Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሬስ ኢንጂነሪንግ ምርት ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው ፕሮግራም ሠራተኞች የመብት ጥያቄ በማንሳት ተቃውሞ አሰሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሼክ መሐመድ አል አሙዲ ከተሸጠ ዓመታትን ያስቆጠረው የሬስ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ሠራተኞች፣ ምርት ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ የኩባንያው ፕሮግራም ወቅት ድንገት በመውጣት የመብት ጥያቄዎችን የሚያስተጋቡና የኩባንያውን አሠራር የሚኮንኑ መፈክሮችን በማሰማት ተቃውሞ አቀረቡ፡፡

ከመስከረም 23 እስከ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የሚቆየው የምርት ማስተዋወቂያ ፕሮግራም፣ ማክሰኞ ጠዋት ሳሪስ አቦ አካባቢ በሚገኘው የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊጀመር ዝግጅት ሲደረግ በነበረት ወቅት ድንገት ብቅ ያሉት ሠራተኞች፣ ኩባንያው እየተጓዘበት የሚገኘውን መንገድ በመተቸት ጭምር ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ ዘጠኝ ነጥቦችን ያካተተ ጥያቄም በደብዳቤ ለኩባንያው ኃላፊዎች ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሬስ ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማኅበር ሠራተኞች፣ የኩባንያው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሥጋት ላይ እንደጣላቸው ገልጸዋል፡፡ ኩባንያው የታዋቂዎቹ የካተርፒላርና የሜሲ ፈርጉሰን ኩባንያዎችን ምርቶች በወኪልነት በማከፋፈል ላለፉት 50 ዓመታት ያህል ሲሠራ የቆየ ነው፡፡ ባልተጠበቀ መንገድ የተሰማው የሠራተኞች ተቃውሞ ካካተታቸው መፈክሮች መካከል ‹‹ወኪል ኩባንያውን ታደጉት››፣ ‹‹ሬስ ኢንጂነሪንግን ታደጉት››፣ ‹‹ደንበኞች እያማረሩ ነው››፣ ወዘተ. የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የጽሑፍ መፈክሮችን በማሳየትም ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ለጥቂት ሰዓታት በዚህ ሁኔታ የዘለቀው የሠራተኞቹ ተቃውሞ ሰላማዊ ከመሆኑም በላይ፣ ጥያቄያቸውም በአብዛኛው በኩባንያው ህልውና ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ ይሁንና ድርጅቱ በሚከተለው የሠራተኞች ቅጥር ሁኔታ፣ በቦነስና በደመወዝ ጭማሪ አሠራሮች ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ምንም እንኳ ኩባንያው ዘግይቶም ቢሆን ለሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝ በቦነስ መልክ ቢከፍልም፣ ሠራተኞቹ ግን ደስተኞች አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሬስ ኢንጂነሪንግ የቀድሞ ማኔጅመንት አባላት በአብዛኛው መባረራቸውም በሠራተኛውና በኩባንያው ባለቤቶች መካከል ክፍተት እንደፈጠረ ተገልጿል፡፡

በሠራተኛ ቅጥር ወቅት በተለይ ለጥበቃ፣ ለፅዳት፣ ለሜካኒክና ለመሳሰሉት የሙያ ዘርፎች ኩባንያው የቅጥር ሥራ በሚያከናውኑ ድርጅቶች አማካይነት ሠራተኞችን ማምጣቱ፣ በሠራተኞቹ ከሚነሳው ቅሬታ መካከል ይጠቀሳል፡፡ አብዛኞቹ በዚህ አኳኋን የተቀጠሩ ሠራተኞች ለቅጥር ድርጀቱ ከደመወዛቸው እየተቆረጠ በሚከፈለው ከፍተኛ ኮሚሽን ቅሬታ አድሮባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በኮንትራት የተቀጠሩ ሆኖም ረዘም ላሉ ዓመታት በቋሚ ሥራ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችም፣ ችግራቸውን የሚያዳምጣቸው የኩባንያው ማኔጅመንት አካል እንዳላገኙ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያውያን ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎችን የውጭ ዜጎች በድርጅቱ ውስጥ ሲሠሩ መታየታቸውም ጥያቄ ከቀረበባቸው ቅሬታዎች መካከል ይመደባል፡፡ በደብዳቤ አቤቱታቸውን ለማሰማት ያደረጉት ሙከራም ሰሚ በማጣቱ፣ ዕለቱ ተቃውሟቸውን ለማሰማት እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የኩንባያው ማኔጅመንትና የሠራተኛ ማኅበሩ የኅብረት ስምምነት እንዳላቸው ከኩንባያው አስተዳደር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሬስ ኢንጂነርንግ ቅጥር ግቢም የሠራተኛ ማኅበር ጽሕፈት ቤት እንዳለ ሪፖርተር አረጋግጧል፡፡

የሬስ ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንሱር አላሚን ስለሁኔታው በጋዜጠኞች ተጠይቀው፣ ሠራተኞቹ ከእሳቸው ይልቅ ለኩባንያው የቦርድ አስተዳደር ጥያቄያቸውን እንዳቀረቡ፣ በደብዳቤ የቀረበው ጥያቄም ታይቶ ምላሽ እንደሚሰጥበት አስታውቀው፣ ከዚህ በላይ ምላሽ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ሠራተኞቹ የኩባንያው ባለቤቶች ጥያቄያቸውን ካልተቀበሉ በቀር አንሠራም በማለታቸው፣ ነዋሪነታቸው በዱባይ እንደሆነ የተገለጸውና አቶ ሑሴን አሊ የተባሉ የኩባንያው የበላይ ኃላፊ በሠራተኞቹ አመራሮች የቀረበውን ጥያቄ፣ ከሠራተኛ ማኅበሩ ምክትል ኃላፊ አቶ ሥዩም ወርቅነህ እጅ በመቀበል የተስተጓጎለው ፕሮግራም ሊካሄድ ችሏል፡፡ ይሁንና አቶ ሥዩምም ሆኑ የሠራተኛ ማኅበሩ ሌሎች ኃላፊዎች ጉዳዩ ከማኔጅመንቱ ጋር በውስጥ ድርድርና ውይይት እንዲፈታ ማድረጉን ስለሚመርጡ፣ ለመገናኛ ብዙኃን ምንም ዓይነት መግለጫ ከመስጠት እንደሚታቀቡ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካው ኩባንያ ካተርፒላር እ.ኤ.አ. በ2008 በገዛው የቻይናው ኤስኢኤም ኩባንያ አማካነት የሚመረቱ፣ ሙሉ የብራንድ ባለቤትነታቸው በካተርፒላር ሥር የሆኑ ልዩ ልዩ ባለጎማ ሎደሮች፣ ሞተር ግሬደሮች፣ መሬት መጠቅጠቂያ ማሽነሪዎችና ሌሎችም ምርቶችን ለማስተዋወቅ በሬስ ኢንጂነሪንግ የተሰናዳ ፕሮግራም ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኩባንያው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችና የተሟላ የመለዋወጫ አቅርቦት እንዳለው ለማሳየት የተዘጋጀ ፕሮግራም ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች