Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበአስፈጻሚው ላይ ‹የትግል ጥሪ› ያቀረበ ስብሰባ

በአስፈጻሚው ላይ ‹የትግል ጥሪ› ያቀረበ ስብሰባ

ቀን:

የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕክል በዚሁ ስም የሚጠራ የሕግ ሰውነት ያለው፣ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ የተቋቋመው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 311/2006 ነው፡፡ የተቋቋመበት ዓላማ ጥናትና ምርምር በማካሄድ የፖሊሲና የስትራቴጂ ሐሳቦችን ማመንጨት ነው፡፡ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡

ማዕከሉ በመጋቢት 2009 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ በጠራውና የክልሎችና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔዎች፣ የመንግሥት ሚዲያ ተቋማት አመራሮች በተገኙበት የሳሮ ማርያ የአንድ ቀን ዓውደ ጥናት ላይ የሕዝብ ተሳትፎን ችግር ያጠና ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡ ውይይትም ተካሂዷል፡፡ የፖሊሲና ጥናትና ምርምር ማዕከሉ መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ያስተዋወቀው የጥናት ሰነድም በ2008 ዓ.ም. ውስጥ በማዕከሉ ከተጠኑ 14 ጥናቶች መካከል አንዱ መሆኑን ሰምተናል፡፡ ‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች ጥናት ሪፖርት›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኼ ጥናት፣ በተለያዩ ጊዜያት ለሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ለዘርፉ ምሁራን ቀርቦ ግብዓቶችን በማሰባሰብ እንዲዳብር መደረጉንም በስብሰባው መክፈቻ ላይ ከተሰጡ የማስተዋወቂያና የመግቢያ መግለጫዎች ተረድተናል፡፡ የዕለቱ ዓውደ ጥናት የተዘጋጀውም ጥናቱን አጠናቅቆ (ማለትም ተጨማሪ ግብዓቶችን አሰባስቦ) ለሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፍ አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነ ከዚሁ የዓውደ ጥናቱ የመግቢያ ገለጻ ሰምተናል፡፡

አቶ ዓባይ ፀሐዬ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስብሰባውን የከፈቱት የስብሰባውን ዋነኛ ጭብጥ ማጠንጠኛ ሐሳብ፣ መሠረታዊ ጉዳይና ግብ በገለጸውና በውይይቱ መግቢያ ላይ በአጭሩና ጠቅለል አድርገው የዘረገፉትም እሳቸው ናቸው፡፡ እውነትም በቃሉ/በሐረጉ ትክክለኛ ትርጉሙና አግባብ የመክፈቻ ንግግር (Keynote) ነበር፡፡ 

የሕዝብ ተሳትፎ በተፈለገው ደረጃና በተፈለገው ፍጥነትና ጥልቀት እንዳይሄድ የሕዝብ ወሳኝነት ሚና፣ የሕዝብ ጫና ፈጣሪነት ድርሻ፣ የሕዝብ የበላይነት ሚና ወደ ማረጋገጥ ደረጃ እንዳይደርስ ያደረጉ ማነቆዎችን ገና ከመነሻውና በመግቢያው ንግግራቸው ሲገልጹ ዋነኛው ችግር፣ የመንግሥት የሥራ አስፈጻሚው አካል እንቅፋቶች መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ የምክር ቤቶች፣ የማኀበራት፣ የመገናኛ ብዙኃን የራሳቸው እጥረቶችና ችግሮች ሌላው በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ችግርና ማነቆ ነው፡፡ የሪፖርቱም ይዘትና ግኝት የሚከሰውና የሚወቅሰው በመጀመሪያ ደረጃ ሥራ አስፈጻሚውን በተለይም አመራሩን፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ‹‹የሕዝብ ተሳትፎ የሚረጋገጥባቸው ተቋማት›› የሚላቸውን የተወካዮች ምክር ቤቶችን፣ ማኅበራትንና መገናኛ ብዙኃንን ነው፡፡

የስብሰባውም፣ የጥናቱም፣ የጥናቱ ሪፖርትም ዋንኛ ባለጉዳዮች አስፈጻሚው፣ ምክር ቤቶች፣ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኃን ናቸው፡፡ ምክር ቤቶች ማለት በየደረጃው የተመረጡ የፌዴራም የክልልም ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በፌዴራልም፣ በክልልም፣ የየመንግሥታቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ናቸው የሚላቸው ናቸው፡፡ በጠቅላላ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ምርጫ የሚመረጡ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ፣ ወይም የቀበሌ ምክር ቤቶችም በዚህ ውስጥ ይካተታሉ፡፡

ሌላው ባለጉዳይ ጥናቱ፣ የጥናቱ ማዕከል ‹‹ማታገያ ፕላትፎርሙ›› ለትግል የጠራቸው ማኅበራት ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ፣ የመንግሥትም ፖሊሲ ‹‹አደረጃጀቶች›› የሚላቸውን ነው፡፡ ሚዲውም ባለጉዳይ ተብሎ የጥናቱ ባለጉዳይ፣ የጥናቱ ርዕሰ ጉዳይና የስብሰባው ተሳታፊ ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ ሚዲያ ማለት ግን የመንግሥት ሚዲያን ብቻ ነው፡፡

አስፈጻሚው አካል ዋናው ባለጉዳይ ቢሆንም የጥናቱም፣ የሪፖርቱም፣ የስብሰባውም ዋነኛ መሐንዲስም፣ (የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከሉ) መደብ ሥራ አስፈጻሚው ውስጥ ቢሆንም፣ ትግሉ ያነጣጠረው ግን በአስፈጻሚው ላይ ነው፡፡ አቶ ዓባይ ፀሐዬ በስብሰባው መግቢያ ላይ እንደ ነገሩንም ‹‹አስፈጻሚው አካል በአብዛኛው እዚህ [ስብሰባው ውስጥ] የለም›› ምክንያቱም አቶ ዓባይ በመግቢያቸው እንደተናገሩት ዓላማው በጥናቱ ላይ ተነጋግሮ፣ አዳብሮ በተለይም መፍትሔ ሐሳብ ላይ የሚፈለገው ደረጃ ላይ እንዲደረስ አድርጎ ከዚያ በኋላ ‹‹አስፈጻሚው አካል ትኩረት ሰጥቶ እንዲያየውና ተጨባጭ ምላሽ እንዲሰጥበት›› ስለተፈለገ ነው፡፡

የመንግሥት  ሥራ አስፈጻሚው ‹‹ሂድ፣ ዞር በል መባል አለበት››፣ ‹‹ሃይ የሚለው ያጣ ነው›› የተባለበት፣ ፓርቲውም ለገዛ ራሱ ግምገማ እንዲታመን የተጠየቀበት ይህ መድረክ፣ በተለይም የአቶ ዓባይ ፀሐዬ የመዝገቢያ ንግግር ከተለመደውና ከለመድነው አሠራር ለየት ያለ በመሆኑ (በሪፖርተር መልካም ፈቃድ) የዛሬው ተሟገት ርዕሰ ጉዳይ አድርጌ ሙሉውን ቃል አቅርቤዋለሁ፡፡      

 

አቶ ዓባይ ስብሰባውን የዘጉትና የመዝጊያ ንግግራቸውን የጀመሩት ጉዳይ ከተለያየ አቅጣጫ በማዕከሉ ብቻ ሳይሆን በሚዲያውም፣ በምክር ቤትም ሲጠናና ሲመከርበት እንደነበር ገልጸው፣ ‹‹እዚህ ሰብሰብ ሲል ሐሳቡ ትንሽ ጉልበት የሚያገኝበት ሁኔታ የተፈጠረ ይመስለኛል፤›› ብለው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡

. . . ስለዚህ አሁን ዋናው ነገር የሚመስለኝ የተነገሩ ሐሳቦች የሚሰጡት መልዕክት አለ፡፡ ምክር ቤትም ሄዶ ሄዶ በፌዴራልና በክልል ደረጃ ያሉት ምክር ቤቶች እንኳን በርካታ መሻሻል ያሳዩ ቢሆንም፣ የመሻሻል ጥረት ያለ ቢሆንም፣ መሠረታዊ ለውጥ አላመጡም፡፡ ለምን? የሚለው ያው የራሳቸውን ድክመትና የአስፈጻሚው ጫና ነው የሚል ጥቅል የመፍትሔ ምንጭ ተቀምጧል፡፡

ይኼን እንዴት ነው ሰብረን የምንወጣው? ይኼን እንዴት ነው የምንቀይረው? የሚል ነገር፣ አሁን ከፓርላሜንተሪ ሥርዓታችን የመነጨ ችግር አይደለም፡፡ ጠንካራ ፓርላማዎች አሉ በፓርላማ ሥርዓት፡፡ የፓርላማ ሥርዓት ባላቸው አገሮች፡፡

አብላጫ ድምፅ ያለው ፓርቲ መኖርም አይደለም ችግሩ፡፡ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ፓርቲዎች ሆነው፣ ግን የገዛ ራሳቸውን ፓርቲ፣ የገዛ ራሳቸውን መንግሥት፣ ቀን ተቀን፣ በየሰዓቱ ሲፈትሹ፣ ሲወጥሩ፣ ሲቆጣጠሩ የሚውሉ ምክር ቤቶች አሉ፡፡ በዓለም፡፡  

ስለዚህ የእኛም ይቻላል፡፡ የፓርላሜንተሪ ሲስተሙን ሳንቀይር፣ የአብላጫ ወንበር የያዘ ገዢ ፓርቲ መኖር እንደ ችግር ሳንቆጥር፣ ግን አሠራሩ ላይ፣ አፈጻጸሙ ላይ፣ በተለይም አመለካከት ላይ፣ ያሉ ችግሮች መቀየር የሚቻልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ዝግ አይደለም፡፡ መወሰድ ያለባቸው ተጨባጭም ዕርምጃዎች አሉ፡፡ ዛሬ ሲዘረዘር እንደዋለው፡፡

ለምሳሌ አስፈጻሚው ለምክር ቤት የሚያቀርበው የክልልም የፌዴራልም ሕግ ካለ ሹመት ካለ፣ ሪፖርት ካለ፣ በጀት ካለ፣ (በጀት እንኳን ይሻላል ጥቂት ጊዜ ይሰጧቸዋል)፡፡

አሁን ያለው በጥድፊያ ነው፡፡ በሰዓታት ውስጥ አፅድቁ ነው፡፡ በተለይ ሹመትና ሪፖርት፣ ለበጀትና ለሕግ በሚሰጥ ጊዜም ለቋሚ ኮሚቴዎች የተሰጠ የተወሰነ ጊዜ ይሰጣል ማብራሪያ ይደረጋል፡፡ ሕዝብ የውይይት መድረክ ይጠራል፡፡ “Routine” ፕሮሲጀሮች አሉ፡፡ ሕዝቡም ለውጥ አያመጣም ስለሚል አይመጣም፡፡ አይሳተፍም፡፡ የሚሳተፈው ጥቂት ነው፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም የሚለውጠው ነገር ስለማይኖር እንዲገባው ግን ጥረት ያደርጋል፡፡ የግድ ይለውጠው ማለትም አይደለም፡፡ ብቃት ያለው ሕግ ከመጣ ወይ ጥራት ያለው ተዓማኒነት ያለው በጀት ከመጣ የግድ ካልቀየረ ሥልጣን የለውም ማለት አይደለም፡፡

አምኖበት ማፅደቁ፣ በብቃትና በብስለት ፈትሾት ማፅደቁ ላይ ነው ዋናው ጉዳይ፡፡ ስለዚህ ይኼን ለማድረግ ድርጅታዊ አሠራርም ሊገታው የሚችል አይመስለኝም፣ እንዲገታው እየተደረገ ነው፡፡ በአፈጻጸም፡፡ ግን “Necessarly” እንዲገታው አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ገዢ ፓርቲ አሜሪካም ጭምር ሪፐብሊካን አብላጫ ድምፅ ካላቸው የፈለጉትን ሕግና በጀት ያፀድቃሉ ነው የሚባለው፡፡ ግን በሰዓታት አያፀድቁትም እነሱም፡፡ አንዳንዴ በሳምንታት አንዳንዴ በወራት ነው የሚያፀድቁት፡፡ አገላብጠው፣ ፈትሸው፣ አንቀጥቅጠው ፕሬዚዳንቱን ወይም ፈጻሚውን የራሳቸው ፓርቲ ያስመረጠው ፕሬዚዳንት ያቀረበውን፡፡ ዝም ብለው አይፈርሙም፡፡ አንድ የብቃት ችግር [የለም]፡፡ ሁለት የዴሞክራሲ ባህል ብስለት አለ፡፡ ሦስት የአሠራር ሥርዓት አለ፡፡

ስለዚህ አንጣደፍም ካሉ አንጣደፍም ነው፡፡ የፈለገው ኡኡ ይበል ፕሬዚዳንቱ፣ ካቢኔው፣ በሁለት ወር ጊዜ ወስደን ነው የምናፀድቀው ካሉ፣  የራሱ ጉዳይ የት ከርሞ ነው . . . የሚያጣድፏቸው?  በጊዜ ማቅረብ አለበት፡፡ ሂድ ዞር በል መባል አለበት፡፡ ይህን የማለት ድፍረቱ እንዲኖር ከተፈለገ፣ መጀመሪያ መስተካከል ያለበት ኢሕአዴግ ነው፡፡ ካቢኔ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ፣ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የየድርጅቱ አመራሮች ናቸው፡፡ ፀረ ዴሞክራቲክ አመለካከት የተጠናወተው ስለሆነ (ይኼ በተሃድሶው አሁን የተገመገመ ግምገማ ነው፡፡ (የግሌ ግምገማ አይደለም፡፡) ፀረ ዴሞክራሲ በጣም የገነገነበት ነው፡፡

ስለዚህ ሂድ ያመጣኸውን ሪፖርት፣ ሕግ ወይም በጀት አልቀበልም፣ ሹመት አልቀበልም ሊባል ይቅርና ጠንከር ያለ ጥያቄ ከቀረበ እንኳን የሚያንገራግርና የሚያኮርፍ አካኪ ዘራፍ የሚል አመራር ነው ያለን፡፡ ስለዚህ ይኼን አደብ ግዛ! ሥርዓት ያዝ! የሚል የፓርቲ፣ የራሱ ፓርቲው ጥንካሬ ከሌለና ፓርቲው በዚህ ዙሪያ ሕዝቡን አነቃንቆ፣ የድርጅቱን አባል አነቃንቆ አስተካክል፣ ይኼንን የሚል ንቅናቄ ‘ሙቭመንት’፣ ትግል ካልተቀጣጠለ ቅድም እንደተባለው በልመና በማሳሰቢያ አይስተካከልም!

የተሃድሶ ግምገማ የኢሕአዴግ፣ የዘጠና አራቱ፣ የዘጠና ሦስቱ ራሳችን እጅ እግራችንን ካላሰርን፣ በሕዝቡ፣ በዴሞክራሲ ተቋማት፣ በአሠራር፣ በሕግ ካልታሰርን እንዘቅጣለን፡፡ ፀረ ሕዝብ ፓርቲ እንሆናለን፡፡ ፀረ ሕዝብ መንግሥት እንመሠርታለን፡፡ ወይ ወደዚያ እንቀይረዋለን ነው የሚለው የተሃድሶ ግምገማው፡፡ ከ15 ዓመት በፊት የተገመገመ፡፡ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

ይቅርና የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት ባለበት ሥርዓት ያለ፣ በሠለጠኑ በበለፀጉ አገሮችም፣ በሕግ፣ በሕዝብ ንቃት በተቋማት፣ እጅ እግሩ ካልታሰረ አስፈጸሚው ይፈነጫል፣ ይባልጋል፡፡ እልም ያለ አምባገነን ይሆናል፡፡ በሠለጠኑት አገሮችም፡፡ ‘ኢንኸረንት’ ባህሪይ ነው ይኼ፡፡ ከሥልጣን የሚመነጭ፡፡

ስለዚህ ይታረም እሺ፣ ሒስ ይደረግ እሺ፣ ምክር ይሰጠው እሺ፣ የማይስተካከል ከሆነስ? የማይስተካከል ከሆነ ሊወገድ የሚችልበት፣ ሊስተካከል የሚችል ሌላ አመራር ከዛው ፓርቲ ከራሱ ከፓርቲው ሊወጣ እንደሚችል ግለሰቡን በመቀየር ይሁን፣ ቡድኑን በመቀየር ይሁን፣ አካሉን በመቀየር ይሁን፣ ‘ሪስትራክቸር’ በማድረግ ይሁን፣ . .  ማሳየት የሚችል ምክር ቤት፣ ማኅበር፣ የሕዝብ ንቅናቄና ዴሞክራሲ ተቋማት መኖር አለባቸው፡፡

ይኼ በዚህ ጥናት ብቻ አይመጣም፡፡ አጠቃላይ ፓርቲው በማድረግ ላይ ያለው ጥረት ይኼን ለማድረግ ነው፡፡ እየተንገራገጨ፣ እየተኮላሸ ቢሆንም፡፡ ዓላማው ግን ይኼን ለማምጣት ነበር፣ የጥልቀት ተሃድሶ ምናምን ያልነው፡፡ እርሱ ወደዚያ ለመሄድ ነበር፡፡ ወደዚያ ለመሄድ መንገዱ አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ አይሆንም፡፡ [እየሆነ አይደለም]

ግን ይቺ አገር እንዳትፈርስ ወደ ትርምስ እንዳትገባ ከተፈለገ መንገዱ እሱ ብቻ ነው፡፡ መፍትሔው እሱ ብቻ ነው፡፡፡ አለበለዚያ ይቺ አገር እንደ እሳት ትቀጣጠላለች፡፡ ኢሕአዴግም ይኼን ያውቃል ፡፡ ሕዝቡም ያውቃል፡፡ አይተናል፡፡ በሁለት ወር በሦስት ወር ውስጥ ምን [ዓይነት] እሳት መቀጣጠል ጀምሮ እንደነበር፡፡

ስለዚህ ለራሱ ሲልም ይስተካከል፣ ኢሕአዴግ በተለይ አመራሩ፡፡ ሕዝቡም ለራሱ ሲል ይህን ያስተካክል፡፡ ምክር ቤቱ፣ ማኅበሩ፣ ሚዲያው ምኑ ምኑ እገሌ ያስተካክለው ብሎ ጣት ቀስሮ ከእሱ [ከሌላው] መጠበቅ የትም አያደርስም፡፡ ሁሉም የየድርሻውን ካልተወጣ፡፡

ስለዚህ ለዚህ ነገር ባለቤት የሆኑ አካላት አሉ:: እዚህ፡፡ ኢሕአዴግ ራሱ አለ፡፡ ኢሕአዴግ ሲባል አመራሩ ብቻ አይደለም፡፡ አባሉ ነው፡፡ አባሉ ደግሞ ለሕዝቡ ቅርበት ያለው ነው፡፡ ለፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ የተሻለ ሊወግን የሚችል ነው፡፡ ለሥልጣን፣ ለሀብት ብዙ ቅርበት ስለሌለው፡፡ ታች ያለው፡፡ እና እሱ ሊቆምለት ይችላል ይኼን ሐሳብ፡፡ የማስተካከል ሐሳብ፡፡ ማኅበራትም ሊቆሙለት ይችላሉ፡፡

የምክር ቤት አባላትም በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ብለው ሊቆሙ ይችላሉ፣ በሕዝብ ግፊት ታግዘው፣ በአባላት ግፊት ታግዘው፣ በቀና አመራሮች ተደግፈው፣ . . . መስተካከል ይቻላል፡፡

ከአመራሩ ውስጥም ይኼንን ማስተካከል የሚፈልግ አለ ብዙ . . . ፡፡ በርካታ፡፡ ወይ አቅም አጥቶ ወይ አቅጣጫ አጥቶ . . . የሚንከላወስ ደግሞ ሊኖር ይችላል፡፡ የማይፈልግ ደግሞ አለ፡፡ ደንቃራ፡፡

ይኼ (For the sake of) ጥናት አልተሠራም፡፡ ሌሎች እምናደርጋቸው ጥናቶችም እናንተም የምታደርጓቸው አሁን እንደተገለጸው፡፡

