Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን እንዲሁ ሥራ ላይ እናሰማራ ቢባል ጊዜና ሀብት ሊባክን...

‹‹በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን እንዲሁ ሥራ ላይ እናሰማራ ቢባል ጊዜና ሀብት ሊባክን ይችላል››

ቀን:

ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ጥናት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር፣ የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

/ ሰለሞን ተፈራ በአጠቃላይ ሕክምና የመጀመሪያ ዲግሪ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዕምሮ ሕክምና የስፔሻሊቲ ሥልጠና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በአዲክሽን ሳይካትሪ የሰብስፔሻሊስት ሥልጠና ከቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ፣ የፒኤችዲ ዲግሪ በአዕምሮ ጤና ምርምር ከኡሚዮ ዩኒቨርሲቲ (ስዊድን) አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ሕክምና ጥናት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምናና የአልኮልና አደንዛዥ ዕጾች ሕክምና አገልግሎት አማካሪ ስፔሻሊስትና ኃላፊም ናቸው፡፡ 2006 .ጀምሮ የኢትዮጵያ የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ አዕምሮ ሐኪሞች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል፣ የዓለም የሳይካትሪስቶች ማኅበር የአዲክሽን ሳይካትሪ ሴክሽን አባል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና አገልግሎት  የአማካሪ ባለሙያዎች ቡድን አባል ናቸው፡፡ በአገሪቱ እንደ ትልቅ ችግር የሚታየው በተለይም የወጣቶች ሱሰኝነትን፤ መንግሥት በአገሪቱ የወጣት ሥራ አጥነት ችግርን ለመፍታት ይዞ ከተነሳው የአሥር ቢሊዮን ብር ፈንድ ዕቅድ ጋር በተያያዘ የወጣት ሱሰኝነት ላይ ቀድሞ ሊሠራ ይገባል የሚሉትን በሚመለከት ምሕረት አስቻለው ከዶ/ር ሰለሞን ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የወጣቶች ሱሰኝነት ምን ያህል አሳሳቢ ችግር ነው ይላሉ?

ዶ/ር ሰለሞን፡- እንደ እኔ አረዳድ ወጣቶቹን በሁለት መንገድ ከፍሎ መመልከት ያስፈልጋል የመጀመሪያው በሥራና በትምህርት ላይ ያሉ ወጣቶች ምድብ ሲሆን ሁለተኛው ከትምህርትና ከሥራ ውጪ የሆኑት ነው፡፡ እነዚህ ሁለተኛ ቡድን ውስጥ ያሉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መዝለቅ ያልቻሉና ከሥራ ውጪ የሆኑም ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው ምድብ ውስጥ ካሉ ጋር ሲነፃፀር ከትምህርትና ከሥራ ውጪ የሆኑ በእጥፍ ለአልኮል፣ ለጫት፣ ለሲጋራና ለሌሎችም ሱሶች የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሥርጭቱንና አሁን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሊያሳይ የሚችል አገር አቀፍ ጥናት እጄ ላይ የለም ተሠርቷል ብዬም አላምንም፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባና ሌሎችም ቦታዎች ላይ የተሠሩ ጥናቶች የሚያሳዩት ከትምህርትና ከሥራ ውጪ የሆኑ ወጣቶች ላይ መጠጥ አብዝቶ የመጠጣት፣ ጫት የመቃም እንዲሁም ለአደጋ የሚያጋልጡ ባህሪያት (Sexual Behaviors) እንደሚታይባቸው ነው፡፡ በተለይም አዲስ አበባ ላይ የተሠራ ጥናት እነዚህ ነገሮች በንፅፅር ከትምህርትና ከሥራ ውጪ የሆኑት ወጣቶች ላይ ለሱስ ተጋላጭነት ሁለት እጥፍ ከፍ እንደሚል ያሳያል፡፡ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 24 የሆኑ 20,434 ወጣቶች ላይ የተሠራ ጥናት እንዳሳየው 23 በመቶ የሚሆኑ ከትምህርት ቤት ውጪ የሆኑ ወጣቶች በየቀኑ ወይም በሳምንት አንድ ጊዜ ጫት እንደሚቅሙ ሲገልጹ፣ ተማሪ ከሆኑት ደግሞ 7.5 በመቶ የሚሆኑት በየቀኑ ወይም በሳምንት አንድ ጊዜ እንደሚቅሙ ተናግረዋል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከትምህርት ውጪ የሆኑ ወጣቶች ለጫት፣ ለአልኮልና ለሌሎችም ዕጾች ተጋላጭ መሆናቸውንም ጥናቱ ይደመድማል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሁኔታ እነዚህ ወጣቶች በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ እንዳይሆኑ ተፅዕኖ ያደርጋል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ሱስ በከፍተኛ ሁኔታ ውጤታማነትን የሚጎዳ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ እነዚህ ከሥራና ከትምህርት ውጪ ያሉና በሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን እንዲሁ ሥራ ላይ እናሰማራ ቢባል ጊዜና ሀብት ሊባክን ይችላል፡፡ ሱስ ትምህርት ሥራም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡ የሥራ ሥነ ምግባር ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከዚህም አልፎ ወደ ወንጀል የማምራት ተፅዕኖም ያሳድራል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ወጣቶች ወደ ትምህርትና ሥልጠና ከማስገባት፣ ሥራ ላይ ከማሰማራት በፊት መሠራት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሱሶች በቀላል የሚታዩ አይደሉም፡፡ ብዙዎች ከአሥራዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የሚገቡበት ነው፡፡ በተለይም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ልጆች ለሱስ የሚጋለጡበት አደገኛ ጊዜ ነው፡፡ ብዙ ወላጆች ሱስ ውስጥ የገቡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ልጆቻቸውን ለዕርዳታ ይዘው ይመጣሉ፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ካናቢስ የመጠቀም ነገር በብዛት ተማሪዎች ላይ እየታየ ነው፡፡ ሻጮች የሆኑ ተማሪዎች ሁሉ አሉ፡፡ ቀደም ብሎ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በግል ትምህርት ቤቶች 30 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ቢያንስ አንድ ጊዜ ካናቢስ መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡ ምን ያህሉ ደግሞ እንደሚያዘወትሩ ተከታታይ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ እኛ ጠንካራ በሚባሉ አደንዛዥ ዕጾች (ኮኬይንና ሄሮይን) ሳይሆን በጣም እየተቸገርን ያለነው በአልኮል፣ ጫት፣ ሲጋራና ካናቢስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ወጣቶች በግልም ይሁን በቡድን ውጤታማ ነገር ላይ ለማሰማራት መጀመሪያ መደረግ አለበት የሚሉት ምንድነው?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ሱስ እንቅፋት በመሆኑ ሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ውጤታማ ነገር ውስጥ መግባት ይቸገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ብዙዎች በሥራቸው ላይ መቆየት አልቻሉም፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ከሱስ ጋር በተያያዘ ትምህርት ማቋረጥ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው በሥራ፣ በትምህርት ከመሰማራቱ በፊት እነዚህ ችግሮች አለመኖራቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ሱስ እንቅፋት በመሆኑ በዚህ ውስጥ ያለ ሰው ስኬታማ ይሆናል ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ከዚህ በመነሳት በግልም ይሁን በመንግሥት ድጋፍ ተደራጅተው ወደ ሥራ ሊሰማሩ ያሉ ወጣቶች ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምንድነው መደረግ ያለበት?

ዶ/ር ሰለሞን፡- መፍትሔ የሚመስለኝ ነገር ሁለት ነው፡፡ አንደኛው የመከላከል ሥራ ነው፡፡ በዚህ ችግር ውስጥ ያልገቡ እንዳይገቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ማስተማርና ሕግ የማስከበር ሥራን በአግባቡ መሥራት ነው፡፡ ለምሳሌ የአልኮል መጠጥ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ አይሸጥም ተብሏል፡፡ ግን ይህንን ማን ነው የሚተገብረው? በምኖርበት አካባቢ በጊዜው የ14 እና የ16 ዓመት ልጆች ሰክረው ወድቀው አያለው፡፡ ማን ነው መጠጥ የሸጠላቸው? ሲጋራ ላይ ያለው ነገርም ተመሳሳይ ነው፡፡ ገደብ የተጣለባቸው ላይ ገደብ እንዲኖር በማድረግ የተከለከሉት ላይም ሕግ እንዲከበር በማድረግ የመከላከል ሥራውን ማጠናከር ይቻላል፡፡ ሁለተኛው የሕክምናና የተሃድሶ አገልግሎትን ማደራጀት ነው፡፡ በተለይም ጥልቅ በሆነ ሱስ ውስጥ ያሉ የሚታከሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ በእኛ አገር ያለውን ሁኔታ ስናይ ነገሩ እንደ ችግር ሁሉ አለመታየቱን ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ላይ አንዳንድ ጊዜ ፕሮግራም ሲሠራ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በተቋማት በዘመቻ ሲሠራ ይታያል፡፡ ነገር ግን ስትራቴጂም የለም፣ ፖሊሲም የለም፡፡ ይህንን የሚያስፈጽምም፤ በተደራጀ መልኩ እንቅስቃሴዎችን የሚመራ ተቋምም የለም፡፡ ሊያስፈጽም የተቀመጠውም አካል በሰው ኃይልና በአቅም የተደራጀ አይደለም፡፡ ሥራው እንዲሁ ባልተቀናጀ መንገድ እየተሠራ ነው፡፡ ስለዚህም የሚታይና ትርጉም ያለው ነገር አልመጣም፡፡ የሕክምናን፣ የመከላከልና የተሃድሶ ሥራን በተቀናጀ መልኩ መሥራት የሚችል ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች አገሮች የአልኮልና የአደንዛዥ ዕጾች ቁጥጥር፣ መከላከል፣ ሕክምናና ተሃድሶ ተቋም አለ፡፡ ይህ ተቋም የሚሠሩ ሥራዎችን አቀናጅቶ የሚመራ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ጤና ጥበቃ፣ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ ፖሊስ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም ባልተደራጀና ባልተቀናጀ መልኩ የመሰላቸውንና የበኩላቸውን ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም ችግሩ ግን እየሰፋ ነው፡፡ ስለዚህ ሥራዎች በወጥነት እንዲሄዱ የሚያደርግ ተቋም መፍጠር ላይ ሊተኮር ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነት ተቋም በጎረቤት ኬንያ አለ፡፡ በፓርላማ ፀድቆ ሥልጣን ያለው አገር አቀፍ በሆነ መልኩ ከአልኮልና ከዕፅ ጋር በተያያዘ የቁጥጥር፣ የማስተማር፣ የሕክምናና የተሃድሶ አገልግሎት የማደራጀት ሥራን የሚመራ ተቋም ነው፡፡ በአሜሪካም ተመሳሳይ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሦስት አራት ተቋማት አሉ፡፡ እንደ አሜሪካ ባይሆን እንኳ የኬንያን ተሞክሮ መውሰድ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ መሠረት መንግሥት ከአሥር ቢሊዮን ብሩ የወጣቶች ፈንድ ጋር በተያያዘ ምን ማድረግ ይኖርበታል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- በችግሩ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ተገቢውን ዕርዳታ ሳያገኙ ወደ ሥራ እንዲገቡ የሚደረግ ከሆነ እነዚህ ወጣቶች ብዙዎቹ ችግር ውስጥ ያሉ ስለሚሆኑ ውጤታማ አይሆኑም፡፡ በዚህም ሀብት ይባክናል የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ይህ ዕቅዱ የታለመለትን ግብ ሳያሳካ የሚቀርበት ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ወጣቶቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት በሱስ ውስጥ ያሉ መለየት አለባቸው፡፡ ከዚያም የሕክምናና የተሃድሶ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ዕርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ እንደማንኛውም ወጣት ፕሮግራሙን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንደ ባለሙያ እንደ ዜጋም ይህ ትኩረት እንዳልተሰጠው ይሰማኛል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህንኑ ሐሳቤን ባገኘሁት አጋጣሚ በመገናኛ ብዙኃን ለመግለጽ እየሞከርኩኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሐሳብ ሰሚ ጆሮ ካገኘ ምን ነገሮች ላይ ሊተኮር ይገባል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ የተለያየ የዕይታ አቅጣጫ ይኖራቸዋል፡፡ አንድ ኃላፊነት ላይ የተቀመጠ ባለሙያ ወይም የመንግሥት ተቋም ደግሞ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አይቶ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይገባዋል፡፡ ከተቻለ በአፋጣኝ ለሥራ ፈጠራ ዕቅዱ ብቻም አይደለም ለቀጣዩም ትውልድን ከሱስ ለማዳን፤ በችግሩ ውስጥ ያሉትንም ለማውጣት አንድ ተቋም ያስፈልጋለ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...