Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ ተወያየ

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ ተወያየ

ቀን:

  • ያልተማከለ አስተዳደር እንዲዘረጋ ሐሳብ ቀርቧል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቲክሱ እስካሁን የሄደበት መንገድና ቀጣይ መደረግ በሚገባው ጉዳይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መከረ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማክሰኞ መስከረም 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፣ ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ክለቦችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተካፋይ ነበሩ፡፡

ሙሉ ቀን በፈጀ የውይይት መድረክ በፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በቀረበው መነሻ ጽሑፍ፣ አትሌቲክሱ እስካሁን ሲሄድበት የቆየው አሠራርና የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ወዳልተማከለ አሠራር መቀየር እንዳለበት፣ ክልሎችም ሆኑ በሥራቸው የሚተዳደሩ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ትክክለኛ ስፖርታዊ አደረጃጀትና አሠራሮችን እንዲከተሉ ጠይቋል፡፡

አሐዳዊ ሲባልም ከማዕከል በሚደረግ እንቅስቃሴ ለአትሌቶች ምርጫና ዝግጅት፣ ለብሔራዊ ቡድን አወቃቀር ያስፈልግ የነበረው የዓመታትና ወራት ዝግጅት ከአሁን በኋላ ቀርቶ በምትኩ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች እንዲሁም ሌሎችም እንደ አትሌት ማናጀርና የማናጀር ተወካዮች በተገቢው መሥፈርትና የብቃት ደረጃውን የሚያሟሉ ትክክለኛ አትሌቶች በመመልመል በየክለቦቻቸው የታቀፉትንም በተገቢው መንገድ በመምረጥ ለብሔራዊ ቡድን እንዲያዘጋጁ ተጠይቋል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽን ይህን መነሻ ጽሑፍ ከማዘጋጀቱ በፊት ከ70 በላይ  ባለሙያዎችን በአገሪቱ አሰማርቶ ጥናት ማድረጉንም አቅራቢው አቶ ዱቤ ተናግረዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ፌዴሬሽኑ አትሌቲክሱን በአገር አቀፍ ደረጃ መምራት ከጀመረበት ጀምሮ በርካታ ሁለንናዊ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ እንደ መነሻ ጽሑፍ አቅራቢው፣ በዚያው ልክ በዕቅድ ላይ ያልተመሠረቱ መርሐ ግብሮች ፌዴሬሽኑን አስቸጋሪ ሆነውበት ቆይቷል፡፡

ከተግዳሮቶቹ መካከልም ፌዴሬሽኑ በውድድሮች ላይ በመሳተፍና ያሉትን ተሳትፎዎች ለማጠናከር ከ1979 ዓ.ም. ጀምሮ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር የፕሮጀክት ሙከራ በግማሽና ሙሉ ማራቶን አትሌቶችን በማቀፍ በአራት የክልል ከተሞች ሥልጠናዎችን መስጠት ጀምሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይም በ1993 ዓ.ም. ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እንዲቻል በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይና በደቡብ ክልሎች የሥልጠና ጣቢያዎችን በመክፈት እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የሥልጠና ጣቢያዎቹ የታቀደላቸውን ያህል ውጤታማ ባይሆኑም፣ እስካሁን እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ አትሌቲክሱን በታቀደለትና በታለመለት ልክ ለማሳደግና ለማስፋት ብሎም አገሪቱን ወክለው ለተለያዩ አህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች ማብቃት አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ መድረኮች የሚወዳደሩ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከወረዳና ቀበሌ ጀምሮ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም ትኩረት ተሰጥቶ ስፖርቱን ማስፋፋት የሚያስችል አደረጃጀት አልተዋቀረም፡፡ አሁንም ድረስ ይህ ግድ የሚባል መዋቅር እንደሌለ ጭምር ጥናቱ አረጋግጧል፡፡

ይህንኑ በምልከታ ወቅት በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በአካል በመገኘት ውጤቱን ለመመልከት እንደተሞከረው ያተተው ጥናቱ፣ በዋናነት በስፖርቱ ዙሪያ ኃላፊነት ያለባቸው በየደረጃው የተቀመጡ አካላት ወቅታዊም ሆነ ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥና የመስጠት ከፍተኛ ድክመት ታይቶባቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአፈጻጸም ሪፖርቶች በአብዛኛው መሬት ካለው ጋር የሚጣጣም አለመሆኑ ጭምር በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

እንደ ጥናቱ አገላለጽ፣ በታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች፣ ሥልጠናና ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ ባለድርሻ አካላት አደረጃጀት ተግባርና ኃላፊነት በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ስፖርቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ እንዲዘወተርና እንዲስፋፋ የተቀናጀ ወጥ የሆነ አሠራርም እንደሌለም ተመልክቷል፡፡

ሌላው በዕድሜና በፆታ የተከፋፈለ አሠራር አለመኖር፣ ምልመላዎች ሲካሄዱ ብቃቱና ክህሎቱ ባላቸው ሙያተኞች አለመሆኑ፣ ተሰጥዎንና የተሰጥዎን ቦታ በአግባቡ መለየት አለመቻልና በአጠቃላይ ግምት ላይ የተመሠረተ ስለመሆኑም ጭምር ጥናቱ አንኳር ያላቸው የአትሌቲክሱ ችግሮች ያላቸው ይጠቀሳሉ፡፡ የዕቅድ ዝግጅትም በተመሳሳይ በመስክ ምልከታው ወቅት በትልቁ የታየ ክፍተት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

መነሻ ጽሑፉን ተከትሎ የተለያዩ ቅሬታዎችና አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከተሰጡት አስተያየቶች መካከል ኮማንደር ግርማ ፈዬ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አትሌቲክስ ክለብ ይጠቀሳሉ፡፡ ኮማንደሩ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅትን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ወዳልተማከለ አሠራር መለወጥ እንደሚገባው የቀረበው ሐሳብ አቅም ለሌላቸው ክለቦች አስቸጋሪ እንደሚሆን ሥጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአትሌቲክሱን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ እንደ ሥጋት ያቀረባቸው ሐሳቦች፣ እሳቸውን ጨምሮ የችግሩ አካል እንደመሆናቸው ሁሉ የመፍትሔውም አካል በመሆን የተሻለውን አካሄድ መምረጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡    

የአማራ ክለቦችን በመወከል የተናገሩት ኮማንደር ሰለሞን ታደሰ በበኩላቸው፣ እስካሁን ባለው አካሄድ በማናጀሮችና በክለቦች መካከል ሊኖር ስለሚገባው የአሠራር ቅደም ተከተል የሕግ ማዕቀፍ እንደሌለው፣ ይህንኑ በሚመለከት በማናጀሮችና ክለቦች እንዲሁም አትሌቶችን ሊያግባባ የሚችል በፌዴሬሽኑ ምንም ዓይነት የተቀመጠ ደንብም ሆነ መመርያ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ይኼ ጉዳይ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ አስካልተቀመጠለት ድረስ በጥናቱ የተረጋገጡት ምልከታዎችና ክፍተቶች ላለመቀጠላቸው ምንም ዓይነት ዋስትና እንደሌለም ነው ያስረዱት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪው፣ ‹‹ባለውና በነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ማኔጀር ማለት ለክለቦች ምን ማለት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ክለቦች ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሰው ለዕውቅና የሚያበቋቸው አትሌቶቻቸው ማናጀር ሲያገኙ ክለቡን እስከመኖሩ አያውቁትም፡፡ ማናጀር ተብየውም አትሌቱ የሚያስገኝለት ዶላር ካልሆነ፣ የአትሌቱ መገኛ ስለሆነው ክለብ የሚያስበው አንዳች ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በፌዴሬሽኑ ክለቦችን በሚመለከት ምንም ዓይነት የተቀመጠለት የሕግ ማዕቀፍ ሊፈረድለትም ሊፈርድበትም አይገባም፤›› ብለው በዚህ ረገድ አሁንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለክለቦችም ሆነ ለማናጀሮች እንዲሁም አትሌቶች በሕግ ፊት ሊፀና የሚችል መመርያና ደንብ ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ ፆታዊ ጥቃትንና በስፖርት ስለሚከለከሉ አበረታች ንጥረ ነገሮች የተመለከቱ መነሻ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...