ቋቅ እስኪለው ድረስ ሕዝቡም፣ የኢሕአዴግ አባልም የተከማቹ፣ የተከመሩ፣ ሊፈነዱ የተቃረቡ ችግሮች አሉ እዚህ አገር፡፡ ጊዜ ደግሞ የለም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መደራደር፣ ያው እሳቱ እንዲቀጣጠል መጋበዝ ነው፡፡ ወይ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡ ይኼ እንደተባለው፣ ሲባል እንደዋለው፣ አስፈጻሚው የቻለውን ያህል አምኖበት፣ ባመነበት ልክ፣ የተወሰነ ቁርጠኝነት ፈጥሮ፣ ሊያስተካክለውን የሚችለው ነገር እንዲያስተካክል ነው ይቅረብለት ተሻሽሎ፣ አሁን በዳበረው መልኩ፡፡ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ምክንያቱም እሱም ሊያስተካክል ጥረት እያደረገ ስለሆነ፣ አስፈጻሚው አመራር፡፡ አላስተካክልም ብሎ ድርቅ አላለም፡፡ የማስተካከሉ ፍጥነትና ጥልቀት ላይ ነው ችግር ያለው፡፡ ከቁርጠኝነት ጉድለት፡፡

ይኼ ግን፣ ማኅበራቱም ከአሁን በኋላ በለመዳችሁት መንገድ፣ በትዕዛዛችሁ፣ ተቀጥላ ሆነን፣ መልዕክተኛ ሆነን አንሄድም ካላሉ፣ ብትፈልጉ አፍርሱን ካላሉ፣ ወይ ደግሞ ይህን የሚያደርጉ እዚህ ያሉ አስተዳደሮች ይሁኑ፣ የማኅበር አመራሮች ይሁኑ፣ ምን ይሁኑ ዞር አድርጉ ካላሉ ቆርጠው ምን እንዳይጎድላቸው ነው? ምግባቸውን ራሳቸው ለፍተው ሠርተው የማያመጡት ነው፡፡ እንደ ደመወዝተኛው አይደሉም ማኅበራት፡፡

ምክር ቤትም ወይ ምክር ቤት እንሁን፣ ሕገ መንግሥት በሰጠን ሥልጣን እናድርግ [እንገልገል]፡፡ በአንድ በኩል የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት አባላት ነን፡፡ መሠረታዊውን የፓርቲውን ውሳኔዎች እናስፈጽማለን፣ ፖሊሲዎቹን ሕጎቹን ምኖቹን፡፡ ይህን ስናደርግ ደግሞ ገብቶን፣ ተከራክረንበት፣ ፈትሸነው፣ አምነንበት፣ ነገ የምንቆምለት፣ የምንዋደቅለት እንዲሆን በሚያደርግ ‘ፕሮሰስ’ ይሁን፡፡ “ፕሮሰሱ” ይስተካከል፡፡ እንቢ አናፀድቅም በሉ አይደለም፡፡ አሳማኝ ምክንያት ካቀረቡ ደግሞ ማዳመጥ አለበት፣ ማስተካከል አለበት አስፈጻሚው፡፡ ፈጻሚው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፣ ቁርዓን አይደለም፡፡ ካቢኔ ያፀደቀው ወይ ሥራ አስፈጻሚው አፀደቀው ማለት፣ ላከው ማለት ወደ ፓርላማ አንድ ቃል ወይም አንድ ሐረግ አትቀየርም ማለት አይደለም ኤሰንሱ (Essence)፡፡ ዋናው ፍሬ ነገሩ፣ ቁም ነገሩ ነው፡፡ የማይቀየረው፡፡

በየስድስት ወሩ፣ በየዓመቱ የሚቀየር፣ ሰባት ጊዜ አምስት ጊዜ የሚቀደድ ሕግ አይደለም እንዴ ያለው እዚህ አገር በርካታ ሕግ እናውቃለን እኮ! ይመሰክራል እኮ ምክር ቤቱ! በዘመቻ ይዘጋጃል፣ ያለበቂ ዝግጅትና ብስለት ይዘጋጃል፡፡ በጥድፊያ ይፀድቃል፣ ዓመት ሳይሞላው ይንገራገጫል፡፡ ይኼ ችግር አለው፣ ይኼ ችግር አለው ይባላል፡፡ ምክንያቱም ባለድርሻዎቹ በበቂ መንገድ አልመከሩበትም፣ አፈጻጸም ላይ ሊያጋጥም የሚችል ችግር በደንብ አልተፈተሸም፣ የሚያስፈጸም አካል፣ ተቋም የለም፣ ወይም አይረባም፣ ሰንካላ ነው፡፡ ድውይ ነው፡፡ ተመልሶ ይሻሻል ይባላል ሕጉ፡፡

የኢንቨስትመንት አዋጃችን አምስት ጊዜ ነው ስድስት ጊዜ ነው የተሻሻለው፡፡ ሁለቴ ሦስቴ የተሸሻሉ ሕጎች ብዙዎች ናቸው፡፡

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ፡፡ እንደዚህ መሆኑን እያወቅን ሥራችን እንደገና በጥድፊያ እናፀድቃለን፡፡ በለብ ለብ እንሄዳለን፣ በመደፍጠጥ እንሄዳለን፡፡

“No more” መባል አለበት!

ስለዚህ ይኼ ጉዳይ ምክር ቤቶችም ተወያይተውበት (In Whateever Forum) ካመኑበት ከዚህ ተነስተው እንዲህ ይደረግ አይደረግ የሚል ፕሮፖዛል ይዘው ከአስፈጻሚ ጋር ይከራከሩ፡፡

ሦስት ጊዜ አራት ጊዜ አምስት ጊዜ ያደረቀንን ሚኒስትር ወይም የቢሮ ኃላፊ ይኼ ብቁ አይደለም ብለን ለርዕሰ መስተዳደሩ/ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቤት ብለን ያቀረብነውን ሰው ለምንድነው እንደገና በሹመት እሚቀጥለው? ሂድ! ቀይረው!! አመኔታ የለንም፣ ኮንፊደንስ የለንም፡፡ ኮንፊንስ እንደሌለለን እናውጃለን ከፈለግክ በሚዲያ ማለት መቻል አለባቸው፡፡ ያስተካክል፡፡ አስተካክለን የለም እንዴ አሁን ደቡብ ክልል በየዞኑ እነኚህ እነኚህ የዞን አመራር ይሆናሉ ብሎ አምጥቶ አስፈጻሚው፣ እከሌ እከሌ አይሆንም፣ እገሌ እገሌ ደግሞ መሆን ሲገባው አስቀርታችሁታል አስገቡት፣ ይኼን አውጡ ተብሏል፡፡ ተጠየቁ በአሁኑ ተሃድሶ በበርካታ ዞኖች፣ በአንዳንድ ወረዳዎችና ምናምኖች፡፡

ለምንድነው እዚህ እንደዚያ የማይደረገው? ‘ደብል እስታንዳርድ!’፡፡

ስለዚህ ምክር ቤቶች ጥርስ ይኑራቸው ሊባል ከሆነ (ከተባለ) መጀመሪያ ጥርስ ይኑረን ብለው ጥርስ እንዲያወጡ እነሱም ይታገሉ፡፡ ‘ሳክሪፋይስ’ ያድርጉ፡፡ መስዋዕትነት ይክፈሉ፡፡ ‘ሪስክ’ ይውሰዱ፡፡ ምንድነች? ይሞት የለ እንዴ!? ለማስተካከል ደግሞ ማንስ ነው ምንድንነው የሚላቸው? ምክር ቤቱ በሙሉ ምን እንዳይሆን ነው? ‘ዲስሚስድ’ እንዳይሆን?

ስለዚህ ምክር ቤቱ አቋም ይያዝ፡፡ ይታገል፡፡ ሚዲያውም እንዲሁ፡፡ ቅድም ይቀርቡ የነበሩ ‘ቦልድ’ ሐሳቦች አሉ፡፡ ጠንካራ ሐሳቦች፡፡ ተጠሪነቱ ለምክር ቤት ነው ተብሎ ቦርዱ [ግን] ይኼን የሚዘጋ የሚያስናክል፡፡ አሠራሩ ይኼን የሚያኮላሽ፡፡ ስለዚህ ዱሮውንም የግብር ይውጣ ነው ማለት ነው አዋጁ፡፡ የይስሙላ ነው አዋጁ፡፡

ስለዚህ ወይ ከልብ የሚታመንበት ከሆነ ጥሩ፡፡ “Consistently” ሂድ በዛ፡፡ ልክ እንደ ምርጫ ቦርድ፡፡ ምርጫ ቦርድ እጅ ውስጥ ማን ይገባል? ሊገባ ከተሞከረም እዚያው “Resist” ይደረጋል፡፡

ይኼ ሲሆን ግን [ሚዲያውን ለማለት ነው]  የእኔ ነው፣ እንደፈለግሁ ነው የማደርገው ብሎ ነው እንደ ጓዳ፡፡ አታደርገውም!! [መባል አለበት]

ስለዚህ ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ የማይከራከረው ለምንድነው? ፓርቲው በዚህ ጉዳይ አስፈጻሚውን የማይከራከረውና አስተካክል የማይለው ለምንድነው? ይኼን ካደረገ እነኚህ የምክር ሐሳቦች በተግባር ይረጋገጣሉ፡፡ ይሸጋገራሉ፡፡ መመርያ፣ ደንብ፣ ሕግ ይሆናሉ፡፡

ስለዚህ ምክር ቤት ለራሱ መብት፣ ለራሱ አዋጅ እንኳን እስኪ ይቁም፡፡ ጠንከር ብሎ፡፡ ራሱ ያፀደቀው አዋጅ ጭምር ነው እየተጣሰ ያለው፡፡

ሕግ በመጣስ እኮ የእኛ አስፈጻሚ ከላይ እስከ ታች የሚመረር ሆኗል “Already”፡፡ “Solid Facts” አሉ፡፡ መዓት ጊዜ የሚገመገሙ አሉ፡፡ ሕግ የማያከብር ‘ኤግዝኪዩቲቭ’ ነው ያለው፡፡ ሊያስከብር ይቅርና ራሱ አያከብርም፡፡ ሃይ የሚለው ያጣ ስለሆነ፡፡

