላ አማራጭ ትምህርት ቤት እንዲፈልጉም ይገደዳሉ፡፡ ለልጆቻቸው በጥራትና በዋጋ የሚመጥን ትምህርት ቤት ማግኘት ግን ፈታኝ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ወላጆች ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...