Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

ቀን:

ላስ ቬጋስ ከሚገኘው ታዋቂው ማንዳላይ ቤይ ሆቴል 32ኛ ፎቅ ትይዩ ከሆነው የቬጋስ ጎዳና ላይ ጥይቱን እንደ ዝናብ አወረደው፡፡ ጥይቱ ግን እንዲሁ ጎዳና ላይ ያገኘውን ለመምታት አልሞ የሚርከፈከፍ አልነበረም፡፡ ጥይቱ በሚዘንብበት ሥፍራ ከ22 ሺሕ በላይ ሰዎች የሙዚቃ ፌስቲቫል እየታደሙ ነበር፡፡

ለሦስት ቀናት የተካሄደው ‹‹የሩት 91 ሃርቨስት ካንትሪ ሚዩዚክ ፌስቲቫል›› መዝጊያ በአሜሪካውያኑ እሑድ ኦክቶበር 1 ቀን 2017 ምሽት ሲከናወን፣ ሁለቱን የፌስቲቫል ቀናት ከ32ኛው የሆቴሉ ፎቅ ሆኖ ሲታዘብ የነበረው የ64 ዓመቱ ስቴፈን ፓድዶክ በፌስቲቫሉ ሲደሰቱና ሲፈነጥዙ የነበሩ ታዳሚዎች ላይ የተኩስ እሩምታውን አወረደው፡፡ ጥይት ሳይሆን ርችት የመሰላቸውም ነበሩ፡፡

የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

- Advertisement -

 

ሲኤንኤንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች እንደለቀቁት ምሥል፣ ታዳሚዎች በየጎዳናው መንጠባጠብ ጀመሩ፡፡ ራሳቸውን እንደ ዝናብ ከሚወርደው ጥይት ለመሸሸግ በየሥፍራው ተሯሯጡ፡፡ ጓደኛና ቤተሰብ ፍለጋ ተተራመሱ፡፡ እርስ በርሳቸው ተረጋገጡ፡፡ ባገኙት አጥር በመዝለል እግሬ አውጭኝ አሉ፡፡ የወደቁትንና ደም የሚፈሳቸውን ለመርዳት መሬት ተደፍተው ትንፋሻቸውን የሚያጋሩም ነበሩ፡፡ የሙዚቃው ፌስቲቫል ወደ ሁካታና ለቅሶ ተቀየረ፡፡

ከተለያዩ ዓይነት መሣሪያዎች አፈሙዝ በሚዘንበው ጥይት 59 ሲገደሉ 527 ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከጥይት ባለፈም ለማምለጥ በሚያደርጉት ጥረት አጥር ሲዘሉ፣ እንዲሁም በነበረው ትርምስ ተረጋግጠው የተጎዱ አሉ፡፡ ቢቢሲ እንደሚለው፣ ፖሊሶች ጥይቱ እንደ ዝናብ ተርከፍክፎበታል ከተባለው የሆቴሉ 32ኛ ፎቅ የሚገኘውን ክፍል ሲወሩ፣ ፓድዶክ ራሱን በጥይት መትቶ አሸልቦ ነበር፡፡ ፖሊስም በክፍሉ ውስጥ አሥር ጠመንጃዎችን አግኝቻለሁ ብሏል፡፡

እንደ ዋሽንግተን ፖስት፣ ፓድዶክ በአሜሪካ መንግሥት በወንጀለኛነቱ አይታወቅም፡፡ ምንም ዓይነት የወንጀል ታሪክ የሌለው ሲሆን፣ ከየትኛውም አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎም አይታወቅም፡፡

የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

 

በታዋቂው ማንዳላይ ቤይ ሆቴልም ጥቃቱን ከማድረሱ ሦስት ቀናት በፊት ጀምሮ ሰፊ የሆቴሉን ክፍል ተከራይቶ ሲቀመጥም ጥርጣሬ ያደረበት አልነበረም፡፡ በፓድዶክ ክፍል ግን እንደ ቢቢሲ ዘገባ አሥር፣ እንደ ዋሽንግተን ፖስት ደግሞ 23 የተለያየ መጠን ያላቸው የጦር መሣሪያዎች ተገኝተዋል፡፡

በኒቫዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በተደረገ ብርበራም 19 ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችና ቦምብ ለመሥራት የሚያገለግሉ ኬሚካሎች ተገኝተዋል፡፡

ጭፍጨፋውን ብቻውን ፈጽሞታል የተባለው ፓድዶክ መሣሪያዎቹንም በሕጋዊ መንገድ እንደገዛቸው የሕግ አስፈጻሚ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡ መሣሪያዎቹን የሸጠለት ‹‹ገንስ ኤንድ ጉትረስ›› ኩባንያም፣ ሰውየው ያልተረጋጋና መሣሪያ ለመያዝ ያልበቃ ነው ብሎ ለመገመት ያስቸግራል፣ ምንም ዓይነት ጥርጣሬን አያሳድርም ብሏል፡፡ የሆቴሉ ሠራተኞችም ቢሆኑ በፓድዶክ ላይ ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ ክፍሉን ለማፅዳት ሲገቡም ምንም እንዳላዩ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ግን ክፍሉን ሲፈትሽ አሥር ሻንጣዎች ማግኘቱን ተናግሯል፡፡

ስቴፈን ፓድዶክ ማን ነው?

የ64 ዓመቱ ስቴፈን ፓድዶክ ከዚህ ቀደም በወንጀል ተሳትፎ አያውቅም፡፡ ሁለት ጊዜ አግብቶ የፈታ ቢሆንም፣ ልጆች አላፈራም፡፡ ወንድሙ ኤሪክ ፓድዶክ ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገረው፣ አካውንታንት ሆኖ አገልግሏል፡፡ በኦርላንዶ የሪል ስቴት ባለቤትም ነበር፡፡ ‹‹የሚረዳቸው ልጆች ስለሌሉት ሀብታም ነው›› ሲልም ወንድሙን ይገልጸዋል፡፡

የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

 

ፓድዶክ መሣሪያ የሚገዛ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ለእኩይ ተግባር ሲጠቀምበት አልተገኘም፡፡ የወንድሙን ልጆችም ተኩስ ለማለማመድ ወስዷቸው ያውቃል፡፡

የተረጋጋ ባህሪ እንዳለው የሚነገርለት ፓድዶክ ኑሮውም በሰሜን ምሥራቅ ላስ ቬጋስ ነው፡፡ በማንዳላይ ሆቴል ክፍል የያዘው ደግሞ ጭፍጨፋውን ከመፈጸሙ ሦስት ቀናት አስቀድሞ ነው፡፡

ጭፍጨፋውን የፈጸመበትን ሚስጥር ፖሊስ ማወቅ አቅቶታል፡፡ የላስ ቬጋስ ፖሊስ ጆ ሎምባርዶ፣ ፓድዶክ ለምን ድርጊቱን እንደፈጸመ ማወቅ አልቻልኩም ብለዋል፡፡ ለብቻው የፈጸመው ጥቃት ብለውታል፡፡

ከሰውየው ጥቃት ጀርባ ማንም የለም፣ የአዕምሮ መቃወስ ችግር ሊሆን ይችላል የሚል መላምት ቢሰማም፣ አይኤስ ከድርጊቱ ጀርባ ነኝ ብሏል፡፡ ፓድዶክ ወደ እስልምና ሃይማኖት ከወራት በፊት እንደተለወጠም አሳውቋል፡፡ ሆኖም ይህንን የሚያሳይ ማስረጃ ያልተገኘ ሲሆን፣ ቡድኑ እንደ ልማዱ በማስረጃ ያልተደገፈ መረጃ ሰጥቷል ተብሏል፡፡

ለቢቢሲ ስለጀሃዲስት ቡድኑ ትንተና የምትሰጠው ሚና አል ላሚ በበኩሏ፣ አይኤስ የሚለውና ፓድዶክ የፈጸመው ፍጹም የማይጣጣም፣ የፓድዶክ ድርጊት የአይኤስ ወታደሮች ወይም ደጋፊዎች ከሚፈጽሙት የተለየ መሆኑን በማውሳት የአይኤስን እኔ ነኝ ባይነት ታጣጥለዋለች፡፡

እውነት ነው ቢባል እንኳን፣ ‹‹አይኤስ የእስልምና አስተምህሮ ነው›› እንደሚለው ድርጊቱ አልተፈጸመም፡፡ የአይኤስ ጥቃቶች የሚፈጸሙት ራስን በቦምብ አጋይቶ ሌላውን በማጥፋት በመሆኑ አይኤስ ‹‹እኔ ነኝ›› ያለው እውነት ሊሆን እንደማይችል አክላለች፡፡

የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ

 

በኔቫዳ የመሣሪያ ቁጥጥር ምን ይመስላል?

በአሜሪካ መሣሪያ ሸመታ ያለው ሕግ ከግዛት ግዛት የተለያየ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጣ ቁጥርም የመከራከሪያ አጀንዳ ነው፡፡ ግለሰቦች መሣሪያ እንዳይዙ ከያዙም መመዝገብ እንዳለበት፣ ከእጃቸው ሲወጣም ሕጋዊ መስመር መከተል እንዳለበት በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ቢደረግበትም፣ በአሜሪካ የጦር መሣሪያ ለመያዝ ከባድ አይደለም፡፡

የፓድዶክ መኖሪያ ኒቫዳ ደግሞ ከሌሎች ግዛቶች በተለየ የላላ የጦር መሣሪያ ሕግ ያለበት ነው፡፡ ነዋሪዎች መሣሪያ መያዝ የሚፈቀድላቸው ቢሆንም፣ መመዝገብ አይጠበቅባቸውም፡፡ መሣሪያ ሲገዙ ብቻ የቀደመ ታሪካቸው ይጠናል፡፡ የገዙትን መሣሪያ ለፈለጉት ሰው ሲሸጡም ሆነ ሲሰጡ የሚያስመዘግቡበት ሥርዓት የለም፡፡

ከዚህ ቀደምም በኒቫዳ ያለው የመሣሪያ ቁጥጥር ሕግ እንዲጠብቅ ለፖለቲካ መሪዎች ሐሳብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ምላሽ አላገኘም፡፡ ይህም ነዋሪዎች መሣሪያ እንደፈለጉ እንዲገዙና ሰዎችን እንዲጨፈጭፉ ምክንያት ሆኗል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1991 ወዲህ በአሜሪካ በግለሰብ በተያዙ ጠመንጃዎች ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎት የላስ ቬጋሱ ጭፍጨፋ ከፍተኛውን ሥፍራ ቢይዝም፣ በአሜሪካ ግለሰብ ታጣቂዎች ንፁኃንን ባነገቡት መሣሪያ ሲፈጁ የመጀመርያ አይደለም፡፡

እ.ኤ.አ. በ1999 በኮሎራዶ 13፣ በ2009 በቴክሳስ 13፣ በ2015 በካሊፎርኒያ 14፣ በ1991 በቴክሳስ 23፣ በ2012 በኮኔክቲከት 27፣ በ2007 በቨርጂኒያ 32፣ በ2016 በፍሎሪዳ 49 ሰዎች በግለሰብ ታጣቂዎች ሲገደሉ፣ በ2017 የኒቫዳው ጭፍጨፋ ደግሞ 59 ተገድለዋል፡፡ ይህም በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ ተብሏል፡፡

በአሜሪካ ፖለቲከኞችም ሆነ በሚዲያው የስቴፈን ፓድዶክ የላስ ቬጋስ ጭፍጨፋ በሽብርተኝነት አለመፈረጁ ደግሞ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ አሜሪካ ውስጥ ሳይሆን በተቀረው ዓለም፡፡ በሽብርተኝነት ትርጓሜ ላይ የማይግባባው የዘመኑ ፖለቲካ አሁንም በነበረበት መቀጠሉ እንቆቅልሽ ነው ያስብላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...