ስለዚህ እነኚህን ሁሉ ለማስተካከል በምክር ቤት ደረጃ፣ በማኅበራት ደረጃ፣ በሚዲያ ተቋማት ደረጃ አሁን ጥሩ መፍትሔ አቅርበዋል፡፡ ራሳቸው መክረው አጥንተው፡፡ ጥሩ፡፡

ተቀበል አትቀበል ትግል ያስፈልገዋል፡፡ ዝም ብሎ አይቀበልም፡፡ አውቃለሁ፡፡ በትግል ይቀበላል፡፡ ዘጠና በመቶ ወይም ሰማንያ አምስት በመቶው፡፡ አሳማኝ ነገር ካመጣ ደግሞ ጥሩ፣ ከእሱም መቀበል ነው፡፡

ስለዚህ ሁለት ነገር ነው ለማለት እየሞከርኩ ያለሁት፡፡ አንደኛ ይኼ ዛሬ የተወያየንበት ምክር ቤቶች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ መንግሥትና ማኅበራት “Own” ያድርጉት፡፡ የእኛ ነው፣ ከዚህ በኋላ ይኼ ‘ፔፐር’ የጥናትና ምርምር ማዕከል አይደለም፣ የብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ አይደለም፣ የእኛ ሰነድ ነው ብለው እንዲይዙት ነው የሚፈለገው፡፡

ለዚያ ይታገላል ይኼ ማዕከል፡፡ ፓርቲውም ለዚያ መታገል አለበት፡፡ ፕላትፎርም ነው ይኼ፡፡ ማታገያ ነው፡፡ ይኼን እንተግብር፡፡ በትግል ነው የሚተገበረው፡፡ አልጋ በአልጋ መንገድ አይተገበርም ይኼ፡፡ ሌላ ነው፣ “ሻርፕ” ነው፡፡ ከነበረው ለየት ያለ አቀራረብ ነው፡፡ እዚህ ደግሞ አጠናክራችሁታል ዛሬ በደንብ፡፡ በዚህ መንገድ ይስተካከላል፡፡ ወደ ኋላ ወደፊት ይኖር ይሆናል፡፡ ግን መሄድ አለበት፡፡ ዳር መድረስ [አለበት]፡፡

ይኼ ደግሞ በክረምት በተደረገ የኢሕአዴግ ግምገማ ከዚህ በላይ ነው የተገመገመው፡፡ ከዚህ በላይ:: ምክር ቤቶችን፣ ማኅበራትን፣ መገናኛ ብዙኃንን ፀረ ዴሞክራቲክ በሆነ አመለካከታችን ምክንያት አሰናክለን፣ አኮላሽተን፣ አፍነን ‘ፓራላይዝ’ አድርገናቸዋል ነው ግምገማው፡፡ የኢሕአዴግ ግምገማ ነው ይኼ፡፡ ኢሕአዴግ የገመገመው በሰነዱ ነው፡፡ አዲስ ግምገማ አላስቀመጠም፡፡ “Loyal to Its Own”. ግምገማ ይሁን እስቲ፡፡ [እስቲ ለገዛ ራሱ ግምገማ ይታመን]፡፡

ካፉ ባወጣት፣ በብዕሩ በጻፋት ይጠየቅ፡፡ “Keep your Words” ይባል፡፡ ይኼንን ነው የሚለው፡፡ ይኼ ጥናት “Nothing New”. የገመገምከው፣ በገመገምከው ልክ መረጃ አስደግፈን አመጣነው እንጂ፣ አሁን ደግሞ ዛሬ እናንተ [አበለፀጋችሁት] መፍትሔውን እንጂ፣ ዋነው ቁም ነገሩ (ቤዚክ ኤሴንሱ) የተገመገመው ነው፡፡

አዎ ይኼ ችግር አለብን ተብሎ ታምኗል፡፡ እንግዲያውስ ይኸው በመረጃ ተደግፎ ተዘርዝሮ መጥቷል፡፡ ዘርዘር ያለ መፍትሔ መጥቷል፡፡ በል ወደ ሕግ፣ ወደ ደንብ፣ ወደ ተቋም፣ ወደ አሠራር፣ ወደ ሥልጠና፣ ወደ አቅም ግንባታ ፓኬጅ ዕቅድ ይውጣለት በሚል እንሂድ፡፡

ይኼ ከአንድ ሰው ጋር፣ ከአምስት ሰው ጋር፣ ከምን ጋር በመወያየት አይሳካም፡፡ ስለዚህ የፓርቲው አመራር፣ ካቢኔው፣ በክልልም በፌዴራልም ያለ፣ ከዚያም ደግሞ የማኅበር አመራሮች፣ የምክር ቤት አባላት፣ የሚዲያ ጋዜጠኞችና አመራሮች አምነውበት፣ አውቀውት፣ ታግለውለት ነው የሚሳካው የሚተገበረው፡፡

