Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፖሊስ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኔትወርክና በዝምድና የተሳሰረ ነው አለ

ፖሊስ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኔትወርክና በዝምድና የተሳሰረ ነው አለ

ቀን:

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በኔትወርክና በዝምድና የተሳሰረ በመሆኑ በሙስና ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙትን የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች የምርመራ ጊዜ ለማጠናቀቅ፣ ተጨማሪ የ14 ቀናት ጊዜ እንደሚያስፈልገው ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቀረበ፡፡

መርመሪ ቡድኑ ለሦስተኛ ጊዜ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተቃወሙት ተጠርጣሪዎቹ፣ በተቋሙ ውስጥና በሌሎች ተቋማት የሚገኙ ሰነዶችን ለመሰብሰብ በየቀጠሮው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየተባለ መጠየቁ አግባብነት የሌለውና ሆን ተብሎ ለማጓተት የሚቀርብ ጥያቄ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ የምርመራ ሥራውን 24 ሰዓታት በትጋት እየሠራ ነው፡፡ ድርጅቱ በኔትወርክ የተያያዘና ሠራተኞቹም በዝምድና የተቀጠሩ በመሆናቸው የማስረጃ ሰነዶችን በቀላሉ ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል፡፡ ኃላፊዎቹ ከተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ጋር የሚገናኙ የማስረጃ ሰነዶችን ሲበረብር፣ አንዳንድ ሠራተኞች በዝምድና የተቀጠሩበትን ሰነድ ማግኘቱን መርማሪው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ድርጅቱ ‹‹በኔትወርክና በዘመድ የተሳሰረ ነው›› ያለውን ፍሬ ነገር አዲስ አለመሆኑን፣ በማንኛውም ተቋም በተለይ የሙስና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ የሚያጋጥምና ለምርመራው አዲስ ካልሆነ በስተቀር የተለመደ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የ22 የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ 215 የጭነት ተሽከርካሪዎች ከግዥ ስምምነት ውጪ መገዛታቸውን፣ በርካታ አስመጪዎች ኪራይ አለመክፈላቸውን የሚያስረዱ ሰነዶችን መሰብሰቡንና የመተንተን ሥራ ማከናወኑን መርማሪ ቡድኑ ገልጿል፡፡ ከሚያጣራቸው 29 ክሶች 21ን መለየቱንና የመርማሪ ቡድን በማዋቀር በርካታ የምርመራ ሥራዎችን መሥራቱን መርማሪ ቡድኑ አክሏል፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተገኙ ንብረቶችን በመለየት የማሳገድ ሥራም እንደሚያከናውን አስታውቋል፡፡

ቀሪ የ25 ሰዎች ምስክርነት ቃል መቀበል፣ ለኦዲት የሰጠውን ሪፖርት መቀበልና የባለሙያ አስተያየት መቀበል፣ ቀሪ በርካታ ሰነዶችን ከአዲስ አበባና ከውጭ አገር ጭምር ማሰባሰብ፣ ማስረጃዎቹን መሠረት አድርጎ ከተጠርጣሪዎቹ ተጨማሪ ቃል መቀበል፣ ማስተንተንና በፎረንሲክ በማስመርመር ውጤቱን መቀበል ስለሚቀረው ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ተመሳሳይ ተቃውሞና የመብት ጥያቄ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በየጊዜው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ እንደሌለበትና ተገቢም እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ የምርመራ ሒደቱ እየተጓተተ መሆኑን የገለጹት ተጠርጣሪዎቹ፣ መርማሪ ቡድኑ ቀሩኝ የሚላቸው ሥራዎች በማን ላይ ምን እንደሆነ እንዳልገለጸም ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ምርመራ ማድረግ የነበረበት እነሱን አስሮ ሳይሆን ቀደም ብሎ መሆን እንደነበረበት ተናግረዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ምርመራ የሕግ መሠረት የሌለውና አግባብነት የጎደለው መሆኑንም ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ ተሳትፎ በመለየት በማን ላይ ምን እንደሠራና ምን እንደቀረው መግለጽ ሲገባው፣ በጥቅሉ መናገሩም ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ሰው አስሮ ኦዲት ማስደረግ፣ በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ሰነዶችን መሰብሰብና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቅ ተገቢ እንዳልሆነና ሆን ተብሎ ጊዜ ማራዘሚያ ምክንያት መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ አስረድተዋል፡፡ ንብረት ለማሳገድ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቅ እንደማያስፈልግ ጠቁመው፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ከሆነ ለመሬት ልማት አስተዳደር፣ ገንዘብ ከሆነ ለባንክ፣ ተንቀሳቃሽ ንብረት ከሆነ ደግሞ ለትራንስፖርት መሥሪያ ቤት ደብዳቤ ጽፎ ማሳገድ ስለሚቻል ሰው ማሰር ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁሉም ተጠርጣሪዎች በግላቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት የመርማሪ ቡድኑን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመቃወም የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ጠበቃ እንደተናገሩት፣ ደንበኛቸው ከፍተኛ የሆነ የኩላሊት ሕመምተኛ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን በመግለጽ በቂ ዋስ ጠርተውና ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ ተጥሎባቸው በዋስ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡

የሞጆ ደረቅ ወደብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዬ ጫላ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ ‹‹እኔ ምንም የሚመለከተኝ ነገር የለም፡፡ ለምን እንደታሰርኩም አልገባኝም፡፡ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤቱ ባመለክትም መፍትሔ አላገኘሁም፡፡ መርማሪ ቡድኑንም ለምን እንደታሰርኩ ብጠይቅ ምንም የተነገረኝ ነገር የለም፤›› በማለት ያለምንም ምክንያት መታሰራቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ባነሱት የተቃውሞ ሐሳብና የዋስትና ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጠው መርማሪ ቡድኑ፣ ዋስትናን እንደሚቃወም ገልጿል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ማሰር ያስፈለገበት ምክንያት፣ ከሚሠሩበት ተቋም ማስረጃ ስለሚሰበስብ እንዳያጠፉበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጠርጣሪ በምን እንደተጠረጠረ መናገሩንም አክሏል፡፡ አቶ ታዬ ጫላም መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. በምን ወንጀል እንደተጠረጠሩ እንደ ነገራቸው መርማሪ ቡድኑ አስታውቋል፡፡ በሞጆ ደረቅ ወደብ እያሉ ከፎርክሊፍትና ከኮንቴይነር ኪራይ ጋር በተገናኘ በፈጸሙት ድርጊት መሆኑን እንደ ነገራቸው ጠቁሟል፡፡ የተቋሙን ኮንቴይነር በመተው የግለሰቦችን ኮንቴይነር በማስቀደም አንድ አንድ ሺሕ ብር ጉቦ ይቀበሉ እንደነበር እንደነገራቸው መርማሪ ቡድኑ ተናግሯል፡፡ ለምን እንደተያዙና ወዲያው የተጠረጠሩበት ጉዳይ እንዳልተነገራቸው ፍርድ ቤቱ ጠይቆት፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ የዘገየው መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ የእያንዳንዱን ተጠርጣሪ ድርጊት ሲለይ ቆይቶ ዘግይቶ ስለደረሳቸው መሆኑንም አስረድቷል፡፡ ሕክምናን በሚመለከትም ተቋማቸው 24 ሰዓት የሚሠራ ክሊኒክና ሪፈራል ሆስፒታል እንዳለው በማስረዳት፣ ከዚያም ባለፈ ተጠርጣሪው በፈለጉበት ቦታ ማሳከም እንደሚቻልም ገልጿል፡፡ በመሆኑም የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የተጠርጠሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ አሥር ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ፣ ለመስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተጠርጠሪዎቹ አቶ ደሳለኝ ገብረ ሕይወት፣ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ፣ አቶ ሲራጅ አብዱላሂ፣ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ፣ አቶ ሳሙኤል መላኩ፣ አቶ እውነቱ ታዬ፣ አቶ ታዬ ጫላና አቶ መስፍን ተፈራ ሲሆኑ፣ ማን ምን ኃላፊነት እንዳለው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...