Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክያላለቀው የቋንቋ መብት አጠቃቀም በኢትዮጵያ

ያላለቀው የቋንቋ መብት አጠቃቀም በኢትዮጵያ

ቀን:

ያላለቁ በጣም በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ካሉባቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ሰብዓዊ መብትን ከሚመለከቱት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች በስተቀር የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ልሂቃንና ምሁራን ላይ ብቻ ሳይወሰን፤ ቀላል የማይባል የኅብረተሰብ ክፍል የተለያየ አቋምና አመለካከት የያዘባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በሚመለከት ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመንግሥታዊ ሥራ መዋል ያለበትን ቋንቋ ይመለከታል፡፡ አገሮች የማዕከላዊ መንግሥቱ  ሥራውን የሚያከናውንበትና አገልግሎት የሚሰጥበትን ቋንቋ በሚመለከት የተለያዩ አካሔዶችን ይከተላሉ፡፡ ለሚጠቀሙበትም ቋንቋ የተለያዩ ክብር ወይም ደረጃ ይሰጣሉ፡፡ አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቋንቋዎችን ሊጠቀሙም ይችላሉ፡፡ ዋና ነገር የየአገሮቹ ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊው መንግሥት የአማርኛ ቋንቋን መጠቀም ከጀመረ በመቶዎች የሚቆጠር ዓመታት ሞልቶታል፡፡ ይህ ማለት ግን ለማዕከላዊው መንግሥት የሚገብሩት ገዥዎችና ሕዝቦች የአማርኛ ቋንቋን ይጠቀሙ ነበር ማለት አይደለም፡፡ ሁኔታው ከዘመነ መሳፍንት በኋላም ቀጥሎ አፄ ቴዎድሮስም፣ አፄ ዮሐንስም ይጠቀሙበት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ፣ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት ምሥረታን ተከትሎ ማዕከላዊ መንግሥቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች መብዛትና በመንግሥቱ ውስጥ ለመሳተፍ   ብሎም ተገልጋዮች በሚገባቸው ቋንቋ ለመገልገል ሲባል እንደ ጥንቱ አንድ ብቻ የማዕከላዊ ቋንቋን መጠቀም ተገቢነቱ አጠያያቂ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ በመሆኑም አገሮች ከአንድ በላይ ቋንቋን በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ መጠቀም ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል፡፡

- Advertisement -

በኢትዮጵያም የማዕከላዊው (የፌደራል) መንግሥት ከአንድ በላይ ቋንቋ በኦፊሴል መጠቀም እንዳለበት የሚጠየቁም የሚመክሩም አሉ፡፡ በተለይ ከማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ከጥናቶችም ወዘተ መረዳት እንደሚቻለው የኦሮምኛ ቋንቋ ተጨማሪ የፌደራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቁ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓቢይ ትኩረትም የቋንቋ መብትና የሥራ ቋንቋን ይመለከታል፡፡

የቋንቋ መብት ሲባል

ቋንቋ ከመግባቢያነት የዘለለ ፋይዳ አለው፡፡ ምናልባትም ከመግባቢያነትም የበለጠ የቋንቋ ዕሴት ከማንነት ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ነው፡፡ አንድ ሰው የትም ተንደላቆ እየኖረ እትብቱ ለተቀበረበት ቦታ እንደሚናፍቅና ልዩ ፍቅር እንደሚኖረው ሁሉ በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሳይኛ እየተግባባና እየሠራ በሚኖርበት አካባቢ ምንም ጥቅም ባይሰጥም እንኳን የዘመድ አዝማድ/የዝርያ ቋንቋውን ግን ‹‹የኔ›› በማለት የባለቤትነት ስሜት ያይላል፡፡ የማንነት አሻራም ነው፡፡ በእርግጥ የማንነት መለያ ቋንቋ ብቻ ነው ባይባልም ዋናው ግን ቋንቋ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት ከአንድ ወር በላይ የሕገ መንግሥት አፅዳቂ ጉባዔያተኞች ውይይት ሲያደርጉ ከየብሔሩ፣ ብሔረሰቡና ሕዝቦች የመጡ ተወካዮች ለአማርኛ ቋንቋ ተሰጥቶት ነበር ያሉትን የተለየ እንክብካቤ፣ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አስከተለው ያሉትን ጦስ፣ እንዲሁም  ሌሎች ቋንቋዎች ዕድገት ላይ ያሳረፈውን በትር ከነፍጠኛው ሥርዓት የመስፋፋት ዘመቻ ጋር በማያያዝ በሰፊው አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡ እነዚህ አስተያየቶች የተሰነዘሩት የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋን ምርጫ የሚመለከተውን አንቀጽ 5፣ እንዲሁም ስለብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ቋንቋን የማሳደግ፣ በራስ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ መብት ስለሚያትተው አንቀጽ 39(2) ውይይት ሲያካሂዱ ነው፡፡

ጉባዔያተኞቹ የፌዴራሉን መንግሥት የሥራ ቋንቋ ማለትም የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት  (የልማት ድርጅቶችም ጭምር)፣ እንዲሁም ከክልል መንግሥታት ጋር ለመገናኘት የአማርኛ ቋንቋ ሲታጭ በተለይ ከጉባዔያተኞቹ በኩል የቀረበ ተቃውሞም አልነበረም፤ ሁለትና ከዚያ በላይ የሥራ ቋንቋ እንዲኖርም የቀረበ ሐሳብ ስለመኖሩ በቃለ ጉባዔው ላይ አልሰፈረም፡፡

አማርኛ እንዲፀድቅ የቀረቡት ምክንያቶችም በወቅቱ ከነበሩት ሌሎች ቋንቋዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ዕድገት ስላለው፣ የራሱ ፊደላት ያሉት ስለሆነ፣ ሌላ የተሻለ አማራጭ አለመኖሩና ስላላደጉ፣ በታሪክ አጋጣሚ በተለይም ከምኒልክ በኋላ ገባሮች ከአስገባሪው (ነፍጠኛው) ጋር ለመግባበት ሲባል አማርኛን የግድ ማወቅ ስለነበረባቸውና በዚህ ሁኔታ መስፋፋቱ፣ በመላው ዓለም እንደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ስፓኒሽ ያሉ ቋንቋዎች በቅኝ ግዛት ምክንያት እንደተስፋፉት ሁሉ በኢትዮጵያም ውስጥ አማርኛ በዚሁ ዓይነት በመስፋፋቱ ለሥራ ምቹነትን ስለፈጠረ፤ የሚሉ ምክንያቶችን በመዘርዘር የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ  እንዲሆን፤ ነገር ግን ሁሉንም ቋንቋዎች እኩል  ዕውቅና በመቸር ብሎም ክልሎች የራሳቸውን (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ፣ የቀበሌንም ጨምሮ) የሥራ ቋንቋ መምረጥ እንደሚችሉ በመወሰን አንቀጽ 5 ፀደቀ፡፡

በዚህም መሠረት ክልላዊ የሥራ ቋንቋዎች ዕውቅና አገኙ፡፡ የትግራይ ክልል ትግርኛን፣ አፋር ክልል አፋርኛን ለአርጎባ ብሔረሰብና ቋንቋ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የአማራ ክልል አማርኛን በተጨማሪም በልዩ ዞኖችና ወረዳ ደረጃ አዊኛ፣ ኽምጣንኛ (አገውኛ)፣ ኦሮምኛና አርጎብኛ፣ የኦሮሚያ ክልል አፋን ኦሮሞ፣ የሐረሪ ክልል ሐረሪኛና አፋን ኦሮሞ፣ የኢትዮጵያ ሶማሊያ ክልል አፋን ሶማሊ ሆኗል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አማርኛን ተግባራዊነቱ ላይ የተወሰነ ችግር ቢኖርም አምስቱም ነባር ብሔረሰቦች ማለትም የበርታ (ሩጣንኛ)፣ ጉምዝ ጉምዝኛ፣ ሺናሻ ሺናሽኛ በልዩ ዞንና ማኦና ኮሞ በልዩ ወረዳ ደረጃ ማኦኛና ኮሞኛን፤ ጋምቤላ ክልል የክልሉን የሥራ ቋንቋ አማርኛ በማድረግ ከአምስቱ ነባር ብሔረሰቦች ለሦስቱ ልዩ ዞን በመፍቀድ ኑዌር፣ አኙዋና መዠንገር በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ ፈቅዷል፡፡ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ደግሞ የክልሉን አማርኛ በማድረግ ልዩ ዞንና ልዩ ወረዳ ላላቸው በራሳቸው ቋንቋ እንዲናገሩ፣ እንዲጽፉ ሕገ መንግሥታዊ  ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የአዲስ አበባ የድሬዳዋ አማርኛ ሆኗል፡፡

ከዚህ አንፃር ከአሐዳዊ የመንግሥት አወቃቀር በተለየ መልኩ፣ የፌዴራል ሥርዓት ለልዩነት ብዙ ሥፍራ መኖሩን ያጤኗል፡፡ ለሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሙሉ በእኩልነት መልስ መስጠት ባይቻልም ከቀደሙት ሥርዓታት አንፃር በእጅጉ የተሻለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ30 በማያንሱ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ይሰጣል፡፡ Anchor

የቋንቋ መብቶች ይዘት

የቋንቋ፣ ወይም በብዙ ሥነ ጽሑፍ እንደሚታወቀው፣ የሥነ ልሳናዊ ሰብዓዊ መብት (Lingustic Human Right)፣ ይዘቱ በግልጽ ያልተለየ፣ የሰብዓዊ መብቶችን ባሕርያት ሙሉ በሙሉ ማሟላት አለማሟላቱ አጠራጣሪ ከሆኑ መብቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ለአብነት በሕይወት የመኖር፣ የመናገር፣ የማሰብ ወዘተ መብቶች ከሰውየው የማይነጠል፣ የማይለይ ተፈጥሮአዊ መሆን አለመሆኑ፣ የትም ቦታና አገር ሊተገበር ስለመቻል አለመቻሉና የመሳሰሉት ነጥቦች ላይ አከራካሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የመብቱ ተጠቃሚዎች ማንነት፣ የመብቱ ይዘትና ገደብ እንዲሁም ባለግዴታዎቹ እነማን ስለመሆናቸውም ቢሆን ጠርቶና ነጥሮ አልወጣም፡፡

የዩኔስኮን (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) ድረ ገጽ ለጎበኘ ሰው የቋንቋ ወይም የሥነ ልሳናዊ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ወደ 50 የሚጠጉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ መግለጫዎች፣ የቃል ኪዳን ሰነዶች ማግኘት ይችላል፡፡ በእርግጥ ሰፊ የይዘት ልዩነት ባይታይባቸውም ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ ከመብዛታቸው የተነሳ ግን የጋሸቡ ቢመስልም እንኳን! የቋንቋ መብት በአብዛኛው የሚመለከተው የመንግሥት ተቋማት የሚጠቀሙበትን (አገልግሎት) የሚሰጡበትን ቋንቋ ድንጋጌ ነው፡፡ አንድም ቋንቋቸው የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ያልሆነላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቋንቋቸው ሲጠፋ እነሱም እንዳይጠፉ ሥነ ልሳናዊ ታጋሽነትን በማስፈን፣ የቋንቋ ማጥፋት ድርጊት እንዳይፈጸም መከላከል ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት እንደነዚህ ዓይነቶቹን ቋንቋዎች ለትምህርት ቤት፣ ለፍርድ ቤትና ለሌሎች መንግሥታዊ ግልጋሎቶች መግባቢያ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ ሥነ ልሳናዊ ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ መንግሥት የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በግል ሕይወትም ይሁን በየትም ቦታ በየትኛውም ቋንቋ  መነጋገር፣ መጻጻፍ ወዘተ ላይ መንግሥት ምንም ዓይነት ጣልቃ መግባት የለበትም፡፡ ጥንተ ፍጥረቷ ሐሳብን በነፃ ከመግለጽ ጋር መሆኗን ያጤኗል፡፡ በተጨማሪም መንግሥት እነዚህ መብቶች ሲጣሱ የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡

በተለይ ለፌደራሉ የሥራ ቋንቋ ጥላቻ የሚያሳድሩ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ማድረግም ይጠይቃል፡፡ ጥላቻ የሚፈጥሩ ነገሮች እየበዙ ከሔዱ፣ ቋንቋውን አለማወቅን/አለመማርን ወደ መምረጥ እንዲያዘነብሉ ስለሚያደርግ ውጤቱ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ተቀጣሪና ተወዳዳሪ እንዳይሆኑም ጭምር ስለሚያደርግ ድጋሚ ጉዳት ያመጣል፡፡ ይሔንን ግዴታ በተመለከተ ማንኛውም ሰው በቋንቋው ምክንያት ልዩነት ወይም መድልኦ እንዳይደረግበት በሕገ መንግሥቱና በተለያዩ ሕጎች ተደንግጓል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ግዴታዎች በአብዝኃኛው ቡድንን ከመጠበቅ ይልቅ ወደ ግለሰቦች መብት ያዘነብላሉ፡፡

ሌላው የመንግሥት ግዴታ ቋንቋው ሊያድግ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና መጣርን ይመለከታል፡፡ ይህን በተመለከተ መንግሥት ላይ ግዴታ የሚጥለው  የሕገ መንግሥት አንቀጽ 90(1) ይመስላል፡፡ ይህም ለጠጥ አድርገን በመተረጎም ቋንቋ የባህል አካል እንደሆነ በመውሰድ መንግሥት ባህሎች በእኩልነት እንዲጎለብቱ የመርዳት ኃላፊነት አለበት ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ የሕገ መንግሥት አፅዳቂ ጉባዔያተኞቹ ስለ አንቀጽ 5 ሲወያዩ የአንቀጹ አካል እንዲሆን ቢጠይቁም፣ ስለመብትና ግዴታ በሚደነግገው ክፍል ይካተታል በሚል ምላሽ ታልፏል፡፡ ከዚያ ሕገ መንግሥቱም ለጠቅላላው አለፈው፡፡

ስለሆነም የፖሊሲ አቅጣጫ ከማስቀመጥ በዘለለ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ የተቀመጠ ግዴታን አናገኝም፡፡ ይህ ሁኔታ በእርግጥ እንደማንኛውም የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች በየጊዜው እያደገ የሚሔድ፣ አቅም የቻለውን ያህል ተጨባጭ ዕርምጃ በመውሰድ የሚወጡት እንጂ በአንድ ጊዜ የሚፈጸም አለመሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የቅማንት ቋንቋ እንዲያድግ፣ ተወላጆቹም በዚሁ ቋንቋ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን እንዲማሩ ለማድረግ ቢፈለግ የመንግሥት ግዴታ የሚሆነው ፊደል መቅረፅ፣ መዝገበ ቃላት፣ ሌሎች መጽሐፍት ማሰናዳት፣ መምህራን ማሠልጠንና የመሳሰሉት ተግባራት ሲሆኑ እነዚህ ደግሞ በአንድ ጀምበር የሚፈጸሙ ባለመሆናቸው መንግሥት በአንድ ጊዜ ግዴታውን ሊወጣ አይችልም፡፡ ይህ ግዴታና መብት ከግለሰብ ይልቅ አትኩሮቱ ወደ ቡድን ነው፡፡

ሌላው አጨቃጫቂ የመብት ጉዳይ የፊደል/የሆሄያት መረጣን የሚመለከት ነው፡፡ ምንም እንኳን ማንኛውም ብሔር በራሱ ቋንቋ የመናገርና የመጻፍ መብት እንዳላቸው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሰነዶች ዕውቅና ቢሰጡም፣ እንደሩሲያ ያሉት ግን ማንኛውም ብሔር ከሩሲያኛ ቋንቋ ፊደላት ውጭ መጠቀም እንደማይቻል የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤታቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ዓላማውም የአገር አንድነትን ማጠናከር ነው፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስናይ ቋንቋን የማሳደግ መብት እስከምን ድረስ ነው? የሚለው ጉዳይ ወሳኝ ነው፡፡ ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የላቲንኛ ፊደላትን መጠቀምን መርጠዋል፡፡ የግዕዝ ፊደላት በበቂ ሁኔታ የቋንቋዎቹን ድምፅ መወከል ስላልቻሉ፣ ላቲንኛ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ በረከት ለመቋደስ ቀላል ስለሆነ፣ የግዕዙ ሆሄያት ድምፅን ወደ ንባብ በትክክል ለመቀየር ስለማያስችሉ ነው የሚሉ ናቸው መከራከሪያዎቹ፡፡

በእርግጥ ሌሎች ደግሞ አንዳንድ የግዕዝ ፊደላትን ለድምጾቹ ወካይ እንዲሆኑ ማድረግ ሲቻል (ለምሳሌ መቀሌ መቐለ እንደሆነው ማለት ነው፡፡ ‹‹ቐ›› በግዕዝ ውስጥ የሌለች መሆኗን ልብ ይሏል፡፡) ለአማርኛ ካላቸው ጥላቻ የመነጨ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ከልብ ካዘኑ እንባ አይገድም›› ነበር ነው የክርክሩ ማጠንጠኛ፡፡ በተጨማሪም የአማርኛ ፊደልን አንዴ ካወቁ ለመጻፍ መቅለሉ፣ እንዲሁም አናባቢ ፊደል መጻፍን ስለማይፈልግ ኢኮኖሚያዊ መሆኑም ሌላው ፋይዳው ነው፡፡ የግዕዝ ቋንቋ ፊደላት ድክመት ሌላ፣ አለመፈለግ ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች የተለያዩ ፊደላትን በማጥናት እንዲቸገሩ ያደርጋል፤ ለአማርኛ የሚኖረውን ጥላቻ እንዲጨምር ማበረታቻ ይሆናል፤ ስለዚህ የአገር አንድነት ላይ ጥላውን ማጥላቱ አይቀሬ ነው፣ እንደማንኛውም መብት ገደብ ቢኖረው ጥሩ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በቀጥታ አንድ የጋራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመመሥረት ከሚደረገው ጥረትም ጋር ተያይዞ ሊታይ ይገባዋል፡፡ Anchor

የሥራ ቋንቋ ምርጫ

በዓለም ላይ ወደ 175 አገሮች አካባቢ በሕገ መንግሥታቸው የቋንቋን ጉዳይ ደንግገዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ወይ ሕገ መንግሥት የላቸውም፤ ወይም ደግሞ በሕገ መንግሥታቸው ዝምታን መርጠዋል፡፡ ዝምታን ከመረጡት ውስጥ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድ፣ ዴንማርክ፣ ቼክ፣ አውስትራሊያ፣ አንጎላ፣ ቺሊ፣ አይስላንድ፣ ጃፓን ይገኙበታል፡፡ ይህ ማለት ግን በእነዚህ አገሮች ውስጥ የቋንቋ መብት የሚባል ጉዳይ የለም ማለት አይደለም፡፡

አገሮች የሥራ ቋንቋቸውን ሲመርጡ ለአብነት ስዊትዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ፊጂና ሲንጋፖር በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ሁሉንም አሊያም ብዙ ቋንቋዎችን የሥራ ቋንቋቸው አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል በሲዊዘርላንድ የሚነገሩት ጀርመንኛ፣  ጣሊያንኛ፣ ፈረንሳይኛና ሮማኒሽ፤ በቤልጅየም ዳችና ፈረንሳይኛ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላ ቋንቋ የላቸውም፡፡ በፊጂና ሲንጋፖርም ከአምስት አይበልጡም፡፡ በተቃራኒው በደቡብ አፍሪካ እንግሊዝኛን ጨምሮ 11 የሥራ ቋንቋዎች ዕውቅና ተችሯቸዋል፡፡ ይህም የእኩልነት ሞዴል ይባላል፡፡

በኢትዮጵያ ሁሉም እኩል ዕውቅና እንጂ በእኩልነት የሥራ ቋንቋነት ቡራኬን አላገኙም፡፡ ከ80 በላይ የሥራ ቋንቋ ቢደረግ እውነትም የሰናኦር ግንብ ሲደረመስ እንደነበሩት የባቢሎን ሰዎች መደነቋቆር እንጂ መግባባት ገደል መግባቱ ዕሙን ነው፡፡ ስለዚህ ከላይ ያለውን ሞዴል ለመከተል የቋንቋዎቹ ብዛት ወሳኝ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካውም ቢሆን በሕግ 11 ቢሆኑም በተግባር ግን እንግሊዝኛ ከመሆን አላለፈም፡፡

ከዚህ በተለየ አኳኋን የመንግሥትን ግዴታ ከተናጋሪው ብዛት ጋር የሚያገናኙት አሉ፡፡ ልሳናት ሲበዙ የመንግሥት ግዴታ እየበዛ ሲሄድ፣ የቋንቋው ዓይነት ሲቀነስ እንዲሁም የተናጋሪው ብዛት ሲቀንስ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ አንድ ቋንቋ ብዙ ተናጋሪ ካለው መንግሥት ከቋንቋ ጋር የተያያዙ መብቶችን ማክበር ግዴታዎቹንም መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ ቁጥሩ እየጨመረ ሲሔድ የሕዝብ አገልግሎት በዚሁ ቋንቋ መስጠት መቻል ፍትሐዊ ይሆናል፡፡ ለዚያም ነው በኒውዚላንድ የማኦሪ ሕዝቦች ከጠቅላላው 8.1 በመቶ፣ በፊላንድ የሲውዲሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች 6.5 በመቶ ቢሆኑም የሥራ ቋንቋ የሆኑት፡፡

ከአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ውጭ የሚናገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፖለቲካውና ከኢኮኖሚያዊ በረከቶች የበለጠ እየተገለሉ እንዳይሔዱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ብቻ ተወስነው በመቅረት፣ በቋንቋ መሰናክልነት ከተለያዩ ኃላፊነቶችና ዕድሎች ውድድር ውጪ እንዳይሆኑ፣ ከብዙኃኑ ጋር ሳይቀላቀሉ ወይም ሳይግባቡ በመቅረት በኢኮኖሚው መስክም እንዳይጎዱ ለማድረግ በተለይም የአገሪቱን የሥራ ቋንቋ ማወቅ የሚያስችላቸው ሁኔታ ማመቻቸት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ አለበለዚያ ጉዳዩን ተስፋዬ ገብረአብ ‹‹የጋዜጠኛው ማስታወሻ›› በሚለው መጽሐፉ፣ ወንድሙ ጩበሮ የሚባል አንድ ሰው አጫወተኝ ያለው በጥሩ ሁኔታ ይገልጸዋል፡፡ ጨዋታው እንዲህ ነው፡፡

‹‹ለመለስ ዜናዊ ‘ሁሉንም እናውቃለን’ የሚል መልዕክት ንገረው፡፡ እሱ ሴት ልጁን በእንግሊዝኛ ቋንቋ እያስተማረ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ምነው ታዲያ በትግርኛ ሳያስተምራት ቀረ! ‘የታገልነው በቋንቋችን ስላልተማርን ተበድለናል’ ብሎ አልነበረም? ምነው ታዲያ ሴት ልጁን ከትግሉ ፍሬ ሳያቀምሳት ቀረ! የማናውቅ አይምሰላችሁ! የባለሥልጣናት ልጆች አፋቸውን በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየፈቱ አይደለም እንዴ! እኛን ደግሞ ‘በዶርዚኛ ቋንቋ በመማር መብታችሁን አስከብሩ ትሉናላችሁ?’ እኔ ልጆቼ በአማርኛ ቋንቋ ነው እንዲማሩ የምፈልገው! ቢቻል ደግሞ በእንግሊዝኛ! ምክንያቱም ልጄ አማርኛ ከቻለ በኢትዮጵያ ተዘዋውሮ የመሥራት ዕድል ያገኛል፡፡ እንግሊዝኛ ከቻለ ደግሞ በመላው ዓለም፡፡ በዶርዝኛ ተማሩ የምትሉን ልጆቻችን ሸማኔ ሆነው እንዲቀሩ ነው?››

የታሪኩ እውነትነት ምንም ይሁን ምን፣ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ይህ ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስ መላ መላ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የመማር አንደኛው ጥቅሙ ዕድልን ማስፋት ነውና! ሳይወሳ መታለፍ የሌለበት የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ መሆኑ ቀርቶ እንግሊዝኛ መሆን አለበት የሚለውን ክርክር በተመለከተ ነው፡፡ አማርኛ ለሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ገለልተኛ ባለመሆኑ፣ የጨቋኞችና የነፍጠኞች ቋንቋ ስለነበረም የግጭት ምንጭ ሊሆን ስለሚችል፣ ለአማራው የተለየ ዕድል ስለሚያመቻችና የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ፣ ሌሎችን እኩል ሚዛን ላይ ስለማያስቀምጥ፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂም እንግሊዝኛ ስለሚሻል፣ አማርኛን የሥራ ቋንቋ ማድረግ ውጠትን/ውህደትን ስለሚያባብስ፣ ብዙ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች እንዳደረጉት ሁሉ አማርኛ በእንግሊዝኛ መተካት አለበት፤ የሚሉም አሉ፡፡

ይሁን እንጂ ቋንቋን ከመግባቢያነት ያለፈ አድማስን የሚያሳይ ጠቀሜታ እንዳለው የረሱም የተጋረዱም ይመስላሉ፡፡ ቋንቋ ከመግባቢያነቱ ባሻገር የባህልና የማንነት መገለጫ አክርማና ሰበዝ መሆኑንም የተዘነጋ ይመስላል፡፡ ዶ/ር ገላውዲዎስ አርዓያ የተባሉ ምሁር ይህን ሐሳብ እንዲህ ያብራሩታል፡፡ ‹‹ከሁሉ የላቀና ያየለ የባህል መግለጫና አለኝታ ቋንቋ ነው። ያለ ቋንቋ፣ ባህል እንኳንስ  ሊገለጽና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ቀርቶ ህልውናው ሳይቀር አጠራጣሪ ነው የሚሆነው። በዚህ ላይ ቋንቋ የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ አንድ የማንነት መለኪያ ነው። እንግዲያውስ ቋንቋ ከሐሳብ መግለጽ፣ ግንኙነት መፍጠርና መልዕክት ማስተላለፍ አልፎ በባህል ላይ ዓብይና ወሳኝ ሚና ስለሚጫወት በዝርዘር መወያየቱ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።››

ጠቅለል ለማድረግ ያህል የቋንቋን ጉዳይ ይበልጥ ፖለቲካዊ የሚያደርገው የብሔራዊ ወይም የሥራ ቋንቋን አመራረጥ ጉዳይ መሆኑን አይተናል፡፡ በኢትዮጵያም ይኼው እስካሁን ድረስ ምናልባት ወደፊትም በሚቀጥል መልኩ፤ የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑን ቀጥሏል፡፡ በአንድ በኩል የውህደት/ውጤት (Assimilation) አስተሳሰብ አራማጆች አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ በተግባር አማርኛ ሌሎቹን ወደእሱ መሳቡ እንደቀጠለ ነው ይላሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ ላይ ውይይት ሲደረግ ስለአገራችን ቋንቋዎች ዕጣ ፋንታና በፈቃድ ላይ የተመሠረተ ውህደትን/ውጤትን አስፈላጊነትና የብዙ ቋንቋዎችን መኖር አስቸጋሪነት፣ ዶ/ር አብዱልመጂድ ሑሴን ሲያስረዱ፣ በጊዜ ሒደት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ስትገነባ ሁሉም ሰው አንድ ቋንቋ ተናጋሪና ተመሳሳይ ባህል አንፀባራቂ  ኅብረተሰብ ቢፈጠር በጣም ጥሩ እንደሆነ በማብራራት ምኞታቸውም ይኸው እንደሆነ ገልጸውል ነበር፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የቻይነት/ታጋሽነት (Accomodation) አራማጆች ቢቻል ሁሉም የፌደራል የሥራ ቋንቋ (በኢትዮጵያ የማይቻልና የማይተሰብ ቢሆንም) ባይቻል ግን ቀበሌ ያላቸው በቀበሌያቸው፣ ወረዳ ያላቸውም በወረዳቸው፣ ዞን ያላቸው በዞናቸው፣ ክልል ያላቸው ደግሞ በክልላቸው የሥራ ቋንቋ እንዲያደርጉ ማስቻልና መታገስ ካልተቻለ የመብቱ መከበር ጉዳይ አጠያያቂ ነው የሚሆነው፡፡

ይሁን እንጂ የፌዴራሉ አማርኛ ከሆነ አይቀር የአገር አንድነትንና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠርን ለማበረታት አማርኛ የሁሉም (የትግራይ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊያ) ሁለተኛ፣ ለሐረሪ ክልል አማርኛ ሦስተኛ የሥራ ቋንቋ ቢሆን የፌደሬሽን ምክር ቤትም ይህንኑ ቢያበረታታ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

የኦሮምኛ ቋንቋ ደግሞ ተጨማሪ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ማድረግም በብዙ መልኩ ተገቢ ነው፡፡ ሁለት የሥራ ቋንቋዎችን ማድረግ በብዙ አገሮች የተለመደ ነው፡፡ የቋንቋው ተናጋሪም ከፍተኛ ነው፣ በተሻለ ሁኔታም አንድነትን ለማምጣት ይጠቅማል፣ ቁሳዊ ከሆነው ጠቀሜታ ባለፈም ሥነ ልቦናዊ ፋይዳም እንዳለው መረዳት ይገባል፡፡ የአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ጥናት ማድረግ ሳያስፈልግ መገመት ስለሚቻልና ተናጋሪውም ብዙ ከመሆኑ አንፃር ፍትሐዊነቱን የበለጠ ያጎላዋል፡፡

በተጨማሪም የአማራ ክልል፣ ኦሮምኛን እንደተጨማሪ ቋንቋ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ መስጠት ቢጀምር አንድም በተሻለ ሁኔታ የኦሮሞን ማንነት፣ ባህል፣ እምነትና ታሪክ ለመረዳትና ለመገንዘብ፣ ወንድማማችነትና (Fraternity) አብሮነትን (Solidarity) ያጠናክራል፡፡ እንዲሁም ክልሉ በሁለት ቋንቋ ብቻ (በአማርኛና እንግሊዝኛ) የሚያስተምርም በመሆኑ ለተማሪዎችም ከሌሎች ክልል በተለየ ሁኔታ ጫና ስለማይሆንና በክልሉ ውስጥ በሚገኘው በኦሮሞ አስተዳደር ብሔረሰብ ዞን ውስጥ የሚሰጠውን ማስፋት በመሆኑና የትምህርት ፖሊሲውም ስለ ቋንቋ በሚያትተው ክፍሉ አንድ ብሔር ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ውጪ የመረጠውን ቢማር ስለሚያበረታታ የክልሉ መንግሥት በቀናነት ቢቀበለው ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...