Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ልብስ እንጂ ልብ አይሸጥም!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ነው የከባድ ሚዛን ትግሉ? ኑሮን ማለቴ ነው። ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ከጥቂት ዓመታት በፊት የከባድ ሚዛን የቦክስ ውድድር የሚደረገው በስንት አንዴ ስለነበር፣ ዓለም ፍልሚያውን ለማየት የሚኖረው ጉጉት ላቅ ያለ ነበር (በተለይ በጆሮ ተናካሹ ማይክ ታይሰን ዘመን)። አሁንስ? አሁንማ ኑሯችን በራሱ ከባድ ሚዛን ነው፡፡ እነሱስ (የከባድ ሚዛን ቦክስ ተፋላሚዎች) አንድም ለድልና ለዝና ብሎም ጠቀም ላለ ገንዘብ ነበር የሚፋለሙት። የእኛ አለ እንጂ ታግሎ ለሽንፈት፣ ሳይኖሩ ለመሞት። ኧረ ተውኝ እቴ! በቃ ምን የለን ምን የለን እንዲያው በባዶ ተስፋ ነው ያለነው፡፡ ጥቂቶች ተሳክቶላቸው ለኖሩ አብዛኞቻችን ዕድሜን በባዶ ስንገፋ እንደነ ባሻዬ አርጅተን ገርጅፈን ቁጭ። ያን ጊዜ ‘እርጅና መጣና ድቅን አለ ፊቴ እባክህ ተመለስ ልጅነት በሞቴ’ ቢሉ ቢጮሁ፣ ‘ዋ!’ ብሎ መቅረት ይሆናል እንደ ሰማይ አሞራ። አይ ጉድ፣ ዝም ብዬ በትካዜና በትችት ስንደረደረው ዝም ትሉኛላችሁ? ‹‹አንበርብር እንኳን እኛ የሦስተኛው ዓለም መሬት ራሱ ባይኖር ምንም አይጎድልም እኮ?›› አለኝ የባሻዬ ልጅ ደርሶ አፉ ቢያመጣለት።

ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ምንም እንኳ ዕውቀት ባያጥረው አንዳንዴ ማስተዋል እየከዳው ኩምሽሽ ይላል። ተስፋ ይቆርጥና የሚያየውን ሁሉ ይራገማል። ‹‹ተው! አንተ ወጣት አይደለህ እንዴ? ምንድነው እንዲህ በህዳሴ ዘመን ንግግርህ ሁላ ከፋ?›› ስለው፣ ‹‹አዬ አንበርብር ዘንድሮ እኮ ተስፋ መቁረጥ ያውቃሉ በሚባሉት ብሷል፤›› አለኝ። ሳስበው ካለማወቅ የሚጎዳውና የሚጠፋው ሳይሆን እያወቀ የሚቀልጠው ልቋል። በራሱ ቢያደርጉበት የማይወደውን ሆነ ብሎ በሌሎች የሚያደርገው በዝቷል። ሚስቱን ቢያሸፍቱበት የማይታገስ ሁላ የሰው ትዳር ለማፍረስ መከራውን ያያል። አምስት ሳንቲም ከኪሱ ብትጠፋ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው በሕዝብና አገር ሀብት ይነግዳል። መብቴን አትጋፉ ለማለት ማንም የማይቀድመው ደግሞ በሰው መብት ‘ዕቃ ዕቃ’ ይጫወታል። ታዲያ በዚህ ዘመን ሰው መኖር ቢፀየፍ ይፈረድበታል? እስኪ ፍረዱ!

