Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለብይን ተቀጥረው ያለፍርድ ቤት ዕውቅና የተለቀቁት ተጠርጣሪ ጉዳይ ፍርድ ቤቱን አስቆጣ

ለብይን ተቀጥረው ያለፍርድ ቤት ዕውቅና የተለቀቁት ተጠርጣሪ ጉዳይ ፍርድ ቤቱን አስቆጣ

ቀን:

  • የተለቀቁት የሚያስከስሳቸው ስለሌለ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ ተናግሯል
  • ሁለት ተጠርጣሪዎች የ50,000 እና 150,000 ብር ዋስትና ተፈቀደላቸው

ከቤተሰቦቻቸው ጋር አሜሪካ ዕረፍት ላይ ቆይተው ሲመለሱ በቁጥጥር ሥር ውለው በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ምርመራ ሲደረግባቸው የከረሙት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ፣ ለብይን ተቀጥረው ሳለ መለቀቃቸው ፍርድ ቤቱን አስቆጣ፡፡ የሚያስከስሳቸው ነገር ባለመገኘቱ ከፖሊስ ጣቢያ እንደተለቀቁ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የባለሥልጣኑ ባልደረባ አቶ በቀለ ባልቻም ምርመራቸው ተቋርጦ በተመሳሳይ መንገድ መለቀቃቸውንም አክሏል፡፡ አቶ የኔነህ አሰፋና የሀዚአይአይ ተቋራጭ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዛኪር አህመድ በዋስ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ በነበረው የችሎት ውሎ አቶ ሳምሶን፣ አቶ በቀለና አቶ የኔነህ ከገቢያቸው በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራታቸውን በመጠቆም ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዳስፈለገው ገልጾ፣ የሰባት ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት የተቃውሞ ሐሳብ፣ በቂ የምርመራ ጊዜ ወስዶና ምርመራውን አጠናቆ ለዓቃቤ ሕግ እንዳስረከበና ዓቃቤ ሕግም የምርመራ መዝገቡን መረከቡን አረጋግጦ ሕጉ በሚፈቅደው 15 ቀናት የክስ ማቅረቢያ ጊዜ እንደተፈቀደለት አስታውሰው፣ በሕግ የተፈቀደለትን ጊዜ አሟጦ በመጠቀሙ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊያስፈቅድበት የሚችል የሕግ አግባብ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረት እንዳልቻለ ተቆጥሮ በነፃ እንዲሰናበቱ ወይም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

የተጠርጣሪዎቹን መቃወሚያ ሐሳብ በመቃወም ለፍርድ ቤቱ በድጋሚ አቤቱታውን ያሰማው ዓቃቤ ሕግ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 ክስ የማቅረቢያ ጊዜን ከመፍቀድ ሌላ እንደማይከለክልና ለትርጉም ክፍት መሆኑን በማስረዳት፣ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎ የጠየቀው ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በምርመራ መዝገቡ ላይ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ያዘጋጀውን ብይን ለመንገር ተጠርጣሪዎቹን በመጥራት ላይ እያለ፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹አቶ ሳምሶን ወንድሙ ላይ ክስ መመሥረት ስላልተቻለ ምርመራ ተቋርጦ ተለቀዋል፡፡ በአቶ በቀለ ባልቻ ላይም ክስ መመሥረት ስላላስፈለገ ምርመራው ተቋርጦ ተለቀዋል፤›› አለ፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ከላይ የገለጸው ተገቢ ያልሆነና ሥነ ሥርዓቱን ያልጠበቀ ነው ብሏል፡፡ ለብይን የተቀጠረ መዝገብ ማቋረጥ እንደማይቻልም አስረድቷል፡፡ ‹‹የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝና የሕግ የበላይነት ሊከበር ይገባል፡፡ ይህ ድብብቆሽ ጨዋታ አይደለም፤›› ብሏል፡፡

ዓቃቤ ሕጉ ቀጥለው እንዳስረዱት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ክስን የማቋረጥ ሥልጣን ስላላቸው የተጀመረው ምርመራ እንዲቋረጥ አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የተጀመረ ምርመራና ክስ የማቋረጥ ሥልጣን እንዳላቸው ፍርድ ቤቱ አረጋግጦ፣ ያ መሆን ያለበት ግን ለብይን በተቀጠረ መዝገብ ላይ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ የተጠርጣሪዎቹ የምርመራ ሒደት የተቋረጠውና ከእስር የተፈቱት መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በዕለተ ሰንበት (እሑድ መሆኑን የሚያሳየውን ደብዳቤ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ) ‹‹እሑድ ትሠራላችሁ እንዴ?›› በማለት ዓቃቤ ሕጉን ጠይቋል፡፡ ‹‹አዎ እንሠራለን፤›› ሲሉ ዓቃቤ ሕጉ መልሰዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ሳያሳውቅ ለብይን የተቀጠሩትን ተጠርጣሪዎች ከእስር መፍታቱን በመግለጽ፣ የተዘጋጀው ብይን ሳይነገር መቅረቱን ለችሎቱ ታዳሚዎች አስታውቋል፡፡

ከእነ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ጋር ለብይን ተቀጥረው የነበሩበት የኢትኮን ድርጅት አማካሪ መሆናቸውን የተናገሩትን አቶ የኔነህ አሰፋንና የሀዚአይአይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ባለቤት አቶ ዛኪር አህመድ ላይ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብት ፈቅዷል፡፡ አቶ የኔነህ የተጠረጠሩት በእነ አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የምርመራ መዝገብ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ተፈጽሟል ከተባለው የሙስና ወንጀል ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ በሌሎቹ ላይ ክስ ሲመሠርት በእሳቸው ላይ ሳይመሠርት ቀርቷል፡፡ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ማፍራታቸውን ተከትሎ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚፈልግ የገለጸ ቢሆንም፣ በዋስ ቢወጡ ተቃውሞ እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ በመግለጹ የ50,000 ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸዋል፡፡

የሀዚአይአይ ሥራ ተቋራጭ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዛኪር አህመድ በሌላ የክስ መዝገብ ከእነ አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው የዋስትና መብት ተነፍጓቸው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ አቶ ዛኪር አህመድ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ጋር በተያያዘ የፈጸሙት የሙስና ወንጀል እንዳለ በመግለጽ፣ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር፡፡ አቶ ዛኪር በበኩላቸው፣ ‹‹እኔ ምንም የምጠረጠርበት ምክንያት የለም፡፡ እንዲያውም እኔ መክሰስ ሲገባኝ የተገላቢጦሽ እኔን ተጠያቂ ማድረግ ሆን ተብሎ በእስር ለማቆየት የተደረገ በመሆኑ ያሳዝናል፤›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግረው ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ በሰጠው ብይን አቶ ዛኪር የ150,000 ብር ዋስ ጠርተው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ግን ዋስትናውን በመቃወም ይግባኝ እንደሚጠይቅ ለፍርድ ቤቱ በማመልከቱ፣ ዋስትናው ከመስከረም 22 እስከ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ እንደታገደ ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ መርማሪ ቡድኑ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚያቀርበው ይግባኝ ተቀባይነት ካጣ ዋስትናው እንደሚፀና አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ለአቶ የኔነህ የዋስትና መብት የፈቀደው፣ ዓቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 መሠረት የተፈቀደለትን ክስ የመመሥረቻ ጊዜ ቢያጠናቅቅም፣ ሕጉ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ እንደማይቻል ወይም እንደሚቻል የሚለው እንደሌለና ለትርጉም ክፍት መሆኑን በመግለጽ የጠየቀውን ተጨማሪ ሰባት ቀናት የምርመራ ጊዜ ውድቅ በማድረግ ነው፡፡

ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው አንቀጽ 109 የትርጉም ክፍተት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውን ጭብጥ ይዞ ሲመረምር፣ አንቀጽ 109 ክስ የመመሥረቻ ጊዜን የሚፈቅድ እንጂ ወደኋላ ተመልሶ የምርመራ ጊዜን የሚፈቀድ ሆኖ እንዳላገኘው አስረድቷል፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጥያቄ እንዳልተቀበለው ገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...