Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢሬቻ ውሎ

የኢሬቻ ውሎ

ቀን:

የኢትዮጵያ 13 ወራት መባቻ መስከረምን ከሚያደምቁ በዓላት አንዱ ኢሬቻ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የሚከበሩ ኢሬቻና ሌሎችም በዓላት ጭጋጋማውን ክረምት አልፎ ወደ በጋ መሸጋገርን መነሻ ያደረጉ ናቸው፡፡ ከዘመን ዘመን መሸጋገርን፣ ብርሃን ማየትን፣ ልምላሜን ያሞግሳሉ፡፡ በበዓላቱ አዲስ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የብልጽግና እንዲሆን ምኞቶች ይስተጋባሉ፡፡ ለፈጣሪም ምስጋና ይደርሳል፡፡ ከበዓላቱ አንዱ የሆነው ኢሬቻም ተመሳሳይ ድባብ አለው፡፡

ኢሬቻ ከክረምት ወደ ብራ መውጣትን ምክንያት በማድረግ የሚቀርብ ምስጋና ነው፡፡ የሚሞገሰው ልምላሜ ነውና ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ የበዓሉ ልዩ መገለጫ ናቸው፡፡ የበዓሉ ታዳሚዎች ከኦሮሞ ባህላዊ አልባሳቶቻቸው በተጨማሪ ቄጠማና አደይ አበባ ይዘው ይታያሉ፡፡ ፈጣሪን እያወደሱ መልካሙን ሁሉ ይመኛሉ፡፡ በየዓመቱ በወርሐ መስከረም በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (ሐይቅ) ዳርቻ የሚከበረው ኢሬቻ በእንስቶች ‹‹መሬ ሆ…›› ዜማ ማልዶ ይጀመራል፡፡

የኢሬቻ ውሎ

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

 

ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለበዓሉ በቢሾፍቱ የከተሙ ሰዎች በባህላዊ ዜማ ታጅበው ወደ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ይተማሉ፡፡ የአባ ገዳና የዕድሜ ባለጸጎች ምርቃት በማኅረሰቡ ዘንድ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የተወለዱ እንዲያድጉ፣ የተዘራ እንዲበቅል፣ አገር ሰላም እንዲሆን ሲመርቁ ታዳሚዎች በኦሮምኛ ‹‹ያታኡ›› ማለትም ይሁን ይላሉ፡፡

ከማለዳ አንስቶ ረፋድ ድረስ ልዩ ልዩ ኅብረ ዝማሬዎች በሐይቁ ዙርያ ይስተጋባሉ፡፡ በኢሬቻ ከአባ ገዳዎች ምርቃት በመቀበል የሚጀመር ትዳር መልካም እንደሚሆን ስለሚታመን ጥንዶችም በቦታው ይገኛሉ፡፡ የኦሮሞን ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ገበያ እንዲሁም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የታሪክ መጻሕፍት ሽያጭም የበዓሉ ገጽታ ናቸው፡፡

ከጥንት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ኢሬቻ ከማኅበረሰቡ ክብረ በዓሎች አንዱ ነው፡፡ ኢሬቻ እርጥብ ሳር፣ ቅጠል፣ ቄጠማ፣ አበባ ማለት እንደሆነ አባ ገዳዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹13ቱን ወር በሰላም ያስጨረስከን ፈጣሪ፣ ለመጪው ዓመት በሰላም አድርሰን፡፡ ለሰው ልጅና ለሁሉም ፍጥረት ብለህ አጥርተህ የፈጠርከው ሐይቅ ላይ ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ ውኃ ንፁህ ነውና፤›› ይባላል፡፡

በኢሬቻ ሳሩን አበባውን ያበቀለ ፈጣሪ ለሰው ልጆች ዘርና ፍሬ በመስጠቱም ይመሰገናል፡፡ በክረምት መልካው፣ ወንዙ ሞልቶ ዘመድ ከዘመዱ፣ ወዳጅ ከጓደኛው ሳያጠያይቅ ከርሞ በበጋ ውኃው ጎድሎ በመገናኘቱም ውዳሴ ይቀርባል፡፡ በኢሬቻ በዓል ምርቃት የሚሰጥበት ቦታ ‹‹ድሬ›› ይባላል፡፡ የተስተካከለ ቦታ እንደማለት ሲሆን፣ በቦታው ምርቃት ካልተከናወነ ወደ ሐይቁ አይሄድም፡፡

የኢሬቻ ውሎ

 

ወደ መልካው ሲኬድ ዳለቻ ኮርማ ታርዶ፣ ‹‹እንኳን በሰላም ከክረምቱ ወደ ብርሃኑ አመጣኸን፡፡ ዘመኑን የሰላም አድርግልን፡፡ ሕዝቡና አገሪቱን ይባርክልን፤›› ይባላል፡፡ የበዓሉ አክባሪዎች የያዙትን ለምለም ቅጠል፣ ቄጠማ፣ ርጥብ ሳርና አደይ አበባ ሐይቁ ውስጥ እየነከሩ ይረጫሉ፤ ሰውነታቸውን ያስነካሉ፤ በሐይቁ ዳርቻም ያስቀምጡታል፡፡ በሥርዓቱ ክርስቲያኖች፣ ሙስሊሞችና የዋቄ ፈታ ተከታዮችም ይካፈላሉ፡፡ ዝማሬ፣ ምርቃትና ሌሎችም ሥርዓቶች በዋርካው ‹‹ኦዳ›› ሥር ይከናወናሉ፡፡

ኢሬቻ እርቅ ማለት ስለሆነና የሰላምና ፍቅር ዐውደ ዓመት በመሆኑም በማኅበረሰቡ መካከል ያለ መከፋፈል ይከበራል፡፡ መስከረም ከጠባ በኋላ በዓይነ ሥጋ ለመተያየት የበቁ ወዳጅ ዘመዶች ‹‹እኛ ደርሰናል፤ እናንተ ደረሳችሁ?›› ይባባላሉ፡፡ በበዓሉ የተጣሉ ይታረቃሉ፡፡ የበደሉም ይቅርታ ይጠይቃሉ፡፡ የተለያየ ሃይማኖት የሚከተሉ የማኅበረሰቡ ተወላጆች በዓሉን በጋራ የሚያከብሩትም ለዚሁ ነው፡፡

ከኢሬቻ በኋላ በቡራዩ ከተማ የሚከበረው የመልካ አቴቴ በዓልም በርካታ አባ ገዳዎችና በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በቦታው ተገኝተው የሚካፈሉት ነው፡፡ እንደ ኢሬቻ ሁሉ ከክረምቱ ወራት ወደ በጋ ለመሸጋገር ምስጋና የሚስተጋባበት ነው፡፡ ባህላዊ ጭፈራዎችና የፈረስ ግልቢያም የበዓሉ አካል ናቸው፡፡   

የገዳ ሥርዓት አንድ አካል የሆነው ኢሬቻ፣ ዝማሬ፣ ውዝዋዜና ፉከራን የመሰሉ ክውን ጥበባትን ማቀፉ እንዲሁም የሰው ልጆች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው መኖራቸውን ማንፀባረቁ የዓለም ሕዝብ ለገዳ ሥርዓት ትኩረት እንዲሰጥ ካደረጉ መካከል ይጠቀሳል፡፡ ኢሬቻ ባህላዊ ሥርዓቶችንና አገር በቀል እውቀትን እንዳቀፈ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮም ዛሬ ደርሷል፡፡

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ባህላዊ ምግቦችና መጠጦችም የበዓሉ መገላጫ ናቸው፡፡ ከዕድሜ ባለፀጎች የሚተላለፈው ምርቃት ማኅበረሰቡን በማስተሳሰር ረገድ ያለው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ባህላዊ ግጭት አፈታትና ባህላዊ ሕክምና አገር በቀል እውቀቱን የሚያጎሉ ሲሆኑ፣ በተለይ ለተፈጥሮ የሚሰጠው ትልቅ ቦታ የኢሬቻ መሠረት ነው፡፡ ለበዓሉ ከሚመረጠው ቦታ አንስቶ፣ ሥርዓቱ ተጀምሮ የሚጠናቀቀው ተፈጥሮን ባማከለ ሁኔታ ነው፡፡

አብዛኛው የአገሪቱ ማኅበረሰብ የሚተዳደረው በግብርና እንደ መሆኑ ልምላሜና ምርታማነት የሕልውና መሠረት ናቸው፡፡ መሬት ካላፈራ፣ የተዘራ በቅሎ ካልታጨደ አይሆንምና ኢሬቻ ተፈጥሮ ላይ ያተኩራል፡፡ ስለ ልምላሜ እያመሰገኑ ፍሬያማ ስለመሆን መለማመን የሥርዓቱ የማዕዘን ድንጋይ ነው፡፡

