Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሙስና የተከሰሱ አራት ደረጃ አንድ ተቋራጮችና መርማሪ ፖሊስ በንብረትና ገንዘብ አያያዝ ላይ...

በሙስና የተከሰሱ አራት ደረጃ አንድ ተቋራጮችና መርማሪ ፖሊስ በንብረትና ገንዘብ አያያዝ ላይ ክርክር አደረጉ

ቀን:

  • ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ፖሊስ ገልጿል

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደ ገብርኤል የክስ መዝገብ የተካተቱት ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ የክስ መዝገብ የተካተቱት አሰር ኮንስትራክሽን፣ የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭና ኢሊሌ ዓለም አቀፍ ሆቴል በተጣለባቸው የንብረትና የገንዘብ ዕግድ ላይ፣ ከፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ጋር መስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ክርክር አደረጉ፡፡

የድርጅቶቹ ባለቤቶችና ባለድርሻዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉና ከአገር ከወጡ በኋላ ድርጅት ያቋቋሙት በሕገወጥ መንገድ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ያካበቱትን ሀብት ሽፋን ለማድረግ በማሰብ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብና ቋሚ ንብረታቸው እንዲታገድና ለድርጅቶቹ አስተዳዳሪ እንዲቀጠር የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፍርድ ቤት ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት ዕግድ ተጥሎባቸው ይገኛል፡፡

በተለይ ተንቀሳቀሽ ገንዘብ በመታገዱ ድርጅቶቹ የሠራተኛ ደመወዝ መክፈል አለመቻላቸውን፣ ድርጅቶቹ ከተለያዩ ዕቃ አቅራቢዎች ለወሰዷቸው ዕቃዎች ክፍያ መፈጸም አለመቻላቸውን፣ ከውጭ ተገዝተው ወደብ ላይ የደረሱ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች በየቀኑ የዲመሬጅ ክፍያዎች እየጨመረ መምጣቱንና ሌሎች እየደረሱባቸው ያሉ ኪሳራዎችን በመጥቀስ ዕግዱ እንዲነሳላቸውና ሥራቸውን እየሠሩ የተጀመረውን የሕግ ክርክር እንዲያደርጉ፣ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ተረኛ ችሎቱን ለሚያስችለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም የድርጅቶቹ ባለቤቶችና ተወካዮች ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን በማመን፣ ‹‹በደርጅቶቹ ላይ የተጣለው ዕግድ ሊነሳ ይገባል ወይስ አይገባም?  ድርጅቶቹን ለመምራት አስተዳዳሪ ሊሾም ይገባል ወይስ አይገባም? በተለይ የሠራተኞች ደመወዝና ቀጣይ የሥራ ዋስትና ምን ሊሆን ይገባል?›› የሚሉ ጭብጦችን በማውጣት፣ ግራ ቀኙ መከራከሪያ ሐሳብ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አድርጓል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ያቀረቡትን ሐሳብና አስተያየት ከተመለከተ በኋላ፣ ክርክር መደረግ እንዳለበት መረዳቱን ገልጾ፣ ግራ ቀኙን መስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም. አከራክሯል፡፡

የመጀመሪያ ክርክር የተደረገው በመርማሪ ቡድኑና በገምሹ በየነ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ለምን ዕግድ መነሳት እንደሌለበትና አስተዳዳሪ መሾም እንዳለበት  ሲከራከር አቶ ገምሹ በየነ በአውራ ጎዳና መሥሪያ ቤት በ50 ብር ደመወዝ ተቀጥረው ሲሠሩ የነበሩና መሥሪያ ቤቱን ሲለቁ 450 ብር ደመወዝተኛ  እንደነበሩ አስረድቷል፡፡ በአጭር ጊዜ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ማቋቋማቸውንና በሕገወጥ መንገድ ያፈሩትን ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ሕጋዊ ለማስመሰል፣ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴልን መገንባታቸውን መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር 900 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መንገዶችን ያለጨረታ በመውሰድ፣ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥትና ሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን አክሏል፡፡ አቶ ገምሹ በሕገወጥ መንገድ ያገኙትን ሀብት ሕጋዊ ለማስመሰል ለኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴልና ለገምሹ በየነ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ማውጣታቸውን አክሏል፡፡ በመሆኑም አቶ ገምሹ በተመሠረተባቸው የሙስና ክስ ጥፋተኛ ቢሆኑ፣ ለደረሰው ጉዳት ማካካሻ ስለሚሆን ንብረታቸውና ተንቀሳቃሽ ሒሳባቸው ታግዶ መቆየት እንዳለበት መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡ ተከሳሹ በመንግሥትና በሕዝብ ሀብት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና ክሱም እንደተመሠረተባቸው የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ የጥቅም ግጭት በማያስከትል ሁኔታ ንብረት አስተዳዳሪ ሊሾም እንደሚገባ አስረድቷል፡፡ ለሆቴሉ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው ባህልና ቱሪዝም ተቋም፣ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ድርጅቱን የኢትዮጵያ መንገዶች ሥራ ኮርፖሬሽን በአስተዳዳሪነት እንዲሾሙ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የአቶ ገምሹ ጠበቆች የመርማሪ ቡድኑ ሐሳብን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ አቶ ገምሹ አገር ዘርፈው አልበለፀጉም፡፡ በ1990 ዓ.ም. አውራ ጎዳናን ሲለቁ፣ አንድ አሮጌ ኤንትሬ ተሽከርካሪ በመግዛት የትራንስፖርት ሥራ መጀመራቸውን፣ በመቀጠልም ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን በመግዛትና በማከራየት፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን በማከራየት ቢዝነሳቸውን እያሳደጉ የመጡ ታታሪ ነጋዴ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአሥር ዓመታት የተጠቀሱትን ሥራዎች ከሠሩ በኋላ በ2000 ዓ.ም. ገምሹ በየነ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ማቋቋማቸውንና ሌሎች በርካታ ሥራዎች በመሥራት የተመሰከረላቸው ነጋዴ መሆናቸውን ጠበቆቻቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሁለት አሥርት ዓመታትን የፈጀ ሀብት እንጂ በአንድ ሌሊት የተገኘ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

መርማሪ በቡድኑ ዕግድ እንዲጣል ያደረገው ከማይፀብሪ እስከ ዲማ ያለውን መንገድ ኮንትራት ሲፈራረሙ ብዙ ገንዘብ እንደወሰዱና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ እንደተሰማሩ በመግለጽ መሆኑን ያስታወሱት ጠበቆቹ፣ አቶ ገምሹ ግን ከ1990 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው እንደነበር፣ በወቅቱ የገንዘብ ዝውውሩን አድርገዋል ቢባል እንኳን እሱን የሚከለክለው አዋጅ የወጣው በ1997 ዓ.ም. ከመሆኑ አንፃር ጥፋት እንዳልነበረ አስረድተዋል፡፡

አዋጅ 882/2007 ዕግድ ይሰጣል የሚለው በንብረት ላይ እንጂ በንግድ ሥራ ላይ አለመሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ በገንዘብ ላይ ማስከበር እንጂ ማገድ እንደማይቻል ተከራክረዋል፡፡ ለንግድ ሥራ የሚውል ገንዘብም ላይም ዕግድ እንደማይጣል ሕጉን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን የንግድ ገንዘብ በመታገዱ ድርጅቶቹ እንዳይሠሩና 4,000 የሚጠጉ ሠራተኞች የሥራ ዋስትና እንዳይረጋገጥ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ደንበኛቸው ሕገ መንግሥታዊ ንፁህ ሆነው የመገመት መብታቸው መታለፉንና በአንቀጽ 40 እና 41 መሠረት በፈለጉት የሥራ መስክ የመሰማራትና ሀብት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያሳጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልል የወሰዷቸው አምስት ፕሮጀክቶች ከሥራ ውጪ መሆናቸውን፣ ከተለያዩ ኩባንያዎች ለወሰዷቸው ዕቃዎች ክፍያ ባለመፈጸማቸው ተጨማሪ ዕቃ ማግኘት አለመቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ ከማይፀብሪ እስከ ዲማ በወሰዱት የመንገድ ሥራም 36 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንደደረሰ ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተ ቢሆንም፣ እንዲታገድ የተደረገው ገንዘብ ከጉዳዩ ጋር እንደማይገናኝ አስረድተዋል፡፡ ቋሚ ንብረቶች ታግደው በገንዘቡ  ላይ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳላቸው አመልክተዋል፡፡

የንብረት ጠባቂ ሹመትን በሚመለከት፣ ሕጉ የሠራተኛ መሪ ፍርድ ቤት ይሾማል እንደማይል በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2204 ላይ መደንገጉን አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑም ንብረት እንደሚባክን ከመግለጽ ባለፈ ምክንያቱን በግልጽ ባልተናገረበት ሁኔታ፣ በደፈናው ጉዳት ይደርሳል ብሎ ስላመለከተ ብቻ ሊሾም እንደማይገባና የሕግ ድጋፍም እንደሌለው ጠበቆቹ ተከራክረዋል፡፡ ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽን 455 ሚሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል ያለውና ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ አንድም ጊዜ ከስሮ የማያውቅና ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ያተረፈ ድርጅት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴልም ባለአምስት ኮከብና ዓለም አቀፍ መስተንግዶ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮንስትራክሽን ድርጅቱ ምን ያህል ለሥራው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በክርክሩ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ያመለከተው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንም ምስክር መሆኑን ጠቁሞ፣ ድርጅቶቹ በሚመሯቸው ፕሮፌሽናል አመራሮች መመራት ስለሚችሉ አስተዳዳሪ ሊሾም እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡ የሆቴሉና የኮንስትራክሽን ድርጅቱ ኃላፊዎች በችሎት ተገኝተው ድርጅቶቹ አሁን ስለሚገኙበት ሁኔታ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ድርጅቶቹ ለመዘጋት ጫፍ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው፣ ኃላፊነት ወስደው ለመምራት የሚችሉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አረጋግጠዋል፡፡

የማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክቶች ያላግባብ ክፍያዎችን በመውሰድ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን በመግለጽ፣ ዕግዱ ተጠብቆ እንዲቆይና የንብረት አስተዳዳሪ እንዲሾም ጠይቋል፡፡ የሠራተኛ ደመወዝን በሚመለከት አስተዳዳሪ ሊሾም እንደሚገባም አክሏል፡፡

የየማነ ጠቅላላ ተቋራጭ ጠበቆች፣ ‹‹መርማሪ ቡድኑ የሚያነሳቸው ሐሳቦች የሕግ መሠረት የላቸውም፤›› በማለት ምላሽ መስጠት ጀመሩ፡፡ የድርጅቱ ባለቤት  በቀረበባቸው ክስ ላይ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን የታገደውን ያህል እንዳልሆነ በመጠቆም፣ የተሻሻለው የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ አዋጅ ቁጥር 434 አንቀጽ 17 (1)ም የሚለው፣ ፍርድ ቤቱ የሚመች መስሎ ሲታየውና ሲገምት ሊሾም ይችላል ይላል እንጂ፣ ንብረት ጠባቂ መሾም ግዴታ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ አንድ ነጋዴ በሙስና ሲጠረጠር፣ ሊታገድ የሚገባው ንብረትና ገንዘብ በሙስና የተገኘው ተለይቶ መሆኑን አዋጅ ቁጥር 434 አንቀጽ (9) ላይ መደንገጉን አስታውሰው፣ አቶ የማነ በ2008 ዓ.ም. በውጭ ኦዲተር የተረጋገጠ 580 ሚሊዮን ብር ሀብታቸው ላይ ዕግድ እንደተጣለባቸው አስረድተዋል፡፡ ገንዘብ ወይም ንብረት ሲታገድ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ማካካሻ ቢሆንም፣ አቶ የማነ ያደረሱት የጉዳት መጠን ግን አለመገለጹን ተናግረዋል፡፡ ስለሚባክን ንብረትም የተባለ ነገር እንደሌለ አክለዋል፡፡ የማነ  ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ የተረከባቸው ስምንት ፕሮጀክቶች ሥራ ማቆማቸውን፣ የሠራተኞች ደመወዝ መክፈል  አለመቻሉን፣ በየጊዜው መከፈል የነበረበት የባንክ ዕዳም መቆሙን በመግለጽ ቋሚ ንብረቱ ታግዶ ተንቀሳቃሽ ገንዘብ እንዲለቀቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

ከመንግሥት የተረከቧቸው ፕሮጀክቶችን ቀድሞም የሚመሩት በአቶ የማነ ሳይሆን በባለሙያዎች መሆኑን ጠቁመው፣ ንብረት አስተዳዳሪ ቢሾም ሥራ ከማጓተትና ከማዳከም ባለፈ ሌላ የሚፈጥረው ነገር ባለመኖሩ ሊሾም እንደማይገባ ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡ በመሆኑም በሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ኃላፊነት ወስደው ማስተዳደር እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

አሰር ኮንስትራክሽንን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ባለድርሻና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ የማነ አብረሃ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት  ሠራተኛ ነበሩ፡፡ አቶ የማነ በሥራ ላይ በነበሩበትና ከሥራ ከወጡ በኋላ ያለው ንብረታቸው ሲመረመር፣ በለቀቁ በአራት ወራት ውስጥ 11 ሚሊዮን ብር በስማቸው እንደተገኘ አክሏል፡፡ በወንጀል የተገኘን ሀብት ሕጋዊ ለማስመሰል ብዙ ነገር መሥራታቸውን፣ ነገር ግን ምርመራ ሲደረግ ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት ይዘው በመገኘታቸው፣ በተንቀሳቃሽ ሒሳባቸውና ንብረታቸው ላይ የተጣለው ዕግድ እንደተጠበቀ ቆይቶ አስተዳዳሪ ሊሾምለት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የአሰር ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጠበቆች ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ተጠርጣሪው አቶ የማነ አብርሃ ባለድርሻ ናቸው፡፡ በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሚሠሩበት ወቅት፣ ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ ያለጨረታ ሥራ ሰጥተሀል በሚል ተጠርጥረው ምርመራ እንደተደረገባቸው ገልጸዋል፡፡ አሰር ኮንስትራክሽን በአምስት ባለድርሻዎች የተቋቋመው ግን እሳቸው ምርመራ ከተደረገባቸው ከዓመት በኋላ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል፡፡ በድርጅቱ ላይ ዕግድ ይጣል ቢባል እንኳን፣ አቶ የማነና ድርጅቱ ተለይተው በእሳቸው ድርሻ ላይ ብቻ መጣል ሲገባው፣ በሁሉም ባለድርሻዎች ላይ መጣሉ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሌሎቹ መብት ሊከበር ይገባ እንደነበረም አክለዋል፡፡ ዕግዱ ሊነሳ እንደሚገባና አስተዳዳሪም መሾም እንደሌለበት በመከራከር ተቃውመዋል፡፡