እና ጨዋታም አይደል የያዝነው? ያለፈውን ከማሞገስ የያዙትን ከማክፋፋት ምንም እንደማይገኝ የማውቀው እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ‘ወደፊት’ ብዬ ወደ ሥራዬ ተሰማርቻለሁ። ዘመኑን አማነውም አላማነውም፣ መንግሥትን አማረርነው አሞገስነውም መዓልት ሌቱ መምሸት መንጋቱን መቼ ይተዋል? እንዲያው ነው ኧረ! ታዳያላችሁ አንድ የሚከራየው ቤት ማግኘት የተቸገረ ሰው አላስቆም አላስቀምጥ ብሎኝ እንከራተታለሁ። ይገርማችኋል ይኼ ቤት አጥቶ ዕረፍት አሳጣኝ የምላችሁ ሰው፣ የተከራየውን ቤት ለቆ እንዲወጣ ምሕረት የለሽ ውሳኔ የተላለፈበት በዚህ ወር ነው። ‹‹ምንስ ቢሆን አሁን ሰላማዊ ሰው ቀርቶ ጠላት ይሸኛል?›› ብላቸው ባሻዬ፣ ‹‹ወይ አንተ ድሮና ዘንድሮ አንድ መሰለህ? ድሮ የሰው መድኃኒቱ ሰው ነውና እንዴት ተደርጎ? የአሁኑን ግን ምን እነግርሃለሁ አንበርብር? ያለ ገንዘብ ሰው ዘመድ አላውቅ ብሏል እኮ፤›› አሉኝ ከልጃቸው በባሰ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ፊታቸውን ሸፍኖት።

እነሆ ይኼን ያህል ዘመን ያስቆጠረ የሰው ልጅ የሥልጣኔ ሩጫ መጨረሻው በአፍቅሮተ ንዋይ ግብግብ ሊቋጭ ያሰፈሰፈ ይመስላል። ‘ትዝታ ታማኝ ነው ወረትን አያውቅም፣ እንደ ሰው ለገንዘብ ቦታውን አይለቅም’ እየተባለ እስከ መቼ ሰው በሰው ትዝታ ይዘልቅ እንደሆነም እንጃ። ‘እኔ አላማረኝም አዲስ ነገር በዝቷል፣ በኪስህ ተማመን ጎበዝ ፍቅር ጠፍቷል’ ያለው ሙዚቀኛ ትዝ ሲለኝ ደግሞ ግራ ይገባኝ ይጀምራል። ስንቱ ግራ አጋብቶን እንደምንዘልቀውም በራሱ ግራ ይገባል!

ሳናስበው የጀመርናትን የጭውውት ቀዳዳ እያሰፋን (ወግ አያልቅምና በዚህች ምድር) መጓዝ ጀመርን። ትንሽ እንደሄድን ጨዋታችንን አቁመን በስሱ ተከፍቶ ወደምንሰማው ‘ኤፍ ኤም’ ራዲዮ ሁለታችንም ጆሯችን ቀሰርን። የራዲዮ ለፋፊው እየደጋገመ ከዓመት በፊት ጋብቻቸውን ፈጽመው የመጀመሪያ ልጃቸውን ዓይን ለማየት ስለበቁት የእንግሊዝን ልዑላን ቤተሰብ ያወራል። ያወራል እንጂ አይጨርስም። ደንበኛዬ በጣም ተናዶ፣ ‹‹እሺ እንደ ዜና ይወራ ግድ የለም። ትንታኔ ውስጥ መግባት ምን አገባንና እኛ? ምናለበት ግን መንግሥት ቀልዶ ባያስቀልድብን?›› አለ። ‹‹እንዴት?›› አልኩት ጥቂት ላናግረው። ቀልብ በጠፋበት ዘመን ከቀልቡ ሆኖ የሚያወራ ሰው ጥቂት በመሆኑ፣ በሰማው ነገር እጅግ ተቆርቁሮ ሳየው ከልቡ መሆኑ ስለገባኝ። ‹‹እንዴት?›› አለኝ ዞር ብሎ አይቶኝ።