ኢሬቻ የገዳ ሥርዓትን ልዩ ከሚያደርጉ አንዱ መሆኑ የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ ለመካተቱም ምክንያት ነው፡፡ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ከኢሬቻ በተጨማሪ ጉዲፈቻ፣ ዋቄ ፈና ሲንቄና ሌሎችም ሥርዓቶች ይካተታሉ፡፡ የማኅበረሰቡ መገለጫ የሆኑ እነዚህ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓቶችን ያጣመረው ገዳ በወካይ ቅርስነት የተመዘገበው ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተደረገው በአሥራ አንደኛው የዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ጉባኤ ነበር፡፡

የኢሬቻ ውሎ

 

የገዳ ሥርዓትን በቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት የተጀመረው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ በተመዘገበበት ዓመት በኢሬቻ በዓል ላይ የተፈጠረው ክስተት በርካቶችን ያሳዘነ ነበር፡፡ አምና በአገሪቱ የነበረው ተቃውሞ ከተገለጸባቸው መድረኮች አንዱ በነበረው በኢሬቻ በዓል ልብ በሚሰብር ሁኔታ የብዙዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ የበዓሉ የዓመታት የደስታ ገጽታ ሐዘን አጥልቶበትም ከርሟል፡፡ ኢሬቻን ተከትሎ የመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ የአምናው ክስተትም ዓመት አስቆጥሯል፡፡

መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም. የዋለው የዘንድሮው ኢሬቻ እንዳለፉት ዓመታት ማልዶ ሲጀመር፣ ከአክባሪዎች መካከል የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ያለበት ባህላዊ ልብስ ለብሰው የተገኙ ነበሩ፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ደግሞ ‹‹የኦነግን ዓርማ›› በግንባራቸውና በእጃቸው አስረው እንዲሁም በልብሳቸው አሰፍተው ታይተዋል፡፡ በሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ የሚከናወነው ባህላዊ ሥርዓት ቢካሄድም ወጣቶች ፖለቲካዊ ተቃውሟቸውን ያስተጋቡ ነበር፡፡

በኢሬቻ ባህላዊ ሥርዓት መሠረት በመጻፍ የሚያዘውን ለምለም ቄጠማና አደይ አበባ ይዘው የአገሪቱን ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚሸነቁጥ ድምፅ የሚያሰሙም ነበሩ፡፡ በቦታው ወደ 300 ሺሕ የሚጠጉ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ያለውን ግጭትና ሌሎችም ወቅታዊ ሁኔታዎችን የሚተቹ መልዕክቶች ያስተላለፉ ነበሩ፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል ለተነሳው ግጭት መንግሥትን ተጠያቂ የማድረግ ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ በዓሉን ከሚገልጹ ባህላዊ ልብሶችና ትውፊታዊ ሥርዓቶች ባሻገር ፖለቲካዊ ድምፅ ተሰምቶበት ያለፈ ነበር፡፡

ኢሬቻ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ቢሆንም ሥርዓቱን ለመጠበቅ ቁሳዊ ቅርሶች ያስፈልጋሉ፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል በሥርዓቱ ቦታ የሚሰጠውን የኦዳ ዛፍ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ማኅበረሰቡ ተፈጥሮን የሚወድና የሚያከብር ከመሆኑም ባሻገር፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን የባህላዊ ሥርዓቶች ዋነኛ አካል አድርጎም ይቀበላል፡፡ በገዳ ሥርዓት መሠረት ማኅበረሰቡ በዓመት ሁለት ጊዜ ለፈጣሪ ‹‹ዋቃ›› ምስጋና የሚያቀርበው ተፈጥሮን በመመርኮዝ ነው፡፡

ዩኔስኮ ገዳን በመዘገበበት ወቅት ለባህሉ ከዘመን ወደ ዘመን መሸጋገር የሚረዱ ቁሳዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ አሳስቧል፡፡ ኢሬቻ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለውን ጉልህ ስፍራ ከግምት በማስገባትና ቅርሱ የአንድ አገር ብቻ ሳይሆን የዓለምም ጭምር ነው ብሎ ሲመዘግበው፣ ባህሉ እንዲጠበቅ በመጠየቅም ነበር፡፡

ዘመኑ ተናኘ ለዚህ መጣጥፍ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...