Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልበ291 ከተሞች የታየው የማህተመ ጋንዲ ቴአትር በአዲስ አበባ

በ291 ከተሞች የታየው የማህተመ ጋንዲ ቴአትር በአዲስ አበባ

ቀን:

በህንድ መዲና ኒው ደልሒ የሚከናወኑ ጥበባዊ መርሐ ግብሮች የሚዘገቡበት ኦል ኢቨንስት ኢን ኒው ደልሒ ድረ ገጽ፣ በቅርቡ ያስነበበው ዮግፑሩሽ ማህተመ ከማህተመ ስለተባለ ቴአትር ነበር፡፡ ‹‹ዩግፑሩሽ ልብ የሚነካ ቴአትር ነው፡፡ በሽሪማዲ እና በማህተመ ጋንዲ መካከል ያለውን ጥብቅ ትስስር ያንፀባርቃል፡፡ ከቀላል ጓደኝነት የጀመረው ግንኙነት ሽሪማዲ የጋንዲ መንፈሳዊ መሪ (ስፕሪችዋል ሜንቱር) እስከመሆን ዘልቋል፡፡ በመላው ዓለም የሰላም ልዑክ በመሆን የሚታወቁት ማህተመ ጋንዲ የተቀረጹት በሽሪማዲ አስተምህሮ ነው፡፡ ትስስራቸው በህንድ እንዲሁም በመላው ዓለም ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ መንፈሳዊና ባህላዊ ገጽታ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤›› በማለት ነበር በቴአትሩ የተገለጸው፡፡

ዮግፑሩሽ ማህተመ ከማህተመ (በአጭሩ ዮግፑሩሽ) በኡታም ገዳ ተጽፎ በራጀሽ ጆሲ የተዘጋጀ እውነተኛ ታሪክ የተመረኮዘ የህንድ ቴአትር ነው፡፡ ስለ ማህተመ ጋንዲ በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎች ብዙ ቢባልም በርካቶች የማያውቁት የሕይወታቸው ክፍል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቴአትሩ ህንድን አልፎ በመላው ዓለም የታወቀ ነው፡፡ ቴአትሩ ህንድ ውስጥ ብቻ በ210 ቀናት 250 ጊዜ የታየ ሲሆን፣ በመላው ዓለም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደታደሙትም ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ 936 ጊዜ በ291 ከተሞች የታየ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ 18 ጊዜ ቀርቧል፡፡

ስለ ቴአትሩ የዳሰሳ ዘገባ ያቀረቡ ባለሙያዎች የሚስማሙበት ነገር፣ የቴአትሩ ይዘት ፍቅርን፣ መልካምነትን፣ መቻቻልንና ጥንካሬን የሚሰብክ መሆኑን ነው፡፡ ሰዎች ለበጎ ነገር ሙሉ አቅማቸውን እንዴት ማፍሰስ እንዳለባቸውና በመልካምነታቸው ማኅበረሰቡን እንዴት መጥቀም እንደሚችሉ ያሳያል፡፡ በሽሪማዲ በኋላም በጋንዲ አስተሳሰብ መሠረት ቅድሚያ የሚሰጠው ስለ ራስ ማንነት መገንዘብ ሲሆን፣ ቀጥሎም ባለኝ ዕውቀትና ጉልበት ለአካባቢዬ ምን ማበርከት እችላለሁ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጋንዲና ሽሪማዲ ወዳጅነት ላይ የተመሠረተው ቴአትሩ፣ ሰዎች እውነትን ተመርኩዘው ማንኛውንም መሰናክል እንደሚያልፉ የህንድን ነፃነት መቀዳጀት ማሳያ አድርጎ ያንፀባርቃል፡፡

‹‹የአገራችን ባህል፣ ፍልስፍና፣ መንፈሳዊነት በቴአትሩ ተገልጿል፡፡ ሸሪማዲ እና ጋንዲ ለዓለም ሰላምና ለሰው ልጆች ዕድገት የሚረዱ ሐሳቦቻቸው እነሆ  የሚሉበት ነው፤›› ሲል ኦል ኢቨንትስ ኢን ኒው ደልሒ ቴአትሩን ገልጿል፡፡ የቴአትሩ አዘጋጆች በመላው ዓለም ለማሳየት የሚያደርጉት ጉዞ ባለፈው ሳምንት መዳረሻው ያደረገው ኢትዮጵያ ነበር፡፡ የህንድ ኤምባሲ የአገሪቱን 70ኛ ዓመት የነፃነት በዓል ለማክበር ካዘጋጃቸው አንዱ ቴአትሩ ሲሆን፣ ባለሙያዎቹ ሥራቸውን በጣልያን ባህል ማዕከል አሳይተዋል፡፡

ኑሯቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ህንዳውያን መምህራን፣ የቢዝነስ ሰዎችና ኢትዮጵያውያንም የቴአትሩን መጀመር በጉጉት ይጠባበቁ ነበር፡፡ ቴአትሩ ከአገር አገር ስለሚዘዋወር ለመድረክ የሚጠቀሙባቸው ግብዓቶች በቀላሉ የሚጓጓዙ ናቸው፡፡ ተዋንያኑ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላው ሲሻገሩ መድረክ ላይ ያሉ ቁሳቁሶችን በሌላ ግብዓት የሚተኩ ተባባሪዎች አሉ፡፡ ተዋንያኑ ከመድረክ ሳይወርዱ የታሪኩን ፍሰት ተከትለው ግብዓት ሲለዋውጡ ተመልካችን በሚረብሽ ሁኔታ አይደለም፡፡ እንደየአስፈላጊነቱ መኖሪያ ቤት፣ አዳራሽ፣ መናፈሻ፣ መርከብ፣ የመቃብር ቦታ፣ እሥር ቤትና ሌሎችም የታሪኩን መቼት የተከተሉ ሲነሪዎችን የሚለዋውጡት መጋረጃ ዘግተው ሳይሆን ተዋንያኑ ሥራቸውን ለሕዝብ እያሳዩ ነው፡፡

በ291 ከተሞች የታየው የማህተመ ጋንዲ ቴአትር በአዲስ አበባ

 

ቴአትሩ መነሻ ያደረገው ጋንዲ ከእንግሊዝ የሕግ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ሽሪማዲን እ.ኤ.አ. በ1891 ሲተዋወቁ ነው፡፡ የምዕራባውያኑን ሙሉ ልበስ ለብሰው ወደ አገራቸው የተመለሱት ጋንዲ፣ ወጣቱ ሽሪማዲ ሕይወትን በሚመለከት ሁኔታ ይማረካሉ፡፡ የሰው ልጆች በዚህ ምድር የመኖራቸው ግብ ምንድነው? ከሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ጀምሮ እያንዳንዱን ሁነት የሚገልጽበት ሁኔታ ከሳቸው አረዳድ የተለየ በመሆኑም በአንክሮ ይከታተሉት ጀመረ፡፡

ወደ ሽሪማዲ የሕይወት ፍልስፍና በበለጠ መሳብ የጀመሩት በአንድ ጊዜ አሥርና ከዛም በላይ ሁነቶችን ማከናወን ስለሚቻልበት ጥበብ (ሻታቫዳን) ሽሪማዲ ሲያስረዳቸው ነበር፡፡ ጥበቡን ለሕዝብ ያሳዩበት ወቅትም የቴአትሩ አካል ነው፡፡ በአንድ አዳራሽ ሽሪማዲ የተለያዩ ክንውኖችን በተመሳሳይ ሰዓት እያካሄደ የማስታወስ ችሎታው የሚፈተሽበት ፈተና ነበር፡፡

በክፍሉ ካርታና ዳማ የሚጫወቱ ሁለት ወንዶች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደወል እየደወለች የሒሳብ ስሌት የምትጠይቅ ሴት አለች፡፡ ጋንዲ በተለያዩ ቋንቋዎች ያሉ ቃላትን ሲያነሱ ሌላ ወጣት ሽሪማዲ ላይ ፍሬ ይወረውራል፡፡ ሌላ ጎልማሳ ደግሞ መጻሕፍት ደርድሮ ርዕሳቸውን እየተናገረ መጠናቸውን ለሽሪማዲ ያሳያል፡፡ ሁሉም ነገሮች የሚከናወኑት በተመሳሳይ ሰዓት ሲሆን፣ ፈተናው የሽሪማዲን አዕምሮ ብቃት መመዘን ነው፡፡ ሽሪማዲ ካርታና ዳማ በተመሳሳይ ሰዓት እየተጫወተ ሁለቱንም ወንዶች አሸነፈ፡፡ ሴቷ የሰጠችውን ከባድ የሒሳብ ስሌት በቃሉ አስልቶ መልሶ በተለያዩ ቋንቋዎች ከጋንዲ የተሰጡትን የተዘበራረቁ ቃላት አገጣጥሞ ዓረፍተ ነገር ሠራ፡፡ ግጥምም ገጠመ፡፡ ደወል ስንት ጊዜ እንደተደወለና ስንት ፍሬ ጀርባው ላይ እንዳረፈም በትክክል ተናገረ፡፡ ዓይኑ ተሸፍኖ የመጻሕፍቱን መጠን እየዳሰሰ ርዕሳቸውን አሳወቀ፡፡  ፈተናውንም አለፈ፡፡

ጋንዲ ቀጣዩን ሁለት ዓመታት በሙንባይ ውስጥ ሲቆዩ አዘውትረው ከሽሪማዲ ጋር ይገናኙ ነበር፡፡ በጥሞና ማሰላሰል፣ ከራስ ጋር መነጋገር፣ ዕርዳታ ለሚሹ ሁሉ መስጠትንና ሁሉንም ሰው በእኩል ዓይን መመልከትን ተማሩ፡፡ ሃይማኖትን ጨምሮ በዓለም ላይ ያሉ ልዩ ልዩ ጽንሰ ሐሳቦችን ፈተሹ፡፡ ስለዚህ ዓለም እውነታዎችና ስለ ቀጣዩም ዓለም ተመራመሩ፡፡ የጋንዲ የሕግ ሥራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሲወስዳቸውም ውይይታቸውን በደብዳቤ ቀጠሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1901 ሽሪማዲ በ31 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ የቴአትሩ ቀጣይ ክፍል መሸጋገሪያ ነው፡፡

ጋንዲ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ በሽሪማዲ ማለፍ ቢያዝኑም የሕይወት ፍልስፍናዎቹን በአቅራቢያቸው ላሉ ሰዎች ማስተላለፍን ተያያዙት፡፡ የህንድን ባህላዊ ልብስ ለብሰው በሽሪማዲ የተጻፉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ይተረጉሙም ጀመር፡፡

የቴአትሩ ቀጣይ ክፍል ጋንዲ ህንድን ነፃ ለማውጣት ያደረጉት ትግል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የሁለት ሰዓት ርዝማኔ ያለው ቴአትሩ፣ በተለይም ጋንዲ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞን የመግለጽ ሐሳባቸው ለተከታዮቻቸው ሲያስተላልፉ ያስቃኛል፡፡ በተቃውሟቸው ምክንያት ለእስርና እንግልት ሲዳረጉም ሰላማዊነትን ነበር የመረጡት፡፡ ይህ ሰላማዊ ተቃውሞ ህንድን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ከማውጣት ባሻገር በመላው ዓለም ሰላማዊ ተቃውሞን የማስረጽ አስተዋፅኦም አበርክተዋል፡፡ ጋንዲ ከአገራቸው ባሻገር በደቡብ አፍሪካ ለሰብአዊ መብት መከበር ያደረጉት ትግልም ተያይዞ ይነሳል፡፡

በ291 ከተሞች የታየው የማህተመ ጋንዲ ቴአትር በአዲስ አበባ

 

ቴአትሩ እንግሊዝ በህንድ የጫነችውን የታክስ ሥርዓት በመቃወም የተነሳውና ደንዲ ሳልት ማርች በመባል የሚታወቀውን የጋንዲ የተቃውሞ ጉዞም ያጎላል፡፡ የ400 ኪሎ ሜትር ጉዞው በርካታ ተከታዮችን ያፈራ ሲሆን፣ በጋንዲይዝም ጽንሰ ሐሳብ ከሚገኙት ነጥቦች መካከል ይጠቀሳል፡፡ እንደ እውነተኛነት (አሒምሳ) እና ድሀርማ ያሉ መሠረታዊ ሐሳቦችም ተካተዋል፡፡

ማህተመ ጋንዲ ለንባብ ባበቁት ግለ ታሪክ ሽሪማዲን የገለጹት፣ ‹‹መሰናክሎች በገጠሙኝ ጊዜ ሽሪማዲ ከለላዬ ነበር፤›› በማለት ነበር፡፡ ህንድን ነፃ ለማውጣት ጥረት ሲያደርጉ የመንፈስ ብርታት የሰጣቸው የሽሪማዲ ምክር መሆኑንም በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ ቴአትሩ የሚጠናቀቀው ጋንዲ በ78 ዓመታቸው በጥይት ተመተው ሲገደሉ ሲሆን፣ ካለፉ በኋላ በመንፈስ ከሽሪማዲ ጋር ዳግም ሲገናኙም ይታያል፡፡

በቴአትሩ የቀረበው ማህተመ ጋንዲ በዕድሜ ከገፉ በኋላ ስለ ቀደመ ሕይወታቸው ለወጣቶች ሲተርኩ ነው፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የተተረጎመው ቴአትር በጣሊያን ባህል መድረክ የቀረበው በእንግሊዝኛ ሲሆን፣ በሒንዲ በቀጥታ የቀረቡ ምልልሶችም ነበሩ፡፡ ሽሪማዲ ራጀቻንድራ ሚሽን ቴአትሩን በመላው ዓለም የሚያሳየው ቡድን ሲሆን፣ ከቴአትሩ የሚገኘውን ገቢ ህንድ ውስጥ ሕክምና መስጫ ተቋሞች ለማስገንባት ያዋሉበት ወቅት ነበር፡፡ ቴአትሩ በህንድና በሌሎች አገሮችም በምርጥ ድራማ፣ ምርጥ ዝግጅትና ምርጥ ትወና ሽልማቶች አግኝቷል፡፡ ከነዚህ መካከል ዳድሻሀብ የተባለው የተከበረ የህንድ ሽልማት ይገኝበታል፡፡

ቴአትሩን ከኢትዮጵያ በመቀጠል በዚህ ዓመት ብቻ በሌሎች 36 መድረኮች የማሳየት ዕቅድ አላቸው፡፡ የያዝነው ዓመት የሽሪማዲ 150ኛ ዓመት የሚከበርበት በመሆኑ ከህንድ የነፃነት ቀን ጋር በማያያዝ ቴአትሩን በዓለም ማዘዋወራቸውን አጠንክረው እንደሚቀጥሉም በድረ ገጻቸው ተመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...