‹‹ስንት ለፕሬስ ነፃነትና ዕድገት የሚታገሉ ጋዜጠኞችን ‘እያከሸፈ’ እንደነዚህ ያሉትን የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊና ከማጎልበት ጨርሶ የሚያኮስስ ረብ አልባ ዘገባ የሚዘግቡትን ዝም ማለቱ ነዋ። ስንት ቁም ነገር ማውራት በሚገባን ሰዓት፣ ስንት ልንነጋገርባቸው የሚገባን ጉዳዮች እያሉ ሕዝቡ በኳስ ተጫዋቾች የጫማ ቁጥር፣ በፊልም ተዋናይ የአልጋ ልብስ ቀለም ሲደነቁር መዋል አለበት? መንግሥትስ ዝም ብሎ ከማየት አልፎ በዚህ ተጨባጭ ሀቅ ‘የሚዲያና የፕሬስ ነፃነት አለ’ ብሎ እንደ መከራከሪያ ይዞ ሊሟገት ይገባዋል? ኧረ ተወኝ ባክህ!›› አለኝ በረጅሙ ተነስፍሶ። ‘ኧረ በደንብ ተንፍስ’ አልኩ እኔም በልቤ። ትችትና አስተያየት ስያሜ እያሰጡ እንካሰላንቲያ በሚያስነሱበት አገር ወደ ውስጥ ተናግሮ ወደ ውስጥ ተንፍሶ እንዴት ይኖራል? እንዴትም! ምነው ‘ኤፍ ኤሞቻችን’ እንዲህ መካሪ አጡ?!

ጉድና ጉዳንጉዱን እዚህ እዛ ስባክን እያየሁ ከአንደኛው ጉዳይ ወደ ሌላው እዘላለሁ። በድለላ ሙያ ከተሰማራችሁ ‘ያልተገላበጠ ያራል’ የሚሉት አባባል በደንብ እንደሚሠራ ታረጋግጣላችሁ። ዳሩ የዘመኑ ሰው እንዲህ ያለውን ሥራ ማነቃቂያ አባባል የሚሞክረው አጉል አጉል ቦታ ሆኗል። እስኪ አስቡት ሕዝብ ለማገልገል ተሹሞ እንደ መዥገር የሰው ደም ሲመጥ፣ የትውልድ አርዓያና ተምሳሌት ለመሆን በቃል ኪዳን ታስሮ ትዳር መሥርቶ ሲያበቃ ከአንዷ ወደ ሌላዋ ሲገለባበጥና ተነካክቶ ሲያነካካ ምን እንደሚባል አይጨንቅም? ስል የሰማኝ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹በጣም እንጂ! ደግነቱ በቤተሰብና በትዳር ላይ ያለውን የሞራል ዝቅጠት ለመታደግ ራሱን የቻለ ‘ፀረ ወዲያ ወዲህ’ የሚባል ኮሚሽን ባይቋቋምም፣ በሙስናው በኩል ፀረ ሙስና እየሠራ ያለው ነገር እውነት ለመናገር ጥሩ ጅማሮ ነው፤›› አለኝ። ታዲያ አፋችንን ሞልተን በሚጀመረው መልካም ተግባር ጮቤ እንዳንረግጥ የምንጀምረው እንጂ የምንጨርሰው ነገር እጅግ ጥቂት ነው። ቢሆንም እንዳስጀመረን ያስጨርሰን ማለት ወግ ነው!

እናም ስዘዋወር ያገኘሁት ሥራ ያው የቤት ድለላ ሆነ። ምን ይደረግ ቤት በሌለበት አገር ቤት ፈላጊው በዝቶ እኮ ነው። ቤቱን ለመሸጥ የቀረበውን ዋጋ ስሰማ ሄጄ ለማየት ጓጓሁ። የተባለውን ቤት ሄጄ ሳየው የተጠሩት ሚሊዮን ብሮች ያንሱታል እስክል ድረስ አስገራሚ ነበር። ወዲያው የማገኘውን ረብጣ ሳሰላው ሐሴት ያቁነጠኝጠኝ ጀመር። ገዢ ይገኛል ብዬ ካሰላሁት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሁለት ደንበኞች ሲገጥሙኝ ግን ድንግጥ አልኩላችሁ። ምን አስደነገጠህ አትሉኝም? በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል ልክ ሚሊዮን ምንም የማይመስለው የኅብረተሰብ ክፍል መበራከቱ ነዋ። ‘ካፒታሊዝም ይሏል ይኼ ነው!’ የሚለው የባሻዬ ልጅ ስላቅ ምፀት አዘል አባባል ጆሮዬ ላይ ደወለ። ይኼኔ አንድ ጆሮ ጠቢ ሰማኝ መሰል ‹‹ታዲያስ! ዕድገት የለም ትላላችሁ ግን ይኼው ሚሊዮን በግለሰብ ደረጃ አስቆጠርናችሁ፤›› ብሎ ገላመጠኝ። ምን ትሉታላችሁ? የጆሮ ጠቢው ንግግር ደንበኛዬ ጆሮ ጥልቅ አለ መሰል፣ ‹‹ምንድን ነው የሚለው?›› ብሎ ጠየቀኝ። እኔም የተናገረውን ስደግምለት፣ ‹‹ተወው እባክህ ‘ሞኝና ወረቀት ያስያዙትን መቼ ይለቅና?’›› ብሎ ተረተበት። ወዲያውም መሄዳችን ስለነበር የመኪናውን ጋቢና በር ከፈተልኝ።

እንሰነባበት እስኪ። ሥራዬን ጨራርሼ በነጋታው ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀጠሮ ይዤ ሳበቃ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ። ሰፈር ስደርስ ከባድ ዝናብ መጣል ጀምሯል። ሁሉም ባገኘው መጠለያ ሽጉጥ ሲል አሻፈረኝ ብዬ እኔ ወደ ቤቴ ሮጥኩ። ልክ በሩን ከፍቼ ስገባ ባሻዬና ማንጠግቦሽ ተቀምጠው ወግ ይዘዋል። ‹‹ባሻዬ? ምን እግር ጣለዎ?›› አልኳቸው የበሰበሰ ካፖርቴን እያወለቅኩ። ‹‹ዝናብ ሲይዘኝ ልጄ ቤት ላባራው ብዬ ነዋ፤›› አሉኝ የአባትነት ፈገግታቸው በቅንነት ፊታቸውን እያበራው። ሳቅ አልኩና ከጎናቸው ስቀመጥ፣ ‹‹ሰሞኑን እጅግ ከባድ ዝናብ ይዘንባል ብሎ ራዲዮ ሲናገር ሰምቻለሁ። ጠንቀቅ ብላችሁ ነቅታችሁ ተኙ። መቼም ከላይ ትዕዛዝ ከመጣ መመለስ ባይቻልም መጠንቀቅ አይከፋም፤›› ብለው ማንጠግቦሽን እያዩ ሲናገሩ ስለተፈጥሮ አደጋ እንደሚያወሩ ገብቶኛል። ‹‹አዬ ባሻዬ! በምናችን ልንችለው አምላክ እንዲህ ያለውን ነገር በእኛ እንዲሆን ይፈቅዳል?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው። በዚህ ኪራይ ሰብሳቢው፣ በዚያ ቀማኛውና ምቀኛው፣ በዚህ ሰንካላው ዴሞክራሲያችንና የመልካም አስተዳደር እጦት፣ በዚህ የአመለካከትና የአስተሳሰብ ዕጦት እያሰቃኙን መቼ አገገምን? ጭራሽ የተፈጥሮ አደጋ ተጨምሮበትማ ስንቱን እንቻል?›› አሉኝ ደስ እያላቸው። የደስታቸውን እንቆቅልሽ መፍታት አቃተኝ። የተናገሩት ግን ውስጤ ቀርቷል። ‘ስንት ልባም አለ እናንተ? ልብስ እንጂ ልብ አለመሸጡ አይቆጭም?  ቸር ያሰንብተን እስኪ! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት