Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ማኅበሩ አማተሮች ፕሮፌሽናል ሆነው የሚወጡበት ነው››

ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ፣ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ፕሬዚዳንት

የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) የተመሠረተው በ1952 ዓ.ም. ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሁለት ሺሕ አባላት አሉት፡፡ ከአባላቱ መካከል ሰባት መቶው ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ለአንባቢያን እንዲደርሱ፣ በዘርፉ ያሉ ችግሮች እንዲቀረፉ፣ አማተር ደራስያን ሙያዊ ብቃታቸው እንዲጎለብትና የንባብ ባህል እንዲዳብር በማድረግ ሠርተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ እንዲሁም የተቀሩት አፍሪካ አገሮች ጸሐፍት ማዕከል የሚገነባበት ቦታ ላይ የመሠረተ ድንጋይ ተጥሏል፡፡ በማዕከሉና በማኅበሩ እንቅስቃሴዎች ዙርያ የማኅበሩን ፕሬዚዳንት ሙሴ ያዕቆብን (ዶ/ር) ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው ሳምንት ሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ከሊዝ ነፃ ቦታ ተረክባችኋል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤትና የፓን አፍሪካን ደራስያን ማዕከል ይሆናል ተብሏል፡፡ ማዕከሉን ለመገንባት ሐሳቡ የተጠነሰሰበት ምክንያትና ለዘርፉ የሚያበርክተው አስተዋፅኦ ምንድነው?

ዶ/ር ሙሴ፡- የመሠረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ዕለት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማርያም (ዶ/ር) እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመሬት ጥያቄ ስናቀርብ ነበር፡፡ ጉዳዮን ለአቶ ድሪባ ኩማ ካስረዳናቸው በኋላ ለከተማ መስተዳድር ካቢኔው አቀረቡና ቦታ እንዲሰጠን ውሳኔ ተሰጠ፡፡ ትንሽ የመጓተት ሒደት ነበር፡፡ መሬቱ የካ ክፍለ ከተማ ሲኤምሲ ሚካኤል ነው የተሰጠን፡፡ አርክቴክቸራል ዲዛይኑ ሲያልቅ የሕንፃ ከተማ በሆኘችው ጎንደር አስመርቀናል፡፡ ለዲዛይን እስከ 106 ሚሊዮን ብር ነበር የተጠየቀው፡፡ የማኅበሩ አባልና አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራሁ ግን ዋጋውን ዝቅ አድርጎ ሠራልን፡፡ አሁን የሕንፃው ጠቅላላ ወጪ ከ80 እስከ 100 ሚሊዮን ብር ይሆናል፡፡ ሕንፃው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካን ደራስያን ማኅበር መቀመጫ እንዲሆን ነው የታሰበው፡፡ ሕንፃው የብሔር ብሔረሰቦች ሥነ ጽሑፍ፣ ቋንቋና ሌሎችም ተጓዳኛ ትውፊቶች ይንፀባረቁበታል፡፡ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ስፍራ ተሰጥቶት ሥነ ጽሑፍ ለሕዝብ የሚቀርብበት፣ ጥናት የሚካሄድበት ኢትዮጵያን የሚወክል የብሔር አምባ ይሆናል፡፡ ማኅበሩ 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር የመላው አፍሪካ ደራስያን ስብሰባ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ የፓን አፍሪካን ደራስያን ማኅበር መቀመጫ አዲስ አበባ ቢሆን የሚል ሐሳብ ተነሳ፡፡ ከሌሎች አኅጉሮች አንፃር በአፍሪካ  የሥነ ጽሑፍ እንቅስቃሴው ከተዳከመባቸው ምክንያቶች አንዱ በፍራንኰፎንና አንግሎፎን አፍሪካ መካከል ያለው መከፋፈልና ፉክክር ነው፡፡ የአፍሪካ ደራስያን ማኅበር መቀመጫ ኢትዮጵያ ላይ ቢሆን ክፍፍሉን ሊያጠፋው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ ለ3,000 ዓመት በልዕልና የቆየች አገር ናት፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና በመሆኗ ከብዙ የአፍሪካ ጉዳዮች ጋርም ሊያያዝ ይችላል፡፡ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ጽሕፈት ቤቶች ጋር አንድ ላይ መሆኑ ብዙ ነገሮችን ያስተሳስራል፡፡ ከሌላው በተለየ በራሳችን ፊደል መጻፋችን ሌላው ምክንያት ሲሆን፣ የማኅበሩ መቀመጫ አዲስ አበባ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ጸሐፍቶቻችን ወደ አፍሪካ አገሮች ሲሄዱ ጉዳዩን እንዲነጋገሩበት እናደርግ ነበር፡፡ የደቡብ ሱዳንና ሰሜን ሱዳን ደራስያን እዚህ ሲመጡም ተነጋግረናል፡፡ በቀጣይ ስምንትና ዘጠኝ ወር የአፍሪካን ደራስያን ለመጥራት አስበናል፡፡ የማኅበሩ 50ኛው ዓመት ሲከበር ጥሪውን እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው የሱዳን ደራስያን ቢሆኑም፣ በመከፋፈላቸው ምክንያት ለሰባት ዓመት የአፍሪካ ደራስያንን አልጠሩም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ለማድረግ ትጠራለች፡፡ የአፍሪካ አምባሳደሮችና የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንሰበስብና በስፋት በጉዳዩ  እንወያያለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሕንፃው ግንባታ ስለሚካሄድበት በጀት ጉዳይና ከተጠናቀቀ በኋላ ስለሚሰጠው አገልግሎት ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ሙሴ፡- ሕንፃው የራሱ ገቢ እንዲኖረው ማተሚያ ቤት ይኖረዋል፡፡ ጸሐፍቶቻችን በረከሰ ገንዘብ መጽሐፍ የሚያሳትሙበት ይሆናል፡፡ በፀጥታና በሰላም ድባባቸው ወደ ገዳም የተጠጉና ጸሐፍት ሊጽፉባቸው የሚችሉ መኝታ ክፍሎች ይኖሩበታል፡፡ ቤተ መጻሕፍት፣ ጥበብ የሚከናወንባቸው አዳራሾችም ይገነባሉ፡፡ የታችኛው የሕንፃው ክፍል ከጥበብ ጋር የተያያዘ ቢዝነዝ የሚሠራበት ነው፡፡ መጻሕፍት ቤት፣ ኮፒ ራይት ተጠብቆ ሙዚቃና ሌላም የሚሽጥበትም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሕንፃው ገቢ እንዲኖረው የሚያስችል ሁኔታ ይኖራል፡፡ አሁን 1.2 ሚሊዮን ብር አለን፡፡ የምናካሂደውን የአፍሪካ ደራስያን ስብሰባና ማኅበሩ የሚንቀሳቀስበትን ገንዘብ ጨምሮ ስለሆነ ያን ያህል አይደለም፡፡ ገንዘብ ለማሰባሰብ በርካታ አካሄዶችን ይኖሩናል፡፡ መንግሥት ምሥጋና ይግባውና አሁን ባንኮቻችን ያለ ውጪ ጫና እየጠነከሩ መጥተዋል፡፡ ሠርተን የምንከፍለው የተወሰነ ብድር ከባንኮቻችን እናገኛለን የሚል እምነት አለ፡፡ ከጥበብ አፍቃሪ በርካታ ባለሀብቶች የተወሰነ ገንዘብ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ በኤስኤምኤስ የተለያየ ሽልማት በማቅረብ ገቢ እናሰባስባለን፡፡ ጉዳዩ የክልሎች ስለሆነ እጃቸውን ይዘረጋሉ የሚል ትልቅ እምነት አለ፡፡ በናይጄሪያና ሌሎችም አገሮች የደራስያን ማኅበር ሕንፃዎችን ሙሉ በሙሉ መንግሥት ከፍሎ አሠርቷል፡፡ እንደሰማነው አገራችን በዚህም ዓመት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ እንደምትካተት ነው የሚጠበቀው፡፡ አቅም እየተፈጠረ ስለሆነ ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ሳንገባ መንግሥት የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በማየት በጸሐፍት አምባ ግንባታ ጣልቃ ሊገባ ይችላል ብለንም እንገምታለን፡፡ ዋናው ሐሳቡን አመንጭቶ፣ ቦታ አግኝቶ መሠረት ድንጋዩን መጣል ነው፡፡ ጉዳዩ የማኅበራችን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥበብ ወዳድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ጥሩ ምላሽ ካገኘን ከአንድ ዓመት ተኩል እስከ ሦስት ዓመት ይጠናቀቃል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂደው የጥበብ ጉዞ ሙያተኞችን በማስተሳሰርና ለሥነ ጽሑፍ ሥራ የሚያነሳሱ ቦታዎችን በማስቃኘት ስለነበረው እንቅስቃሴ ቢገልጹልን?

ዶ/ር ሙሴ፡- ጉዞው ሲጀመር የጸሐፍትን አገርና ሥራዎች መቼት አድርጎ ይነቃነቅ ነበር፡፡ የመጀመሪያው ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ፍቅር እስከመቃብር አገር ነበር፡፡ የሀዲስ ዓለማየሁን ፍቅር አስከ መቃብር መቼት አድርጎ መጽሐፉ ጎጃም ውስጥ የጠቀሳቸውን አካባቢዎች የአባ ዓለም ለምኔ፣ ሰብለ ወንጌል ማረፊያ ብለን ከሰየምነው ጀምሮ እስከ ማንኩሳ ያካትታል፡፡ ሁለተኛው ጉዞ የፍቅረ ማርቆስ ደስታን ከቡስካ በስተጀርባ መጽሐፍ መቼት አድርጎ ወደ ደቡብ የተደረገ ሲሆን፣ ቀጥሎ ወደ ዘርዐ ያዕቆብና ቅዱስ ያሬድ አገር ትግራይ የተካሄደ ነው፡፡ አራተኛው ሕያው የጥብበ ጉዞ ወደ ፀሐይ መውጫ አገር በሚል ወደ ድሬዳዋና ሐረር የተደረገ ነው፡፡ በዚህኛው ጉዞ ከደራስያን መቼት በተጨማሪ የአገሪቱ የቱሪስት መስህብ የምንላቸውንም ጭምር ልናስተዋውቅ የምንችልበት አድርገነዋል፡፡ ዋናው ዓላማ ደራስያኑ የወለደና ያሳደገ አገርና ሕዝባቸው እንዲያውቁ ነው፡፡ አንዳንድ ጸሐፍት በምናባቸው ብቻ አገር አካለው ይጽፋሉ፡፡ በዓይን ማየት ማለት በእጅ መዳሰስና ማዳመጥም ነው፡፡ ለወደፊት የጥበብ ሥራቸው የእዝነ ሕሊናቸውን አድማስ ያሰፋል፡፡ በሚጎበኘው አገር ችግርም ካለ ችግሩን ቀርፈን የምንወጣበት መንገድ ተጀምሯል፡፡ ሕያው የጥበብ ጉዞ ወደ ዓባይ ጣና ምድር ትልቁና ብዙ ሰው ያነቃነቅንበት ነው፡፡ ከጉዞው በፊት ወደ ለምለሚቱ ኦሮምያ በሁለት የተከፈለ ጉዞ ልናደርግ አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ጉዳይ ስንሄድ ስለ እንቦጭ ችግር ሰማን፡፡ ከክለሉ መንግሥት ጋር ተነጋግረን ችግሩን በጥበብ አብረን ለመፍታትም ወሰንን፡፡ የአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ጉዳይ ስለሆነ ለሕዝብ የምናሳውቅበት መንገድ እንፈልግ ተባለ፡፡ በእንቦጭ ጉዳይ የጣና ተፋሰስ ባጠቃላይ ችግር ላይ ስላለ ጉዞው ከዓባይ በረሃ ተጀመረ፡፡ የዓባይ ምንጭ የሆነው የጮቄ ተራራ የሰፈራው ቅፍለት ወደ ላይ እየተጠጋ በሄደ ቁጥር ደኑ እየመነመነ መሆኑን አየን፡፡ በጉዳዩ ግጥም ተጻፈ፣ ዲስኩር ተደሰኰረ ሕዝቡንም አነጋገርነው፡፡ በቀጣይ ግሽ ዓባይን ዓይተን መስተካከል ያለበትን ተነጋግረናል፡፡ በጉዞው ጎንደር፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ታቦር የአለቃ ገብረ ሀናን፣ የብርሃኑ ዘሪሁንን ሀገር ሁላ አካለን ነው የመጣነው፡፡ የሄዱት ጸሐፍት ተደስተዋል፡፡ ማኅበሩም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተቀርረበበት ቆንጆ ሁኔታ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ሰኔ ሰላሳ የንባብ ቀን ስታከብሩ የንባብ ባህልን በማጎልበት የተጫወተው ሚና ምን ይመስላል? ቀኑን በብሔራዊ ደረጃ ለማክበር ለመንግሥት ያቀረባችሁት ጥያቄስ ምላሽ አገኘ?

ዶ/ር ሙሴ፡- በኛ ማኅበርና ሌሎችም ንባብ ጉዳዬ ነው ብለው የሚሠሩ አካላት የሚደረገው እንቅስቃሴ በጊዜና በቦታ የተበታተነ ነው፡፡ በአዲስ አበባና በተወሰኑ የክልል ከተሞች አልፎ አልፎ የሚደረግ ነው፡፡ ንባብ በዓለማችን ከፍተኛ ተግዳሮት አለበት፡፡ በተለይ ከማኅራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ በአገራችንም የንባብ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል፡፡ በአንድ ዩኒቨርሲቲ አንድ የጥናት ሰው ‹‹እያነበበ ሳይሆን እያዳመጠ የሚማር ትውልድ መጣብን›› ያሉት ትዝ ይለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ላለፉት አራት ዓመታት ጥረናል፡፡ እየሠሩ እንደሆነ ብናውቅም ካለው በበለጠ መሠራት አለበት ድሮ የትምህርትና የሥነ ጥብብ ሚኒስቴር የባህልና የሥነ ጥበብ ጉዳይ ይይዝ ነበር፡፡ ትምህርት ደግሞ በዋነኛነት ማንበብ ነው፡፡ የተንጠባጠበ ጉዳይ ሳይሆን ብሔራዊ ንቅናቄ ማድረግ አለብን ብለን ነው ከአራት ዓመት በፊት የጀመርነው፡፡ ብሔራዊ ንቅናቄ ለንባብ በቦታም በጊዜም ሰፊ ዕድል ይፈጥራል፡፡ እንደ ማርች 8 በመላው አገሪቱ መከበር አለብት፡፡ ሰኔ 30ን ለምን መረጣችሁ ይባላል፡፡ ሰኔ 29 በጀት መዝጊያ መሆኑ ችግር እንደማይፈጥር አጣርተናል፡፡ በቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ ክልልና በፌዴራል ደረጃ የሚከበር ነው፡፡ የትምህርት ጉዳይ የሚመለከታቸው የትምህርት ቢሮዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች፣ ተማሪዎችና መምህራን የሚሳተፉበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለንባብ ተነሳ ማለት ትልቅ ተሳትፎ ስለሚፈጥር ቀላል አይደለም፡፡ ሰኔ 30 በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትውፊት ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የመደበኛ ትምህርት ጊዜ ማብቂያ ነው፡፡ ሰኔ ሠላሳ የተማሪ አበሳ ይባላል፡፡ ያለፈና የወደቀ የሚለይበት ነው፡፡ ከሁለት ወር ተኩል በላይ ብዕር ይታሠራል፤ መጻሕፍት ይጠፈራሉ፡፡ በኛ ጊዜ በሐምሌ በጭጋኑ መጻሕፍት እየተዋዋሰን እናነባለን፡፡ ቴሌቪዥን፣ ስልክና ሌሎችም ንባብን የሚጋሩ ኤሌክትሮኒክሶች አልነበሩም፡፡ ዛሬ ወደ 35 ሚሊዮን ተማሪዎች በአገሪቱ አሉ፡፡ ነርሰሪ ካለው ዩኒቨርሲቲ ፒኤችዲ እስከሚሠራው ሰኔ 30 ደወሉ ከተደወለ ክረምቱን ወደ ንባብ ጉባኤ የሚገባበት ይሆናል፡፡ አሁን ጉዳዩን ከያዙት አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ጋር ስናወራ የመንግሥት ሠራተኛው አንድ ሰዓትም ቢሆን ቢያነብ ብለናል፡፡ አንድ ሰዓት ማንበብ አንባቢ ባያደርግም ሐሳቡ ይሰርፃል፡፡ በተጨማሪ  ዓመቱን ሙሉ በየወሩ ንባብ የሚዘከርባቸው ሥነ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ፡፡ ስለ ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጽፈን አስገብተን ጥሩ መልስ አግኝተናል፡፡ በሕግ ወይም በሚኒስቴሪያል ደረጃ ይውጣልን ብለን መንግሥት ያግዛችኋል ተብለናል፡፡ ቀኑ ለፓርላማ ቀርቦ፣ በሕግ ብሔራዊ የንባብ ቀን እንዲከበርልን የጠየቅነው ገፍቶ ሄዶ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕግ ረቂቁን አውጥቶ፣ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በኩል፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም በሚመለከተው ሚኒስትር በኩል ቀርቦ በ2010 ዓ.ም. በመላው አገሪቱ ይከበራል ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መኖሪያ ቤት ለሌላቸው ደራስያን ቤት ለመገንባት የጀመረው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ሙሴ፡- የጸሐፍት መንደር የመሥራት እቅድ አለን፡፡ መንግሥት ለጦር ጉዳተኞች፣ ለመምሕራንና ለሌሎችም አገርና ትውልድን አንፀዋል ላላቸው የመኖሪያ ቤት ቦታ የመኖሪያ ቤት መገንቢያ የረዥም ጊዜ ብድር እያመቻቸላቸው ነው፡፡  ማኅበሩ ጸሐፍትም ይገባቸዋል ይላል፡፡ ላለፉት 60ና 70 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ሕሊና ውስጥ ብዙ በማስረጽ ለአገር ውለዋል፡፡ አሁን ምዝገባው እያለቀ ሲሆን፣ ያልሰሙ ጸሐፍት ካሉ መጥተው ይመዝገቡ፡፡ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለምም የመጀመሪያው የጸሐፍት መንደር ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡  ከቤት ኪራይ፣ ከደባል ኑሮ ወጥተው አርፈው ሥራቸውን የሚሠሩበት ቦታ ይሆናል፡፡ የመዘገብነውን እንደተለመደው ለአጋራችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እናቀርባለን፡፡ ለአስተዳደሩ ብቻ ሳይሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና ሌሎችም አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትና አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ለማኅበሩ የሰጡት ሪቮልቪንግ ፈንድ በምን መንገድ የደራስያንን ሥራዎች ለሕዝብ ለማብቃት ውሏል? ከየካቲት ወረቀት ፋብሪካ ያገኛችሁት አዲስ ፈንድስ?

ዶ/ር ሙሴ፡- ሪቮልቪንግ ፈንድ ጸሐፍት የሚያሳትሙበት አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡ የካቲት ወረቀት ፋብሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር ፈቅዶልናል፡፡ ጸሐፍት መጻሕፍታቸውን አሳትመው ከሽያጩ መጽሐፉን ለማሳተም የወጣውን ወጪ ሪቮልቭ በሚያደርግ ባንክ አካውንት አንዲቀመጥ እየተደረገ ሌሎች ጸሐፍት የሚጠቀሙበት አካሄድ ነው፡፡ ጥሩ ሥራ ሠርተው ለማሳተም አቅም ያጡ ጸሐፍት የሚገለገለቡት ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ብሌን መጽሔትን ለማሳተም በፊት ኢክሊፕስ ማተሚያ ቤት ሲረዳን ነበር፡፡ ቅብብሎሽ ስለሆነ አሁን ብርሃንና ሰላም አትሞልናል፡ ብሌን በጥበብና በአካዳሚክስ መካከል ሚዛን እየፈጠረች ሕዝባችንን የምታስተምር መጽሔት ናት፡፡ የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ ብርሃንና ሰላም 500 ሺሕ ብር፣ አርቲስቲክ  300 ሺሕ ብር፣ የሰጡን ገንዘብ በተለያየ ምክንያት ወደ ሪቮልቪንግ ፈንደ መመለስ አልቻለም፡፡ ገንዘቡን ከማባከን ሳይሆን መጽሐፍ አልሸጥ ያላቸው ስለነበሩ መጽሐፍ ተሸጦ ገቢ መሆን አልቻለም፡፡ ገንዘቡን ከሰጡን ድርጅቶች ገንዘቡ መሰብሰብ አለበት የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ ዕቅዱ ሲወጣ ከነበረው የገንዘብ አሰባሰብ አንፃር ብዙ አልተሠራበትም ነበር፡፡ ቀድሞ ይኼን ጉዳይ ካስጀመሩ ማተሚያ ድርጀቶች ጋር መቀጠልም አልተቻለም፡፡ አሁን ግን ገንዘቡ ሊሰበሰብ የሚችልበት፣ መጻሕፍቱም የሚሸጡበት ጠንካራ የሆነ አሠራር እየታሠበ ነው፡፡ ፈንዱ የሚያገኙት ተወዳድረው የሚያሸንፉ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም በፈንድ ሁለት ሦስቴ የሳተሙም አሉ፡፡ ለምሳሌ የኢሳያስ ወርዶፋ መጻሕፍትና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በየዓመቱ ክረምት ላይ የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ ላላቸው ወጣቶች የምትሰጡት ሥልጠና ምን ያህል ውጤታማ ነው?

ዶ/ር ሙሴ፡- አሁን ተማሪዎቹ ወደ 500 ደርሰዋል፡፡ ሥልጠናው ምንሊክ ትምህርት ቤት በሥነ ሥስ፣ ኪነ ግጥምና ሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ዘርፎች ይሰጣል፡፡ ልምድ ያካበቱ የዩኒቨርስቲ መምህራንና እንደ ዓለማየሁ ገላጋይ ያሉ በሙያው ያሉ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ነው፡፡ ከሥልጠናው የወጡ ወደ ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ቤት ለረዥም ትምህርት የገቡ፣ ጋዜጠኞች የሆኑም አሉ፡፡ የማኅበሩ የጥበብ አምባ የሬዲዮ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ዓለሙ ይጠቀሳል፡፡ ለውጡ በአንድ ጀንበር የሚታይ ባይሆንም፣ የምናሠራው ሕንፃ የክረምት ብቻ ሳይሆን ዓመቱን በሙሉ ሥልጠና የሚሰጥበት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የደራስያን ሥራዎች እንዲታተሙና እንዲተዋወቁ በማድረግ ያለው ሚና ምንድነው?

ዶ/ር ሙሴ፡- ለማሳተም ሪቮልቪንግ ፈንዱን ከመጠቀም ውጪ ገንዘብ ሰጥቶ እያንዳንዱን ደራሲ ሊደጉም የሚችልበት አግባብም አቅምም የለውም፡፡ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ይመረቃል ታደሙ የምንለው መጽሐፉ እንዲተዋወቅ ነው፡፡ የአቅም ችግርን ለመቅረፍ ሪቮልቪንግ ፈንድን አጠንክረን እየሄድንበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የሕትመት ዋጋ መወደድ፣ መጻሕፍት ገበያ ላይ ከዋሉ በኋላ ያላግባብ ዋጋቸው ተፍቆ በውድ መሸጥና ሌሎችም ችግሮች ዘርፉን ይፈትኑታል፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ ያሉት የዘርፉ ችግሮች ምንድናቸው?  በማኅበሩስ ችግሮችን ለመፍታት ምን አድርጓል?

ዶ/ር ሙሴ፡- በዋነኛነት የሕትመት ዋጋ መናር ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ መጻሕፍትን ለአንባቢ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ አልተቻለም፡፡ ጉዳዩን በስብሰባና በደብዳቤ በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው አቅርበናል፡፡ መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን ጋዜጣም ከንባብ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጃፓን በየቀኑ ሁለት ሚሊዮን አንባቢ አለ ስንል ጋዜጣ የሚያነበውንም ጨምሮ ነው፡፡ የጋዜጣ ዋጋ አሁን እየጨመረ መጥቷል፡፡ አሁን ጋዜጦች ያለማስታወቂያ ሽያጭ መኖር አይችሉም፡፡መጻሕፍትም ውድ ሆነው ከመግዛት ይልቅ በኪራይ አንብቦ የሚመለስበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡  እኛ የበኩላችንን ብንጥርም የሚያዳምጠን አላገኘንም፡፡ ለዚህ ጉዳይ መንግሥት ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትን አካቶ መንግሥት ላይ ጫና መፈጠር አለበት፡፡ የወረቀት፣ ቀለምና ተጓዳኝ ግብአቶች ዋጋ መጨመር በሕትመቱ ያለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የመንግሥት ፖሊሲ መቀየር አለበት፡፡ ወረቀቶቹ በምን ዓይነት ቀረጥ ነው የሚመጡት የሚለው ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ መንግሥት ሊያግዘን ይገባል፡፡ ሌላው መጽሐፍ አዝዋሪዎች የመጻሕፍትን ዋጋ ፍቀው ጨምረው መሸጣቸው ነው፡፡ አዝዋሪዎች ዋጋ ፍቀው የ100ውን 300 ብር ሲያደርጉት ገዢ ስላላቸው ለምን አዝዋሪዎችን ትነኳቸዋላችሁ የሚሉ አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ግራ ያጋባሉ፡፡ የመጽሐፍ ዋጋ ተፍቆ ምን ያህል ሰው ገዛው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ መፋቅ አግባብም ሕጋዊም አይደለም፡፡ ይኼ ከማኅበሩ አቅም በላይ ነው፡፡ አንዳንዴ ፀጥታ አስከባሪ ፖሊሶች ይይዟቸውና በዚ አቅጣጫ በቂ ሕግ ስለሌለ ይለቀቃሉ፡፡ አንዳንዱ ጸሐፊ እንዲፋቅ የሚመች ቁጥር ይሰጣልም ይባላል፡፡ አዝዋሪዎቹን ጨምሮ የሚመለከታቸው ሁሉ በሚገባ ሊነጋገሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከመጻሕፍት ይዘት፣ ከአርትኦትና አጠቃላይ የጥራት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶችስ?

ዶ/ር ሙሴ፡- በጥራት ረገድ ደራስያን ማኅበር ልንሰጥ የምንችለው የአርትኦት ሥራ ነው፡፡ እያንዳንዱ ደራሲ የጻፈውን ተገቢ የሆነ የአርትኦት ሥራ ቢያሠራበት ጥሩ ይሆናል፡፡ አሁን አንጋፋ ጸሐፍቶቻችን ናቸው የአርትኦቱን ሥራ እየሠሩ በርካታ መጻሕፍት እንዲወጡ የሚያደርጉት፡፡ ይዘትን ለአንባቢ ከመተው ወጪ ከባህል፣ አስተሳበብና የይዘቱ ከፍታ አንፃር በማኅበር ማድረግ የምንችለው የለም፡፡ ቺቺንያ ነክ የሆኑ ነገሮች በዙ ማኅበሩ ለምን ቁጭ ብሎ ያያል? ተብለን ተጠይቀን ነበር፡፡ አንባቢው የማይመቸውና የማይሆነው ነገር ሲሆን፣ ይተወዋል፡፡ ለብዙ ዓመታት ሳንሱር እንዳይኖር ስንታገል ቆይተን በሌላ አቅጣጫ ሳንሱርን መጥራት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ደራሲው ኃላፊነት ወስዶ የሚያሳትመው እንጂ አንድ መጽሐፍ ለሕዝብ መቅረብ የለበትም ተብሎ ማተሚያ ቤት ከመግባቱ በፊት በሳንሱር አይቆምም፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከሌሎች የኪነ ጥበብ ማኅበሮች ጋር በመሆን ባለሙያዎች ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነፃ ሕክምና እንዲያገኙ በጀመረው አሠራር ሙያተኞች እየተጠቀሙ ነው?

ዶ/ር ሙሴ፡- ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሰጠንን ዕድል ጸሐፍቱ ይገለገሉበታል፡፡ የታመሙ የጥበብ ሰዎች መታከም የማይችሉበት ሁኔታ ሲኖር ደብዳቤ ለሆስፒታሉ እየጻፍን በአንደኛ ደረጃ መኝታ ክፍል በነፃ እንዲታከሙ እያደረግን ነው፡፡ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ማኅበር መቋቋሙ የጥበቡን ሥራ የተጠቀሙ ሁሉ እንዲከፍሉ ያደርጋል፡፡ ሁኔታው ቀደም ብሎ ቢኖር የኪነ ጥበብ ሰዎች በጥበብ ሥራቸው ሮያሊቲ ክፍያ ይጠቀሙ ነበር፡፡ ማኅበሩ የሮያሊቲውን እየሰበሰበ ሲመጣ፣ የጥበብ ሰው ከሚያገኘው ገቢ የተወሰነውን ለጤና ኢንሹራንስ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ ከጥቁር አንበሳው ጉዳይ ጋር አገናኝተን በስፋት እንሄድበታለን፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ አዲስ አበባ ካለው ዋና ጽሕፈት ቤት ባሻገር በክልሎች ያለው ተሳትፎ ምን ድረስ ነው?

ዶ/ር ሙሴ፡- ወደ ክልል ደረጃ ያሸጋገርናቸው ቅርንጫፎች አሉ፡፡ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በሰመራ፣ በመቐለና በሐዋሳ ቅርንጫፎች ነበሩ፡፡ በየከተሞቹ ማኅበሩን ማቋቋሙ አድካሚና፣ ለክትልልና ለድጋፍ ማኅበራቱን ወደ ክልል ቅርንጫፍ አሳድገናል፡፡ የአማራ ክልል፣ የትግራይና የአፋር፣ ማኅበራት ሲሆኑ፣ ደቡብ ላይም ወደ ክልል ከፍ እንደምናደርግ ቃል ገብተናል፡፡ ለወደፊት በሌሎች ክልሎችም የማበሩን ቅርንጫፍ እናቋቁማለን፡፡ በተለይ በሰኔ 30ና በሌሎችም ብሔራዊ ጉዳዮች ከኛ ጋር ቆመው እየተሳተፉ ነው፡፡ በክልል መንግሥትም ጥሩ ተቀባይነት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ እነዚህን ሥራዎች ሲያከናውን ገጥመውታል የሚሏቸውን መሰናክሎች ቢገልጹልን?

ዶ/ር ሙሴ፡- የሙያ ማኅበራትን መምራት ያለ ሥልጣንና ያለ ገንዘብ መምራት ማለት ነው፡፡ አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም በፍቃደኝነትና በስምምነት የሚሆን ነው፡፡ የጥበብ ማኅበራት የራሳቸውን ገቢ የሚፈጥሩበት አካሄድ ውስን ነው፡፡ ዋናው ተግዳሮት አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ሲሞክር የገንዘብ እጥረት መኖሩ ነው፡፡ አንድ ፕሮጀክት ለማስፈጸም 250 ድረስ ደብዳቤዎች በመላው አገሪቱ ይላካሉ፡፡ ማን ይረዳናል? ማን አብሮን ይቆማል? ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከተላኩት ውስጥ በጥሩ ሁኔታ መልስ የሚሰጡን ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከአምስት አሠርታት በላይ ሲዘልቅ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ አበርክቷቸዋል የሚሏቸው ጉልህ ሚናዎች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ሙሴ፡- የማኅበሩ በትልቅ ከፍታና ልዕልና መኖር ወደ ድርሰቱ የሚሳቡ ወጣቶችን የማምጣት ከፍተኛ ኃይል ፈጥሯል፡፡ በተለይ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት አማተር ወጣቶች ወደ ማኅበሩ ሲመጡ የተለያዩ ግጥሞቻቸውን የሚያቀርቡበት፣ መጻሕፍቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረኮች ይመቻችላቸዋል፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ልጆቹ ፕሮፎሽናል ይሆናሉ፡፡ ዛሬ በሥነ ጽሑፍ፣ በሚዲያው ያሉት የማኅበሩ ውጤቶች ናቸው፡፡ የማኅበራችን ምክትል ፕሬዚዳንት የአያልነህ ሙላት ቀንዲል ቤተ ተውኔት ያሳደጋቸው ወጣቶችም አሉ፡፡ ማኅበሩ አማተሮች መጥተው ፕሮፌሽናል ሆነው የሚወጡበት ቤት ነው፡፡ የመጀመሪያ መጽሐፌን በ2000 ዓ.ም. ሳሳትም የመጡ በጣም ወጣት ልጆች ዛሬ ያሉበትን ቦታ መገመት ይቻላል፡፡ እነ አባባው መላኩ፣ ምሥራቅ ተረፈና ብዙ ልጆች ማኅበሩ ኮትኩቶ አሳድጓል፡፡ ከዛ ውጪ በደርግ ጊዜ ሳንሱር ነበር፡፡ ማኅበሩም ለብዙ ዓመታት በተዳከመ ሁኔታ ቀጥሎ ነበር፡፡ ማኅበሩ ከፍታ ያገኘው በንጉሡ በተመሠረበት የመጀመሪያዎቹ ዘመናትና ባለፉት አሠርታት ነው፡፡ በነዚህ ዓመታት ሥነ ጽሑፍ፣ ንባብና ደራሲ ክብር እንዲሰጣቸው ማድረግ ቀላል አይደለም፡፡ ማኅበሩ ሥራ ላይ እንዳለ የመንግሥት ቢሮ በሳምንት ስድስት ቀን ይሠራል፡፡ የተለያዩ ኮሚቴዎቹ እየተነቃነቁ ነው፡፡ በሕዝቡና በመንግሥት ትልቅ ቦታ አግኝቷል፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ሲባል በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ አንድ የሆነ ምስል ይቀረጻል፡፡ ይኼ ነገር ይቀጥላል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አራት ዓመታት የሠሩ የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በቅርቡ ይለወጣሉና ማኅበሩ በቅርብ ርቀት ሊያሳካቸው የያዛቸው ዕቅዶች ምንድናቸው?

ዶ/ር ሙሴ፡- አንድ የምርጫ ዘመን አራት ዓመት ነው፡፡ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባኤው   ተካሂዶ የምርጫው ቀን ይወሰናል፡፡ ሌላ ተተኪ ትውልድ ማኅበሩን የሚመራበት ሁኔታ እያመቻቸን ነው፡፡ እንደ እርሾ ልንቆጥረው የምንችል ወደ ቀጣዩ ሥራ አስፈጻሚ ሊገባ የሚችል ኃይል እንዳለ እምነት አለን፡፡ የማኅበሩ ዋንኛ ጉዳይ ንባብ፣ ደራሲውና መጽሐፍ እንጂ ሕንፃ መሥራት አይደለም፡፡ ስለዚህ ሰኔ 30 የንባብ ቀን ሆኖ በዚህ ዓመት በመላው አገር መከበሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ቀጥሎ ሕንፃውን ማስጨረስ ነው፡፡ መሬቱን አግኝቶ መሠረት ድንጋይ ማስቀመጡ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ በኋላ የቀረው በምን መልክ መንግሥትና ጥበብ ወዳዱን ሕዝብ እንቅረብ የሚለው ነው፡፡ በሕንፃ ግንባታ ኰሚቴው በር አንኳኩተው ማሳመን የሚችሉና የሚታመኑ በአገሪቱ ጥበብ፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን ማካተት እንፈልጋለን፡፡ ሌላው የፓን አፍሪካ ደራስያንን አዲስ አበባ መጥራት ነው፡፡ የደራስያን የመኖሪያ መንደር መሬት ጉዳይና ተዘዋዋሪ ብድር (ሪቮልቪንግ ፈንድ) መቀጠል አለባቸው፡፡ ሕያው የጥበብ ጉዞ በጸሐፍት መቼት እንደተጀመረ የአገሪቱን የቱሪስት መስህቦች ይዞ የሚሄድ ነው፡፡ ‹‹ኑ ድረሱልኝ›› እንዳለው ጣና ሐይቅና ጮቄ ተራራ ሁሉ የዱር እንስሳት አሉ፡፡ የነጭ ሳር የሜዳ አህዮች፣ የባቢሌ ዝሆኖች፣ የሻላና አብያታ ሐይቆች እየሸሹ ነው፡፡ በርካታ ጉዳዮችን ለሕዝባችን፣ ለመንግሥት ነቅሰን እያወጣን የምናሳውቅበት ነው፡፡ በማኅበሩ የጥበብ ጉዞ አንድ ሌላ እርከን ተሻግሯል ብዬ አምናለሁ፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...