Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ዓለም ሐሰተኛ ወሬ (Fake News) የመነጋገሪያ አጀንዳው ከሆነ ሰነባበተ፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር አካውንታቸው የሚለቋቸው መልዕክቶች በሐሰተኛ ወሬነት እየተፈረጁ ነው፡፡ ‹‹ባራክ ኦባማ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ስልኬን አስጠልፈው ነበር፤›› በማለት ያሠራጩት ወሬም መሳቂያ መሳለቂያ አድርጓቸው ነው የሰነበተው፡፡ ‹‹ይኼን ዓይነቱን በደኅንነት ተቋማት የማይታወቅ ወሬ ከየት አመጡት?›› ሲባሉ፣ ‹‹እኔም የሰማሁት ከሌሎች ዘገባዎች ነው፤›› ማለታቸው ደግሞ የበለጠ ማላገጫ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ሰውየው ሳያጣሩና ሳይመረምሩ የሚዘረግፏቸው መረጃዎች ወደፊት ብዙ ጣጣ ሳያመጡባቸው አይቀርም፡፡ ይኼ የእኔ ግምት ነው፡፡

በቀደም ዕለት በጠዋት አንድ የማውቀው ሰው ይደውልልኛል፡፡ ከተጣደፈ ሰላምታው በኋላ፣ ‹‹እንኳን ደስ አለህ፣ እንኳን ደስ አለን፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ተገኘ?›› አልኩት፡፡ አሁንም የጥድፊያ በሚመስል ድምፀት፣ ‹‹አሜሪካ ኢትዮጵያዊያን ያለ ቪዛ እንዲገቡ ፈቀደች፤›› እያለ በደስታ ተውጦ ሲነግረኝ ያበደ ነው የመሰለኝ፡፡ ‹‹ለመሆኑ ደህና ነህ?›› በማለት ጥያቄ ሳቀርብለት፣ ‹‹ይህንን የመሰለ የማይገኝ ዕድል ተገኝቶ እንደ መደሰት ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የምታቀርብልኝ?›› ሲለኝ አስደነገጠኝ፡፡ ይኼ ሰው ያበደ መሰለኝ፡፡ ‹‹አንተ ይህንን የመሰለ ዜና እየነገርኩህ ትደሰታለህ ስል ጭራሽ የእኔን ጤንነት ትጠራጠራለህ?›› ሲለኝ ግራ ገባኝ፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹ስማ የሰማኸውን ወሬ በሚገባ አጣራ፡፡ ያልተጣራ ወሬ ይዘህ ስትዘባርቅ በኋላ ለአንተ ኃፍረት ይሆናል…›› ስለው ስልኩን ጆሮዬ ላይ ዘጋው፡፡

ቁርሴን ቀማምሼ ወደ ሥራዬ ሳመራ ስልኬ ጮኸ፡፡ ሌላ የቅርብ ወዳጄ ነው፡፡ ‹‹ምንድነው የምሰማው?›› አለኝ፡፡ ጉድ ፈላ፡፡ ይኼ ደግሞ ምን ይዞ መጥቶ ይሆን? ‹‹ምን ሰማህ?›› አልኩት፡፡ ጓደኛዬ ግራ የተጋባ በሚመስል ድምፅ፣ ‹‹አሜሪካ ለኢትዮጵያዊያን ከቪዛ ነፃ ወደ አገሯ እንዲገቡ ፈቀደች የሚል ወሬ አንዱ ደውሎ ሹክ አለኝ፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹የሰማኸው ነገር አለ?›› አለኝ፡፡ ‹‹አሁን አንዱ ደውሎ ነግሮኛል፡፡ ነገር ግን የማይታመን ወሬ ስለሆነብኝ ለመቀበል አዳግቶኛል፤›› ብዬ መለስኩለት፡፡ ‹‹ኧሃ! ይኼ ፌክ ኒውስ መልኩን ቀይሮ መጣ? እኔ እኮ ትራምፕ የሚሉት ዕብድ ስደተኞችን መጥላቱ በአደባባይ እየተናገረና ከስድስት የሙስሊም አገሮች ማንም አይምጣብኝ እያለ፣ ለእኛ ምን ያህል ፍቅር ቢኖረው ነው ከቪዛ ነፃ ኑልኝ የሚለው…›› እያለ ልቡ ፍርስ እያለ ሲስቅ፣ ሳቁ ከእኔ አልፎ ተርፎ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ የሚሰማ ይመስል ነበር፡፡