ባለድርሻና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ሚኬኤሌ አብርሃ በተንቀሳቃሽ ሒሳብና ንብረት ላይ ዕግድ የተጣለው ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑን አስታውሰው የሠራተኛ ደመወዝ፣ የቢሮ ክፍያ፣ በወደብ የሚገኙ ንብረቶች የዲመሬጅ ክፍያ፣ የተለያዩ ዕቃ አቅራቢዎች ክፍያ፣ በየወሩ የሚከፈል የኮንትራት ማስከበሪያ ክፍያዎች በሁለት ወራት ውስጥ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሳቸውንና ጉዳቱ እየቀጠለ መሆኑን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዕግዱን ቢያነሳላቸው ድርጅቱን የመምራትና የማስተደደር ኃላፊነት እንደሚወስዱም ለፍርድ ቤቱ አስታውቀዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ግን በሰጠው ምላሽ አቶ ሚኬኤሌ ባለድርሻ ሆነው ድርጅቱን የተቀላቀሉት በ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል መሆኑን አስታውቆ፣ በ1996 ዓ.ም. ከመመረቃቸው አንፃር በአጭር ጊዜ ይኼንን ያህል ሀብት ይኖራቸዋል ተብሎ እንደማይገመት አስረድቷል፡፡ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል ከአቶ የማነና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር በተባባሪነት የቀረቡና እንደ ሽፋን የተጠቀሙባቸው መሆኑን አስረድቷል፡፡

ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያን በተመለከተ መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው፣ ድርጀቱ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከወሰዳቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት ማድረሱን አስረድቷል፡፡ በሕገወጥ ያገኘውን ሀብት ሕጋዊ ለማስመሰልም በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ማዋሉንም አክሏል፡፡ በመሆኑም ላደረሰው ጉዳት ማካካሻ ንብረት አስተዳዳሪ እስከሚሾም የተጣለው ዕግድ ተጠብቆ እንዲቆይ ጠይቋል፡፡

ክሱ የሚለው የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት የሚል ቢሆንም፣ የዲኤምሲ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት አቶ ዳንኤል ማሞ ሕንፃና ኢንዱስትሪ እንደታገደባቸው ወክለው የቀረቡ ነገረ ፈጅ አስረድተዋል፡፡ የድርጅት ባለቤት ስለተጠረጠሩ ብቻ የድርጅቶቹ ህልውና አደጋ ውስጥ መውደቅ እንደሌለበትና ሕጋዊ መሠረት እንደሌለውም ነገረ ፈጁ አስረድተዋል፡፡ ዲኤምሲ የገነባቸው ሪል ስቴቶች ተጠናቀው ከአንድ ወር በኋላ ለ42 አባወራዎች የሚተላለፉ ቢሆንም፣ ዕግድ ስለተጣለባቸው ምን ማድረግ እንደሚገባቸው ግራ መጋባታቸውንም ተናግረዋል፡፡

ደመወዛቸውና የባንክ ሒሳባቸው ታግዶባቸው በነበሩት በገንዘብና ኢኮኖሚ  ትብብር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አለማየሁ ጉጆ የክስ መዝገብ የተካተቱት ወ/ሮ ስህን ጎበናን በሚመለከት፣ መርማሪ ቡድኑ ፍርድ ቤቱ የመሰለውን ቢወስን ተቃውሞ እንደሌለው በመግለጹ ክርክር አልተደረገም፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ የታገዱ ንብረቶችና ተንቀሳቃሽ ሒሳቦች ስንት እንደሆኑ፣ የግለሰቦችና የድርጅቶች የሀብት ክፍፍል ስንት እንደሆነ እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የመርማሪ ቡድኑን ሪፖርት ለመጠባበቅ ለመስከረም 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...