እንደ ሌላው ቀለል ያለ ዓይነት ሕግና [ሌላ ነገር] ካቢኔው ተወያይቶ አፅድቆት ወደ ፓርላማው ልኮት ፀድቆ ዓይነት የሚሄድ አይደለም፡፡ አይደለም፡፡ ይኼ ኢንተረስትስ ይነካል፡፡ ይነካል፡፡ እንዲነካም ነው የተፈለገው፡፡

ስለዚህ ምከር ቤት መገናኛ ብዙኃን፣ የብዙኃን ማኅበራት (ችግሩን ድክመቱን እንዲፈትሸው የማይፈልግ አመራር አለ፡፡ ሁላችንም እንደዚያ ያለ ማንገራገር አሳይተናል በተለያየ ጊዜ፡፡ “Nobody is Exception” እኛም ሌሎችም) ስለዚህ ለዚህ ተገዢ እንሁን ለሕዝቡ ብለን፣ ለአገር ብለን፣ ለዓላማ ብለን፡፡

ይጠቅማል ተገቢም ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ላይ ለምን አሰፈርነው ታዲያ? እና ይኼ ማታገያ ፕላትፎርም ነው፡፡ “ፒዩር” ጥናት አይደለም፡፡ በትግል ካልሆነ በስተቀር አይተገበርም፡፡

ሥራ አስፈጻሚውም ታግሎ ከልብ ሊያፀድቀውና በቁርጠኝነት ሊተገብረው በውስጡ ትግል ያስፈልገዋል፡፡ ካቢኔውም እንደዚሁ፡፡ ምክር ቤቱም እንደዚሁ፡፡ ሚዲያውም እንደዚሁ፡፡ ማኅበራትም እንደዚሁ፡፡ ሁላችንም በውስጣችን ታግለን ከሌላው ጋርም ታግለን፣ ተላልጠንም ወጥተን ወርደንም እዳር የምናደርሰው ነው፡፡

የዴሞክራታይዜሽን አንድ ትልቅ አጀንዳ ነው ይኼ፡፡ ይኼን ካደረግን ከዚህ በተረፈ በየጊዜው የሚዘረዘሩ ቅድም እንደተባለው ዘርዘር ያለ መፍትሔ ስለሚዲያ የቀረበ አለ፡፡ ስለማኅበራትም የሆነ ነገር ቀርቦ ይሆናል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤትም በየጊዜው የሚያቀርበው ሐሳብ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ ያሻሻለው ነገር የውስጥ አሠራር ይሁን፡፡ ከፈጻሚዎች ጋር ያለም እንዳለ ይታወቃል፡፡ ግን ከዚህም በላይ እንሂድ ብሎ ዘንድሮም እየሠራ ነው፡፡ ጥሩ፡፡

ይኼ ተደምሮ ወደዚህ እንዲወስደን ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ጠዋት [አቶ] ሽፈራው ‘ንቅናቄ’ ይለው የነበረው ንቅናቄ፣ እኮ በተፈጥሮ ሀብትና በምርጫ ብቻ አይደለም፡፡ አሁንም እኮ ንቅናቄ ተብሎ ነው የተገባው ወደ ተሃድሶ፡፡ አንድ አጀንዳ ሆኖ ይኼ አብሮ እንዲሄድ፡፡ ስለዚህ ያ ንቅናቄ ግን ‘ሲዝናል’ (የወረት) አይሁን፡፡ ቦግ ብሎ ድርግም የሚል መሆን የለበትም፡፡ ቀጣይ ከሆነ ብቻ ነው ‘ሞመንተም’ የሚኖረውና ለውጤት የሚደርሰው፡፡ ዛሬ በሰጣችሁን አስተያየት ስላዳበራችሁት በጣም እናመሰግናለን፡፡

ግን ይኼ የመጀመሪው “Kick Off” ነው፡፡ ጉዞውና መንገዱ ትግል የሚጠይቅ፣ ውጣ ውረድ የሚኖረው፣ ትንሽ ረዘም ያለ ነው፡፡ ይኼ ወረቀት ላይ የሰፈረውና ዛሬ የታከለውና የተጨመረው ነገር ተግባራዊ ሆኖ፣ ተቋም ሆኖ፣ ሕግ ሆኖ፣ ደንብ ሆኖ፣ መመርያ ሆኖ፣ አመላከከት ሆኖ፣ ልናየው [እናየው ዘንድ] የተወሰነ ትግል፣ የተወሰነ ጊዜ፣ የተወሰነ ዋጋ ይጠይቃል፡፡

ግን ይተገበራል፡፡ ለምን? ሕዝቡ ይፈልገዋል፡፡ አገሪቱ ትፈልገዋለች፡፡ ይኼ ሁሉ የሚማረር ተቋም ይፈልገዋል፡፡ አመራሩም አብዛኛው ይፈልገዋል፡፡ አባሉ ደግሞ ከሞላ ጎደል ነው ሁሉም የሚፈልገው [ነው]፡፡

ስለዚህ የሚፈልገው ስለሚበዛ ይህን ኃይል ማነቃነቅ ከተቻለ፣ ማስተካከልና ተግባራዊ ማድረግ፣ ህያው ማድረግ፣ ለውጤት ማብቃት ይቻላል፡፡

እናመሰግናለን፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...