ከጓደኛዬ ጋር ተሳስቀን ከተሰነባበትን በኋላ በቀጥታ ወደ ቢሮዬ አመራሁ፡፡ ገብቼ ከመቀመጤ ስልኬ አሁንም ጮኸ፡፡ የማላውቀው ቁጥር ነው፡፡ ‹‹ይቅርታ አቶ … ደውል ብለውኝ ነው ቁጥርዎን የሰጡኝ፡፡ አንዴ ያነጋግሯቸው…›› ብላ ደስ የሚል ድምፅ ያላት ሴት ወደማውቀው ሰው አስተላለፈችኝ፡፡ ሰውየው የደወለልኝ ለሥራ ጉዳይ ስለነበር ለደቂቃዎች ያህል ተነጋግረን ልንሰነባበት ስንል ከጠዋት ጀምሮ የምሰማውን ጉዳይ ለማጣራት ፈለግኩ፡፡ ‹‹የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ያለ ቪዛ ወደ አሜሪካ ለመግባት ፈቀደ የሚባል ወሬ ሰምቼ ነበር፡፡ እባክህ ስለሁኔታው ሰምተህ ከሆነ ንገረኝ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ሰውየው ምንም አለመስማቱን፣ ነገር ግን አሜሪካ ኤምባሲ የሚያውቀው ሰው ስላለ አጣርቶ እንደሚነግረኝ ቃል ገብቶልኝ ተሰነባበትን፡፡

ከጥቂት ቆይታ በኋላ ስልኬ ሲጠራ አነሳሁት፡፡ የቅድሙ ቁጥር ነው፡፡ ድምፀ መረዋዋ ‘ይጠብቁ’ ብላኝ ከአለቃዋ ጋር አገናኘችኝ፡፡ ሰውየው በሳቅ በታጀበ ድምፅ፣ ‹‹አቶ እስክንድር የሰማኸው ወሬ ብዙ ቦታ ተዳርሷል፡፡ ባይገርምህ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀሩ በትዊተር አካውንታቸው ሲቀባበሉት ነበር፡፡ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማት የፌስቡክ ገጾች ላይም ‘ሼር’ ተደርጓል፡፡ በጣም ይገርማል፡፡ ከኤምባሲው ወዳጄ እንዳጣራሁት ወሬው በጣም የተሳሳተ ነው፡፡ የፈጠራ ወሬ ነው ብልህ ይቀላል፡፡ ዘመኑን ታውቀው የለ? ሐሰተኛ ወሬዎች በጣም ከመለመዳቸው የተነሳ አንተ ሽሮ አሮብህ እያለ ደልቶህ በጥጋብ እንደምትኖር ይወራብሃል፡፡ ሐሰተኛ የወሬ ፋብሪካዎች ስለበዙ በማናቸውም ጉዳይ ላይ እጅ እግር የሌለው ወሬ ይሠራጫል፡፡ ለማንኛውም የተባለው ሐሰት ነው፡፡ ያልተጣራ ወሬ ነው፡፡ ችላ በለው፤›› ብሎኝ ተለያየን፡፡

የዚያን ቀን እስከ ምሣ ሰዓት ድረስ ይኼው የሐሰት ወሬ ብዙ ቦታ መዳረሱን ሰማሁ፡፡ አንድ በነገሩ የተገረመ ወዳጄ፣ ‹‹ሰፊው ሕዝብ ይህንን ወሬ ሲሰማ ምን ይል ይሆን?›› አለኝ፡፡ እኔም ከሰው ሰው እንደሚለያይ ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ እሱ ግን በፍፁም አለ፡፡ ‹‹ወዳጄ አሜሪካ ያለ ቪዛ መሄድ ይቻላል የሚለውን ወሬ የሚያስተባብለው ከሌለ አዳሜ ያለ የሌለውን ባገኘው ዋጋ ሸጦ ይነሳል፡፡ ያኔ ከሃያ ዓመት በፊት ትዝ አይልህም? ገና ለገና ዲቪ ሎተሪ በመሙላታቸው ብቻ ቤታቸውን በደላላ አሽጠው በኪራይ ቤት መኖር የጀመሩ? ቲቪ፣ ሶፋ፣ ቁም ሳጥን፣ አልጋ፣ ወዘተ የሸጡ ሁሉ ነበሩ…›› እያለ ሲዘረዝር በዓይነ ህሊናዬ ታየኝ፡፡ ያኔማ ትዳራቸውን ፈትተው ጭምር ለጉዞ ሲዘገጃጁ የነበሩ አይረሱኝም፡፡ መኖሪያ ቤታቸውን ሸጠው አጨብጭበው የቀሩም ነበሩ፡፡ ያለ የሌለ ንብረታቸውን ሸጠውም ዳግም የማይመለሱ ይመስል ስንት ነገር ይናገሩ የነበሩም አይረሱኝም፡፡ አገር የጠላ ትውልድ ምሳሌ ነበሩ፡፡ ወይ ጊዜ?

‹‹እና የአሁኑና የዚያን ጊዜው እንዴት ይነፃፀራል?›› በማለት ቀለል አድርጌ ጠየቅኩት፡፡ ‹‹የእኔ ወንድም አሜሪካ ሲባል አቅሉን የሚስተው ብዙ ነው፡፡ ለምን፣ መቼ፣ እንዴት፣ የት፣ … ማለት መቼ ይታወቃል? መጠየቅና መመራመር ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ አሉባልታ አይደለም ወይ ትዳር የሚበትነው? የሰው ነፍስ የሚያስጠፋው? የዘመናት ጓደኝነትን የሚያጠፋው? ያልተጣራ ወሬ አይደለም ወይ በሰላም ከምትኖረው ጎረቤትህ ጋር እሳትና ጭድ የሚያደርገው? እናትና ልጅን የሚያባላው ሐሰተኛ ወሬ አይደለም ወይ?›› ሲለኝ ዝም አልኩ፡፡ ጓደኛዬ ቀጠለ፡፡ ‹‹ይልቅ የሰማሁትን ልንገርህ፡፡ አሜሪካ ያለ ቪዛ የመግባት ዕድል ተገኝቷል የሚለውን ፌክ ኒውስ የሰሙ አሽሟጣጮች ምን አሉ መሰለህ? ሻንጣቸውንና ሌጣ ፓስፖርታቸውን የያዙ ምስኪኖች አውሎ ንፋስ ይሁን ጎርፍ ይውሰዳቸው አይታወቅም ሜክሲኮ ደረሱ አሉ፡፡ በደስታ ብዛት አሜሪካ ለመግባት ተንደርድረው ሜክሲኮና አሜሪካ ድንበር ሲደርሱ ደነገጡ፡፡ ምክንያቱ ምን መሰለህ? ለካ እነሱ ሜክሲኮ ከመድረሳቸው በፊት ትራምፕ ግንቡን ግጥም አድርጎ ገንብቶታል…›› እያለ ትንፋሽ እስኪያጥረው ሲስቅ፣ የሐሰተኛ ወሬ ጦሱና መዘዙ እየዘገነነኝ ድርቅ ብዬ ቀረሁ፡፡ ምን ይታወቃል? ከዚህ የባሰ ሐሰተኛ ወሬ ተፈብርኮ የሰው ልጅ ሕይወት አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ያኔ ‹‹አፕሪል ዘ ፉል›› እያሉ ማላገጥ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ‘ለምን፣ መቼ፣ የት፣ ማን፣ እንዴት…’ ብሎ መጠየቅ ማንን ገደለ? (እስክንድር መካሻ፣ ከሲኤምሲ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...